በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 9

ሌሎችን በማገልገል የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ

ሌሎችን በማገልገል የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ

“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—ሥራ 20:35

መዝሙር 17 “እፈልጋለሁ”

ማስተዋወቂያ *

1. የይሖዋ ሕዝቦች ምን ዓይነት ግሩም መንፈስ እያሳዩ ነው?

 ከብዙ ዘመናት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገረ አንድ ትንቢት አለ፤ ትንቢቱ የአምላክ ሕዝቦች በኢየሱስ አመራር ሥር ሆነው ይሖዋን ለማገልገል ‘በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን እንደሚያቀርቡ’ ይናገራል። (መዝ. 110:3) ይህ ትንቢት በዛሬው ጊዜ በሚገባ እየተፈጸመ ነው። ቀናተኛ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ ላይ በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዓታት ያሳልፋሉ። ይህን የሚያደርጉት በገዛ ፈቃዳቸውና መሥዋዕትነት እየከፈሉ ጭምር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለእምነት ባልንጀሮቻቸው አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ለማድረግ ጊዜያቸውን ይሰጣሉ። የተሾሙ ወንድሞች የስብሰባ ክፍሎችን በመዘጋጀትና ለእምነት ባልንጀሮቻቸው እረኝነት በማድረግ ብዙ ሰዓታት ያሳልፋሉ። ይህን ሁሉ እንዲያከናውኑ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ፍቅር ነው፤ ለይሖዋና ለባልንጀሮቻቸው ያላቸው ፍቅር።—ማቴ. 22:37-39

2. በሮም 15:1-3 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቷል?

2 ኢየሱስ ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት በማስቀደም ግሩም ምሳሌ ትቷል። እኛም የእሱን አርዓያ ለመከተል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። (ሮም 15:1-3ን አንብብ።) የእሱን ምሳሌ የሚከተሉ ሁሉ ብዙ ጥቅም ያገኛሉ። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል።—ሥራ 20:35

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ ኢየሱስ ሌሎችን ለማገልገል ሲል ምን መሥዋዕት እንደከፈለ እንዲሁም የእሱን ምሳሌ እንዴት መከተል እንደምንችል እንመለከታለን። ከዚህም ሌላ ሌሎችን የማገልገል ፍላጎታችንን ለማሳደግ ምን ማድረግ እንደምንችል እንወያያለን።

የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ

ኢየሱስ ደክሞት የነበረ ቢሆንም ብዙ ሕዝብ ወደ እሱ ሲመጣ ምን አድርጓል? (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)

4. ኢየሱስ የሌሎችን ፍላጎት ከራሱ ያስቀደመው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ ደክሞት በነበረ ጊዜም እንኳ ሌሎችን ረድቷል። እስቲ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት፤ በቅፍርናሆም አቅራቢያ ሳይሆን አይቀርም ከተራራ ሲወርድ ብዙ ሰዎች ሊያገኙት መጡ። ታዲያ ኢየሱስ ምን ተሰምቶት ይሆን? ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሮ ነበር። ስለዚህ በጣም ደክሞት መሆን አለበት፤ ሆኖም በሕዝቡ መካከል ያሉትን ድሆችና የታመሙ ሰዎች ሲመለከት አንጀቱ አልቻለም። ሕዝቡን መፈወስ ብቻ ሳይሆን ንግግር ሰጣቸው፤ ይህ ንግግር እስከ ዛሬ ከቀረቡት ሁሉ ቀስቃሽ የሆነውና የተራራው ስብከት ተብሎ የሚጠራው ንግግር ነው።—ሉቃስ 6:12-20

ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)

5. የቤተሰብ ራሶች በሚደክማቸው ጊዜ እንደ ኢየሱስ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

5 የቤተሰብ ራሶች ኢየሱስን እየመሰሉ ያሉት እንዴት ነው? እስቲ ይህን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናችሁ ሣሉ፦ አንድ የቤተሰብ ራስ ሲለፋ ውሎ ድክም ብሎት ወደ ቤት መጣ። በዚያ ምሽት የሚያደርጉትን የቤተሰብ አምልኮ ለመሰረዝ ተፈትኗል፤ ሆኖም ይሖዋ ጥናቱን ለመምራት የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠው ጸለየ። ይሖዋም ለጸሎቱ ምላሽ ስለሰጠው ጥናቱ በፕሮግራማቸው መሠረት ተካሄደ። ልጆቹ በዚያ ምሽት አንድ አስፈላጊ ቁም ነገር ይማራሉ፤ ይኸውም ወላጆቻቸው ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት ለመንፈሳዊ ነገሮች እንደሆነ ይገነዘባሉ።

6. ኢየሱስ ብቻውን መሆን የሚፈልግበትን ጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ሲል መሥዋዕት ያደረገው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ ብቻውን መሆን የሚፈልግበትን ጊዜ ለሌሎች ሰጥቷል። ኢየሱስ ወዳጁ የሆነው አጥማቂው ዮሐንስ እንደተገደለ ሲሰማ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስብ። በጣም አዝኖ መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ [የዮሐንስን ሞት] ሲሰማ ብቻውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍሮ ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ።” (ማቴ. 14:10-13) ብቻውን መሆን የፈለገበትን ምክንያት መረዳት አይከብደንም። ብዙ ሰዎች ሐዘን ሲያጋጥማቸው ብቻቸውን መሆን ይፈልጋሉ። ኢየሱስ ግን እንደፈለገው ብቻውን መሆን አልቻለም። እጅግ ብዙ ሰዎች እሱ ሊሄድበት ወዳሰበው ገለል ያለ ስፍራ ቀድመውት መጡ። ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? ሕዝቡ ያሉበትን ችግር ስላስተዋለ “በጣም አዘነላቸው።” ሕዝቡ መንፈሳዊ ማበረታቻ በጣም እንደሚያስፈልጋቸው አስተውሎ ነበር፤ ደግሞም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ወዲያውኑ አድርጎላቸዋል። እንዲያውም የተወሰኑ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን ‘ብዙ ነገር ያስተምራቸው ጀመር።’—ማር. 6:31-34፤ ሉቃስ 9:10, 11

7-8. አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎች እርዳታ በሚያስፈልግበት ጊዜ ኢየሱስን እየመሰሉ ያሉት እንዴት ነው?

7 አፍቃሪ ሽማግሌዎች ኢየሱስን እየመሰሉ ያሉት እንዴት ነው? ለእኛ ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ሽማግሌዎች የሚያከናውኑትን ሥራ በጣም እናደንቃለን! የሚያከናውኑት ሥራ በአብዛኛው በጉባኤ ውስጥ ባሉት ዘንድ የሚታይ አይደለም። ለምሳሌ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚጠይቅ ሁኔታ ሲያጋጥም የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባላት ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ይሯሯጣሉ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለ አጣዳፊ ሁኔታ የሚያጋጥመው በሌሊት ነው። ሆኖም እነዚህ ውድ ሽማግሌዎችና ቤተሰቦቻቸው ከራሳቸው ይልቅ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ፍላጎት ያስቀድማሉ፤ ይህን እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው፣ ችግር ላይ ለወደቀው ወንድማቸው ወይም እህታቸው ያላቸው ርኅራኄ ነው።

8 በተጨማሪም ሽማግሌዎች በስብሰባ አዳራሾችና በሌሎች ሕንፃዎች ግንባታ እንዲሁም በአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራዎች ይካፈላሉ። በየጉባኤያችን ያሉት ሽማግሌዎች እኛን በማስተማር፣ በማበረታታትና በመደገፍ ስለሚያሳልፉት ጊዜም አስቡ። በእርግጥም እነዚህ ወንድሞችና ቤተሰቦቻቸው ልባዊ ምስጋናችን ይገባቸዋል። ይሖዋ የሚያሳዩትን መንፈስ እንዲባርክ እንመኛለን! በእርግጥ እንደ ማንኛችንም ሁሉ ሽማግሌዎችም ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ቤተሰባቸውን ለመንከባከብ የሚሆን ጊዜ እስኪያጡ ድረስ እንዲህ ባሉት ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መጠመድ የለባቸውም።

የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?

9. በፊልጵስዩስ 2:4, 5 መሠረት ሁሉም ክርስቲያኖች ምን ዓይነት አስተሳሰብ ሊያዳብሩ ይገባል?

9 ፊልጵስዩስ 2:4, 5ን አንብብ። ሁላችንም ሽማግሌዎች እንዳልሆንን የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሁላችንም ኢየሱስ ካሳየው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የምንማረው ነገር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “የባሪያን መልክ ያዘ” ይላል። (ፊልጵ. 2:7) ይህ ጥቅስ የያዘውን ትምህርት ለማሰብ እንሞክር። የሚወደድ ባሪያ ወይም አገልጋይ ጌታውን ማስደሰት የሚችልበትን አጋጣሚ ይፈልጋል። እኛም የይሖዋ ባሪያና የወንድሞቻችን አገልጋይ እንደመሆናችን መጠን ምኞታችን ለይሖዋም ሆነ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት ማከናወን ነው። ከዚህ በታች የቀረቡት ሐሳቦች ይህን ለማድረግ ይረዱናል።

10. ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?

10 አመለካከትህን ገምግም። ራስህን እንዲህ እያልክ መጠየቅ ትችላለህ፦ ‘ሌሎችን ለመርዳት ስል የራሴን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነኝ? ለምሳሌ አንድን በዕድሜ የገፉ ወንድም ሄጄ እንድጠይቅ ወይም አንዲትን አረጋዊት እህት ወደ ስብሰባዎች እንድወስድ ብጠየቅ ምን አደርጋለሁ? የትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ የሚያጸዱ ወይም የስብሰባ አዳራሽ የሚጠግኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሲያስፈልጉ ወዲያውኑ ራሴን አቀርባለሁ?’ ይሖዋ ጊዜያችንን እና ያለንን ነገር ሳንሰስት ሌሎችን ለመርዳት ስንጠቀምበት ይደሰታል፤ ደግሞም እነዚህን ነገሮች ለእሱ ለመስጠት ቃል ገብተናል። በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልገን ቢሰማን ምን ማድረግ እንችላለን?

11. ጸሎት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ለማዳበር የሚረዳን እንዴት ነው?

11 ወደ ይሖዋ ከልብህ ጸልይ። ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ብትገነዘብም አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ተነሳሽነት ባይኖርህስ? ሁኔታህ እንዲህ ከሆነ ወደ ይሖዋ ከልብህ ጸልይ። በሐቀኝነት ስሜትህን ለይሖዋ ንገረው። ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርብህና ኃይል እንድታገኝ’ ጠይቀው።—ፊልጵ. 2:13

12. የተጠመቁ ወጣት ወንድሞች ጉባኤ ውስጥ የትኛውን ክፍተት መሙላት ይችላሉ?

12 የተጠመቅህ ወጣት ወንድም ከሆንክ ጉባኤውን ይበልጥ የማገልገል ፍላጎት ለማዳበር እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። በአንዳንድ አገሮች የጉባኤ አገልጋዮች ቁጥር ከሽማግሌዎች ያንሳል፤ ብዙዎቹ የጉባኤ አገልጋዮች ደግሞ በመካከለኛው ዕድሜ የሚገኙ ወይም ከዚያ ከፍ ያሉ ናቸው። ድርጅቱ በቁጥር ይበልጥ እያደገ ሲሄድ የይሖዋን አገልጋዮች የሚንከባከቡ ተጨማሪ ወንድሞች ያስፈልጋሉ። በምትፈለግበት ቦታ ሁሉ ለማገልገል ፈቃደኛ ከሆንክ ደስተኛ ትሆናለህ። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ካደረግህ ይሖዋን ታስደስታለህ፤ ጥሩ ስም ታተርፋለህ እንዲሁም ሌሎችን መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ ታጣጥማለህ።

የይሁዳ ክርስቲያኖች የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ፔላ ከተማ ሸሹ። ቀደም ብለው ወደ ከተማዋ የገቡት ወንድሞች በኋላ ላይ ለመጡ የእምነት ባልንጀሮቻቸው የእርዳታ ምግብ እያከፋፈሉ ነው (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13-14. ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን? (ሽፋኑን ተመልከት።)

13 ሌሎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር በንቃት ተከታተል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ዕብራውያን ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል መክሯቸዋል፦ “መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታልና።” (ዕብ. 13:16) ይህ በጣም ጠቃሚ ምክር ነበር! በይሁዳ የነበሩ ክርስቲያኖች ይህ ደብዳቤ ከደረሳቸው ብዙም ሳይቆይ ቤታቸውን፣ ንግዳቸውን እንዲሁም የማያምኑ ዘመዶቻቸውን ትተው ‘ወደ ተራሮች ለመሸሽ’ ተገድደዋል። (ማቴ. 24:16) በዚያ ወቅት እርስ በርስ መረዳዳት የሚጠይቅ ሁኔታ እንደተፈጠረ አይካድም። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ፣ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን እንዲያካፍሉ ጳውሎስ የሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ያደርጉ ከነበረ አዲሱን ሁኔታ መልመድ እንደማይከብዳቸው ግልጽ ነው።

14 ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ምን እንደሚያስፈልጋቸው ሁልጊዜ ላይነግሩን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም ባለቤቱን በሞት አጥቷል እንበል። ወንድማችን ከምግብ፣ ከትራንስፖርት ወይም ከቤት ውስጥ ሥራዎች ጋር በተያያዘ እገዛ ያስፈልገው ይሆን? ይህ ወንድም፣ እንዳያስቸግረን ብሎ ምንም አይለን ይሆናል። ሆኖም ቅድሚያውን ወስደን የሚያስፈልገውን ድጋፍ ብናደርግለት በጣም ይደሰት ይሆናል። የሚያስፈልገውን ነገር ሌሎች እንደሚያደርጉለት ወይም እርዳታ ሲያስፈልገው እንደሚጠይቀን ልናስብ አይገባም። ‘እኔ በእሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን ቢደረግልኝ ደስ ይለኛል?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ።

15. ሌሎችን ለማገልገል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 የምትቀረብ ሁን። በየጉባኤዎቻችን ሌሎችን ለመርዳት ሁልጊዜ ዝግጁ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች አሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች መቼም ቢሆን እያስቸገርናቸው እንደሆነ እንዲሰማን አያደርጉም። አንድ ችግር ሲያጋጥመን እንደሚደርሱልን እንተማመናለን። ደግሞም እኛም እንደ እነሱ ብንሆን ደስ ይለናል! በ40ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አላን የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ የሚቀረብ ሰው መሆን ይፈልጋል። አላን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ ሥራ የሚበዛበት ሰው ነበር፤ ሆኖም በሁሉም ዕድሜ የሚገኙ ሰዎች ወደ እሱ ይቀርቡ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሳይሳቀቁ ይጠይቁት ነበር። በጥልቅ እንደሚያስብላቸው ይሰማቸው ነበር። እንደ ኢየሱስ ዓይነት ሰው መሆን ከልቤ የምፈልገው ነገር ነው፤ የምቀረብ፣ አፍቃሪና አሳቢ በመሆኔ ብታወቅ ደስ ይለኛል።”

16. መዝሙር 119:59, 60 የሚለንን ማድረጋችን የኢየሱስን ምሳሌ በጥብቅ ለመከተል የሚረዳን እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በተሟላ መንገድ መከተል ባንችል ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። (ያዕ. 3:2) አንድ የሥነ ጥበብ ተማሪ የአስተማሪውን ሥራ ፍጹም በሆነ መንገድ አስመስሎ መሥራት እንደማይችል የታወቀ ነው። ሆኖም ተማሪው ከስህተቱ ሲማርና የአስተማሪውን ሥራ በተቻለው መጠን ለመከተል ጥረት ሲያደርግ እየተሻሻለ ይሄዳል። እኛም በተመሳሳይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የተማርነውን ነገር በተግባር የምናውል እንዲሁም ያሉብንን ድክመቶች ለማሻሻል የቻልነውን ያህል የምንጥር ከሆነ የኢየሱስን አርዓያ ስኬታማ በሆነ መንገድ መከተል እንችላለን።መዝሙር 119:59, 60ን አንብብ።

የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚያስገኘው ጥቅም

ሽማግሌዎች እንደ ኢየሱስ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ለወጣቶች ምሳሌ መሆን ይችላሉ (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት) *

17-18. ኢየሱስ የተወውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ስንከተል ምን ጥቅም እናገኛለን?

17 የምናሳየው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ወደ ሌሎችም ይጋባል። ቲም የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤያችን ውስጥ እድገት አድርገው የጉባኤ አገልጋይ የሆኑ ወጣት ወንድሞች አሉ፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም ዕድሜያቸው በጣም ትንሽ ነው። እንዲህ እንዲያደርጉ የረዳቸው አንዱ ነገር ሌሎች ያሳዩትን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ መመልከታቸው ነው። እነዚህ ወጣት ወንድሞች ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ጉባኤያችንን ይረዳሉ፤ እንዲሁም ለሽማግሌዎች ድጋፍ ይሰጣሉ።”

18 የምንኖረው ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። የይሖዋ አገልጋዮች ግን ይለያሉ። ኢየሱስ ያሳየው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፤ የእሱን ምሳሌ ለመከተልም ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። የእሱን ምሳሌ ፍጹም በሆነ መንገድ መከተል እንደማንችል የታወቀ ነው። ሆኖም ‘ፈለጉን በጥብቅ መከተል’ እንችላለን። (1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስ የተወውን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ለመከተል የቻልነውን ያህል የምንጥር ከሆነ የይሖዋን ሞገስ ማግኘት የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን።

መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ

^ አን.5 ኢየሱስ ምንጊዜም የሌሎችን ጥቅም ከራሱ ያስቀድም ነበር። በዚህ ርዕስ ውስጥ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመለከታለን። በተጨማሪም ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ የተወውን ምሳሌ መከተላችን ምን ዘላቂ ጥቅሞች እንደሚያስገኝልን እናያለን።

^ አን.57 የሥዕሉ መግለጫ፦ ዳን የተባለ ወጣት ወንድም፣ ሁለት የጉባኤ ሽማግሌዎች አባቱን ሆስፒታል መጥተው ሲጠይቁት ይመለከታል። ዳን ሽማግሌዎቹ ያሳዩት ፍቅር ነክቶታል። እሱም በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎችን ለመርዳት ተነሳሳ። ቤን የተባለ ሌላ ወጣት ወንድም ደግሞ ዳን የሚያሳየውን አሳቢነት ተመለከተ። የዳን ምሳሌ እሱም በአዳራሽ ጽዳት ሥራ እንዲካፈል አነሳሳው።