በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 6

በይሖዋ አሠራር ላይ እምነት አላችሁ?

በይሖዋ አሠራር ላይ እምነት አላችሁ?

“እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው፤ ጻድቅና ትክክለኛ ነው።”—ዘዳ. 32:4

መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን

ማስተዋወቂያ *

1-2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ማመን የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ማመን ይከብዳቸዋል። የፍትሑና የፖለቲካው ሥርዓት ለሀብታሞችና አቅም ላላቸው ሲያዳላ ድሆችን ግን እንደሚበድል ይመለከታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” ማለቱ በእርግጥም ትክክል ነው። (መክ. 8:9) አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች የሚያደርጉት ነገርም ቢሆን ብዙዎችን ለሐዘን ዳርጓል። ይህ ሁኔታ አንዳንዶች በአምላክ ላይም ጭምር እምነት እንዲያጡ አድርጓል። በመሆኑም አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ስንጀምር የሚገጥመን አንዱ ተፈታታኝ ነገር፣ ግለሰቡ በይሖዋና በምድራዊ ወኪሎቹ ላይ እምነት እንዲያዳብር መርዳት ነው።

2 እርግጥ ነው፣ በይሖዋ እና በድርጅቱ ላይ እምነት መገንባት የሚያስፈልጋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብቻ አይደሉም። በእውነት ውስጥ በርካታ ዓመታት ያሳለፍን ክርስቲያኖችም እንኳ የይሖዋ አሠራር ምንጊዜም ትክክል መሆኑን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባም። አንዳንድ ጊዜ ይህን እምነታችንን የሚፈትኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። በዚህ ርዕስ ላይ እምነታችን የሚፈተንባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች እንመለከታለን፦ (1) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ስናነብ፣ (2) ከይሖዋ ድርጅት መመሪያ ሲሰጠን፣ (3) ወደፊት የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ስንጋፈጥ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስታነቡ በይሖዋ ተማመኑ

3. አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ስናነብ በይሖዋ ላይ ያለን እምነት የሚፈተነው እንዴት ነው?

 3 የአምላክን ቃል ስናነብ ይሖዋ አንዳንድ ሰዎችን የያዘበትን መንገድ እንዲሁም አንዳንድ ውሳኔዎችን ያደረገበትን ምክንያት በተመለከተ ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል። ለምሳሌ በዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ ይሖዋ በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም የተገኘን አንድ እስራኤላዊ በሞት እንዲቀጣ እንዳዘዘ እናነባለን። የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ደግሞ ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በኋላ የተከናወነውን ነገር ሲናገር ይሖዋ፣ ምንዝር የፈጸመውንና ነፍስ ያጠፋውን ንጉሥ ዳዊትን ይቅር እንዳለው ይገልጻል። (ዘኁ. 15:32, 35፤ 2 ሳሙ. 12:9, 13) በዚህ ጊዜ እንዲህ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል፦ ‘ይሖዋ ነፍስ ያጠፋውንና ምንዝር የፈጸመውን ዳዊትን ይቅር ብሎ በአንጻሩ ቀላል የሚመስል ጥፋት የፈጸመውን ሰው እንዲገደል ያዘዘው ለምንድን ነው?’ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ ሦስት ነገሮችን እንመልከት።

4. ዘፍጥረት 18:20, 21 እና ዘዳግም 10:17 በይሖዋ ፍርድ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩልን እንዴት ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንድ ታሪክ ሁሉንም ዝርዝር መረጃ የማይነግረን ጊዜ አለ። ለምሳሌ ዳዊት በፈጸመው ኃጢአት ከልቡ እንደተጸጸተ እናውቃለን። (መዝ. 51:2-4) ሆኖም የሰንበትን ሕግ የጣሰው ሰው ምን ዓይነት ሰው ነበር? በድርጊቱ ተጸጽቷል? ከዚያ በፊት የይሖዋን ሕግ ጥሶ ያውቅ ይሆን? አስቀድሞ የተሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች ችላ ብሎ ይባስ ብሎም አልቀበልም ብሎ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም አንድ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር አለ፦ ይሖዋ “ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል” አምላክ ነው። (ዘዳ. 32:4) ውሳኔ የሚያደርገው ሁሉንም መረጃ ግምት ውስጥ አስገብቶ ነው፤ ብዙውን ጊዜ የሰዎችን ፍርድ የሚያዛቡት አሉባልታዎች፣ ጭፍን ጥላቻ ወይም ሌሎች ነገሮች በእሱ ላይ ተጽዕኖ አያሳድሩም። (ዘፍጥረት 18:20, 21ን እና ዘዳግም 10:17ን አንብብ።) ስለ ይሖዋ እና ስለ መሥፈርቶቹ ይበልጥ በተማርን ቁጥር እሱ በሚሰጠው ፍርድ ይበልጥ እንተማመናለን። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ስናነብ በአሁኑ ጊዜ መልስ የማናገኝለት ጥያቄ ቢፈጠርብን እንኳ “ይሖዋ በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ” እንደሆነ እንድንተማመን የሚያደርግ በቂ እውቀት አለን።—መዝ. 145:17

5. አለፍጽምና በፍትሕ ስሜታችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? (“ አለፍጽምና የፍትሕ ስሜታችንን ያዛባዋል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

5 አለፍጽምና የፍትሕ ስሜታችን እንዲዛባ አድርጓል። አምላክ በመልኩ ስለፈጠረን ሁሉም ሰው ፍትሕ ሲያገኝ ማየት እንፈልጋለን። (ዘፍ. 1:26) ሆኖም ፍጹም ባለመሆናችን፣ ስለ አንድ ጉዳይ በደንብ እንደምናውቅ በሚሰማን ጊዜም እንኳ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ዮናስ ይሖዋ ለነነዌ ሰዎች ምሕረት ለማሳየት በመወሰኑ ምን ያህል እንደተበሳጨ አስታውሱ። (ዮናስ 3:10 እስከ 4:1) ውጤቱን ግን አስቡት። ንስሐ የገቡ ከ120,000 የሚበልጡ የነነዌ ሰዎች ሕይወታቸው ተረፈ! መጨረሻውንም አመለካከቱን ማስተካከል ያስፈለገው ዮናስ እንጂ ይሖዋ አይደለም።

6. ይሖዋ ውሳኔ ያደረገበትን ምክንያት ለእኛ የማብራራት ግዴታ የለበትም የምንለው ለምንድን ነው?

6 ይሖዋ ውሳኔ ያደረገበትን ምክንያት ለሰዎች የማብራራት ግዴታ የለበትም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በጥንት ዘመን የነበሩ አገልጋዮቹ ስላደረጋቸው ወይም ሊያደርጋቸው ስላሰባቸው ውሳኔዎች ያሳሰባቸውን ነገር እንዲገልጹ ፈቅዶላቸዋል። (ዘፍ. 18:25፤ ዮናስ 4:2, 3) ውሳኔውን ያደረገበትን ምክንያት ያብራራበት ጊዜም አለ። (ዮናስ 4:10, 11) ያም ቢሆን ይሖዋ እንዲህ ያለ ማብራሪያ ለእኛ የመስጠት ግዴታ የለበትም። ይሖዋ ፈጣሪያችን በመሆኑ፣ ውሳኔ ከማድረጉ በፊትም ሆነ በኋላ የእኛን ይሁንታ ማግኘት አያስፈልገውም።—ኢሳ. 40:13, 14፤ 55:9

መመሪያ ሲሰጣችሁ በይሖዋ ተማመኑ

7. ምን ነገር ፈተና ሊሆንብን ይችላል? ለምንስ?

7 ይሖዋ ምንጊዜም ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ በሙሉ ልባችን እንተማመናለን። ፈተና የሚሆንብን ግን ሰብዓዊ ወኪሎቹ ላይ እምነት መጣል ሊሆን ይችላል። ‘በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ውሳኔ የሚያደርጉት የይሖዋን መመሪያ ተከትለው ነው ወይስ በራሳቸው?’ ብለን የምናስብበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። በጥንት ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎችም እንደዚህ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል።  በአንቀጽ 3 ላይ የተጠቀሱትን ታሪኮች እንደ ምሳሌ እንመልከት። የሰንበትን ሕግ የጣሰው ሰው ዘመድ የሆነ አንድ ግለሰብ ‘እውነት ሙሴ የሞት ፍርዱን ያስተላለፈው ይሖዋን ጠይቆ ነው?’ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ዳዊት ሚስቱን የወሰደበት የሂታዊው የኦርዮ ጓደኞችም፣ ዳዊት ቅጣት የሚገባው ሆኖ ሳለ ሥልጣኑን ተጠቅሞ እንዳመለጠ ሊያስቡ ይችላሉ። ልናስታውሰው የሚገባ አንድ ሐቅ ግን አለ፦ ይሖዋ በሚያምናቸውና በሾማቸው ምድራዊ ወኪሎቹ የማንተማመን ከሆነ በእሱ እንተማመናለን ማለት አንችልም።

8. በዛሬው ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ የሚሠራበት መንገድ በሐዋርያት ሥራ 16:4, 5 ላይ ከተጠቀሰው ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

8 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የድርጅቱን ምድራዊ ክፍል የሚመራው ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ነው። (ማቴ. 24:45) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው የበላይ አካል ሁሉ ይህ ባሪያም በመላው ዓለም የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦችን ይመራል እንዲሁም ለጉባኤ ሽማግሌዎች መመሪያ ያስተላልፋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5ን አንብብ።) ሽማግሌዎች ደግሞ የተሰጣቸው መመሪያ በጉባኤዎች ውስጥ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ያደርጋሉ። ከድርጅቱ እና ከሽማግሌዎች የምናገኘውን መመሪያ በመታዘዝ በይሖዋ አሠራር እንደምንተማመን እናሳያለን።

9. ሽማግሌዎች የሚያደርጉትን ውሳኔ መደገፍ ከባድ የሚሆንብን መቼ ሊሆን ይችላል? ለምንስ?

9 አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች ያደረጉትን ውሳኔ መደገፍ ሊከብደን ይችላል። ለምሳሌ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ጉባኤዎችና ወረዳዎች እንደ አዲስ ተዋቅረዋል። የስብሰባ አዳራሾቻችንን የመያዝ አቅም በሚገባ ለመጠቀም ሲባል ሽማግሌዎች አንዳንድ አስፋፊዎችን ወደ ሌላ ጉባኤ እንዲዛወሩ ጠይቀዋቸዋል። እኛም ጉባኤ እንድንቀይር ተጠይቀን ከሆነ ወዳጆቻችንን እና ቤተሰቦቻችንን ትተን መሄድ ይከብደን ይሆናል። ሽማግሌዎች እያንዳንዱን አስፋፊ የት መመደብ እንዳለባቸው መለኮታዊ መመሪያ ያገኛሉ? አያገኙም። ይህ መሆኑም መመሪያን መከተል ተፈታታኝ እንዲሆንብን ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ሽማግሌዎች እንዲህ ያለ ውሳኔ ሲያደርጉ ይተማመንባቸዋል፤ እኛም ልንተማመንባቸው ይገባል። *

10. ዕብራውያን 13:17 እንደሚለው ከሽማግሌዎች ጋር መተባበር ያለብን ለምንድን ነው?

10 ሽማግሌዎች የሚያደርጉት ውሳኔ እኛ የምንመርጠው ዓይነት ባይሆንም እንኳ ከእነሱ ጋር መተባበርና ውሳኔያቸውን መደገፍ የሚኖርብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ስናደርግ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ እናበረክታለን። (ኤፌ. 4:2, 3) ጉባኤዎች የሚጠነክሩት፣ ሁሉም አስፋፊዎች የሽማግሌዎች አካል ለሚያደርገው ውሳኔ በትሕትና ሲገዙ ነው። (ዕብራውያን 13:17ን አንብብ።) ከዚህም በላይ ደግሞ በይሖዋ እንደምንተማመን የምናሳየው፣ እሱ አምኗቸው እኛን እንዲንከባከቡ ከሾማቸው ሰዎች ጋር ስንተባበር ነው።—ሥራ 20:28

11. ሽማግሌዎች በሚሰጡን መመሪያ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር ምን ይረዳናል?

11 ሽማግሌዎች ጉባኤውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሲወያዩ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት እንደሚጸልዩ ማስታወሳችን እነሱ በሚሰጡት መመሪያ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። በተጨማሪም ጉዳዩን የሚመለከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እና የይሖዋ ድርጅት ያወጣቸውን መመሪያዎች በጥንቃቄ እንደሚመረምሩ እናስታውስ። ልባዊ ፍላጎታቸው ይሖዋን ማስደሰትና የእሱን ሕዝብ ከሁሉ በተሻለ መንገድ መንከባከብ ነው። እነዚህ ታማኝ ወንዶች ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትን መንገድ በተመለከተ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንደሆኑ ያውቃሉ። (1 ጴጥ. 5:2, 3) እስቲ ይህን እውነታ አስቡ፦ በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የይሖዋ ሕዝቦች እውነተኛውን አንድ አምላክ በአንድነት እያመለኩ ነው። ይሖዋ ድርጅቱን ባይባርከው ኖሮ ይህ ሊሆን አይችልም ነበር!

12. ሽማግሌዎች አንድ ሰው ንስሐ መግባት አለመግባቱን ሲያጣሩ የትኞቹን ጉዳዮች ግምት ውስጥ ያስገባሉ?

12 ይሖዋ ለሽማግሌዎች የጉባኤውን ንጽሕና የመጠበቅ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ ሽማግሌዎች ግለሰቡ የጉባኤው አስፋፊ ሆኖ መቀጠል ይችል እንደሆነ እና እንዳልሆነ እንዲወስኑ ይሖዋ ይጠብቅባቸዋል። ሽማግሌዎች አንዱ የሚያደርጉት ነገር፣ ግለሰቡ በፈጸመው ኃጢአት ከልቡ መጸጸቱን ማጣራት ነው። ግለሰቡ ‘ንስሐ ገብቻለሁ’ ይል ይሆናል፤ ሆኖም የፈጸመውን ኃጢአት ከልቡ ተጸይፎታል? የሠራውን ኃጢአት ላለመድገም ቆርጧል? ወደ ስህተት የመራው መጥፎ ጓደኝነት ከሆነ ግንኙነቱን ሙሉ በሙሉ ለማቆም ፈቃደኛ ነው? ሽማግሌዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመው ጉዳዩን በጸሎት ያስቡበታል፤ እንዲሁም ስህተት የፈጸመው ግለሰብ፣ ላደረገው ነገር ያለውን ዝንባሌ ይገመግማሉ። ከዚያም ግለሰቡ ጉባኤ ውስጥ ይቀጥል አይቀጥል የሚለውን ይወስናሉ። አንዳንድ ጊዜ እንዲወገድ ይወስኑ ይሆናል።—1 ቆሮ. 5:11-13

13. አንድ ጓደኛችን ወይም ዘመዳችን ቢወገድ ምን ስጋት ሊገባን ይችላል?

13 በሽማግሌዎች ላይ ያለን እምነት የሚፈተነው መቼ ነው? የተወገደው ግለሰብ የቅርብ ጓደኛችን ወይም ዘመዳችን ካልሆነ የሽማግሌዎችን ውሳኔ መደገፍ አይከብደን ይሆናል። ሆኖም የተወገደው ግለሰብ ለእኛ የቅርብ ሰው ከሆነስ? ‘ሽማግሌዎች ጉዳዩን በደንብ አጣርተውታል?’ የሚል ጥርጣሬ ሊፈጠርብን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ‘የሰጡት ፍርድ ይሖዋ ጉዳዩን ቢያየው ኖሮ የሚሰጠው ዓይነት ፍርድ ነው?’ ብለን እናስብ ይሆናል። ታዲያ ላደረጉት ውሳኔ ተገቢውን አመለካከት ለመያዝ ምን ሊረዳን ይችላል?

14. ሽማግሌዎች ለእኛ ቅርብ የሆነ ሰው እንዲወገድ ሲወስኑ ምን ሊረዳን ይችላል?

14 ውገዳ የይሖዋ ዝግጅት እንደሆነ እንዲሁም ጉባኤውን አልፎ ተርፎም የተወገደውን ሰው እንደሚጠቅመው ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ንስሐ ያልገባ ኃጢአተኛ በጉባኤ ውስጥ እንዲቀጥል ቢፈቀድለት በሌሎች ላይም መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። (ገላ. 5:9) ከዚህም ሌላ የኃጢአቱን ክብደት መገንዘብ ሊከብደው ይችላል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚያስፈልገውን የአስተሳሰብና የድርጊት ለውጥ ለማድረግ አይነሳሳም። (መክ. 8:11) ሽማግሌዎች አንድ ሰው እንዲወገድ ሲወስኑ ይህን ኃላፊነታቸውን አክብደው እንደሚመለከቱት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በጥንቷ እስራኤል እንደነበሩት ዳኞች ሁሉ ‘የሚፈርዱት ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደሆነ’ ይገነዘባሉ።—2 ዜና 19:6, 7

ከአሁኑ በይሖዋ መታመናችን ለወደፊቱ ጊዜ የሚያሠለጥነን እንዴት ነው?

በታላቁ መከራ ወቅት በሚሰጠን መመሪያ ለመተማመንና ታዛዥ ለመሆን ምን ይረዳናል? (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በይሖዋ መመሪያዎች መተማመን ያለብን አሁን ነው የምንለው ለምንድን ነው?

15 ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረብን ስንሄድ በይሖዋ አሠራር ላይ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መተማመን ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም በታላቁ መከራ ወቅት የሚሰጡን መመሪያዎች በእኛ አመለካከት እንግዳ የሆኑ፣ ግራ የሚያጋቡ ወይም ምክንያታዊ የማይመስሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚያ ጊዜ ይሖዋ በግል ያነጋግረናል ብለን እንደማንጠብቅ የታወቀ ነው። መመሪያ እንደሚሰጠን የምንጠብቀው በሾማቸው ተወካዮቹ አማካኝነት ነው። ያ ወቅት፣ ስለተሰጠን መመሪያ ጥያቄ የምናነሳበት ወይም መመሪያውን በጥርጣሬ ዓይን የምናይበት ጊዜ አይደለም፤ ‘ይህ መመሪያ በእርግጥ ከይሖዋ የመጣ ነው? ወይስ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በራሳቸው ያደረጉት ውሳኔ ነው?’ ብለን የምናስብበት ጊዜ አይደለም። ታዲያ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ በሆነው በዚያ ጊዜ ምን ታደርጉ ይሆን? በአሁኑ ወቅት ለቲኦክራሲያዊ መመሪያዎች የምትሰጡት ምላሽ ያኔ የሚኖራችሁን አመለካከት ይጠቁማችኋል። በዛሬው ጊዜ በሚሰጠን መመሪያ የምንተማመንና ወዲያውኑ የምንታዘዝ ከሆነ በታላቁ መከራ ወቅትም ተመሳሳይ ነገር ማድረጋችን አይቀርም።—ሉቃስ 16:10

16. በይሖዋ ፍርድ ላይ ያለን እምነት በቅርቡ ሊፈተን የሚችለው እንዴት ነው?

16 የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ልናስብበት የሚገባ ሌላም አቅጣጫ አለ፤ ይህም በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ላይ ይሖዋ የሚሰጠው ፍርድ ነው። በአሁኑ ጊዜ፣ የማያምኑ ዘመዶቻችንን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ይሖዋን ማገልገል ይጀምራሉ የሚል ተስፋ አለን። በአርማጌዶን ወቅት ግን ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት በእነዚህ ሰዎች ዕጣ ፈንታ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ያደርጋል። (ማቴ. 25:31-33፤ 2 ተሰ. 1:7-9) የይሖዋ ምሕረት የሚገባው ይሄ ነው ወይስ ያ የሚለውን መወሰን የእኛ ቦታ አይደለም። (ማቴ. 25:34, 41, 46) ታዲያ ይሖዋ ያኔ በሚሰጠው ፍርድ እንተማመናለን? ወይስ ማሰናከያ ይሆንብን ይሆን? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ወደፊት ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን እንድንችል ከአሁኑ በእሱ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከራችን በጣም አስፈላጊ ነው።

17. በዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ላይ ይሖዋ ከሚያስተላልፈው ፍርድ ምን ጥቅሞች እናገኛለን?

17 የይሖዋ ፍርድ ያስገኘውን ውጤት በአዲሱ ዓለም ውስጥ ስናይ ምን እንደሚሰማን አስቡት። የሐሰት ሃይማኖት አይኖርም፤ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የሰው ልጆች እንዲማቅቁና ይህ ነው የማይባል ሥቃይ እንዲደርስባቸው ያደረገው ስግብግብ የንግድ ሥርዓትና የፖለቲካው ሥርዓትም ተጠራርገው ጠፍተዋል። በጤና ችግር፣ በእርጅና ወይም የምንወደውን ሰው በሞት በማጣታችን ምክንያት በየቀኑ አንደቆስም። ሰይጣንና አጋንንቱ ለአንድ ሺህ ዓመት ይታሰራሉ። ዓመፃቸው ያስከተለው ጉዳት ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። (ራእይ 20:2, 3) በይሖዋ አሠራር በመታመናችን ያን ጊዜ ምን ያህል አመስጋኝ እንደምንሆን አስቡት!

18. በዘኁልቁ 11:4-6 እና 21:5 ላይ ከተጠቀሰው የእስራኤላውያን ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

18 በአዲሱ ዓለም ውስጥስ? በይሖዋ አሠራር ላይ ያለንን እምነት የሚፈትኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆን? እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ያጋጠማቸውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንዳንዶች በግብፅ ይበሉት የነበረው ምግብ ስለናፈቃቸው ማጉረምረም ጀመሩ፤ ይባስ ብሎም ይሖዋ የሰጣቸውን መና ጠሉት። (ዘኁልቁ 11:4-6 እና 21:5ን አንብብ።) እኛስ ታላቁ መከራ ካበቃ በኋላ እንዲህ ዓይነት ስሜት ይመጣብን ይሆን? ምድርን ማጽዳትና ወደ ገነትነት መቀየር ምን ያህል ሥራ እንደሚጠይቅ አናውቅም። ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀንና መጀመሪያ አካባቢ አንዳንድ አመቺ ያልሆኑ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግን እንጠብቃለን። ታዲያ ይሖዋ በዚያ ጊዜ በሚያደርግልን ዝግጅት ላይ ለማማረር እንፈተን ይሆን? አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፦ በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ ዝግጅቶች አድናቆት ካለን ያን ጊዜ ደግሞ ይበልጥ አመስጋኞች እንሆናለን።

19. የዚህን ርዕስ ዋና ዋና ነጥቦች ጠቅለል አድርገህ ግለጽ።

19 የይሖዋ አሠራር ምንጊዜም ትክክል ነው። ይህን እውነታ ከልባችን ልናምንበት ይገባል። ይሖዋ መመሪያውን እንዲያስፈጽሙ የሚተማመንባቸውን ሰዎችም ልንተማመንባቸው ይገባል። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ መቼም ቢሆን አንዘንጋ፦ “ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።”—ኢሳ. 30:15

መዝሙር 98 ቅዱሳን መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው

^ አን.5 ይህ ርዕስ በይሖዋና በምድራዊ ወኪሎቹ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝበናል። በተጨማሪም ይህን ማድረጋችን በአሁኑ ጊዜ እንዴት እንደሚጠቅመን እንዲሁም ወደፊት ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች እንዴት እንደሚያዘጋጀን እንመለከታለን።

^ አን.9 አንዳንድ ጊዜ አንድ ግለሰብ ወይም ቤተሰብ ባለበት ጉባኤ እንዲቀጥል የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የኅዳር 2002 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን “የጥያቄ ሣጥን” ተመልከት።