በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 11

ከተጠመቃችሁ በኋላም “አዲሱን ስብዕና” መልበሳችሁን ቀጥሉ

ከተጠመቃችሁ በኋላም “አዲሱን ስብዕና” መልበሳችሁን ቀጥሉ

“አዲሱን ስብዕና ልበሱ።”—ቆላ. 3:10

መዝሙር 49 የይሖዋን ልብ ማስደሰት

ማስተዋወቂያ *

1. ስብዕናችንን በዋነኝነት የሚቀርጸው ምንድን ነው?

 የተጠመቅነው ከጥቂት ቀናት በፊትም ሆነ ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት ሁላችንም ይሖዋ የሚወደው ዓይነት ስብዕና እንዲኖረን እንፈልጋለን። እንዲህ ዓይነት ስብዕና ለማዳበር አስተሳሰባችንን መቆጣጠር ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም ስብዕናችንን በዋነኝነት የሚቀርጸው አስተሳሰባችን ነው። አዘውትረን የምናስበው ሥጋዊ ምኞታችንን ስለማርካት ከሆነ መጥፎ ነገር መናገራችን ወይም ማድረጋችን አይቀርም። (ኤፌ. 4:17-19) በሌላ በኩል ደግሞ አእምሯችን በጥሩ ሐሳቦች የተሞላ ከሆነ አነጋገራችንና ድርጊታችን አባታችንን ይሖዋን የሚያስደስት ይሆናል።—ገላ. 5:16

2. በዚህ ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

2 ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አንድም መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሯችን እንዳይገባ ማድረግ አንችልም። ሐሳቡ ወደ ድርጊት እንዳይመራን መምረጥ ግን እንችላለን። ከመጠመቃችን በፊት ይሖዋ የሚጠላውን አነጋገርና ምግባር መተው ነበረብን። እንዲህ ማድረጋችን አሮጌውን ስብዕና ገፈን ለመጣል በጣም አስፈላጊ ነው። ይሖዋን በሚገባ ለማስደሰት ግን “አዲሱን ስብዕና ልበሱ” የሚለውን ትእዛዝም መታዘዝ አለብን። (ቆላ. 3:10) በዚህ ርዕስ ላይ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ ‘አዲሱ ስብዕና’ ምንድን ነው? አዲሱን ስብዕና መልበስና እንደለበስነው መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

‘አዲሱ ስብዕና’ ምንድን ነው?

3. ‘አዲሱ ስብዕና’ ምንድን ነው? አንድ ሰው አዲሱን ስብዕና እንደለበሰ የሚያሳየው በምንድን ነው? (ገላትያ 5:22, 23)

3 “አዲሱን ስብዕና” መልበስ ሲባል የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብና ምግባር ማንጸባረቅ ማለት ነው። አዲሱን ስብዕና የለበሰ ሰው የአምላክ መንፈስ ውጤት የሆኑ ባሕርያትን ያንጸባርቃል፤ መንፈስ ቅዱስ በአስተሳሰቡ፣ በስሜቱና በድርጊቱ ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ ይፈቅዳል። (ገላትያ 5:22, 23ን አንብብ።) ለምሳሌ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ይሖዋን እና ሕዝቦቹን ይወዳል። (ማቴ. 22:36-39) አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙት ጊዜም እንኳ ደስታውን ይጠብቃል። (ያዕ. 1:2-4) ሰላም ፈጣሪ ነው። (ማቴ. 5:9) ሌሎችን በትዕግሥትና በደግነት ይይዛል። (ቆላ. 3:13) ጥሩ የሆነውን ነገር ይወዳል፤ ያደርገዋልም። (ሉቃስ 6:35) በሰማዩ አባቱ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለው በሥራው ያሳያል። (ያዕ. 2:18) ሌሎች ሲያበሳጩት በገርነት መልስ ይሰጣል፤ ፈታኝ ነገር ሲያጋጥመውም ራሱን ይገዛል።—1 ቆሮ. 9:25, 27፤ ቲቶ 3:2

4. በገላትያ 5:22, 23 ላይ የተጠቀሱትን ባሕርያት ለየብቻ በማዳበር አዲሱን ስብዕና መልበስ እንችላለን? አብራራ።

4 አዲሱን ስብዕና ለመልበስ በገላትያ 5:22, 23 እንዲሁም በሌሎች ጥቅሶች ላይ ያሉትን ባሕርያት በሙሉ ማዳበር አለብን። * እነዚህ ባሕርያት፣ ብቻቸውን እንደሚለበሱ አልባሳት አይደሉም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ባሕርያት ይመሳሰላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ባልንጀራውን ከልቡ የሚወደው ከሆነ በትዕግሥትና በደግነት ይይዘዋል። ከልቡ ጥሩ የሆነ ሰው ደግሞ ገርና ራሱን የሚገዛ ሰው ነው።

አዲሱን ስብዕና መልበስ የምንችለው እንዴት ነው?

የኢየሱስን አስተሳሰብ እያዳበርን ስንሄድ የእሱን ስብዕና በማንጸባረቅ ረገድ ይበልጥ ስኬታማ እንሆናለን (አንቀጽ 5, 8, 10, 12, 14⁠ን ተመልከት)

5. ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ማዳበር ሲባል ምን ማለት ነው? የኢየሱስን ሕይወት ማጥናት ያለብንስ ለምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 2:16)

5 አንደኛ ቆሮንቶስ 2:16ን አንብብ። አዲሱን ስብዕና የምንለብሰው ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ስናዳብር ነው። በሌላ አባባል ኢየሱስ የሚያስብበትን መንገድ መማር ከዚያም ምሳሌውን መከተል ይኖርብናል። ኢየሱስ የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆኑ ባሕርያትን ፍጹም በሆነ መንገድ አሳይቷል። ጥርት እንዳለ መስታወት የይሖዋን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዕብ. 1:3) አስተሳሰባችን እንደ ኢየሱስ እየሆነ ሲሄድ በድርጊታችንም ይበልጥ እየመሰልነው እንሄዳለን፤ እንዲሁም የእሱን ዓይነት ስብዕና እያዳበርን እንሄዳለን።—ፊልጵ. 2:5

6. አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት ስናደርግ የትኞቹን ነጥቦች ልናስታውስ ይገባል?

6 የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚቻል ነገር ነው? ‘ኢየሱስ እኮ ፍጹም ነው። መቼም ቢሆን እሱን ሙሉ በሙሉ መምሰል አልችልም!’ ብለን እናስብ ይሆናል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ የሚከተሉትን ነጥቦች አስታውስ። አንደኛ፣ የተፈጠርከው በይሖዋና በኢየሱስ አምሳል ነው፤ በመሆኑም ምርጫህ እስከሆነ ድረስ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እነሱን መምሰል ትችላለህ። (ዘፍ. 1:26) ሁለተኛ፣ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ኃይል ነው። በዚህ መንፈስ እርዳታ፣ በራስህ ቢሆን ኖሮ ጨርሶ ማከናወን የማትችላቸውን ነገሮች ማድረግ ትችላለህ። ሦስተኛ፣ ይሖዋ በአሁኑ ወቅት የመንፈስ ፍሬ ውጤት የሆኑትን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ እንድታንጸባርቅ አይጠብቅብህም። እንዲያውም አፍቃሪው አባታችን ምድራዊ ተስፋ ላላቸው ሰዎች ፍጽምና ላይ ለመድረስ 1,000 ዓመት ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 20:1-3) ይሖዋ በአሁኑ ወቅት ከእኛ የሚጠብቀው፣ የምንችለውን ሁሉ እንድንጥርና እሱ በሚሰጠን እርዳታ እንድንተማመን ነው።

7. ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?

7 ታዲያ ኢየሱስን በየትኞቹ አቅጣጫዎች መምሰል እንችላለን? እስቲ የአምላክ መንፈስ ውጤት የሆኑ አራት ባሕርያትን በአጭሩ እንመልከት። ከዚያም ኢየሱስ እያንዳንዱን ባሕርይ ካሳየበት መንገድ ምን እንደምንማር እናያለን። ከእያንዳንዱ ባሕርይ ጋር በተያያዘ ‘አዲሱን ስብዕና በመልበስ ረገድ ምን ያህል ተሳክቶልኛል?’ የሚለውን ለመገምገም የሚረዱ ጥያቄዎችንም እንመለከታለን።

8. ኢየሱስ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ ለይሖዋ ያለው ጥልቅ ፍቅር ለአባቱም ሆነ ለእኛ ሲል መሥዋዕት እንዲከፍል አነሳስቶታል። (ዮሐ. 14:31፤ 15:13) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ሕይወቱን የመራበት መንገድ ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። በእያንዳንዱ ቀን ለሁሉም ሰው ሌላው ቀርቶ ለሚቃወሙት ሰዎችም ጭምር ፍቅርና ርኅራኄ ያሳይ ነበር። ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማሩ ለእነሱ ያለውን ፍቅር ያሳየበት ዋነኛ መንገድ ነው። (ሉቃስ 4:43, 44) ኢየሱስ በኃጢአተኞች እጅ ተሠቃይቶ ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑ ለአምላክ እና ለሰዎች ያለውን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳያል። ይህን በማድረጉም ሁላችንም የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ተከፍቶልናል።

9. ፍቅር በማሳየት ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

9 ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንነውና የተጠመቅነው የሰማዩን አባታችንን ስለምንወደው ነው። በመሆኑም ልክ እንደ ኢየሱስ ሰዎችን የምንይዝበት መንገድ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልም” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐ. 4:20) ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር አለኝ? ሌሎች የሚያስከፋ ነገር ሲያደርጉብኝም እንኳ በርኅራኄ ለመያዝ ጥረት አደርጋለሁ? ፍቅር ሰዎችን ስለ ይሖዋ ለማስተማር ስል ጊዜዬንና ንብረቴን እንድጠቀምበት ያነሳሳኛል? የማገኛቸው አብዛኞቹ ሰዎች ይህን ጥረቴን ባያደንቁ ሌላው ቀርቶ ቢቃወሙኝ እንኳ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ነኝ? ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ ተጨማሪ ጊዜ መስጠት እችል ይሆን?’—ኤፌ. 5:15, 16

10. ኢየሱስ ሰላም ፈጣሪ የነበረው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ ሰላማዊ ሰው ነበር። ሰዎች መጥፎ ነገር ሲያደርጉበት ክፉን በክፉ አልመለሰም። ሆኖም በዚህ ብቻ አልተወሰነም። ቅድሚያውን ወስዶ ሰላም ለመፍጠር ጥረት አድርጓል፤ እንዲሁም አለመግባባቶችን እንዲፈቱ ሌሎችን አበረታቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ተከታዮቹ ይሖዋ አምልኳቸውን እንዲቀበል ከፈለጉ ከወንድማቸው ጋር ሰላም መፍጠር እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 5:9, 23, 24) በተጨማሪም በሐዋርያቱ መካከል ‘ማነው ታላቅ?’ የሚል ክርክር በሚነሳበት ወቅት በተደጋጋሚ ጊዜ ጉዳዩን እንዲፈቱ ረድቷቸዋል።—ሉቃስ 9:46-48፤ 22:24-27

11. ሰላም ፈጣሪ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

11 ሰላም ፈጣሪ መሆን ላለመጋጨት ከመጠንቀቅ ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። ቅድሚያውን ወስደን ከሌሎች ጋር ሰላም መፍጠር ይኖርብናል፤ እንዲሁም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አለመግባባቶችን እንዲፈቱ ማበረታታት አለብን። (ፊልጵ. 4:2, 3፤ ያዕ. 3:17, 18) ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ከሌሎች ጋር ሰላም ለመፍጠር ምን ያህል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ስሜቴን ሲጎዱት ቂም እይዛለሁ? ሌላኛው ሰው ቅድሚያውን ወስዶ እስኪያናግረኝ ድረስ እጠብቃለሁ? ወይስ የችግሩ መንስኤ ግለሰቡ እንደሆነ በሚሰማኝ ጊዜም እንኳ ቅድሚያውን ለመውሰድ ፈቃደኛ ነኝ? ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ፣ ሌሎች አለመግባባቶቻቸውን እንዲፈቱ አበረታታለሁ?’

12. ኢየሱስ ደግነት ያሳየው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ ደግ ነበር። (ማቴ. 11:28-30) ሁኔታዎች አስቸጋሪ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ ገርና ምክንያታዊ በመሆን ደግነት አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ፊንቄያዊት ሴት ልጇን እንዲፈውስላት ስትለምነው መጀመሪያ ላይ ጥያቄዋን አልተቀበለም ነበር፤ ያላትን ታላቅ እምነት ሲመለከት ግን ልጇን በመፈወስ ደግነት አሳይቷታል። (ማቴ. 15:22-28) ኢየሱስ ደግ ቢሆንም በስሜት የሚመራ ሰው አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ፣ ለሚወዳቸው ሰዎች ደግነት ያሳየው ጠንከር በማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ጴጥሮስ የይሖዋን ፈቃድ እንዳያደርግ እንቅፋት በሆነበት ወቅት በሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ፊት ገሥጾታል። (ማር. 8:32, 33) ኢየሱስ ይህን ያደረገው ጴጥሮስን ለማሸማቀቅ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ጴጥሮስ ከጥፋቱ እንዲማር፣ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርትም ቦታቸውን አልፈው በመሄድ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሠሩ ለማስጠንቀቅ ነበር። እርግጥ ነው፣ ጴጥሮስ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተሸማቅቆ ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን የተሰጠው ተግሣጽ ጠቅሞታል።

13. እውነተኛ ደግነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

13 እውነተኛ ደግነት ለማሳየት ስንል የምንወዳቸውን ሰዎች በግልጽ ማነጋገር የሚያስፈልገን ጊዜ አለ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምክርህ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ ኢየሱስን ምሰለው። የምትመክረውን ግለሰብ ለስለስ ባለ መንገድ አነጋግረው። ስለ ግለሰቡ አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ፤ ምክንያቱም ለይሖዋና ለአንተ ፍቅር ካለው በአሳቢነት የተሰጠውን ምክር እንደሚቀበል መተማመን ትችላለህ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘አንድ የምወደው ሰው ጥፋት ሲያጠፋ እሱን በግልጽ ለማነጋገር ድፍረቱ አለኝ? ምክር መስጠቴ የግድ በሚሆንበት ወቅት በደግነት አነጋግረዋለሁ? ወይስ ኃይለ ቃል እጠቀማለሁ? ምክር ለመስጠት የሚያነሳሳኝ ምክንያት ምንድን ነው? በግለሰቡ ስለተበሳጨሁበት ነው ወይስ ስለማስብለት?’

14. ኢየሱስ ጥሩነት ያሳየው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ ጥሩ የሆነውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ያደርገውም ነበር። ኢየሱስ አባቱን ይወደዋል፤ ስለዚህ ምንጊዜም በትክክለኛው ዝንባሌ ተነሳስቶ ትክክለኛውን ነገር ያደርጋል። ጥሩነት በተግባር የሚገለጽ ባሕርይ ነው። ጥሩ ሰው ለሌሎች መልካም ነገር ያደርጋል። ‘ማድረግ ያለብኝ ትክክለኛው ነገር ምንድን ነው?’ የሚለውን ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። ትክክለኛውን ነገር በትክክለኛው ዝንባሌ ተነሳስተን ማድረግ አለብን። ‘በእርግጥ አንድ ሰው በመጥፎ ዝንባሌ ተነሳስቶ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። መልሱ አዎ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ሌሎች እንዲያዩላቸው ብለው ለድሆች ምጽዋት ስለሚሰጡ ሰዎች ተናግሮ ነበር። እነዚህ ሰዎች መልካም ያደረጉ ቢመስላቸውም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።—ማቴ. 6:1-4

15. እውነተኛ ጥሩነት የምናሳየው እንዴት ነው?

15 እውነተኛ ጥሩነት ማሳየት የምንችለው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ዝንባሌ ተነሳስተን ትክክለኛውን ነገር ስናደርግ ነው። እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ማድረግ ያለብኝን ትክክለኛ ነገር ማወቅ ብቻ ሳይሆን አደርገዋለሁ? ለሌሎች ጥሩ ነገር የማደርገው በምን ዓይነት ዝንባሌ ተነሳስቼ ነው?’

አዲሱ ስብዕናችን በጥሩ ሁኔታ እንዲቀጥል ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

16. በየቀኑ ምን ማድረግ አለብን? ለምንስ?

16 አዲሱን ስብዕና ለመልበስ የምናደርገው ጥረት ስንጠመቅ እንደሚያበቃ ማሰብ አይኖርብንም። ውብ የሆነው ይህ “አዲስ ልብሳችን” በጥሩ ሁኔታ እንዲቀጥል ማድረግ አለብን። ለዚህ የሚረዳን አንዱ ነገር በየቀኑ የመንፈስ ፍሬ ባሕርያትን ማንጸባረቅ የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ ነው። ታዲያ ይህ የሚረዳን እንዴት ነው? ይሖዋ የተግባር አምላክ ነው፤ መንፈሱም በሥራ ላይ ያለ ኃይል ነው። (ዘፍ. 1:2) በመሆኑም እያንዳንዱ የመንፈሱ ፍሬ ገጽታ ለተግባር ያነሳሳል። ለምሳሌ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ‘እምነት ያለሥራ የሞተ ነው’ ሲል ጽፏል። (ያዕ. 2:26) ከሌሎች የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ጋር በተያያዘም ይህ እውነት ነው። እነዚህን ባሕርያት ስናንጸባርቅ መንፈሱ በውስጣችን እየሠራ እንደሆነ እናሳያለን።

17. የመንፈስ ፍሬ ሳናሳይ ስንቀር ምን ማድረግ ይኖርብናል?

17 ከተጠመቁ ብዙ ዓመታት የሆናቸው ክርስቲያኖችም እንኳ አልፎ አልፎ የመንፈስ ፍሬን ማሳየት የሚያቅታቸው ጊዜ አለ። ዋናው ነገር ግን ተስፋ አለመቁረጥ ነው። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ የምትወደው ልብስ ቢቀደድብህ ወዲያውኑ አውጥተህ ትጥለዋለህ? እንዲህ አታደርግም። የሚቻል ከሆነ በጥንቃቄ ልብሱን ለመጠገን ጥረት ታደርጋለህ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ልብሱ እንዳይቀደድብህ ይበልጥ ትጠነቀቃለህ። በተመሳሳይም አንድን ሰው በደግነት፣ በትዕግሥት ወይም በፍቅር ሳትይዝ ቀርተህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። የተቀደደውን ልብስ እንደምትጠግነው ሁሉ፣ ልባዊ ይቅርታ መጠየቅህም ከግለሰቡ ጋር ያለህን ግንኙነት ለማደስ ይረዳሃል። ለወደፊቱ ደግሞ የቻልከውን ጥንቃቄ አድርግ።

18. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

18 ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ስለተወልን ምንኛ አመስጋኞች ነን! የእሱ ዓይነት አስተሳሰብና አመለካከት እያዳበርን ስንሄድ እሱን በምግባሩ መምሰል ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። በምግባራችን እሱን በመሰልን መጠን ደግሞ አዲሱን ስብዕና መልበስ ይበልጥ ይሳካልናል። በዚህ ርዕስ ላይ የተመለከትነው አራት የአምላክ መንፈስ ፍሬ ባሕርያትን ብቻ ነው። ታዲያ ጊዜ መድበህ የቀሩትን የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ለምን አታጠናም? እንዲህ ስታደርግ እነዚህን ባሕርያት በማሳየት ረገድ ምን ያህል እንደተሳካልህ ራስህን ገምግም። የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች ላይ “ክርስቲያናዊ ሕይወት” በሚለው ሥር “የመንፈስ ፍሬ” የሚለውን ብትመለከት ስለዚህ ጉዳይ በርካታ ርዕሶች ማግኘት ትችላለህ። አንተ የምትችለውን ሁሉ ካደረግህ ይሖዋ አዲሱን ስብዕና ለመልበስና እንደለበስከው ለመቀጠል እንደሚረዳህ እርግጠኛ ሁን።

መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?

^ አን.5 የቀድሞ ሕይወታችንና አስተዳደጋችን ምንም ይሁን ምን “አዲሱን ስብዕና” መልበስ እንችላለን። ይህ እንዲሆን ግን የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግና እንደ ኢየሱስ ለመሆን የምናደርገውን ጥረት መቀጠል አለብን። በዚህ ርዕስ ላይ የኢየሱስን አስተሳሰብና ምግባር የሚያሳዩ ምሳሌዎችን እንመለከታለን። ከተጠመቅን በኋላም የእሱን ምሳሌ መከተላችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት እንደሆነም እናያለን።

^ አን.4 ገላትያ 5:22, 23 የአምላክ መንፈስ ውጤት የሆኑ ባሕርያትን በሙሉ አይዘረዝርም። ስለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ለማግኘት በሰኔ 2020 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።