በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 51

‘እሱን መስማታችሁን’ ቀጥሉ

‘እሱን መስማታችሁን’ ቀጥሉ

“በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት።”—ማቴ. 17:5

መዝሙር 54 “መንገዱ ይህ ነው”

ማስተዋወቂያ *

1-2. (ሀ) ሦስቱ የኢየሱስ ሐዋርያት ምን እንዲያደርጉ ታዘዋል? እነሱስ ምን አደረጉ? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

 በ32 ዓ.ም. ከተከበረው የፋሲካ በዓል በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ሐዋርያው ያዕቆብና ሐዋርያው ዮሐንስ አስገራሚ ራእይ ተመለከቱ። በአንድ ረጅም ተራራ ላይ ምናልባትም በሄርሞን ተራራ ላይ ሳሉ ኢየሱስ በፊታቸው ተለወጠ። “ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።” (ማቴ. 17:1-4) ራእዩ ሊያበቃ ሲል አምላክ “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” ብሎ ሲናገር ሐዋርያቱ ሰሙ። (ማቴ. 17:5) ሦስቱ ሐዋርያት ኢየሱስን እንደሰሙት በሕይወታቸው አሳይተዋል። እኛም የእነሱን ምሳሌ መከተል እንፈልጋለን።

2 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው የኢየሱስን ድምፅ ለመስማት አንዳንድ ነገሮችን ማድረጋችንን መተው አለብን። በዚህ ርዕስ ላይ ደግሞ ኢየሱስ እንድናደርግ ያዘዘንን ሁለት ነገሮች እንመለከታለን።

“በጠባቡ በር ግቡ”

3. በማቴዎስ 7:13, 14 መሠረት ምን ማድረግ አለብን?

3 ማቴዎስ 7:13, 14ን አንብብ። ኢየሱስ ወደ ሁለት መንገዶች የሚመሩ ሁለት በሮችን እንደጠቀሰ ልብ እንበል፤ አንደኛው መንገድ “ሰፊ” ነው፤ ሌላኛው ደግሞ “ቀጭን” ነው። ሦስተኛ መንገድ የለም። በየትኛው መንገድ እንደምንጓዝ መምረጥ ያለብን እኛ ራሳችን ነን። በሕይወታችን ውስጥ የምናደርገው ትልቁ ውሳኔ ይህ ነው፤ ምክንያቱም የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው በምናደርገው ምርጫ ላይ ነው።

4. ስለ ‘ሰፊው’ መንገድ ምን ማለት ይቻላል?

4 በሁለቱ መንገዶች መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል ይኖርብናል። ‘ሰፊው’ መንገድ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ ነው፤ ምክንያቱም መንገዱ ምቹ ነው። የሚያሳዝነው ብዙዎች በዚህ መንገድ ላይ መጓዛቸውን እና ብዙኃኑን መከተላቸውን ለመቀጠል መርጠዋል። በዚህ መንገድ ላይ ሰዎች እንዲጓዙ የሚፈልገው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነና ይህ መንገድ ወደ ጥፋት እንደሚወስድ አይገነዘቡም።—1 ቆሮ. 6:9, 10፤ 1 ዮሐ. 5:19

5. አንዳንዶች ‘ቀጭኑን’ መንገድ ለማግኘትና በዚህ መንገድ ላይ መጓዝ ለመጀመር ሲሉ ምን አድርገዋል?

5 ‘ከሰፊው’ መንገድ በተቃራኒ ሌላኛው መንገድ “ቀጭን” ነው፤ ኢየሱስ ይህን መንገድ የሚያገኙት ጥቂቶች እንደሆኑ ገልጿል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በቀጣዩ ቁጥር ላይ ከሐሰተኛ ነቢያት እንድንጠነቀቅ ማሳሰቢያ የሰጠ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። (ማቴ. 7:15) አንዳንዶች እንደሚናገሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች አሉ፤ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ደግሞ እውነትን እንደሚያስተምሩ ይናገራሉ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ሃይማኖቶች እንዲህ መብዛታቸው ተስፋ ስላስቆረጣቸውና ግራ ስላጋባቸው ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ለማግኘት ጥረት ማድረግ እንኳ አይፈልጉም። ሆኖም ይህን መንገድ ማግኘት ይቻላል። ኢየሱስ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐ. 8:31, 32) አንተ ግን ብዙኃኑን ከመከተል ይልቅ እውነትን ለማግኘት ጥረት ማድረግህ የሚያስመሰግን ነው። አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ለማወቅ ቃሉን በጥልቀት አጥንተሃል፤ እንዲሁም የኢየሱስን ትምህርቶች ሰምተሃል። ከተማርካቸው ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ይሖዋ ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች እንድትርቅ እንዲሁም አረማዊ ምንጭ ባላቸው በዓላትና ልማዶች መካፈልህን እንድትተው ይፈልጋል። በተጨማሪም ይሖዋ የሚጠብቅብንን ነገር ማድረግና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ከሌላቸው ልማዶች መላቀቅ ተፈታታኝ ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበሃል። (ማቴ. 10:34-36) እነዚህን ለውጦች ማድረግ አታግሎህ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሰማያዊውን አባትህን ስለምትወደውና የእሱን ሞገስ ማግኘት ስለምትፈልግ ለውጥ ለማድረግ ጥረት ማድረግህን ቀጠልክ። ይሖዋ ይህን ሲያይ ምንኛ ተደስቶብህ ይሆን!—ምሳሌ 27:11

ከቀጭኑ መንገድ ላለመውጣት ምን ይረዳናል?

አምላክ የሚሰጠን ምክር እና መሥፈርቶቹ ‘ከቀጭኑ’ መንገድ ሳንወጣ እንድንጓዝ ይረዱናል (ከአንቀጽ 6-8⁠ን ተመልከት) *

6. በመዝሙር 119:9, 10, 45, 133 መሠረት ከቀጭኑ መንገድ እንዳንወጣ ምን ይረዳናል?

6 በቀጭኑ መንገድ ላይ መጓዝ ከጀመርን በኋላ ከዚህ መንገድ ላለመውጣት ምን ይረዳናል? አንድ ምሳሌ እንመልከት። በተራራማ አካባቢ ባለ ጠባብ መንገድ ጠርዝ ላይ ለአሽከርካሪዎች ደህንነት ሲባል ብዙውን ጊዜ አጥር ይደረጋል። የአጥሩ ዓላማ አሽከርካሪዎች ወደ ጠርዙ በጣም እንዳይጠጉ፣ ይባስ ብሎም መንገዳቸውን ስተው ገደል እንዳይገቡ መከላከል ነው። አሽከርካሪዎች እንዲህ ያለው አጥር ነፃነታቸውን እንደገደበባቸው እንደማይሰማቸው የታወቀ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የይሖዋ መሥፈርቶችም ከዚህ አጥር ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። የይሖዋ መሥፈርቶች ከቀጭኑ መንገድ እንዳንወጣ ይረዱናል።—መዝሙር 119:9, 10, 45, 133ን አንብብ።

7. ወጣቶች ለቀጭኑ መንገድ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

7 እናንት ወጣቶች፣ አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ መመሪያዎች የማያፈናፍኑ እንደሆኑ ይሰማችኋል? ሰይጣን እንዲህ ብላችሁ እንድታስቡ ይፈልጋል። በሰፊው መንገድ ላይ የሚጓዙ ሰዎች በሚያደርጉት ነገር ላይ እንድታተኩሩ ይፈልጋል፤ እነዚህ ሰዎች አስደሳች ሕይወት የሚመሩ ይመስላሉ። አብረዋችሁ ከሚማሩት ልጆች ወይም ኢንተርኔት ላይ ከምታዩአቸው ሰዎች አንጻር፣ ብዙ ነገር እንደቀረባችሁ እንዲሰማችሁ ይፈልጋል። ሰይጣን የይሖዋ መሥፈርቶች በሕይወታችሁ የተሟላ ደስታ ከማግኘት እንዳገዷችሁ እንድታስቡ ይፈልጋል። * ሆኖም አንድ ነገር አስታውሱ፤ ሰይጣን በእሱ መንገድ ላይ የሚጓዙ ሰዎች መጨረሻ ላይ ምን እንደሚጠብቃቸው እንዲያውቁ አይፈልግም። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ፣ በሕይወት መንገድ ላይ መጓዛቸውን ለሚቀጥሉ ሰዎች ምን እንዳዘጋጀላቸው በግልጽ ነግሯችኋል።—መዝ. 37:29፤ ኢሳ. 35:5, 6፤ 65:21-23

8. ወጣቶች ከኦላፍ ተሞክሮ ምን ትምህርት ያገኛሉ?

8 ኦላፍ ከተባለ ወጣት ወንድም ተሞክሮ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት። * ከኦላፍ ጋር የሚማሩት ልጆች የፆታ ብልግና እንዲፈጽም ጫና ያሳድሩበት ነበር። ይህ ወጣት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ላቅ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንደሚመሩ ለክፍሉ ልጆች ሲነግራቸው አብረውት ከሚማሩት ሴቶች አንዳንዶቹ ከእነሱ ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽም ለማግባባት ይበልጥ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ኦላፍ ግን በአቋሙ ጸና። ኦላፍ ያጋጠመው ፈተና ይህ ብቻ አልነበረም። እንዲህ ብሏል፦ “አስተማሪዎቼ ከፍተኛ ትምህርት እንድከታተል ይገፋፉኝ ነበር። ይህን ካደረግኩ የሌሎችን አክብሮት እንደማተርፍ፣ አለዚያ ግን በሕይወቴ ስኬታማ እንደማልሆን ነገሩኝ።” ኦላፍ እንዲህ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤዬ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር እቀራረብ ነበር። እንደ ቤተሰቤ ሆነውልኝ ነበር። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ማጥናት ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ባጠናሁ መጠን እውነትን እንደያዝኩ ይበልጥ እርግጠኛ ሆንኩ። በመሆኑም ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ።”

9. በቀጭኑ መንገድ ላይ መጓዛቸውን መቀጠል የሚፈልጉ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

9 ሰይጣን ወደ ሕይወት ከሚወስደው መንገድ እንድትወጡ ሊያደርጋችሁ ይፈልጋል። አብዛኛው የሰው ዘር በሚሄድበት ‘ወደ ጥፋት በሚወስደው ሰፊ መንገድ’ ላይ እንድትሄዱ ሊያደርጋችሁ ይፈልጋል። (ማቴ. 7:13) ይሁንና ኢየሱስን መስማታችንን ከቀጠልን እና ቀጭኑን መንገድ ጥበቃ እንደሚያስገኝልን አድርገን ከተመለከትነው ከቀጭኑ መንገድ ሳንወጣ መኖር እንችላለን። እስቲ አሁን ደግሞ ኢየሱስ እንድናደርገው የነገረንን ሌላ ነገር እንመልከት።

ከወንድምህ ጋር ታረቅ

10. በማቴዎስ 5:23, 24 መሠረት ኢየሱስ ምን እንድናደርግ አዞናል?

10 ማቴዎስ 5:23, 24ን አንብብ። ኢየሱስ አይሁዳውያን አድማጮቹ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡት የአምልኮ ሥርዓት እየተናገረ ነው። አንድ ሰው፣ ይዞት የመጣውን የእንስሳ መሥዋዕት ለካህኑ ለመስጠት ተዘጋጅቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቆሟል እንበል። ይህ ሰው ልክ በዚያ ሰዓት፣ ወንድሙ በእሱ ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ቢለው እንስሳውን እዚያው ትቶ ‘መሄድ’ ነበረበት። ለምን? ለይሖዋ መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሊኖር ይችላል? ኢየሱስ “በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ” በማለት በግልጽ ተናግሯል።

ትሑት በመሆን ከወንድሙ ጋር የታረቀውን የያዕቆብን ምሳሌ ትከተላለህ? (ከአንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት) *

11. ያዕቆብ ከኤሳው ጋር ለመታረቅ ምን አደረገ?

11 በያዕቆብ ሕይወት ውስጥ የተፈጸመን አንድ ክንውን መመርመራችን እርቅ መፍጠርን በተመለከተ ጠቃሚ ትምህርቶች ለማግኘት ይረዳናል። ያዕቆብ ለ20 ዓመታት ያህል ከትውልድ አገሩ ርቆ ከቆየ በኋላ፣ ወደ አገሩ እንዲመለስ አምላክ በመልአኩ አማካኝነት አዘዘው። (ዘፍ. 31:11, 13, 38) ይሁንና አንድ ችግር ነበር። ታላቅ ወንድሙ ኤሳው ሊገድለው ይፈልግ ነበር። (ዘፍ. 27:41) ያዕቆብ ወንድሙ አሁንም ቂም ይዞበት ሊሆን እንደሚችል ስላሰበ “እጅግ ፈራ፤ በጭንቀትም ተዋጠ።” (ዘፍ. 32:7) ታዲያ ከወንድሙ ጋር ለመታረቅ ምን አደረገ? በመጀመሪያ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ አጥብቆ ጸለየ። ከዚያም ለኤሳው በርከት ያለ ስጦታ ላከለት። (ዘፍ. 32:9-15) በመጨረሻም ተለያይተው የነበሩት ወንድማማቾች ፊት ለፊት ሲገናኙ ያዕቆብ ቅድሚያውን ወስዶ ለኤሳው አክብሮት አሳየው። ለኤሳው አንዴ ወይም ሁለቴ ሳይሆን ሰባት ጊዜ ሰገደለት! ያዕቆብ ትሕትና እና አክብሮት በማሳየት ከወንድሙ ጋር ታረቀ።—ዘፍ. 33:3, 4

12. ከያዕቆብ ምሳሌ ምን እንማራለን?

12 ያዕቆብ ከወንድሙ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ካደረገው ዝግጅትና ወንድሙን ሲያገኘው ከወሰደው እርምጃ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ያዕቆብ ይሖዋ እንዲረዳው በትሕትና ለምኗል። ከዚያም ከወንድሙ ጋር እርቅ ለመፍጠር አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስዷል። ያዕቆብ ኤሳውን ሲያገኘው ‘ጥፋተኛው ማን ነው?’ በሚለው ጉዳይ ላይ ከእሱ ጋር ሙግት አልገጠመም። የያዕቆብ ዓላማ ከወንድሙ ጋር መታረቅ ነበር። እኛስ የያዕቆብን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

ከሌሎች ጋር እርቅ መፍጠር የምንችለው እንዴት ነው?

13-14. አንድ የእምነት ባልንጀራችን ቅር ቢሰኝብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ የምንጓዝ እንደመሆናችን መጠን ከወንድሞቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ እንፈልጋለን። (ሮም 12:18) ታዲያ አንድ የእምነት ባልንጀራችንን ቅር እንዳሰኘነው ብንገነዘብ ምን ማድረግ ይኖርብናል? እንደ ያዕቆብ ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ይኖርብናል። ከወንድማችን ጋር ሰላም ለመፍጠር የምናደርገውን ጥረት እንዲባርክልን ይሖዋን ልንለምነው እንችላለን።

14 በተጨማሪም ራሳችንን መመርመር ያስፈልገናል። ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ኩራቴን ዋጥ አድርጌ በትሕትና ይቅርታ ለመጠየቅና ሰላም ለመፍጠር ፈቃደኛ ነኝ? ቅድሚያውን ወስጄ ከወንድሜ ወይም ከእህቴ ጋር ለመታረቅ ጥረት ባደርግ ይሖዋ እና ኢየሱስ ምን ይሰማቸዋል?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ኢየሱስን እንድንሰማ እንዲሁም ትሑት ሆነን የእምነት ባልንጀራችንን እንድናነጋግረውና ሰላም እንድንፈጥር ይረዳናል። በዚህ መንገድ የያዕቆብን ምሳሌ መከተል እንችላለን።

15. በኤፌሶን 4:2, 3 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ከወንድማችን ጋር ለመታረቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

15 ያዕቆብ ከወንድሙ ጋር በተገናኘበት ወቅት ትሕትና ባያሳይ ኖሮ ምን ሊፈጠር ይችል እንደነበር አስቡት! ውጤቱ የከፋ ይሆን ነበር። እኛም ከወንድማችን ጋር ሰላም ለመፍጠር ስንሄድ በትሕትና ልናነጋግረው ይገባል። (ኤፌሶን 4:2, 3ን አንብብ።) ምሳሌ 18:19 “የተበደለ ወንድም ከተመሸገች ከተማ ይበልጥ የማይበገር ነው፤ እንደ ግንብ በሮች መቀርቀሪያም የጠነከረ ጠብ አለ” ይላል። በትሕትና ይቅርታ መጠየቃችን ወደዚያ ‘የተመሸገ ከተማ’ ለመግባት ያስችለናል።

16. ወደ ወንድማችን ከመሄዳችን በፊት ልናስብበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ?

16 ከዚህም ሌላ ወንድማችንን ምን እንደምንለው እንዲሁም እንዴት እንደምናነጋግረው አስቀድመን ልናስብበት ይገባል። ወንድማችንን ለማነጋገር ዝግጁ እንደሆንን ሲሰማን የወንድማችን ቅሬታ እንዲወገድ የማድረግ ግብ ይዘን እናነጋግረው። መጀመሪያ ላይ ወንድማችን ደስ የማይለን ነገር ይናገረን ይሆናል። በዚህ ጊዜ እንበሳጭ ወይም ጥፋተኛ እንዳልሆንን ለመግለጽ እንፈተን ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ማድረጋችን ሰላም ለመፍጠር ያስችላል? እንደማያስችል ጥያቄ የለውም። ዋናው ነገር ከወንድማችን ጋር ሰላም መፍጠራችን እንጂ ‘ጥፋተኛው ማን ነው?’ የሚለው እንዳልሆነ ልናስታውስ ይገባል።—1 ቆሮ. 6:7

17. ከዢልበርት ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

17 ዢልበርት የተባለ ወንድም ሰላም ፈጣሪ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። እንዲህ ብሏል፦ “ከአንዲት የቅርብ የቤተሰቤ አባል ጋር ያለኝ ግንኙነት በጣም ሻክሮ ነበር። በመካከላችን እርቅ እንዲሰፍን ለማድረግ ስል በግልጽና በተረጋጋ መንፈስ እሷን ለማነጋገር ከሁለት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ጥረት አደረግኩ።” ዢልበርት ሌላስ ምን አደረገ? እንዲህ ብሏል፦ “እሷን ለማነጋገር ከመሞከሬ በፊት እጸልይ ነበር፤ እንዲሁም መጥፎ ነገር ብትናገረኝ ላለመቆጣት አእምሮዬን አዘጋጅ ነበር። ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን ነበረብኝ። መብቴን ለማስከበር ጥረት ከማድረግ ይልቅ ሰላም ለማስፈን መጣር እንዳለብኝ ገብቶኝ ነበር።” ዢልበርት ይህን ማድረጉ ምን ውጤት አስገኘ? እንዲህ ብሏል፦ “በአሁኑ ጊዜ ከሁሉም የቤተሰቤ አባላት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ስላለኝ የአእምሮ እረፍት አግኝቻለሁ።”

18-19. አንድን ሰው ቅር አሰኝተን ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

18 እስካሁን ከተመለከትነው አንጻር፣ አንድ የእምነት ባልንጀራህ ቅር እንደተሰኘብህ ብትገነዘብ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የኢየሱስን ምክር በመከተል ከወንድምህ ጋር ታረቅ። ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ እንዲሁም ሰላም ፈጣሪ መሆን እንድትችል ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ ጠይቀው። እንዲህ ካደረግክ ደስተኛ ትሆናለህ፤ ኢየሱስን እንደምትሰማም ታሳያለህ።—ማቴ. 5:9

19 ይሖዋ ‘የጉባኤው ራስ’ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ፍቅር የሚንጸባረቅበት መመሪያ ስለሚሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ኤፌ. 5:23) እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ሐዋርያው ያዕቆብ እና ሐዋርያው ዮሐንስ እኛም ‘ኢየሱስን ለመስማት’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ማቴ. 17:5) ቅር ካሰኘነው የእምነት ባልንጀራችን ጋር እርቅ በመፍጠር ኢየሱስን መስማት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተመልክተናል። ከእምነት ባልንጀራችን ጋር እርቅ የምንፈጥር እንዲሁም ወደ ሕይወት በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ ምንጊዜም የምንጓዝ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፉ በረከቶችን እናገኛለን፤ ወደፊት ደግሞ ለዘላለም በደስታ እንኖራለን።

መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ

^ አን.5 ኢየሱስ ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ለማግኘት በጠባቡ በር እንድንገባ አሳስቦናል። በተጨማሪም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር እርቅ እንድንፈጥር መክሮናል። የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ስንጥር ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? ልንወጣቸው የምንችለውስ እንዴት ነው?

^ አን.7 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች በተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 15 ላይ የሚገኘውን “የእኩዮቼን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም በእኩዮች ተጽዕኖ አትሸነፍ! የሚለውን www.pr418.com ላይ የሚገኝ የነጭ ሰሌዳ አኒሜሽን ተመልከት። (የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ወጣቶች በሚለው ሥር ይገኛል።)

^ አን.8 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ የአምላክ መሥፈርቶች እንደ አጥር በሆኑለት “ቀጭን” መንገድ ላይ መጓዛችንን በመቀጠል ከሚከተሉት አደገኛ ሁኔታዎች እንጠበቃለን፦ የብልግና ምስሎች፣ የፆታ ብልግና እንድንፈጽም የሚደረግብን ጫና፣ ከፍተኛ ትምህርት እንድንከታተል የሚደርስብን ግፊት።

^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ ያዕቆብ ሰላም ለመፍጠር ስለፈለገ በወንድሙ በኤሳው ፊት በተደጋጋሚ ሰግዷል።