በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 14

ሽማግሌዎች—የሐዋርያው ጳውሎስን አርዓያ መከተላችሁን ቀጥሉ

ሽማግሌዎች—የሐዋርያው ጳውሎስን አርዓያ መከተላችሁን ቀጥሉ

“የእኔን አርዓያ ተከተሉ።”—1 ቆሮ. 11:1

መዝሙር 99 እልፍ አእላፋት ወንድሞች

ማስተዋወቂያ *

1-2. የሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

 ሐዋርያው ጳውሎስ ለወንድሞቹ ፍቅር ነበረው። እነሱን ለመርዳት በትጋት ይሠራ ነበር። (ሥራ 20:31) በዚህም የተነሳ የእምነት ባልንጀሮቹም ለጳውሎስ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው። በአንድ ወቅት የኤፌሶን ሽማግሌዎች ጳውሎስን ድጋሚ እንደማያዩት ሲያውቁ ‘እጅግ አልቅሰው’ ነበር። (ሥራ 20:37) በዛሬው ጊዜ ያሉ ትጉ ሽማግሌዎችም ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ጥልቅ ፍቅር አላቸው፤ በተጨማሪም እነሱን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። (ፊልጵ. 2:16, 17) አንዳንድ ጊዜ ግን ሽማግሌዎች ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ምን ይረዳቸዋል?

2 ትጉ የሆኑ ሽማግሌዎቻችን የጳውሎስን ምሳሌ መመርመራቸው ይጠቅማቸዋል። (1 ቆሮ. 11:1) ጳውሎስ ከሌሎች ሰዎች የተለየ ኃይል አልነበረውም። ጳውሎስ ፍጹም አልነበረም፤ በዚህም የተነሳ አንዳንዴ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ያታግለው ነበር። (ሮም 7:18-20) በተጨማሪም የተለያዩ ችግሮችን መጋፈጥ አስፈልጎታል። ያም ሆኖ ጳውሎስ ተስፋ አልቆረጠም ወይም ደስታውን አላጣም። ሽማግሌዎች የጳውሎስን ምሳሌ የሚከተሉ ከሆነ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣትና ደስታቸውን ሳያጡ ይሖዋን ማገልገላቸውን መቀጠል ይችላሉ። የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነገሮች እንመረምራለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ሽማግሌዎች ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን የሚከተሉትን አራት ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንመረምራለን፦ (1) የስብከቱን ሥራ ከሌሎች ኃላፊነቶቻቸው ጋር ጎን ለጎን ማስኬድ፣ (2) አሳቢ እረኛ መሆን፣ (3) ከግል ድክመቶቻቸው ጋር ትግል ማድረግ እንዲሁም (4) የሌሎችን አለፍጽምና መቻል። ጳውሎስ እያንዳንዱን ተፈታታኝ ሁኔታ የተወጣው እንዴት እንደሆነና ሽማግሌዎች የእሱን አርዓያ መከተል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

የስብከቱን ሥራ ከሌሎች ኃላፊነቶች ጋር ጎን ለጎን ማስኬድ

4. ሽማግሌዎች በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም መሆን ተፈታታኝ ሊሆንባቸው የሚችለው ለምንድን ነው?

4 ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው? ሽማግሌዎች በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም ከመሆን በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ኃላፊነቶች አሉባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሽማግሌዎች በየተራ በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ሊቀ መንበር ሆነው ያገለግላሉ እንዲሁም የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመራሉ። ሌሎች ንግግሮችን የመስጠት ኃላፊነትም ሊኖርባቸው ይችላል። ሽማግሌዎች በየጊዜው የጉባኤ አገልጋዮችን ያሠለጥናሉ፤ እንዲሁም ለወንድሞችና ለእህቶች ቀጣይ የሆነ ማበረታቻ መስጠት ያስደስታቸዋል። (1 ጴጥ. 5:2) አንዳንድ ሽማግሌዎች የስብሰባ አዳራሾችንና ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎችን በመገንባቱና በማደሱ ሥራ ላይ ይካፈላሉ። ያም ቢሆን እንደ ሌሎች የጉባኤ አስፋፊዎች ሁሉ የሽማግሌዎችም ዋነኛ ኃላፊነት የምሥራቹ አገልጋይ መሆን ነው።—ማቴ. 28:19, 20

5. ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ ምን ምሳሌ ትቷል?

5 ጳውሎስ የተወው ምሳሌ። ከጳውሎስ ስኬት ጀርባ ያለው ሚስጥር በፊልጵስዩስ 1:10 ላይ ተጠቅሷል፤ እዚህ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ጳውሎስ የራሱን ምክር በሥራ ላይ አውሏል። እንዲያከናውን የተሰጠው አገልግሎት የነበረ ሲሆን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይህን አገልግሎት ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ነገር ቆጥሮታል። “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” ሰብኳል። (ሥራ 20:20) በስብከቱ ሥራ ይካፈል የነበረው በቀን ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ወይም በሳምንት አንድ ቀን ብቻ አልነበረም። ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ ይሰብክ ነበር! ለምሳሌ ያህል፣ በአቴንስ የአገልግሎት ጓደኞቹን እየጠበቀ ሳለ ምሥራቹን ለተወሰኑ ታዋቂ ሰዎች ሰብኳል፤ ይህም ግሩም ውጤት አስገኝቶለታል። (ሥራ 17:16, 17, 34) ጳውሎስ ‘ታስሮ’ በነበረበት ጊዜ እንኳ በዙሪያው ለነበሩ ሰዎች ሰብኳል።—ፊልጵ. 1:13, 14፤ ሥራ 28:16-24

6. ጳውሎስ ምን ሥልጠና ሰጥቷል?

6 ጳውሎስ ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞበታል። ብዙ ጊዜ ሌሎች አብረውት እንዲያገለግሉ ይጋብዝ ነበር። ለምሳሌ በመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞው ላይ ከዮሐንስ ማርቆስ ጋር፣ በሁለተኛው ላይ ደግሞ ከጢሞቴዎስ ጋር አገልግሏል። (ሥራ 12:25፤ 16:1-4) ጳውሎስ ለእነዚህ ወንዶች ጉባኤዎችን ማደራጀት፣ እረኝነት ማድረግ እንዲሁም ውጤታማ አስተማሪ መሆን ስለሚቻልበት መንገድ ለማስተማር የተቻለውን ሁሉ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም።—1 ቆሮ. 4:17

ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጁ በመሆን የጳውሎስን አርዓያ ተከተሉ (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት) *

7. ሽማግሌዎች በኤፌሶን 6:14, 15 ላይ ያለውን የጳውሎስን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

7 የምናገኘው ትምህርት። ሽማግሌዎች ከቤት ወደ ቤት ከመስበክ በተጨማሪ በማንኛውም ሁኔታ ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጁ በመሆን የጳውሎስን አርዓያ መከተል ይችላሉ። (ኤፌሶን 6:14, 15ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ ዕቃ ለመግዛት ሲወጡ ወይም በሥራ ቦታቸው ምሥክርነት መስጠት ይችላሉ። በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ሲካፈሉ ደግሞ ለጎረቤቶቻቸውና ለነጋዴዎች ምሥራቹን መስበክ ይችላሉ። ልክ እንደ ጳውሎስ ሁሉ ሽማግሌዎችም በአገልግሎት የሚያሳልፉትን ጊዜ የጉባኤ አገልጋዮችን ጨምሮ ሌሎችን ለማሠልጠን ይጠቀሙበታል።

8. ሽማግሌዎች አንዳንድ ጊዜ ምን ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል?

8 ሽማግሌዎች በጉባኤ ወይም በወረዳ ሥራ በጣም ከመጠመዳቸው የተነሳ ለስብከቱ ሥራ ጊዜ እንዳያጡ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ ሚዛናቸውን ለመጠበቅ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ‘አልችልም’ ብለው መመለስ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ጉዳዩን በጸሎት ካሰቡበት በኋላ አንዳንድ ኃላፊነቶች ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ጊዜ ሊያሳጧቸው እንደሚችሉ ይገነዘቡ ይሆናል። ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ ማድረግ፣ በስብከቱ ሥራ አዘውትሮ መካፈል ወይም ልጆቻቸውን ለስብከቱ ሥራ ማሠልጠን ይገኙበታል። አንዳንዶች አንድን የአገልግሎት መብት ‘አልችልም’ ብሎ መመለስ ሊከብዳቸው ይችላል፤ ሆኖም ይሖዋ በሁሉም ነገር ሚዛናዊ ለመሆን የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚረዳላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።

አሳቢ እረኛ መሆን

9. ሽማግሌዎች ብዙ ሥራ ስላለባቸው ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥማቸው ይችላል?

9 ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው? የይሖዋ ሕዝቦች ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ሁላችንም ማበረታቻ፣ ድጋፍና ማጽናኛ ያስፈልገናል። አንዳንዶች ደግሞ የተሳሳተ ጎዳና እንዳይከተሉ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (1 ተሰ. 5:14) እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች የይሖዋ ሕዝቦች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በሙሉ ሊያስወግዱ አይችሉም። ያም ቢሆን ይሖዋ ሽማግሌዎች የእሱን በጎች ለማበረታታትና ለመጠበቅ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ ይፈልጋል። ታዲያ ሽማግሌዎች ብዙ ሥራ ቢኖርባቸውም ለወንድሞችና ለእህቶች አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ጊዜ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

ሌሎችን አመስግኑ እንዲሁም አንጿቸው (አንቀጽ 10, 12⁠ን ተመልከት) *

10. በ1 ተሰሎንቄ 2:7 መሠረት ጳውሎስ የይሖዋን ሕዝቦች የተንከባከበው እንዴት ነው?

10 ጳውሎስ የተወው ምሳሌ። ጳውሎስ ወንድሞቹን ለማመስገንና ለማነጽ አጋጣሚ ይፈልግ ነበር። ሽማግሌዎች የይሖዋን ሕዝቦች በፍቅር በመንከባከብ የእሱን ምሳሌ መከተላቸው ተገቢ ነው። (1 ተሰሎንቄ 2:7ን አንብብ።) ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን እንደሚወዳቸውና ይሖዋም እንደሚወዳቸው ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (2 ቆሮ. 2:4፤ ኤፌ. 2:4, 5) በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን እንደ ወዳጅ በመቁጠር አብሯቸው ጊዜ ያሳልፍ ነበር። ስለሚያስፈሩት ነገሮችና ስለ ድክመቶቹ በግልጽ በመናገር እንደሚያምናቸው አሳይቷል። (2 ቆሮ. 7:5፤ 1 ጢሞ. 1:15) ያም ቢሆን ጳውሎስ በራሱ ችግሮች ላይ አላተኮረም። ከዚህ ይልቅ ወንድሞቹን በመርዳት ላይ አተኩሯል።

11. ጳውሎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ምክር የሰጠው ለምንድን ነው?

11 ጳውሎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ምክር መስጠት ያስፈለገው ጊዜ ነበር። ሆኖም ይህን ያደረገው በእነሱ ስለተበሳጨ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምክር የሰጣቸው ስለሚያስብላቸውና ከተለያዩ አደጋዎች ጥበቃ ሊያደርግላቸው ስለፈለገ ነው። ምክር ይሰጥ የነበረው ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ ነበር፤ ደግሞም ወንድሞችና እህቶች ለምክሩ የሚሰጡት ምላሽ ያሳስበው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጠንካራ ምክር ሰጥቷል። ይህን ደብዳቤ ከጻፈ በኋላ ቲቶን ላከላቸው። ጳውሎስ ወንድሞች ለደብዳቤው የሰጡትን ምላሽ ለማወቅ ጓጉቶ ነበር። ምክሩን በሥራ ላይ እንዳዋሉት ሲሰማ ምንኛ ተደስቶ ይሆን!—2 ቆሮ. 7:6, 7

12. ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ማበረታታት የሚችሉት እንዴት ነው?

12 የምናገኘው ትምህርት። ሽማግሌዎች ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር ጊዜ በማሳለፍ ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። ይህን ማድረግ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ከጉባኤ ስብሰባዎች በፊት ቀደም ብሎ ደርሶ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር የሚያንጽ ጭውውት ማድረግ ነው። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የሚያስፈልጋቸውን ፍቅራዊ ማበረታቻ ለመስጠት ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በቂ ሊሆኑ ይችላሉ። (ሮም 1:12፤ ኤፌ. 5:16) በተጨማሪም ሽማግሌዎች የአምላክን ቃል ተጠቅመው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በማነጽና ይሖዋ እንደሚወዳቸው ማረጋገጫ በመስጠት የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። ከዚህም ሌላ በሥራቸው ላለው መንጋ ፍቅራቸውን ያሳያሉ። ወንድሞቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅና አጋጣሚውን ፈልገው እነሱን ለማመስገን ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች ምክር መስጠት ካስፈለጋቸው ምክሩን የሚሰጡት በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተው ነው። ወንድሞችና እህቶች ለምክራቸው የሚሰጡት ምላሽ ስለሚያሳስባቸው ምክሩን የሚሰጡት በግልጽ ሆኖም በደግነት ነው።—ገላ. 6:1

ከግል ድክመቶች ጋር ትግል ማድረግ

13. ሽማግሌዎች በግል ድክመቶቻቸው የተነሳ ምን ሊሰማቸው ይችላል?

13 ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው? ሽማግሌዎች ፍጹም አይደሉም። እንደ ማንኛውም ሰው ስህተት ይሠራሉ። (ሮም 3:23) አንዳንድ ጊዜ ለድክመቶቻቸው ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ሊከብዳቸው ይችላል። አንዳንድ ሽማግሌዎች በድክመቶቻቸው ላይ ከልክ በላይ ከማተኮራቸው የተነሳ ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ለድክመቶቻቸው ሰበብ አስባብ ማቅረብ ሊቀናቸው ይችላል፤ ይህም ቸልተኛ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ከመሆኑም ሌላ ተገቢውን ማስተካከያ እንዳያደርጉ እንቅፋት ይሆንባቸዋል።

14. በፊልጵስዩስ 4:13 መሠረት ጳውሎስ ትሑት መሆኑ ለድክመቶቹ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረው የረዳው እንዴት ነው?

14 ጳውሎስ የተወው ምሳሌ። ጳውሎስ በራሱ ጥረት ድክመቶቹን ማሸነፍ እንደማይችል በትሕትና አምኖ ተቀብሏል። አምላክ የሚሰጠው ኃይል ያስፈልገው ነበር። ቀደም ሲል ጳውሎስ በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ስደት የሚያደርስ ግትር ሰው ነበር። በኋላ ላይ ግን ስህተቱን አምኖ በመቀበል አመለካከቱንና ባሕርይውን ለማስተካከል ፈቃደኛ ሆኗል። (1 ጢሞ. 1:12-16) በይሖዋ እርዳታ ጳውሎስ አፍቃሪ፣ ሩኅሩኅና ትሑት እረኛ መሆን ችሏል። ድክመቶቹን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፤ ያም ቢሆን ስህተቶቹን እያሰበ ከመብሰልሰል ይልቅ በይሖዋ ይቅር ባይነት ላይ ለማተኮር መርጧል። (ሮም 7:21-25) ከራሱ ፍጽምናን አልጠበቀም። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያናዊ ባሕርያቱን ለማሻሻል በትጋት ሠርቷል፤ እንዲሁም በትሕትና በይሖዋ በመታመን ሥራውን አከናውኗል።—1 ቆሮ. 9:27፤ ፊልጵስዩስ 4:13ን አንብብ።

ያሉባችሁን ድክመቶች ለማሸነፍ ጠንክራችሁ ሥሩ (ከአንቀጽ 14-15⁠ን ተመልከት) *

15. ሽማግሌዎች ለድክመቶቻቸው ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

15 የምናገኘው ትምህርት። ሽማግሌዎች የሚሾሙት ፍጹም ስለሆኑ አይደለም። ሆኖም ይሖዋ ስህተታቸውን አምነው እንዲቀበሉና ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ይጠብቅባቸዋል። (ኤፌ. 4:23, 24) አንድ ሽማግሌ የአምላክን ቃል ተጠቅሞ ራሱን በመመርመር አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይኖርበታል። እንዲህ ካደረገ ይሖዋ ደስተኛና ስኬታማ እንዲሆን ይረዳዋል።—ያዕ. 1:25

የሌሎችን አለፍጽምና መቻል

16. አንድ ሽማግሌ በሌሎች አለፍጽምና ላይ ካተኮረ ምን ሊፈጠር ይችላል?

16 ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው? ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር ተቀራርበው ስለሚሠሩ የእነሱን ድክመት ሊያስተውሉ ይችላሉ። ሆኖም ካልተጠነቀቁ ሊበሳጩ፣ ደግነት የጎደለው ነገር ሊያደርጉ ወይም ነቃፊ ሊሆኑ ይችላሉ። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ሲያስጠነቅቅ ሰይጣን የሚፈልገው ይህንኑ እንደሆነ ተናግሯል።—2 ቆሮ. 2:10, 11

17. ጳውሎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ምን አመለካከት ነበረው?

17 ጳውሎስ የተወው ምሳሌ። ጳውሎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ አዎንታዊ አመለካከት ነበረው። የሚሠሯቸውን ስህተቶች በሚገባ ያውቅ ነበር፤ እንዲያውም እነሱ በፈጸሙት ስህተት የተጎዳበት ጊዜ ነበር። ይሁንና ጳውሎስ አንድ ሰው መጥፎ ነገር ስላደረገ ግለሰቡ መጥፎ ሰው ነው ብሎ መደምደም ተገቢ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ለወንድሞቹ ፍቅር የነበረው ሲሆን በመልካም ጎናቸው ላይ አተኩሯል። ወንድሞቹና እህቶቹ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ በሚከብዳቸው ጊዜ ውስጣዊ ዝንባሌያቸውን ከመጠራጠር ይልቅ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ያስብ ነበር።

18. ጳውሎስ፣ የኤዎድያንን እና የሲንጤኪን ጉዳይ ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝታችኋል? (ፊልጵስዩስ 4:1-3)

18 ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ጉባኤ የነበሩ ሁለት እህቶችን እንዴት እንደረዳቸው እንመልከት። (ፊልጵስዩስ 4:1-3ን አንብብ።) ኤዎድያን እና ሲንጤኪ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ተቀያይመው ነበር። ጳውሎስ ደግነት የጎደለው ነገር ከመናገር ወይም ከመንቀፍ ይልቅ በመልካም ባሕርያቸው ላይ አተኩሯል። ሁለቱም መልካም ስም ያተረፉ ታማኝ እህቶች ናቸው። ይሖዋ እንደሚወዳቸው ጳውሎስ ያውቅ ነበር። ጳውሎስ ለእነዚህ እህቶች አዎንታዊ አመለካከት መያዙ ቅራኔያቸውን እንዲፈቱ ማበረታቻ ለመስጠት አነሳስቶታል። በተጨማሪም እንዲህ ያለ አመለካከት መያዙ ደስታውን እንዳያጣና በዚያ ጉባኤ ካሉ ወንድሞች ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ይዞ እንዲቀጥል አስችሎታል።

ነቃፊ ላለመሆን ጥረት አድርጉ (አንቀጽ 19⁠ን ተመልከት) *

19. (ሀ) ሽማግሌዎች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው አዎንታዊ አመለካከት መያዝ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) የስብሰባ አዳራሹን እያጸዳ ያለውን ሽማግሌ ከሚያሳየው ሥዕላዊ መግለጫ ምን ትማራላችሁ?

19 የምናገኘው ትምህርት። ሽማግሌዎች፣ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ያሏቸውን መልካም ባሕርያት ለማስተዋል ጥረት አድርጉ። ሁሉም ወንድሞችና እህቶች ፍጹም እንዳልሆኑ የታወቀ ነው፤ ሆኖም እያንዳንዳቸው የሚደነቅ ባሕርይ አላቸው። (ፊልጵ. 2:3) እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች ለአንድ ወንድም ወይም ለአንዲት እህት እርማት መስጠት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሊኖር ይችላል። ሆኖም ልክ እንደ ጳውሎስ ግለሰቡ በሚናገራቸውና በሚያደርጋቸው የሚያበሳጩ ነገሮች ላይ ላለማተኮር ጥረት ማድረግ አለባቸው። ከዚህ ይልቅ ወንድም ለይሖዋ ባለው ፍቅር፣ አምላክን ለማገልገል ሲል እያሳየ ባለው ጽናት እንዲሁም መልካም ለማድረግ ባለው አቅም ላይ ማተኮራቸው የተሻለ ነው። አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ፍቅር እንዲሰፍን ያደርጋሉ።

የጳውሎስን አርዓያ መከተላችሁን ቀጥሉ

20. ሽማግሌዎች ጳውሎስ ከተወው ምሳሌ ቀጣይ የሆነ ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

20 እናንት ሽማግሌዎች፣ የጳውሎስን አርዓያ መመርመራችሁን በመቀጠል ብዙ ጥቅም ማግኘት ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ስለ አምላክ መንግሥት የተሟላ ምሥክርነት መስጠት’ የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 12 ከአንቀጽ 17-20 እና ምዕራፍ 21 አንቀጽ 6-7 መመልከት ትችላላችሁ። የተጠቀሱትን ሐሳቦች ስታነብቡ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ጳውሎስ የተወው ምሳሌ ሽማግሌ እንደመሆኔ መጠን ያለብኝን ኃላፊነት ስወጣ ደስታዬን እንድጠብቅ የሚረዳኝ እንዴት ነው?’

21. ሽማግሌዎች ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን ይችላሉ?

21 ሽማግሌዎች፣ ይሖዋ ከእናንተ የሚጠብቀው ፍጽምናን ሳይሆን ታማኝነትን እንደሆነ አስታውሱ። (1 ቆሮ. 4:2) ይሖዋ ጳውሎስ ያሳየውን ትጋትና ታማኝነት ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል። አምላክ እናንተም በእሱ አገልግሎት የምታከናውኑትን ነገር እንደሚያደንቅ መተማመን ትችላላችሁ። ይሖዋ “ቅዱሳንን በማገልገልም ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር” ፈጽሞ አይረሳም።—ዕብ. 6:10

መዝሙር 87 ኑ! እረፍት አግኙ

^ አን.5 አፍቃሪና አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች እኛን ለመርዳት ሲሉ በትጋት ለሚያከናውኑት ሥራ በጣም አመስጋኞች ነን! በዚህ ርዕስ ውስጥ ሽማግሌዎች ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን አራት ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንመለከታለን። በተጨማሪም የሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲያሸንፉ የሚረዳቸው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። ይህ ርዕስ ሁላችንም የሽማግሌዎችን ስሜት እንድንረዳ ያግዘናል፤ እንዲሁም ፍቅር እንድናሳያቸውና እንድንደግፋቸው ያነሳሳናል።

^ አን.61 የሥዕሉ መግለጫ፦ ከሥራ ቦታው እየወጣ ያለ አንድ ወንድም ለሥራ ባልደረባው ሲመሠክር።

^ አን.63 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ሽማግሌ ራሱን የማግለል ዝንባሌ ያለውን ወንድም በደግነት ሲያበረታታው።

^ አን.65 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም በአንድ ጉዳይ ቅር ለተሰኘ ሌላ ወንድም ጠቃሚ ምክር ሲሰጠው።

^ አን.67 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ሽማግሌ አንድ ወንድም በፈቃደኝነት የተቀበለውን ሥራ ችላ በማለቱ አልነቀፈውም።