በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 12

ዘካርያስ ያየው ይታያችኋል?

ዘካርያስ ያየው ይታያችኋል?

“በመንፈሴ እንጂ፣ በወታደራዊ ኃይል ወይም በጉልበት አይደለም።”—ዘካ. 4:6

መዝሙር 73 ድፍረት ስጠን

ማስተዋወቂያ *

1. ከግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን ከፊታቸው ምን አስደሳች ነገር ይጠብቃቸዋል?

 አይሁዳውያኑ በጣም ተደስተዋል። ይሖዋ አምላክ “የፋርሱን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ [በማነሳሳት]” ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በባቢሎን ግዞት የነበሩትን እስራኤላውያን እንዲለቅ አደረገው። ንጉሡ አይሁዳውያኑ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ‘የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ቤት መልሰው እንዲገነቡ’ የሚገልጽ አዋጅ አወጣ። (ዕዝራ 1:1, 3) ይህ እንዴት የሚያስደስት ነው! አሁን የእውነተኛው አምላክ አምልኮ እሱ ለሕዝቡ በሰጠው ምድር ላይ መልሶ ሊቋቋም ነው ማለት ነው።

2. ከግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን መጀመሪያ ላይ ምን ማከናወን ችለው ነበር?

2 በ537 ዓ.ዓ. ከግዞት የተመለሱት የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን የደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ዋና ከተማ ወደነበረችው ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። ብዙም ሳይቆይ እነዚህ አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን መገንባት ጀመሩ፤ በ536 ዓ.ዓ. መሠረት የመጣሉን ሥራ ማጠናቀቅ ቻሉ!

3. አይሁዳውያኑ ምን ተቃውሞ አጋጠማቸው?

3 ሆኖም ከግዞት የተመለሱት ሰዎች ቤተ መቅደሱን መልሰው መገንባት ከጀመሩ በኋላ ከባድ ተቃውሞ አጋጠማቸው። በዙሪያቸው የነበሩት ሰዎች “የይሁዳን ሕዝቦች ተስፋ ለማስቆረጥና ወኔ ከድቷቸው የግንባታ ሥራውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ዘወትር ይጥሩ ነበር።” (ዕዝራ 4:4) ይህ ያነሰ ይመስል ሌላ የባሰ ፈተናም አጋጠማቸው። በ522 ዓ.ዓ. አርጤክስስ የተባለ ንጉሥ በፋርስ ላይ ነገሠ። * ተቃዋሚዎች ይህን የአገዛዝ ለውጥ የግንባታ ሥራውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም እንደሚያስችል አጋጣሚ ቆጠሩት፤ በመሆኑም “በሕግ ስም ችግር ለመፍጠር [ማሴር]” ጀመሩ። (መዝ. 94:20) ለንጉሥ አርጤክስስ አይሁዳውያኑ በእሱ ላይ ለማመፅ እንዳቀዱና ሌሎች ወንጀሎችን እንደፈጸሙ ነገሩት። (ዕዝራ 4:11-16) ንጉሡም እነዚህን የሐሰት ክሶች በማመን የቤተ መቅደሱ ግንባታ እንዲቆም ትእዛዝ ሰጠ። (ዕዝራ 4:17-23) በመሆኑም የቤተ መቅደሱን ግንባታ በደስታ ያከናውኑ የነበሩት ሰዎች ሥራቸውን ለማቆም ተገደዱ።—ዕዝራ 4:24

4. በቤተ መቅደሱ ግንባታ ላይ ተቃውሞ በተነሳ ጊዜ ይሖዋ ምን አደረገ? (ኢሳይያስ 55:11)

4 ጣዖት አምላኪ የሆኑት የምድሪቱ ነዋሪዎችና አንዳንድ የፋርስ ባለሥልጣናት የቤተ መቅደሱን ግንባታ ለማስቆም ቆርጠው ተነስተው ነበር። የይሖዋ ዓላማ ግን የግንባታ ሥራው ወደፊት እንዲቀጥል ነበር፤ ደግሞም ዓላማውን ሁሌም ዳር ያደርሳል። (ኢሳይያስ 55:11ን አንብብ።) ይሖዋ ዘካርያስ የተባለ ደፋር ነቢይ ያስነሳ ሲሆን ለዚህ ነቢይ ስምንት አስደናቂ ራእዮች ገልጦለታል፤ ዘካርያስም እነዚህን ራእዮች ለአይሁዳውያኑ በመንገር እነሱን ማበረታታት ነበረበት። እነዚህ የሚያጽናኑ ራእዮች ሕዝቡ ተቃዋሚዎቻቸውን የሚፈሩበት ምንም ምክንያት እንደሌለ እንዲገነዘቡ ረድተዋቸዋል፤ በተጨማሪም በይሖዋ ሥራ ወደፊት እንዲገፉ አበረታተዋቸዋል። በአምስተኛው ራእይ ላይ ዘካርያስ መቅረዝና ሁለት የወይራ ዛፎች ተመልክቷል።

5. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

5 ሁላችንም ተስፋ የምንቆርጥበት ጊዜ አለ። በመሆኑም ይሖዋ በዘካርያስ አምስተኛ ራእይ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የሰጠውን ማበረታቻ መመርመራችን ይጠቅመናል። የዚህን ራእይ ትርጉም መረዳታችን ተቃውሞ ሲያጋጥመን፣ ያለንበት ሁኔታ ሲለወጥና የተሰጠንን መመሪያ መረዳት ሲከብደን ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።

ተቃውሞ ሲያጋጥመን

ዘካርያስ ሰባት መብራቶች ያሉት መቅረዝ በራእይ ተመለከተ፤ መቅረዙ ዘይት የሚያገኘው ከሁለት የወይራ ዛፎች ነው (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. በዘካርያስ 4:1-3 ላይ የሚገኘው ስለ መቅረዙና ስለ ሁለቱ የወይራ ዛፎች የሚገልጸው ራእይ ለአይሁዳውያኑ ድፍረት የሰጣቸው እንዴት ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

6 ዘካርያስ 4:1-3ን አንብብ። ስለ መቅረዙና ስለ ሁለቱ የወይራ ዛፎች የሚናገረው ራእይ አይሁዳውያኑ ተቃውሞን በድፍረት እንዲጋፈጡ ረድቷቸዋል። እንዴት? መቅረዙ የማያቋርጥ የነዳጅ አቅርቦት እንዳለው አስተውላችኋል? ከሁለቱ የወይራ ዛፎች የሚመነጨው ዘይት በአንድ ሳህን ላይ ይጠራቀማል፤ ከዚያም ዘይቱ መቅረዙ ላይ ወዳሉት ሰባቱም መብራቶች ይከፋፈላል። ይህ ዘይት መብራቶቹ ያለማቋረጥ እንዲያበሩ ያደርጋል። ዘካርያስ “የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምንድን ነው?” በማለት ጠየቀ። መልአኩም ከይሖዋ የመጣውን ይህን መልእክት በመንገር ጥያቄውን መለሰለት፦ “‘በመንፈሴ እንጂ፣ በወታደራዊ ኃይል ወይም በጉልበት አይደለም’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።” (ዘካ. 4:4, 6) ከዛፎቹ የሚመነጨው ዘይት ኃያል የሆነውንና ፈጽሞ የማይነጥፈውን የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ያመለክታል። ኃያል የሆነው መላው የፋርስ ሠራዊት ከይሖዋ መንፈስ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ቤተ መቅደሱን የሚገነቡት ሰዎች ይሖዋ ከጎናቸው ስላለ ማንኛውንም ዓይነት ተቃውሞ ተቋቁመው ሥራቸውን ዳር ማድረስ ይችላሉ። ይህ እንዴት ያለ የሚያበረታታ መልእክት ነው! ከአይሁዳውያኑ የሚጠበቀው በይሖዋ በመታመን ወደ ሥራቸው መመለስ ብቻ ነው። እነሱም የተጣለባቸው እገዳ ገና ባይነሳም ይህንኑ አደረጉ።

7. ቤተ መቅደሱን የሚገነቡትን ሰዎች የሚጠቅም ምን ለውጥ ተከሰተ?

7 ከጊዜ በኋላ ቤተ መቅደሱን የሚገነቡትን ሰዎች የሚጠቅም አንድ ለውጥ ተከሰተ። ይህ ለውጥ ምንድን ነው? በ520 ዓ.ዓ. ፋርስን ያስተዳድር የነበረው ቀዳማዊ ዳርዮስ የተባለ አዲስ ንጉሥ ነበር። ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በቤተ መቅደሱ ግንባታ ላይ የተጣለው እገዳ ሕጋዊ እንዳልሆነ ተገነዘበ። በመሆኑም የግንባታ ሥራው እንዲጠናቀቅ ፈቃድ ሰጠ። (ዕዝራ 6:1-3) ይህ ውሳኔ በራሱ በጣም አስደናቂ ነው፤ ሆኖም ንጉሡ በዚህ ብቻ አልተወሰነም። በአይሁዳውያኑ ዙሪያ ያሉ ሰዎች በግንባታ ሥራው ላይ ጣልቃ መግባታቸውን እንዲያቆሙ እንዲሁም ገንዘብና ቁሳቁስ በማቅረብ ለግንባታው ሥራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ሰጠ! (ዕዝራ 6:7-12) በዚህም የተነሳ አይሁዳውያኑ ከአራት ዓመት ገደማ በኋላ ማለትም በ515 ዓ.ዓ. የቤተ መቅደሱን ግንባታ ማጠናቀቅ ቻሉ።—ዕዝራ 6:15

ተቃውሞ ሲያጋጥማችሁ ይሖዋ ባለው ኃይል ተማመኑ (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)

8. ተቃውሞን በድፍረት መጋፈጥ የምትችሉት ለምንድን ነው?

8 በዛሬው ጊዜም በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶቹ የሚኖሩት ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ውስጥ ነው። እንዲህ ባሉ አካባቢዎች፣ ወንድሞች ተይዘው “በገዢዎችና በነገሥታት ፊት” ሊቀርቡና ምሥክርነት ሊሰጡ ይችላሉ። (ማቴ. 10:17, 18) አንዳንድ ጊዜ የአገዛዝ ለውጥ በተወሰነ መጠን እፎይታ ሊያስገኝ ይችላል። አሊያም ቀና የሆኑ ዳኞች ለሥራችን የሚጠቅም ውሳኔ ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ሌላ ዓይነት ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል። የሚኖሩት የአምልኮ ነፃነት ባለበት አገር ቢሆንም ቤተሰቦቻቸው ተቃውሞ ሊያደርሱባቸው ይችላሉ፤ እንዲህ ያለው ተቃውሞ ዓላማ አምላክን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ ነው። (ማቴ. 10:32-36) ብዙ ጊዜ እንደታየው ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦቻቸውን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚያደርጉት ጥረት ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ሲገነዘቡ መቃወማቸውን ያቆማሉ። እንዲያውም ኃይለኛ ተቃዋሚ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በኋላ ላይ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ሆነዋል። ተቃውሞ ሲያጋጥማችሁ ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጡ! ደፋሮች ሁኑ! የይሖዋና ኃያል የሆነው ቅዱስ መንፈሱ ድጋፍ ስለማይለያችሁ የምትፈሩበት ምንም ምክንያት የለም!

ያለንበት ሁኔታ ሲለወጥ

9. አንዳንድ አይሁዳውያን የአዲሱ ቤተ መቅደስ መሠረት ሲጣል በጣም ያዘኑት ለምንድን ነው?

9 የአዲሱ ቤተ መቅደስ መሠረት ሲጣል፣ በዕድሜ የገፉ አንዳንድ አይሁዳውያን አለቀሱ። (ዕዝራ 3:12) ሰለሞን ያስገነባውን ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ስለሚያውቁ አዲስ የተገነባው ቤተ መቅደስ “ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር ከምንም የማይቆጠር” እንደሆነ ተሰማቸው። (ሐጌ 2:2, 3) በቀድሞውና በአዲሱ ቤተ መቅደስ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ መሆኑ በጣም ቅር አሰኝቷቸዋል። ዘካርያስ ያየው ራእይ ቅሬታቸውን እንዲያስወግዱ የሚረዳ ነበር። እንዴት?

10. በዘካርያስ 4:8-10 ላይ የሚገኘው መልአኩ የተናገረው ሐሳብ አይሁዳውያኑ ቅሬታቸውን እንዲያስወግዱ የረዳቸው እንዴት ነው?

10 ዘካርያስ 4:8-10ን አንብብ። መልአኩ አይሁዳውያኑ ‘ሐሴት እንደሚያደርጉ’ እና የአይሁድ ገዢ በሆነው ‘በዘሩባቤል እጅ ላይ ቱምቢውን እንደሚያዩ’ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ቱምቢ አንድ ነገር ቀጥ ያለ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሣሪያ ነው። በመሆኑም መልአኩ ቤተ መቅደሱ በአንዳንዶች ዓይን የቀድሞውን ያህል የሚያስደምም ባይሆንም የግንባታ ሥራው እንደሚጠናቀቅና የይሖዋን መሥፈርት እንደሚያሟላ ለሕዝቡ ማረጋገጫ እየሰጠ ነበር። ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ደስ ከተሰኘ ሕዝቡ ቅር የሚሰኝበት ምን ምክንያት አለ? በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው በአዲሱ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚቀርበው አምልኮ ከእሱ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ መሆኑ ነው። አይሁዳውያኑ ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ በማምለክና የእሱን ሞገስ በማግኘት ላይ ትኩረት ካደረጉ ደስታቸውን መልሰው ማግኘት ይችላሉ።

ለአዳዲስ ሁኔታዎች አዎንታዊ አመለካከት አዳብሩ (ከአንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት) *

11. በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?

11 አብዛኞቻችን ለውጥን ማስተናገድ ይከብደናል። በአንድ ዓይነት የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የአገልግሎት ምድብ ለውጥ አጋጥሟቸዋል። ሌሎች ደግሞ በዕድሜያቸው ምክንያት የሚወዱትን የአገልግሎት መብት ለመተው ተገደዋል። እንዲህ ያለ ለውጥ ሲያጋጥመን ብናዝን የሚያስገርም አይደለም። መጀመሪያ ላይ ውሳኔውን ሙሉ በሙሉ ላንረዳው ወይም ላናምንበት እንችላለን። ቀደም ሲል የነበረን ሕይወት ሊናፍቀን ይችላል። በተጨማሪም አሁን ባለንበት ሁኔታ ውስጥ ለይሖዋ ማበርከት የምንችለው ነገር ጥቂት እንደሆነ በማሰብ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። (ምሳሌ 24:10) ታዲያ ዘካርያስ ያየው ራእይ ለአምላክ ምርጣችንን መስጠታችንን እንድንቀጥል የሚረዳን እንዴት ነው?

12. ዘካርያስ ያየው ራእይ ያለንበት ሁኔታ መለወጡ የሚያስከትልብንን ሐዘን ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?

12 የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን ያጋጠመንን ለውጥ በተሻለ ሁኔታ ለማስተናገድ ይረዳናል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ አስደናቂ ነገሮችን እያከናወነ ነው፤ እኛም ከእሱ ጋር አብረን የመሥራት ልዩ መብት አግኝተናል። (1 ቆሮ. 3:9) ያሉን ኃላፊነቶች ሊቀየሩ ይችላሉ፤ ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር ግን ፈጽሞ አይቀየርም። እንግዲያው በድርጅቱ ውስጥ የተደረገ ለውጥ እናንተን በግለሰብ ደረጃ ከነካችሁ ለውጡ የተደረገባቸውን ምክንያቶች በማሰብ አትብሰልሰሉ። ‘የቀድሞውን ዘመን’ ከመናፈቅ ተቆጠቡ፤ ከዚህ ይልቅ ለውጡ ያስገኛቸውን መልካም ነገሮች ለማስተዋል እንዲረዳችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። (መክ. 7:10) አሁን ላይ ማድረግ የማትችሏቸውን ነገሮች ማሰብ ትታችሁ ማድረግ የምትችሏቸውን ነገሮች ለማሰብ ሞክሩ። ዘካርያስ ያየው ራእይ ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት የመያዝን አስፈላጊነት ያስተምረናል። አዎንታዊ አመለካከት መያዛችን ደስታችንን እንዳናጣና ታማኝ እንድንሆን ይረዳናል።

የተሰጠንን መመሪያ መቀበል ሲከብደን

13. አንዳንድ እስራኤላውያን የቤተ መቅደሱ ግንባታ እንዲቀጥል የተሰጠው መመሪያ ጥበብ የጎደለው እንደሆነ የተሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

13 ቤተ መቅደሱን መልሶ በመገንባቱ ሥራ ላይ እገዳ ተጥሎ ነበር። ያም ሆኖ ሥራውን እንዲመሩ የተሾሙት ሊቀ ካህናቱ የሆሹዋ (ኢያሱ) እና ገዢው ዘሩባቤል “የአምላክን ቤት መልሰው መገንባት ጀመሩ።” (ዕዝራ 5:1, 2) አንዳንድ አይሁዳውያን ይህ ውሳኔ ጥበብ የጎደለው እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ቤተ መቅደሱን የመገንባቱ ሥራ ከጠላት እይታ ሊሰወር አይችልም፤ ጠላቶቻቸው ደግሞ ሥራውን ለማስቆም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ኃላፊነት የተጣለባቸው ሁለቱ ወንዶች ማለትም ኢያሱና ዘሩባቤል ይሖዋ ውሳኔያቸውን እንደሚደግፍ የሚያሳይ ማረጋገጫ ያስፈልጋቸው ነበር። ደግሞም ማረጋገጫ አግኝተዋል። እንዴት?

14. በዘካርያስ 4:12, 14 ላይ እንደተገለጸው ሊቀ ካህናቱ ኢያሱና ገዢው ዘሩባቤል ምን ማረጋገጫ አግኝተዋል?

14 ዘካርያስ 4:12, 14ን አንብብ። ዘካርያስ ባየው በዚህ ራእይ ላይ መልአኩ ሁለቱ የወይራ ዛፎች ‘ሁለቱን ቅቡዓን’ ማለትም ኢያሱንና ዘሩባቤልን እንደሚያመለክቱ ለአምላክ ታማኝ ነቢይ ገለጠለት። በምሳሌያዊ ሁኔታ ሁለቱ ሰዎች ‘የምድር ሁሉ ጌታ’ ከሆነው ከይሖዋ ‘አጠገብ እንደቆሙ’ ተገልጿል። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው! ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ይተማመንባቸዋል። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች የሚሰጡት መመሪያ ምንም ይሁን ምን እስራኤላውያን እነሱ በሚያደርጉት ውሳኔና በአምላክ አመራር ሙሉ በሙሉ የሚተማመኑበት በቂ ምክንያት አላቸው።

15. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው የይሖዋ መመሪያ አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያ ከሚሰጥባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። በዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ይሖዋ እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ነግሮናል። ከአምላክ ቃል ለምናገኘው መመሪያ አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ቃሉን በጥሞና በማንበብና ጊዜ ወስደን ያነበብነውን ነገር ለመረዳት ጥረት በማድረግ ነው። ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘መጽሐፍ ቅዱስን ወይም ጽሑፎቻችንን ሳነብ ቆም ብዬ አሰላስላለሁ? “ለመረዳት የሚከብዱ” የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ትርጉም ለማወቅ ምርምር አደርጋለሁ? ወይስ እንዲሁ ገረፍ ገረፍ አድርጌ ነው የማልፈው?’ (2 ጴጥ. 3:16) ይሖዋ በሚያስተምረን ነገር ላይ ለማሰላሰል ጊዜ የምንመድብ ከሆነ የእሱን መመሪያ መቀበልና አገልግሎታችንን መፈጸም እንችላለን።—1 ጢሞ. 4:15, 16

“ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚሰጣችሁ መመሪያ ላይ እምነት ይኑራችሁ (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት) *

16. “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚሰጠንን መመሪያ ሙሉ በሙሉ መረዳት ሲከብደን መመሪያውን ለመቀበል ምን ይረዳናል?

16 ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያ የሚሰጥበት ሌላው መንገድ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ነው። (ማቴ. 24:45) አንዳንድ ጊዜ ታማኙ ባሪያ የሚሰጠውን መመሪያ ሙሉ በሙሉ መረዳት ሊከብደን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚረዱ ዝርዝር መመሪያዎች ይሰጡን ይሆናል፤ ሆኖም ይህ አደጋ በእኛ አካባቢ እንደማያጋጥም ሊሰማን ይችላል። አሊያም ደግሞ ታማኙ ባሪያ በወረርሽኝ ወቅት የሚሰጠው መመሪያ ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። የሚሰጡን መመሪያዎች እኛ ላለንበት ሁኔታ እንደማይሠሩ በሚሰማን ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? እስራኤላውያን በኢያሱና በዘሩባቤል በኩል የተሰጣቸውን መመሪያ በመታዘዛቸው ምን ጥቅም እንዳገኙ እናስብ። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበብናቸውን ሌሎች ዘገባዎችም ልናስብ እንችላለን። የአምላክ ሕዝቦች ከሰብዓዊ እይታ አንጻር ጥበብ የጎደለው የሚመስል መመሪያ የተሰጣቸው ጊዜ ነበር፤ መታዘዛቸው ግን የኋላ ኋላ ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል።—መሳ. 7:7፤ 8:10

ዘካርያስ ያየውን እዩ

17. ስለ መቅረዙና ስለ ሁለቱ የወይራ ዛፎች የሚገልጸው ራእይ በአይሁዳውያኑ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

17 ዘካርያስ ያየው አምስተኛው ራእይ አጭር ቢሆንም አይሁዳውያኑ ለሥራቸውና ለአምልኳቸው አዲስ እይታ እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል። አይሁዳውያኑ ዘካርያስ ካየው ራእይ ጋር የሚስማማ እርምጃ ሲወስዱ የይሖዋን ድጋፍና መመሪያ ማግኘት ችለዋል። ይሖዋ ኃያል በሆነው ቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሞ ሥራቸውን እንዲቀጥሉና ደስታቸውን መልሰው እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።—ዕዝራ 6:16

18. የዘካርያስ ራእይ በእያንዳንዳችን ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

18 ዘካርያስ ስለ መቅረዙና ስለ ሁለቱ የወይራ ዛፎች ያየው ራእይ በእናንተም ሕይወት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ ራእዩ ተቃውሞ ሲያጋጥማችሁ ብርታት እንድታገኙ፣ ያላችሁበት ሁኔታ ሲቀየር ደስታችሁን እንዳታጡና የተሰጣችሁን መመሪያ መረዳት ሲከብዳችሁ እምነት በማሳየት እንድትታዘዙ ይረዳችኋል። በሕይወታችሁ ውስጥ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? በመጀመሪያ፣ ዘካርያስ ያየውን ለማየት ሞክሩ፤ በሌላ አባባል ይሖዋ ሕዝቡን እየተንከባከበ እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለመመልከት ጥረት አድርጉ። ከዚያም በይሖዋ በመታመንና እሱን በሙሉ ልባችሁ ማምለካችሁን በመቀጠል ካያችሁት ነገር ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰዱ። (ማቴ. 22:37) እንዲህ ካደረጋችሁ ይሖዋ እሱን ለዘላለም በደስታ እንድታገለግሉት ይረዳችኋል።—ቆላ. 1:10, 11

መዝሙር 7 ይሖዋ ኃይላችን

^ አን.5 ይሖዋ ለነቢዩ ዘካርያስ በርካታ አስደናቂ ራእዮችን አሳይቶታል። ዘካርያስ ያያቸው ራእዮች እሱም ሆነ የይሖዋ ሕዝቦች ንጹሑን አምልኮ መልሰው ለማቋቋም ጥረት ሲያደርጉ ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ረድተዋቸዋል። እነዚህ ራእዮች እኛም ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩብንም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገል እንድንችል ይረዱናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ዘካርያስ ካያቸው ራእዮች መካከል ከአንዱ የምናገኘውን ጠቃሚ ትምህርት እንመለከታለን፤ ራእዩ ስለ መቅረዝና የወይራ ዛፎች የሚገልጽ ነው።

^ አን.3 ከዓመታት በኋላ በገዢው ነህምያ ዘመን አርጤክስስ የተባለ ሌላ ንጉሥ ለአይሁዳውያኑ ደግነት አሳይቷቸዋል።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም በዕድሜ መግፋትና በጤና ችግር ምክንያት ያጋጠመውን ለውጥ መቀበል ያለበት ለምን እንደሆነ ሲያስብ።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት ይሖዋ ኢያሱንና ዘሩባቤልን እንደደገፋቸው ሁሉ ‘ታማኝና ልባም ባሪያንም’ እንደሚደግፈው ስታሰላስል።