በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 17

እናቶች—ከኤውንቄ ምሳሌ ተማሩ

እናቶች—ከኤውንቄ ምሳሌ ተማሩ

“[የእናትህን] መመሪያ አትተው። ለራስህ የሚያምር የአበባ ጉንጉን፣ ለአንገትህም ውብ ጌጥ ይሆንልሃል።”—ምሳሌ 1:8, 9

መዝሙር 137 ታማኝ ሴቶች፣ ክርስቲያን እህቶች

ማስተዋወቂያ a

ጢሞቴዎስ በሚጠመቅበት ወቅት እናቱ ኤውንቄ እና አያቱ ሎይድ በኩራት ሲመለከቱት (አንቀጽ 1⁠ን ተመልከት)

1-2. (ሀ) ኤውንቄ ማን ነበረች? ልጇን ስታሳድግ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟታል? (ለ) በሽፋኑ ሥዕል ላይ ሐሳብ ስጥ።

 መጽሐፍ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሲጠመቅ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ባይናገርም እናቱ ኤውንቄ በዚያ ዕለት የተሰማትን ደስታ መገመት አያዳግትም። (ምሳሌ 23:25) ጢሞቴዎስ ውኃ ውስጥ ቆሞ ሳለ በኩራት ስትመለከተው ይታያችሁ። ከጢሞቴዎስ አያት ከሎይድ ጋር ፈገግ ብላ ቆማለች። ጢሞቴዎስ ወደ ውኃው ሲጠልቅ ኤውንቄ ልቧ ስቅል አለ። ከዚያም ጢሞቴዎስ ውኃውን አንቦራጭቆ በፈገግታ ወጣ። በዚህ ጊዜ ኤውንቄ እንባዋን መቆጣጠር አቃታት። ኤውንቄ ልጇ ይሖዋንና ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲወድ በማስተማር ረገድ ተሳክቶላታል። ኤውንቄ እዚህ ደረጃ ላይ እስክትደርስ ድረስ ምን ፈተናዎች አጋጥመዋታል?

2 ጢሞቴዎስ ያደገው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቱ ግሪካዊ ነበር፤ እናቱና አያቱ ደግሞ አይሁዳውያን ነበሩ። (ሥራ 16:1) ኤውንቄ እና ሎይድ ክርስትናን ሲቀበሉ ጢሞቴዎስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ያለ ወጣት ሳይሆን አይቀርም። አባቱ ግን ክርስትናን አልተቀበለም። ታዲያ ጢሞቴዎስ የትኛውን ጎዳና ይመርጥ ይሆን? በወቅቱ የራሱን ውሳኔ ማድረግ የሚችልበት ዕድሜ ላይ ደርሶ መሆን አለበት። አማኝ ካልሆነው አባቱ ጎን ይቆም ይሆን? ከልጅነቱ ጀምሮ የተማረውን የአይሁዳውያን ወግ ይከተል ይሆን? ወይስ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ይመርጣል?

3. በምሳሌ 1:8, 9 መሠረት ይሖዋ፣ እናቶች ልጆቻቸው የእሱ ወዳጆች እንዲሆኑ ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት እንዴት ይመለከተዋል?

3 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን እናቶችም ቤተሰባቸውን ይወዳሉ። ከምንም ነገር በላይ የሚፈልጉት ልጆቻቸው ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖራቸው መርዳት ነው። አምላካችንም ጥረታቸውን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ምሳሌ 1:8, 9ን አንብብ።) ይሖዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን እናቶች ልጆቻቸውን ስለ እሱ እንዲያስተምሩ ረድቷቸዋል።

4. በዛሬው ጊዜ ያሉ እናቶች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?

4 እናቶች ‘ልጆቻችን እንደ ጢሞቴዎስ ይሖዋን ለማገልገል ይመርጣሉ ወይስ አይመርጡም?’ የሚለው ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይችላል። ምክንያቱም ልጆች በሰይጣን ዓለም ውስጥ ምን ያህል ፈተና እንደሚያጋጥማቸው ወላጆች በሚገባ ያውቃሉ። (1 ጴጥ. 5:8) በተጨማሪም ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ያለአባት ወይም ይሖዋን ከማያገለግል አባት ጋር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲን b የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ቤተሰቡን የሚወድ ጥሩ አባት ነው። ሆኖም ልጆቻችንን የይሖዋ ምሥክር አድርጌ እንዳላሳድግ ተቃውሞኛል። ልጆቼ ይሖዋን ማገልገል የሚችሉት እንዴት ነው የሚለው ጉዳይ ስለሚያሳስበኝ ብዙ ጊዜ አለቅስ ነበር።”

5. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

5 ክርስቲያን እናቶች፣ እንደ ኤውንቄ ሊሳካላችሁ ይችላል። በቃል እና በምግባር ልጆቻችሁን በማስተማር ረገድ የእሷን ምሳሌ መከተል የምትችሉት እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። ይሖዋ የሚረዳችሁ እንዴት እንደሆነም እናያለን።

ልጆቻችሁን በቃል አስተምሩ

6. በ2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15 ላይ እንደተገለጸው ጢሞቴዎስ ክርስቲያን የሆነው እንዴት ነው?

6 ጢሞቴዎስ ትንሽ ልጅ ሳለ እናቱ በአይሁድ እምነት መሠረት ቅዱሳን መጻሕፍትን ለእሱ ለማስተማር የቻለችውን ሁሉ ጥረት አድርጋለች። እርግጥ እውቀቷ ውስን ነበር፤ ምክንያቱም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የምታውቀው ነገር አልነበረም። ሆኖም ጢሞቴዎስ ከቅዱሳን መጻሕፍት የተማረው ነገር ክርስትናን ለመቀበል ጥሩ መሠረት ሆኖታል። ግን ክርስትናን ይቀበል ይሆን? ወጣት ሳለ ክርስቲያን ለመሆን ወይም ላለመሆን መምረጥ ይችል ነበር። ጢሞቴዎስ ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን እውነት ‘አምኖ እንዲቀበል’ እናቱም የበኩሏን ሚና እንደተጫወተች ጥርጥር የለውም። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15ን አንብብ።) ኤውንቄ ልጇን ስለ ይሖዋ በማስተማር ረገድ የተሳካላት በመሆኑ ምንኛ ተደስታ ይሆን! በእርግጥም ኤውንቄ እንደ ስሟ ትርጉም ‘ድል አድራጊ’ ነበረች።

7. ኤውንቄ ልጇ ከተጠመቀ በኋላ እድገት እንዲያደርግ የረዳችው እንዴት ሊሆን ይችላል?

7 ጢሞቴዎስ ሲጠመቅ በሕይወቱ ውስጥ አንድ ወሳኝ ግብ ላይ ደርሷል። ሆኖም ኤውንቄ ልጇ ከተጠመቀም በኋላ ስለ እሱ መጨነቋን አላቆመችም። ልጇ ቀሪውን ዕድሜውን የሚጠቀምበት እንዴት ይሆን? ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ይገጥም ይሆን? ትምህርቱን ለመከታተል ወደ አቴንስ ሄዶ የአረማዊ ፈላስፎችን ትምህርት ይቀበል ይሆን? የሀብት ባሪያ በመሆን ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ወጣትነቱን ያባክን ይሆን? ኤውንቄ ለጢሞቴዎስ ውሳኔ ልታደርግለት አትችልም። ሆኖም ልትረዳው ትችላለች። እንዴት? ልጇ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር እንዲሁም ለኢየሱስ አመስጋኝነት እንዲያዳብር ለመርዳት ጥረት ማድረጓን መቀጠል ትችላለች። እርግጥ ተፈታታኝ ሁኔታ የሚያጋጥመው በሃይማኖት በተከፋፈሉ ቤተሰቦች ውስጥ ብቻ አይደለም። ሁለቱም ወላጆች እውነት ውስጥ ቢሆኑም እንኳ የወጣቶችን ልብ መንካትና ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ወላጆች ከኤውንቄ ምሳሌ ምን ይማራሉ?

8. እናቶች አማኝ የሆነ የትዳር ጓደኛቸው የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት ሊያግዙት የሚችሉት እንዴት ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስን ከልጆቻችሁ ጋር አጥኑ። እህቶች፣ የትዳር ጓደኛችሁ እውነት ውስጥ ከሆነ የልጆቻችሁን መንፈሳዊ ፍላጎት በማሟላት ረገድ እንድታግዙት ይሖዋ ይፈልጋል። ይህን ማድረግ የምትችሉበት አንዱ መንገድ የቤተሰብ አምልኮ ዝግጅትን አዘውትራችሁ በመደገፍ ነው። ስለ ቤተሰብ አምልኮ ዝግጅት አዎንታዊ ነገሮችን ተናገሩ፤ እንዲሁም አስደሳች መንፈስ እንዲሰፍን ለማድረግ የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። ምናልባት የትዳር ጓደኛችሁ ለየት ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮጀክት እንዲያዘጋጅ ልትረዱት ትችሉ ይሆናል። በተጨማሪም አንዳንዶቹ ልጆቻችሁ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት በግል መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ዕድሜያቸው ደርሶ ከሆነ እነሱን በማስጠናት ረገድ ለትዳር ጓደኛችሁ አስፈላጊውን እርዳታ ማበርከት ትችላላችሁ።

9. አማኝ የሆነ ባል የሌላቸው እናቶች እርዳታ ማግኘት የሚችሉት ከየት ነው?

9 አንዳንድ እናቶች ነጠላ ወላጅ በመሆናቸው ወይም የትዳር ጓደኛቸው አማኝ ባለመሆኑ የተነሳ እነሱ ራሳቸው ልጆቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ይጠበቅባቸው ይሆናል። የቤተሰባችሁ ሁኔታ እንዲህ ከሆነ ከልክ በላይ አትጨነቁ። ይሖዋ ይረዳችኋል። ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት ያዘጋጀላችሁን ውጤታማ የማስተማሪያ መሣሪያዎች ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁን አስተምሩ። እነዚህን መሣሪያዎች ለቤተሰብ አምልኳችሁ መጠቀም የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ጠቃሚ ምክር እንዲሰጧችሁ ተሞክሮ ያላቸውን ወላጆች ለምን አታማክሩም? c (ምሳሌ 11:14) በተጨማሪም ከልጆቻችሁ ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ይሖዋ ይረዳችኋል። በአእምሯቸውና በልባቸው ውስጥ ያለውን ለማወቅ እንዲረዳችሁ ይሖዋን ጠይቁት። (ምሳሌ 20:5) ለምሳሌ ልጃችሁን ‘ትምህርት ቤት የሚያጋጥምህ በጣም ከባዱ ተፈታታኝ ሁኔታ ምንድን ነው?’ ብላችሁ ብትጠይቁት ጥሩ ውይይት ልታደርጉ ትችላላችሁ።

10. ልጆቻችሁ ስለ ይሖዋ እንዲማሩ መርዳት የምትችሉበት ሌላ መንገድ የትኛው ነው?

10 ልጆቻችሁን ስለ ይሖዋ ለማስተማር አጋጣሚ ፍጠሩ። ስለ ይሖዋና እሱ ስላደረገላችሁ ብዙ መልካም ነገሮች ተናገሩ። (ዘዳ. 6:6, 7፤ ኢሳ. 63:7) በተለይም ልጆቻችሁን በቋሚነት ማስጠናት የማትችሉ ከሆነ እንዲህ ማድረጋችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ክርስቲን እንዲህ ብላለች፦ “መንፈሳዊ ነገሮችን ለመወያየት ብዙም አጋጣሚ ስለማላገኝ ያገኘሁትን ማንኛውንም አጋጣሚ ጥሩ አድርጌ ለመጠቀም እሞክር ነበር። በእግር አብረን ስንንሸራሸር ወይም በጀልባ እየቀዘፍን ስንሄድ ስለ ይሖዋ አስደናቂ ፍጥረታትና ሰለተለያዩ መንፈሳዊ ነገሮች እንጨዋወታለን። ልጆቻችን ዕድሜያቸው ከፍ ሲል መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው እንዲያጠኑ አበረታታቸው ነበር።” በተጨማሪም ስለ ይሖዋ ድርጅት እንዲሁም ስለ ወንድሞችና እህቶች አዎንታዊ ነገር ተናገሩ። ሽማግሌዎችን አትተቹ። ስለ ሽማግሌዎች የምትናገሩት ነገር ልጆቻችሁ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ወደ እነሱ ዞር እንዳይሉ እንቅፋት ሊሆን ይችላል።

11. በያዕቆብ 3:18 መሠረት በቤት ውስጥ ሰላም ማስፈን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 በቤት ውስጥ ሰላም አስፍኑ። ለትዳር ጓደኛችሁና ለልጆቻችሁ ያላችሁን ፍቅር አዘውትራችሁ ግለጹ። ስለ ባላችሁ በደግነትና በአክብሮት ተናገሩ፤ ልጆቻችሁም እንዲሁ እንዲያደርጉ አሠልጥኗቸው። እንዲህ ስታደርጉ ስለ ይሖዋ ለመማር የሚያመች ሰላማዊ መንፈስ እንዲሰፍን ታደርጋላችሁ። (ያዕቆብ 3:18ን አንብብ።) በሩማንያ በልዩ አቅኚነት የሚያገለግለውን ዮሴፍን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዮሴፍ ልጅ እያለ እሱ፣ እናቱ፣ እህቱና ወንድሞቹ ይሖዋን እንዳያገለግሉ አባቱ እንቅፋት ፈጥሮባቸው ነበር። ዮሴፍ እንዲህ ብሏል፦ “እናቴ በቤት ውስጥ ሰላም ለማስፈን ጥረት ታደርግ ነበር። የአባቴ ተቃውሞ ሲበረታ የእሷም ደግነት ይጨምር ነበር። አባታችንን ማክበርና መታዘዝ እየከበደን እንደመጣ ስታስተውል ኤፌሶን 6:1-3⁠ን ታወያየን ነበር። ከዚያም አባታችን ያሉትን ግሩም ባሕርያት በመጥቀስ እሱን ማክበር ያለብን ለምን እንደሆነ ታስረዳናለች። በዚህ መንገድ ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን ብዙ ጊዜ ማርገብ ችላለች።”

ልጆቻችሁን በምግባር አስተምሩ

12. በ2 ጢሞቴዎስ 1:5 መሠረት ኤውንቄ ለጢሞቴዎስ ምን ምሳሌ ትታለታለች?

12 ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 1:5ን አንብብ። ኤውንቄ ለጢሞቴዎስ ጥሩ ምሳሌ ሆናለታለች። እውነተኛ እምነት በሥራ መገለጽ እንዳለበት አስተምራው መሆን አለበት። (ያዕ. 2:26) ጢሞቴዎስ እናቱ ማንኛውንም ነገር የምታደርገው ለይሖዋ ባላት ጠንካራ ፍቅር ተነሳስታ እንደሆነ ማየቱ አይቀርም። እናቱ ይሖዋን ማገልገሏ ደስታ እንዳስገኘላት አስተውሎ መሆን አለበት። የኤውንቄ ምሳሌነት በጢሞቴዎስ ላይ ምን ውጤት አምጥቷል? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ጢሞቴዎስ እንደ እናቱ ጠንካራ እምነት ነበረው። ይህ እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ ነገር አይደለም። ጢሞቴዎስ የእናቱን ምሳሌነት አስተውሏል፤ እንዲሁም እንደ እሷ ለመሆን ተነሳስቷል። በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ ብዙ እናቶች “ያለቃል” የቤተሰባቸውን አባሎች ልብ መንካት ችለዋል። (1 ጴጥ. 3:1, 2) እናንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላላችሁ። እንዴት?

13. እናቶች ከይሖዋ ጋር ላላቸው ዝምድና ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው?

13 ከይሖዋ ጋር ላላችሁ ዝምድና ቅድሚያ ስጡ። (ዘዳ. 6:5, 6) እንደ አብዛኞቹ እናቶች እናንተም ብዙ መሥዋዕት ትከፍላላችሁ። የልጆቻችሁን አካላዊ ፍላጎት ለማሟላት ጊዜያችሁን፣ ገንዘባችሁን፣ እንቅልፋችሁን እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን መሥዋዕት ታደርጋላችሁ። ይሁንና ቤተሰባችሁን በመንከባከብ ከመጠመዳችሁ የተነሳ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና መሥዋዕት እንዳታደርጉ መጠንቀቅ ይኖርባችኋል። ብቻችሁን ለመጸለይ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችሁ ለማጥናት እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አዘውትራችሁ ጊዜ መድቡ። እንዲህ ካደረጋችሁ የራሳችሁን መንፈሳዊነት ታጠናክራላችሁ፤ እንዲሁም ለቤተሰባችሁ አልፎ ተርፎም ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ትሆናላችሁ።

14-15. ከሊያን፣ ከማሪያ እና ከዧው ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝታችኋል?

14 እናቶቻቸውን በማየት ይሖዋን መውደድና በእሱ ላይ እምነት ማሳደር የቻሉ ጥቂት ወጣቶችን ምሳሌ እንመልከት። የክርስቲን ልጅ የሆነችው ሊያን እንዲህ ብላለች፦ “በነፃነት ማጥናት አንችልም ነበር። ሆኖም እናቴ በፍጹም ከስብሰባ ቀርታ አታውቅም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ እውቀት ባይኖረንም የእሷ ምሳሌነትና ቁርጠኝነት ጠንካራ እምነት እንድንገነባ ረድቶናል። በስብሰባዎች ላይ መገኘት ከመጀመራችን ከረጅም ጊዜ በፊትም የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንደሚያስተምሩ አውቀን ነበር።”

15 ማሪያ እና ቤተሰቧ በስብሰባ ላይ ሲገኙ አባትየው አንዳንድ ጊዜ ይቀጣቸው ነበር። ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ከማውቃቸው እጅግ ደፋር እህቶች አንዷ ናት። ልጅ ሳለሁ ‘ሌሎች ምን ይሉኛል’ ብዬ በመፍራት አንዳንድ ነገሮችን ከማድረግ ወደኋላ የምልበት ጊዜ ነበር። ሆኖም የእሷን የድፍረት ምሳሌ መመልከቴና ይሖዋን ምንጊዜም እንደምታስቀድም ማስተዋሌ የሰው ፍርሃቴን ለማሸነፍ ረድቶኛል።” የዧው አባት ቤተሰቡ ቤት ውስጥ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች እንዳይወያዩ ይከለክል ነበር። ዧው እንዲህ ብሏል፦ “እናቴ አባቴን ለማስደሰት ስትል ለይሖዋ ካላት ፍቅር በስተቀር ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነበረች፤ ይህም ልቤን በእጅጉ ነክቶታል።”

16. የእናቶች ምሳሌ በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

16 እናቶች፣ መልካም ምሳሌነታችሁ በሌሎች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስታውሱ። እንዴት? የኤውንቄ ምሳሌ በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ ምን ተጽዕኖ እንዳሳደረ ልብ በሉ። ግብዝነት የሌለበት የጢሞቴዎስ እምነት “በመጀመሪያ . . . በኤውንቄ ዘንድ” እንደነበር ጳውሎስ ተናግሯል። (2 ጢሞ. 1:5) ጳውሎስ የኤውንቄን እምነት መጀመሪያ ላይ ያስተዋለው መቼ ነው? ጳውሎስ ከሎይድና ከኤውንቄ ጋር በልስጥራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘው በመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ሳይሆን አይቀርም፤ ምናልባትም ክርስቲያን እንዲሆኑ የረዳቸው እሱ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 14:4-18) የሚገርመው ከ15 ዓመታት ገደማ በኋላ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት የኤውንቄን ታማኝነት አስታውሶ ነበር። እንዲሁም እምነቷ ሊኮረጅ የሚገባው እንደሆነ ገልጿል። የኤውንቄ ምሳሌነት ሐዋርያው ጳውሎስንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖችን አበረታቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። እናንተም ልጆቻችሁን የምታሳድጉት ብቻችሁን ወይም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ከሆነ የታማኝነት ምሳሌያችሁ በዙሪያችሁ ያሉትን እንደሚያጠናክርና እንደሚያነቃቃ አትዘንጉ።

ልጃችሁ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ መርዳት ጊዜ ይጠይቃል። በመሆኑም ተስፋ አትቁረጡ! (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

17. ልጃችሁ ለምትሰጡት ሥልጠና በጎ ምላሽ እንደሰጠ ባይሰማችሁ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?

17 ልጃችሁ ለምታደርጉት ጥረት ጥሩ ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ ባይሰማችሁስ? ልጆችን ማሠልጠን ጊዜ እንደሚወስድ አትርሱ። ሥዕሉ ላይ እንደምታዩት፣ አንድ ዘር ስትዘሩ ተክሉ አድጎ ያፈራ እንደሆነ የምትጠራጠሩበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። የተክሉን እድገት መቆጣጠር ባትችሉም ውኃ በማጠጣት ተክሉ እንዲያድግ ሁኔታውን ልታመቻቹለት ትችላላችሁ። (ማር. 4:26-29) በተመሳሳይም የልጆቻችሁን ልብ መንካት መቻላችሁን ትጠራጠሩ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ውጤቱን መቆጣጠር አትችሉም። ሆኖም እነሱን ለማሠልጠን የምትችሉትን ሁሉ ማድረጋችሁን ከቀጠላችሁ በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታ ትፈጥሩላቸዋላችሁ።—ምሳሌ 22:6

በይሖዋ እርዳታ ታመኑ

18. ይሖዋ ልጆቻችሁ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

18 ከጥንት ዘመን አንስቶ ይሖዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወጣቶች ወዳጆቹ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። (መዝ. 22:9, 10) የእናንተም ልጆች ከፈለጉ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ይሖዋ ሊረዳቸው ይችላል። (1 ቆሮ. 3:6, 7) ልጆቻችሁ ከእውነት ቤት ቢርቁም እንኳ ይሖዋ እነሱን በፍቅር መከታተሉን ይቀጥላል። (መዝ. 11:4) “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” እንዳላቸው በትንሹ እንኳ ካሳዩ እነሱን ለመርዳት ፈጣን እርምጃ ይወስዳል። (ሥራ 13:48፤ 2 ዜና 16:9) ልጆቻችሁ እርዳታ ሲያስፈልጋቸው ትክክለኛውን ቃል በትክክለኛው ጊዜ እንድትናገሩ ሊረዳችሁ ይችላል። (ምሳሌ 15:23) ወይም ደግሞ በጉባኤያችሁ ያለ አንድ አሳቢ ወንድም ወይም እህት ለልጃችሁ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት ሊያነሳሳቸው ይችላል። ልጆቻችሁ አዋቂ ከሆኑ በኋላም እንኳ ይሖዋ ልጅ ሳሉ ያስተማራችኋቸውን ነገር እንዲያስታውሱ ሊረዳቸው ይቻላል። (ዮሐ. 14:26) በቃል እና በምግባር ልጆቻችሁን ማሠልጠናችሁን ከቀጠላችሁ ይሖዋ ጥረታችሁን ይባርክላችኋል።

19. የይሖዋን ሞገስ እንደምታገኙ መተማመን የምትችሉት ለምንድን ነው?

19 ይሖዋ ለእናንተ ያለው ፍቅር ልጆቻችሁ በሚያደርጉት ምርጫ ላይ የተመካ አይደለም። ይሖዋ የሚወዳችሁ ስለምትወዱት ነው። ልጆቻችሁን የምታሳድጉት ብቻችሁን ከሆነ ይሖዋ ለልጆቻችሁ አባት፣ ለእናንተ ደግሞ ጠባቂ ለመሆን ቃል ገብቷል። (መዝ. 68:5) የልጆቻችሁን ምርጫ መቆጣጠር አትችሉም። ሆኖም ይሖዋ በሚሰጣችሁ እርዳታ ከታመናችሁና አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ካደረጋችሁ የእሱን ሞገስ ታገኛላችሁ።

መዝሙር 134 ልጆች ከአምላክ በአደራ የተሰጡ ናቸው

a ይህ ርዕስ፣ ክርስቲያን እናቶች ከጢሞቴዎስ እናት ከኤውንቄ የሚያገኙትን ትምህርት ያብራራል፤ እንዲሁም ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲያውቁትና እንዲወዱት ለመርዳት ያግዛቸዋል።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

c ለምሳሌ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 50 እንዲሁም በነሐሴ 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 6-7 ላይ የወጣውን “ለቤተሰብ አምልኮና ለግል ጥናት የሚሆኑ ጠቃሚ ሐሳቦች” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።