በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ከሕክምና የሚበልጥ ነገር አገኘሁ

ከሕክምና የሚበልጥ ነገር አገኘሁ

“እየነገራችሁኝ ያላችሁት እኮ ከልጅነቴ ጀምሮ ስጓጓለት የነበረውን ነገር ነው!” በደስታ ይህን ሐሳብ የተናገርኩት በ1971 ላገኘኋቸው ሁለት ታካሚዎች ነበር። በወቅቱ በሕክምና መስክ ተመርቄ የራሴን ክሊኒክ ገና መክፈቴ ነበር። እነዚያ ታካሚዎች እነማን ናቸው? ከልጅነቴ ጀምሮ ስጓጓለት የነበረው ነገርስ ምንድን ነው? ያን ዕለት ያደረግነው ውይይት በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጠውን ነገር ያስቀየረኝ እንዴት እንደሆነና በቅርቡ የልጅነት ሕልሜ እውን እንደሚሆን የማምነው ለምን እንደሆነ እስቲ ልንገራችሁ።

በ1941 ፓሪስ፣ ፈረንሳይ ውስጥ ተወለድኩ፤ ቤተሰቦቼ ብዙ ገንዘብ አልነበራቸውም። ትምህርት እወድ ነበር፤ በአሥር ዓመቴ ሳንባ ነቀርሳ በመታመሜ ትምህርቴን ለማቋረጥ ስገደድ ምን ያህል እንዳዘንኩ አስቡት። ሐኪሞች ሳንባዬ እስኪያገግም ድረስ ከቤት እንዳልወጣ ነገሩኝ። ስለዚህ ለበርካታ ወራት ጊዜዬን ያሳለፍኩት መዝገበ ቃላት በማንበብና በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ከሬዲዮ ሶርቦን የሚተላለፉ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን በማዳመጥ ነው። በመጨረሻ ሐኪሜ ከሕመሜ እንደዳንኩና ወደ ትምህርቴ መመለስ እንደምችል ሲነግረኝ በጣም ነው የተደሰትኩት። ‘እነዚህ ሐኪሞች ትልቅ ሥራ ነው የሚሠሩት!’ ብዬ አሰብኩ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ፣ የታመሙ ሰዎችን ማዳን ሕልሜ ሆነ። አባቴ ወደፊት ምን መሆን እንደምፈልግ ሲጠይቀኝ ሁሌም “ሐኪም መሆን ነው የምፈልገው” ብዬ እመልስለት ነበር። ለሕክምና ሙያ ትልቅ ቦታ መስጠት የጀመርኩት ከዚያ ጊዜ አንስቶ ነው።

ሳይንስ ወደ አምላክ እንድቀርብ አደረገኝ

በቤተሰብ ደረጃ ካቶሊኮች ነበርን። ሆኖም ስለ አምላክ የማውቀው ብዙ ነገር አልነበረም፤ ደግሞም በርካታ መልስ ያላገኘሁላቸው ጥያቄዎች ነበሩ። ሕይወት በፍጥረት እንደተገኘ ያመንኩት ራሱ፣ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ሕክምና ማጥናት ከጀመርኩ በኋላ ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ በአጉሊ መነጽር የዕፀዋት ሴል ያየሁበትን ጊዜ አልረሳውም። ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ በሚኖርበት ወቅት የሴሉ ክፍሎች ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ነገር ሳይ በጣም ተገረምኩ። ሳይቶፕላዝም (የሴል ውስጠኛ ክፍል ነው) የማየት አጋጣሚም አግኝቼ ነበር፤ ይህ የሴል ክፍል ከጨው ጋር ሲገናኝ ኩምሽሽ ይላል፤ ንጹሕ ውኃ ውስጥ ሲገባ ደግሞ መጠኑ ይጨምራል። ይህን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሂደቶች ሕይወት ያላቸው ነገሮች ውጫዊ አካባቢያቸው ሲቀየር ሁኔታውን እንዲለምዱት ያስችሏቸዋል። እያንዳንዱ ሴል ያለውን አስደናቂ ውስብስብነት ስመለከት ሕይወት በፍጹም እንዲሁ በአጋጣሚ ሊገኝ እንደማይችል ተረዳሁ።

የሁለተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪ ሳለሁ አምላክ እንዳለ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ አገኘሁ። ስለ ሰውነት ክፍሎች ስናጠና፣ ክንዳችን ጣቶቻችንን ለማጠፍና ለመዘርጋት የሚያስችለን እንዴት እንደሆነ ተማርን። ጡንቻዎቻችን እና ጅማቶቻችን ቦታቸውን ይዘው የተቀመጡበት መንገድ ድንቅ የምሕንድስና ጥበብ የተንጸባረቀበት ነው። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፦ ክንዳችን ላይ ያለውን ጡንቻ እና የጣታችንን ሁለተኛ አጥንት የሚያገናኘው ጅማት ለሁለት ይከፈላል፤ ከዚያም በመካከላቸው ክፍተት ይፈጠራል፤ ወደ ጣታችን ጫፍ የሚሄዱ ሌሎች ጅማቶች በዚህ ክፍተት በኩል ስለሚያልፉ ቦታቸውን ስተው አይወጡም። በተጨማሪም ጅማቶቻችንን ከጣቶቻችን ጋር አጣብቆ የሚይዛቸው ነገር አለ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ባይኖሩ ኖሮ እጃችን ላይ ያሉት ጅማቶች፣ በጣም እንደተወጠረ የቀስት ማስፈንጠሪያ ይሆኑ ነበር። በሰው አካል ላይ የሚታየው ንድፍ፣ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ አለ ብዬ እንዳምን አደረገኝ።

ልጅ ስለሚወለድበት ሂደት ሳጠና ደግሞ ለሕይወት ፈጣሪ ያለኝ አድናቆት ጨመረ። ልጁ በእናቱ ማህፀን ውስጥ ሳለ በእትብት አማካኝነት ከእናቱ ኦክስጅን ያገኛል። በመሆኑም በሳንባው ውስጥ ያሉ አልቪዮላይ የተባሉ ፊኛ መሰል ጥቃቅን ከረጢቶች በዚህ ወቅት አየር አይዙም። ልጁ የሚወለድበት ጊዜ ሲቃረብ እነዚህ አልቪዮላይ የሚባሉት ነገሮች ውስጣቸውን ሰርፋክታንት በተባለ ፈሳሽ ነገር ይሸፍናሉ። ከዚያም ልጁ ተወልዶ የመጀመሪያ ትንፋሹን ሳብ ሲያደርግ አስደናቂ ተከታታይ ሂደቶች ይከናወናሉ። በሕፃኑ ልብ ላይ ያለ ቀዳዳ ይደፈናል፤ ይህም ደም ወደ ሳንባው መሄድ እንዲጀምር ያደርጋል። በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ አልቪዮላይ የተባሉት የአየር ከረጢቶች በፍጥነት አየር መያዝ ሲጀምሩ እርስ በርሳቸው እንዳይጣበቁ የሚረዳቸው ሰርፋክታንት የተባለው ነገር ነው። በዚህ መንገድ ሕፃኑ በቅጽበት በራሱ መተንፈስ ይጀምራል።

እንዲህ ያሉ አስደናቂ ነገሮች የሠራውን ፈጣሪ ማወቅ ስለፈለግኩ መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ማንበብ ጀመርኩ። ከ3,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት አምላክ ከእስራኤል ብሔር ጋር ቃል ኪዳን ሲጋባ የሰጣቸው የንጽሕና ሕጎች በጣም አስደነቁኝ። አምላክ እስራኤላውያንን ዓይነ ምድራቸውን እንዲቀብሩ፣ አዘውትረው በውኃ እንዲታጠቡ እንዲሁም የተላላፊ በሽታ ምልክቶች ያሳየ ሰው ካለ ከሌሎች ተገልሎ እንዲቆይ እንዲያደርጉ አዟቸው ነበር። (ዘሌ. 13:50፤ 15:11፤ ዘዳ. 23:13) መጽሐፍ ቅዱስ በሽታ ስለሚተላለፍበት መንገድ የያዘውን ሐሳብ ሳይንቲስቶች የደረሱበት ገና በቅርብ መቶ ዓመታት ውስጥ ነው። የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ላይ የሚገኙት ሕጎችም ለመላው ብሔር ጤንነት አስተዋጽኦ እንዳደረጉ አስተዋልኩ። (ዘሌ. 12:1-6፤ 15:16-24) ፈጣሪ ለእስራኤላውያን እንዲህ ያሉ ሕጎችን የሰጠው ለደህንነታቸው አስቦ እንደሆነ እንዲሁም ትእዛዛቱን የሚከተሉትን ሰዎች እንደሚባርክ ተረዳሁ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ያስጻፈው መጽሐፍ እንደሆነ አመንኩ፤ በእርግጥ የዚህን አምላክ ስም ገና አላወቅሁትም ነበር።

ከባለቤቴ ጋር ተዋወቅን፤ ስለ ይሖዋም አወቅሁ

እኔና ሊዲ በሠርጋችን ቀን ሚያዝያ 3, 1965

ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሕክምና ትምህርቴን እየተከታተልኩ ሳለ ሊዲ ከምትባል ወጣት ጋር ተገናኘንና ተዋደድን። በ1965 የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን እያጋመስኩ ሳለ ትዳር መሠረትን። በ1971 ከስድስቱ ልጆቻችን መካከል ሦስቱ ተወልደው ነበር። ሊዲ በሕክምና ሥራዬም ሆነ በቤተሰብ ሕይወታችን በጣም ጥሩ አጋር ሆናኛለች።

ለሦስት ዓመታት ሆስፒታል ውስጥ ከሠራሁ በኋላ የራሴን ክሊኒክ ከፈትኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አንድ ባልና ሚስት፣ ማለትም መግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸው ሁለት ታካሚዎች ለሕክምና እኔ ጋ መጡ። ለባልየው የመድኃኒት ማዘዣ መጻፍ ስጀምር ሚስትየው “ዶክተር፣ እባክህ ደም ያለበት መድኃኒት አትዘዝለት” አለችኝ። እኔም ገርሞኝ “ኧረ? ለምን?” አልኳት። “እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ነን” ብላ መለሰችልኝ። ስለ ይሖዋ ምሥክሮችም ሆነ ከደም ጋር በተያያዘ ስላላቸው አቋም ከዚያ በፊት ሰምቼ አላውቅም ነበር። ሚስትየው መጽሐፍ ቅዱሷን አውጥታ ደም የማይወስዱበትን ምክንያት የሚያስረዳ ጥቅስ አነበበችልኝ። (ሥራ 15:28, 29) ከዚያም እሷና ባሏ፣ የአምላክ መንግሥት ወደፊት ምን እንደሚያመጣ እንዲሁም መከራን፣ ሕመምን እና ሞትን እንደሚያስወግድ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩኝ። (ራእይ 21:3, 4) “እየነገራችሁኝ ያላችሁት እኮ ከልጅነቴ ጀምሮ ስጓጓለት የነበረውን ነገር ነው!” ብዬ በደስታ መለስኩላቸው። “ሐኪም የሆንኩት የሰዎችን ሥቃይ ለማቅለል ነው” አልኳቸው። በጣም ስለተደሰትኩ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ተወያየን። ከባልና ሚስቱ ጋር ስንለያይ ከዚያ በኋላ ካቶሊክ እንደማልሆን ወስኜ ነበር። ደግሞም ሥራዎቹን የማደንቅለት ፈጣሪ “ይሖዋ” የሚል ስም እንዳለው አወቅሁ!

ከእነዚያ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ጋር ሦስት ጊዜ ክሊኒኬ ውስጥ ተገናኘን፤ በሦስቱም ጊዜያት ከአንድ ሰዓት በላይ ተወያይተናል። ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንድንወያይ ስለፈለግሁ ቤቴ ጋበዝኳቸው። ሊዲ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ወቅት አብራን ለመሆን ብትስማማም ከዚያ በፊት የተማርናቸው አንዳንድ የካቶሊክ ትምህርቶች ስህተት መሆናቸውን መቀበል አልፈለገችም ነበር። ስለዚህ አንድን የካቶሊክ ቄስ ቤታችን ጋበዝኩት። መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ተጠቅመን ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ትምህርቶች ስንከራከር አመሸን። በዚያን ዕለት ያደረግነው ውይይት የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንደሚያስተምሩ ሊዲን አሳመናት። ከዚያ በኋላ ለይሖዋ ያለን ፍቅር እያደገ ስለሄደ በ1974 ሁለታችንም ተጠመቅን።

ይሖዋን ማስቀደም

አምላክ ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ መማሬ በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ በምሰጠው ነገር ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ይሖዋን ማገልገል በእኔና በሊዲ ሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ ያዘ። ልጆቻችንን በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መሠረት ለማሳደግ ቆርጠን ነበር። ይሖዋን እና ባልንጀራችንን እንድንወድ የተሰጠንን ትእዛዝ በቤተሰብ ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረጋችን አንድነታችንን አጠናክሮታል።—ማቴ. 22:37-39

እኔና ሊዲ የቀድሞውን ጊዜ መለስ ብለን ስናስብ ከልጆቻችን ጋር በተያያዘ አንድ አቋም ያለን መሆናችን በእነሱ ላይ የፈጠረውን ስሜት እያስታወስን እንስቃለን። ልጆቻችን፣ ኢየሱስ “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን” በማለት የሰጠው ትእዛዝ የቤታችን ደንብ እንደሆነ አሳምረው ያውቁ ነበር። (ማቴ. 5:37) ለምሳሌ አንደኛዋ ልጃችን በ17 ዓመቷ፣ ከተወሰኑ ወጣቶች ጋር መዝናናት ትችል እንደሆነ ሊዲን ስትጠይቃት አልፈቀደችላትም። ከእነዚያ ወጣቶች አንዷ ለልጃችን “እናትሽ እንቢ ካለችሽ ለምን አባትሽን አትጠይቂውም?” አለቻት። በዚህ ጊዜ ልጃችን “ዋጋ የለውም ባክሽ። እነሱ ሁሌም አቋማቸው አንድ ነው” ብላ መለሰች። አዎ፣ ስድስቱም ልጆቻችን ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በተያያዘ ሁልጊዜም ተመሳሳይ አቋም እንዳለን አስተውለው ነበር። በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ የቤተሰባችን አባላት በይሖዋ ቤት ውስጥ መሆናቸውን ስናይ እሱን እናመሰግነዋለን።

እውነትን ማወቄ በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጠውን ነገር ቢቀይረውም የሕክምና ሙያዬን ተጠቅሜ የአምላክን ሕዝቦች ማገልገል እፈልግ ነበር። ስለዚህ መጀመሪያ በፓሪስ በኋላ ላይ ደግሞ በሉቭዬ በሚገኘው ቤቴል ሐኪም ሆኜ ለማገልገል ራሴን አቀረብኩ። ቤቴል መመላለስ ከጀመርኩ 50 ዓመት ገደማ ይሆነኛል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከቤቴል ቤተሰብ አባላት መካከል በጣም ጥሩ ወዳጆች አፍርቻለሁ፤ አንዳንዶቹ በአሁኑ ወቅት በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ይገኛሉ። አንድ ቀን ደግሞ ከአንድ አዲስ ቤቴላዊ ጋር ተዋወቅሁ። ለካስ ይህ ወጣት ከ20 ዓመት በፊት ሲወለድ እናቱን ያዋለድኳት እኔ ነበርኩ! ይህን ሳውቅ በጣም ተገረምኩ።

ይሖዋ ሕዝቡን ምን ያህል እንደሚንከባከብ ተመልክቻለሁ

ባለፉት ዓመታት ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት ሕዝቡን ሲመራና ሲጠብቅ ማየቴ እሱን ይበልጥ እንድወደው አድርጎኛል። በ1980ዎቹ መጀመሪያ የበላይ አካሉ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንድ ፕሮግራም አዘጋጀ፤ ይህ ፕሮግራም በሕክምናው ዘርፍ ያሉ አካላት የይሖዋ ምሥክሮችን አቋም በተሻለ መንገድ እንዲረዱ ለማገዝ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

በ1988 የበላይ አካሉ የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት የተባለ አዲስ የቤቴል ዲፓርትመንት አቋቋመ። መጀመሪያ ላይ ይህ ዲፓርትመንት የሚከታተለው በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎችን ነበር፤ እነዚህ ኮሚቴዎች የይሖዋ ምሥክር ታካሚዎች ተስማሚ ሕክምና እንዲያገኙ ይረዳሉ። ይህ ዝግጅት በዓለም ዙሪያ እንዲጀመር ሲወሰን ፈረንሳይ ውስጥም የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ተቋቋሙ። የይሖዋ ድርጅት የታመሙ ወንድሞችና እህቶችን እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ምን ያህል በፍቅር እንደሚደግፋቸው ሳይ በጣም እደነቃለሁ!

ሕልሜ እውን ሆነ

አሁንም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ በደስታ እየተካፈልን ነው

የልጅነት ሕልሜ ሕክምና ነበር። በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጣቸውን ነገሮች ስገመግም ግን ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነው ነገር መንፈሳዊ ፈውስ እንደሆነ ተገነዘብኩ፤ ይህም ሰዎች የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር ሰላም እንዲኖራቸው መርዳት ነው። ጡረታ ከወጣሁ በኋላ እኔና ሊዲ የዘወትር አቅኚዎች ሆነን ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ በየወሩ በርካታ ሰዓታት ማሳለፍ ጀመርን። አሁንም በዚህ ሕይወት አድን ሥራ የቻልነውን ያህል እንካፈላለን።

ከሊዲ ጋር፣ 2021

የታመሙ ሰዎች እፎይታ እንዲያገኙ መርዳቴን አሁንም አላቆምኩም። ሆኖም በጣም ጎበዝ የሚባለው ሐኪምም እንኳ ሁሉንም በሽታዎች መፈወስ ወይም ሞትን ማስቀረት እንደማይችል አውቃለሁ። ስለዚህ ሥቃይ፣ ሕመምና ሞት የማይኖርበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ። በቅርቡ በሚመጣው በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ የሰው አካል የተሠራበትን አስደናቂ መንገድ ጨምሮ ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ለዘላለም የመማር አጋጣሚ አገኛለሁ። አዎ፣ የልጅነት ሕልሜ ገና ሙሉ በሙሉ እውን አልሆነም። ወደፊት የማገኘው ነገር አሁን ካለው እጅግ የላቀ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ!