በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በዚህ ዓመት የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

በያዕቆብ 5:11 ላይ ይሖዋ “እጅግ አፍቃሪ” እና “መሐሪ” እንደሆነ መገለጹ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?

ይሖዋ መሐሪ በመሆኑ ስህተታችንን ይቅር ለማለት ዝግጁ እንደሆነ እናውቃለን። ያዕቆብ 5:11 ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ እንደሚረዳንም ማረጋገጫ ይሰጠናል። እኛም እሱን ለመምሰል ጥረት ማድረጋችን ተገቢ ነው።—w21.01 ገጽ 21

ይሖዋ የራስነት ሥርዓትን ያቋቋመው ለምንድን ነው?

ይህን ያደረገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። የይሖዋ ቤተሰብ ደስተኛና ሥርዓታማ ሊሆን የቻለው የራስነት ሥርዓት ስላለ ነው። ይህን ሥርዓት የሚከተል እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ‘አንድን ውሳኔ የማድረግና ግንባር ቀደም ሆኖ ውሳኔውን የማስፈጸም ኃላፊነት ያለበት ማን ነው?’ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ አይፈጥርበትም።—w21.02 ገጽ 3

ክርስቲያኖች መልእክት መላላኪያ አፕሊኬሽኖችን ሲጠቀሙ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

አንድ ክርስቲያን በእነዚህ አፕሊኬሽኖች ለመጠቀም ከወሰነ ጓደኞቹን በጥበብ መምረጥ ይኖርበታል። ትላልቅ የቻት ቡድኖች ውስጥ የሚገባ ከሆነ ይህን ማድረግ ቀላል አይሆንም። (1 ጢሞ. 5:13) በተጨማሪም አንዳንዶች በእነዚህ አፕሊኬሽኖች አማካኝነት ያልተረጋገጡ ወሬዎች ሊያሰራጩ ወይም የወንድማማች ማኅበራችንን የንግድ ጥቅማቸውን ለማራመድ ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ በዚህ ረገድም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።—w21.03 ገጽ 31

አምላክ፣ ኢየሱስ ተሠቃይቶ እንዲሞት የፈቀደው ለምንድን ነው?

አንደኛ፣ ኢየሱስ በእንጨት ላይ መሰቀሉ አይሁዳውያንን ከእርግማን ነፃ ያወጣቸዋል። (ገላ. 3:10, 13) ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ሊቀ ካህናታችን በመሆን ወደፊት ለሚጫወተው ሚና ይሖዋ እያሠለጠነው ነበር። ሦስተኛ፣ ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆኑ ሰዎች እጅግ ከባድ የሆነ ፈተና ቢደርስባቸውም ለአምላክ ታማኝ መሆን እንደሚችሉ አረጋግጧል። (ኢዮብ 1:9-11)—w21.04 ከገጽ 16-17

በአገልግሎት ላይ ሰዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንብን ምን ማድረግ እንችላለን?

ሰዎች በአብዛኛው ቤታቸው በሚገኙበት ሰዓት ላይ መስበክ እንችላለን። በሌላ ቦታ ሰዎችን ለማግኘት መሞከርም እንችላለን። በተጨማሪም በሌላ ዘዴ ሰዎችን ለማግኘት መሞከር ለምሳሌ ደብዳቤ መጻፍ እንችል ይሆናል።—w21.05 ከገጽ 15-16

ሐዋርያው ጳውሎስ “በሕጉ በኩል ለሕጉ ሞቻለሁ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? (ገላ. 2:19)

የሙሴ ሕግ ሰዎች ፍጹማን አለመሆናቸውን አጋልጧል፤ እንዲሁም እስራኤላውያንን ወደ ክርስቶስ መርቷቸዋል። (ገላ. 3:19, 24) ጳውሎስ በሕጉ በኩል ክርስቶስን መቀበል ችሏል። በዚህ መንገድ ጳውሎስ ‘ለሕጉ ሞቷል’፤ በሌላ አባባል በሕጉ ሥር መሆኑ አብቅቷል።—w21.06 ገጽ 31

ይሖዋ ጽናት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው?

ይሖዋ በጽናት እያሳለፋቸው ካሉት ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ በስሙ ላይ የደረሰው ነቀፋ፣ በሉዓላዊነቱ ላይ የተነሳው ተቃውሞ፣ ከልጆቹ መካከል አንዳንዶቹ ማመፃቸው፣ ሰይጣን ሁልጊዜ የሚያስፋፋቸው ውሸቶች፣ በሚወዳቸው አገልጋዮቹ ላይ የሚደርሰው ሥቃይ፣ በሞት ካንቀላፉ ወዳጆቹ መለየቱ፣ ክፉዎች በሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጭቆና እንዲሁም የሰው ልጆች የፍጥረት ሥራዎቹን ማበላሸታቸው።—w21.07 ከገጽ 9-12

ዮሴፍ ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?

ዮሴፍ የገዛ ወንድሞቹ ግፍ ፈጽመውበታል። በዚህም ምክንያት በግብፅ በሐሰት ተከስሶ ለዓመታት ታስሯል።—w21.08 ገጽ 12

በሐጌ 2:6-9, 20-22 ላይ ስለ ምን ዓይነት ምሳሌያዊ ነውጥ ትንቢት ተነግሯል?

ብሔራት የመንግሥቱን መልእክት አልተቀበሉም፤ ያም ቢሆን ብዙዎች ወደ እውነት መጥተዋል። በቅርቡ በሚኖረው የመጨረሻ ነውጥ ብሔራት ይጠፋሉ።—w21.09 ከገጽ 15-19

ተስፋ ቆርጠን አገልግሎታችንን ማከናወናችንን ማቆም የሌለብን ለምንድን ነው?

ይሖዋ የምናደርገውን ጥረት ይመለከታል፤ በአገልግሎታችንም ይደሰታል። ካልታከትን ወይም ተስፋ ካልቆረጥን የዘላለም ሕይወት እናገኛለን።—w21.10 ከገጽ 25-26

ዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 “በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው? (1 ጴጥ. 1:15)

ይህ ጥቅስ የተወሰደው ከዘሌዋውያን 19:2 ሳይሆን አይቀርም። በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሰፈሩት ሐሳቦች 1 ጴጥሮስ 1:15⁠ን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ያስተምሩናል።—w21.12 ከገጽ 3-4