በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 13

እውነተኛው አምልኮ ደስታ ይጨምርላችኋል

እውነተኛው አምልኮ ደስታ ይጨምርላችኋል

“ይሖዋ አምላካችን . . . ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11

መዝሙር 31 ከአምላክ ጋር ሂድ!

ማስተዋወቂያ *

1-2. አምልኳችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርገው ምንድን ነው?

 “አምልኮ” የሚለውን ቃል ስትሰሙ ወደ አእምሯችሁ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት ከአልጋው አጠገብ ተንበርክኮ ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት የሚያቀርብን አንድ ትሑት ወንድም ታስቡ ይሆናል። አሊያም ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት እያጠና ያለ አንድ ደስተኛ ቤተሰብ ወደ አእምሯችሁ ሊመጣ ይችላል።

2 በሁለቱም ሁኔታዎች ላይ የተጠቀሱት ሰዎች አምልኮ እያቀረቡ ነው። ታዲያ ይሖዋ አምልኳቸውን ይቀበለዋል? አምልኮውን ያቀረቡት ከዓላማው ጋር በሚስማማ መልኩ እንዲሁም ፍቅርና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ከሆነ ይቀበለዋል። ይሖዋን በጣም እንወደዋለን። አምልኮ ሊቀርብለት እንደሚገባም እናውቃለን፤ በተጨማሪም በተቻለን መጠን ጥራት ያለው አምልኮ ልናቀርብለት እንፈልጋለን።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በጥንት ዘመን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ስለነበረው አምልኮ እንመለከታለን፤ በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ስላላቸው ስምንት የአምልኳችን ገጽታዎች እንመረምራለን። እነዚህን ነጥቦች ስንመረምር እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ የአምልኳችንን ጥራት ማሻሻል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ እንሞክር። በዚህ ርዕስ ውስጥ እውነተኛው አምልኮ ደስታ ይሰጠናል እንድንል የሚያደርጉንን ምክንያቶችም እንመለከታለን።

በጥንት ዘመን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የነበረው አምልኮ

4. ከክርስትና ዘመን በፊት የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮች ለእሱ ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?

4 ከክርስትና ዘመን በፊት እንደ አቤል፣ ኖኅ፣ አብርሃምና ኢዮብ ያሉ የእምነት ሰዎች ለይሖዋ ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር አሳይተዋል። እንዴት? ታዛዥ በመሆን፣ እምነት በማሳየትና መሥዋዕቶችን በማቅረብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት አምልኮ ሊያቀርቡ እንደሚገባ የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ አልያዘም። ሆኖም በግልጽ ማየት እንደምንችለው ለይሖዋ ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል፤ ደግሞም አምልኳቸው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ለአብርሃም ዘሮች የሙሴን ሕግ ሰጣቸው። እነዚህ ሕግጋት ይሖዋን እሱ በሚፈልገው መንገድ ማምለክ የሚቻልባቸውን መንገዶች የሚገልጹ ዝርዝር መመሪያዎችን ይዘዋል።

5. ኢየሱስ ከሞተና ትንሣኤ ካገኘ በኋላ በእውነተኛው አምልኮ ላይ ምን ለውጥ ተደረገ?

5 ኢየሱስ ከሞተና ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ይሖዋ አገልጋዮቹ የሙሴን ሕግ እንዲታዘዙ መጠበቁን አቆመ። (ሮም 10:4) ክርስቲያኖች አዲስ ሕግ ማለትም “የክርስቶስን ሕግ” መከተል ነበረባቸው። (ገላ. 6:2) ይህን “ሕግ” የሚታዘዙት አድርግ አታድርግ የሚሉ በርካታ ሕጎችን በቃላቸው በመያዝና በመታዘዝ ሳይሆን የኢየሱስን ምሳሌ በመከተልና ትምህርቶቹን ተግባራዊ በማድረግ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ክርስቶስን በመከተል ይሖዋን ለማስደሰት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ይህም ለራሳቸው “እረፍት” ያስገኝላቸዋል።—ማቴ. 11:29

6. ከዚህ የጥናት ርዕስ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

6 እያንዳንዱን የአምልኳችንን ገጽታ ስንመረምር ‘ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ማሻሻያ አድርጌያለሁ?’ በማለት ራሳችሁን ጠይቁ። ‘የማቀርበውን አምልኮ ጥራት ማሻሻል እችል ይሆን?’ ብላችሁ መጠየቅም ትችላላችሁ። ማሻሻያ ካደረጋችሁ ልትደሰቱ ይገባል፤ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልጋችሁ ከሆነ ግን ጉዳዩን በጸሎት ልታስቡበት ትችላላችሁ።

አምልኳችን ምን ያካትታል?

7. ይሖዋ የምናቀርበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት እንዴት ይመለከተዋል?

7 ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ለእሱ አምልኮ እያቀረብን ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሎታችንን መጀመሪያ ላይ በማደሪያው ድንኳን በኋላም በቤተ መቅደሱ ይቀርብ ከነበረው በጥንቃቄ የተዘጋጀ ዕጣን ጋር ያመሳስሉታል። (መዝ. 141:2) ከዕጣኑ የሚወጣው መዓዛ አምላክን ያስደስተው ነበር። በተመሳሳይም በጣም ቀላል የሆኑ ቃላትን እንኳ ተጠቅመን የምናቀርበው ከልብ የመነጨ ጸሎት አምላክን “ደስ ያሰኘዋል።” (ምሳሌ 15:8፤ ዘዳ. 33:10) ይሖዋ ለእሱ ያለንን ፍቅርና አመስጋኝነት ስንገልጽ መስማት ያስደስተዋል ብለን እንድናምን የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን። ያሳሰበንን፣ ተስፋ የምናደርገውንና የምንመኘውን ነገር ለእሱ እንድንነግረው ይፈልጋል። ወደ ይሖዋ በጸሎት ከመቅረብህ በፊት በጸሎትህ ላይ ልታካትታቸው ስለምትችላቸው ነገሮች ለምን ቆም ብለህ አታስብም? እንዲህ ማድረግህ በሰማይ ላለው አባትህ ምርጥ “ዕጣን” ለማቅረብ ያስችልሃል።

8. አምላክን የምናወድስበት ምን ጥሩ አጋጣሚ አለን?

8 ይሖዋን ስናወድስ ለእሱ አምልኮ እያቀረብን ነው። (መዝ. 34:1) ለይሖዋ ውዳሴ የምናቀርበው እሱ ስላሉት ግሩም ባሕርያትና ስላከናወናቸው ሥራዎች በአድናቆት በመናገር ነው። ውዳሴ የሚመነጨው ከአመስጋኝ ልብ ነው። ጊዜ ወስደን በይሖዋ ጥሩነት ላይ ማለትም እሱ ባደረገልን ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ እሱን የምናወድስበት ምክንያት አናጣም። የስብከቱ ሥራ “የከንፈራችን ፍሬ” የሆነውን ‘የውዳሴ መሥዋዕት ለአምላክ የምናቀርብበት’ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል። (ዕብ. 13:15) ወደ ይሖዋ በጸሎት ከመቅረባችን በፊት ምን እንደምንል ቆም ብለን ማሰብ እንዳለብን ሁሉ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎችም ምን እንደምንል ቆም ብለን ማሰባችን አስፈላጊ ነው። የምናቀርበው “የውዳሴ መሥዋዕት” ምርጣችን እንዲሆን እንፈልጋለን። ለሌሎች እውነትን በልበ ሙሉነት የምንናገረው ለዚህ ነው።

9. እንደ ጥንቶቹ እስራኤላውያን ሁሉ እኛም አብረን በመሰብሰባችን ምን ጥቅም እናገኛለን? በግለሰብ ደረጃ ምን ጥቅም አግኝታችኋል?

9 በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ለይሖዋ አምልኮ እያቀረብን ነው። የጥንቶቹ እስራኤላውያን እንዲህ ተብለው ነበር፦ “በመካከልህ ያሉ ወንዶች ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ . . . አምላክህ ይሖዋ በመረጠው ስፍራ ፊቱ ይቅረቡ።” (ዘዳ. 16:16) እስራኤላውያን በበዓላቱ ላይ ለመገኘት ሲሄዱ ቤታቸውንና እርሻቸውን የሚጠብቅላቸው ሰው አልነበረም። ሆኖም ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶላቸዋል፦ “የአምላክህን የይሖዋን ፊት ለማየት . . . በምትወጣበት ጊዜ ማንም ምድርህን አይመኝም።” (ዘፀ. 34:24) ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት በማሳደር በዓመታዊ በዓላቱ ላይ ይገኙ ነበር። እንዲህ ማድረጋቸው ብዙ በረከት ያስገኝላቸዋል፤ ስለ አምላክ ሕግ ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋት፣ በእሱ ጥሩነት ላይ ማሰላሰልና ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር እርስ በርስ መበረታታት የሚችሉበት ጥሩ አጋጣሚ ያገኙ ነበር። (ዘዳ. 16:15) እኛም መሥዋዕትነት ከፍለን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ተመሳሳይ በረከቶችን እናገኛለን። አጭርና ትርጉም ያለው ሐሳብ ለመስጠት ተዘጋጅተን ስንሄድ ደግሞ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚደሰት አስቡት።

10. መዝሙር የአምልኳችን ወሳኝ ክፍል ነው የምንለው ለምንድን ነው?

10 በኅብረት ስንዘምር ለይሖዋ አምልኮ እያቀረብን ነው። (መዝ. 28:7) እስራኤላውያን መዝሙር የአምልኳቸው ወሳኝ ክፍል እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። ንጉሥ ዳዊት 288 ሌዋውያን በቤተ መቅደሱ ዘማሪ ሆነው እንዲያገለግሉ መድቦ ነበር። (1 ዜና 25:1, 6-8) በዛሬው ጊዜም የውዳሴ መዝሙር በመዘመር ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን። ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የድምፃችን ውበት አይደለም። እስቲ አስቡት፦ ስንናገር “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን”፤ ሆኖም ይህ በጉባኤ ውስጥና በአገልግሎት ላይ ከመናገር አያግደንም። (ያዕ. 3:2) በተመሳሳይም ‘ስዘምር ድምፄ አያምርም’ የሚለው ስጋት ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ከማቅረብ ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን አይገባም።

11. በመዝሙር 48:13 ላይ እንደተገለጸው በቤተሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናበት ጊዜ መመደብ ያለብን ለምንድን ነው?

11 የአምላክን ቃል ስናጠናና ልጆቻችንን ስለ ይሖዋ ስናስተምር አምልኮ እያቀረብን ነው። ሰንበት እስራኤላውያን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን አቁመው ከይሖዋ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ የሚያተኩሩበት አጋጣሚ ይሰጣቸው ነበር። (ዘፀ. 31:16, 17) ታማኝ እስራኤላውያን ልጆቻቸውን ስለ ይሖዋና ስለ እሱ ጥሩነት ያስተምሯቸው ነበር። እኛም በግለሰብ ደረጃ የአምላክን ቃል የምናነብበትና የምናጠናበት ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። ይህ ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ክፍል ሲሆን ወደ እሱ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። (መዝ. 73:28) በቤተሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ደግሞ አዲሱ ትውልድ ማለትም ልጆቻችን አፍቃሪ ከሆነው ሰማያዊው አባታችን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ እንረዳቸዋለን።—መዝሙር 48:13ን አንብብ።

12. ይሖዋ ከማደሪያ ድንኳኑ ግንባታ ጋር ለተያያዙ ሥራዎች ከነበረው አመለካከት ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 የአምልኮ ቦታዎችን ስንገነባና ስንጠግን ለይሖዋ አምልኮ እያቀረብን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የማደሪያ ድንኳኑንና ከዚያ ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን መሥራት ‘ቅዱስ ሥራ’ እንደሆነ ይናገራል። (ዘፀ. 36:1, 4) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ የስብሰባ አዳራሾችንና ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎችን የመገንባቱን ሥራ እንደ ቅዱስ አገልግሎት ይቆጥረዋል። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ሥራ በመካፈል ሰፋ ያለ ጊዜ ያሳልፋሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ለመንግሥቱ ሥራ የሚያበረክቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እናደንቃለን። እርግጥ ነው፣ በስብከቱ ሥራም ይካፈላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ አቅኚ የመሆን ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል። የጉባኤ ሽማግሌዎች እነዚህ ትጉ ወንድሞችና እህቶች ብቃቱን እስካሟሉ ድረስ አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ከመሾም ወደኋላ ባለማለት የግንባታ ሥራዎችን እንደሚደግፉ ማሳየት ይችላሉ። የግንባታ ሙያ ኖረንም አልኖረን ሁላችንም ሕንፃዎቹ ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆኑና ጥሩ ይዞታ ላይ እንዲገኙ በማድረግ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን።

13. የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ መዋጮ ስለማድረግ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

13 የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ መዋጮ ስናደርግ ለይሖዋ አምልኮ እያቀረብን ነው። እስራኤላውያን ባዶ እጃቸውን ይሖዋ ፊት ሊቀርቡ አይገባም ነበር። (ዘዳ. 16:16) ሁኔታቸው በፈቀደላቸው መጠን ስጦታ ይዘው መሄድ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ መንገድ እነሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት ለተደረጉት ዝግጅቶች አድናቆት እንዳላቸው ያሳያሉ። እኛስ ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና ለተደረጉልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ሁኔታችን በፈቀደልን መጠን ለጉባኤያችንና ለዓለም አቀፉ ሥራ የገንዘብ መዋጮ ማድረግ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ለመስጠት ፈቃደኝነቱ ካለ ስጦታው ይበልጥ ተቀባይነት የሚኖረው አንድ ሰው ባለው መጠን ሲሰጥ እንጂ በሌለው መጠን ሲሰጥ አይደለም።” (2 ቆሮ. 8:4, 12) የምናደርገው መዋጮ የቱንም ያህል ትንሽ ቢሆን ከልባችን የመነጨ እስከሆነ ድረስ ይሖዋ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ማር. 12:42-44፤ 2 ቆሮ. 9:7

14. በምሳሌ 19:17 መሠረት ይሖዋ ለተቸገሩ ወንድሞቻችን የምናደርገውን እርዳታ እንዴት ይመለከተዋል?

14 የተቸገሩ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ስንረዳ ለይሖዋ አምልኮ እያቀረብን ነው። ይሖዋ ድሆችን ለሚረዱ እስራኤላውያን ወሮታቸውን እንደሚከፍል ቃል ገብቶላቸዋል። (ዘዳ. 15:7, 10) ለተቸገረ የእምነት ባልንጀራችን የምናደርገውን እርዳታ ይሖዋ ለእሱ እንደተሰጠ ስጦታ አድርጎ ይቆጥረዋል። (ምሳሌ 19:17ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ በፊልጵስዩስ የነበሩት ክርስቲያኖች ጳውሎስ እስር ቤት ሳለ ስጦታ ልከውለት ነበር፤ ጳውሎስ ይህ ስጦታ “ተቀባይነት ያለው መሥዋዕትና አምላክ ደስ የሚሰኝበት” እንደሆነ ተናግሯል። (ፊልጵ. 4:18) በጉባኤያችሁ ውስጥ ስላሉ ወንድሞችና እህቶች በማሰብ ‘የእኔ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው አለ?’ በማለት ራሳችሁን ጠይቁ። ይሖዋ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን፣ ችሎታችንንና ቁሳዊ ሀብታችንን የተቸገሩትን ለመርዳት ስንጠቀምበት ይደሰታል። እንዲህ ያለውን እርዳታ እንደ አምልኳችን ክፍል አድርጎ ይመለከተዋል።—ያዕ. 1:27

እውነተኛው አምልኮ ደስታ ይሰጠናል

15. እውነተኛው አምልኮ ጊዜና ጥረት ቢጠይቅም ከባድ ያልሆነው ለምንድን ነው?

15 እውነተኛው አምልኮ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ሆኖም ከባድ አይደለም። (1 ዮሐ. 5:3) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋን የምናመልከው ስለምንወደው ነው። ለአባቱ ስጦታ ለመስጠት ያሰበን አንድ ትንሽ ልጅ ለማሰብ ሞክሩ። ልጁ ለአባቱ የሚሰጠውን ሥዕል በመሣል በርካታ ሰዓታት ሊያሳልፍ ይችላል። ሆኖም ይህን ያህል ጊዜ በማሳለፉ አይቆጭም። አባቱን ስለሚወደው ይህን ስጦታ ለእሱ በመስጠቱ ይደሰታል። እኛም ይሖዋን ስለምንወደው ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ተጠቅመን በንጹሕ አምልኮ በመካፈላችን ደስተኞች ነን።

16. በዕብራውያን 6:10 መሠረት ይሖዋ እያንዳንዳችን እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት እንዴት ይመለከተዋል?

16 አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ሁሉም ልጆቻቸው ተመሳሳይ ስጦታ እንዲሰጧቸው አይጠብቁም። ሁሉም ልጆች አንድ ዓይነት እንዳልሆኑና ማድረግ የሚችሉት ነገር እንደሚለያይ ይገነዘባሉ። በሰማይ ያለው አባታችንም እያንዳንዳችን ያለንበትን ሁኔታ ይረዳል። ምናልባት ከምታውቋቸውና ከምትወዷቸው ብዙ ሰዎች የበለጠ ማድረግ ትችሉ ይሆናል። አሊያም ደግሞ በዕድሜያችሁ፣ በጤናችሁ ሁኔታ ወይም ባለባችሁ የቤተሰብ ኃላፊነት የተነሳ የሌሎችን ያህል ማድረግ አትችሉ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠማችሁ ተስፋ አትቁረጡ። (ገላ. 6:4) ይሖዋ እያንዳንዳችን የምናከናውነውን ሥራ አይረሳም። በትክክለኛው ዝንባሌ ተነሳስተን ምርጣችንን እስከሰጠነው ድረስ በምናደርገው ነገር ደስ ይሰኛል። (ዕብራውያን 6:10ን አንብብ።) ይሖዋ ለማድረግ የምናስበውን ነገር እንኳ ያያል። ለእሱ ማቅረብ በምንችለው አምልኮ ደስተኛ እንድንሆንና እንድንረካ ይፈልጋል።

17. (ሀ) በአንዳንድ የአምልኳችን ገጽታዎች መካፈል ከባድ ቢሆንብን ምን ማድረግ እንችላለን? (ለ) “ ደስታህን ጨምር” በሚለው ሣጥን ሥር ከሚገኙት የአምልኮ ገጽታዎች ምን ጥቅም አግኝተሃል?

17 እንደ ግል ጥናት ወይም የስብከቱ ሥራ ባሉ አንዳንድ የአምልኳችን ገጽታዎች መካፈል ከባድ ቢሆንብንስ? በእነዚህ እንቅስቃሴዎች አዘውትረን በተካፈልን መጠን ይበልጥ አስደሳች እንደሚሆኑልንና ከእነሱ የምናገኘው ጥቅም እንደሚጨምር ማስተዋላችን አይቀርም። አምልኳችንን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደማድረግ ወይም የሙዚቃ መሣሪያዎችን እንደመለማመድ ካሉ እንቅስቃሴዎች ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የምንካፈለው ከስንት አንዴ ብቻ ከሆነ ያን ያህል ለውጥ ላናደርግ እንችላለን። ሆኖም እነዚህን እንቅስቃሴዎች የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክፍል ብናደርጋቸውስ? መጀመሪያ ላይ በትንሹ ጀምረን ቀስ እያልን ጊዜውን ልናረዝመው እንችላለን። ጥረታችን ያስገኘውን ጥሩ ውጤት ስንመለከት እነዚህን ነገሮች የምናደርግበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ልንጀምር እንችላለን፤ እንቅስቃሴዎቹም በጣም አስደሳች ይሆኑልናል። ይህ ምሳሌ ከአምልኳችን ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ልብ አላችሁ?

18. የተፈጠርንበትን ዓላማ ማሳካት የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል?

18 ይሖዋን በሙሉ ልባችን ስናመልክ የተፈጠርንበትን ዓላማ እናሳካለን። ይህም አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ እንዲሁም ይሖዋን ለዘላለም የማምለክ ተስፋ እንድናገኝ ያስችለናል። (ምሳሌ 10:22) ይሖዋ አገልጋዮቹ ችግር ሲያጋጥማቸው እንደሚረዳቸው ስለምናውቅ የአእምሮ ሰላም አለን። (ኢሳ. 41:9, 10) በእርግጥም ከፍጥረት ሁሉ ‘ግርማና ክብር ሊቀበል የሚገባውን’ አፍቃሪውን አባታችንን ስናመልክ ደስተኛ የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን።—ራእይ 4:11

መዝሙር 24 ኑ! ወደ ይሖዋ ተራራ

^ አን.5 ይሖዋ የሁሉም ነገር ፈጣሪ ስለሆነ አምልኮ ይገባዋል። የይሖዋን ትእዛዛት የምንፈጽምና እሱ ካወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን የምንኖር ከሆነ አምልኳችን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የአምልኳችንን ስምንት ገጽታዎች እንመለከታለን። በተጨማሪም በእነዚህ የአምልኮ ዘርፎች ማሻሻያ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነና እነዚህ የአምልኮ ዘርፎች ደስታችንን የሚጨምሩት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።