በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌለው ፍቺ ከፈጸመ በኋላ ሌላ ሴት ቢያገባ ጉባኤው የቀድሞውን ትዳሩንና አዲሱን ትዳሩን የሚመለከተው እንዴት ነው?

▪ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ጉባኤው ሁኔታውን የሚመለከተው እንደሚከተለው ነው፦ ግለሰቡ ድጋሚ ባገባበት ወቅት የቀድሞ ትዳሩ ፈርሷል፤ አዲሱ ትዳሩ ደግሞ ሕጋዊ ነው። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረስንበትን ምክንያት ለመረዳት ኢየሱስ ስለ ፍቺ እና ድጋሚ ስለማግባት ምን እንዳለ እንመርምር።

በማቴዎስ 19:9 ላይ ኢየሱስ፣ ትዳርን ለማፍረስ የሚያበቃው ብቸኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ምን እንደሆነ ተናግሯል። “በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል” ብሏል። ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ ሁለት ነጥቦችን እንማራለን፦ (1) ትዳር በፍቺ እንዲፈርስ የሚያደርገው ብቸኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የፆታ ብልግና ነው፤ (2) እንዲህ ያለው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ሳይኖር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሰው ምንዝር ይፈጽማል። a

ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ የፆታ ብልግና ፈጽሞ ሚስቱን የሚፈታ ሰው ድጋሚ ለማግባት ቅዱስ ጽሑፋዊ ነፃነት እንዳለው የሚያሳይ ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። በትዳር ውስጥ ምንዝር ሲፈጸም ተበዳይዋ ማለትም ሚስትየዋ ባሏን ይቅር ለማለት ወይም ላለማለት መወሰን ትችላለች። ሚስትየዋ ይቅር ላለማለት ከወሰነችና በሕግ ከተፋቱ የፍቺ ሂደቱ እንዳለቀ ሁለቱም ድጋሚ ለማግባት ነፃ ይሆናሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ተበዳይዋ ሚስት ትዳሯን ለመታደግ ከልቧ ትፈልግ ይሆናል፤ በመሆኑም ባሏን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነች ልትገልጽ ትችላለች። ይሁንና ምንዝር የፈጸመው ባል ሚስቱ ይቅር ልትለው ፈቃደኛ ብትሆንም እንኳ በገዛ ፈቃዱ ሕጋዊ ፍቺ ቢፈጽምስ? ሚስቱ እሱን ይቅር ለማለትና ትዳሩን ለማስቀጠል ፈቃደኛ ስለሆነች ባልየው ድጋሚ ለማግባት ቅዱስ ጽሑፋዊ ነፃነት አይኖረውም። ሆኖም ባልየው ቅዱስ ጽሑፋዊ ነፃነት ሳይኖረው ሌላ ሴት በማግባት በኃጢአት ጎዳናው ቢቀጥል በድጋሚ ምንዝር ይፈጽማል፤ ይህም ተጨማሪ የፍርድ እርምጃ እንዲወሰድበት ያደርጋል።—1 ቆሮ. 5:1, 2፤ 6:9, 10

ቅዱስ ጽሑፋዊ ነፃነት የሌለው ሰው ድጋሚ ቢያገባ ጉባኤው የቀድሞውን ትዳሩንና አዲሱን ትዳሩን የሚመለከተው እንዴት ነው? ከቅዱስ ጽሑፉ አንጻር የቀድሞ ትዳሩ አሁንም እንዳለ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል? ተበዳይዋ ሚስት አሁንም ባሏን ይቅር ለማለት ወይም ላለማለት መወሰን ትችላለች? አዲሱ ትዳር እንደ ምንዝር ጋብቻ ተደርጎ ይቆጠራል?

ቀደም ሲል በነበረን አመለካከት መሠረት፣ ተበዳይዋ በሕይወት እስካለች፣ ሌላ ሰው እስካላገባች ወይም የፆታ ብልግና እስካልፈጸመች ድረስ ጉባኤው አዲሱን ጋብቻ የሚመለከተው እንደ ምንዝር ጋብቻ አድርጎ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ስለ ፍቺ እና ድጋሚ ስለማግባት ሲናገር ያተኮረው በተበዳዩ ወገን ላይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ሳይኖረው ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሰው ምንዝር እንደሚፈጽም ተናግሯል። ኢየሱስ እንደገለጸው፣ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ግለሰቡ ፍቺ መፈጸሙና ድጋሚ ማግባቱ እንደ ምንዝር ስለሚቆጠር የቀድሞውን ትዳሩን ያፈርሰዋል።

“በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።”—ማቴ. 19:9

አንድ ሰው ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት ካገባ ትዳሩ ስለሚፈርስ ተበዳይዋ ማለትም የቀድሞ ሚስቱ ባሏን ይቅር ለማለት ወይም ላለማለት መወሰን አትችልም። በመሆኑም የቀድሞ ባሏን ይቅር የማለት ወይም ያለማለት ኃላፊነት ከእሷ ጫንቃ ላይ ይወርዳል። በተጨማሪም ጉባኤው ለአዲሱ ትዳር ያለው አመለካከት ተበዳይዋ በመሞቷ፣ ድጋሚ በማግባቷ ወይም የፆታ ብልግና በመፈጸሟ ላይ የተመካ አይሆንም። b

ቀደም ሲል በተመለከትነው ምሳሌ ላይ ፍቺው የተፈጸመው ባልየው ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ነው። ይሁንና ባልየው ምንዝር ባይፈጽምም ሚስቱን ከፈታ በኋላ ሌላ ሴት ቢያገባስ? ወይም ደግሞ ባልየው ከፍቺው በፊት ምንዝር ባይፈጽምም ከፍቺው በኋላ ምንዝር ፈጸመ እንበል፤ ከዚያም ሚስቱ እሱን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ብትሆንም ሌላ ሴት ቢያገባስ? በሁሉም ምሳሌዎች ላይ ባልየው ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት ማግባቱ እንደ ምንዝር ይቆጠራል፤ በመሆኑም የቀድሞ ትዳሩ ይፈርሳል። አዲሱ ትዳር ሕጋዊ ጋብቻ ነው። በኅዳር 15, 1979 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 32 ላይ እንደተገለጸው ባልየው “አሁን አዲስ ትዳር መሥርቷል፤ በመሆኑም ትዳሩን አፍርሶ ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለስ አይችልም። በፍቺ፣ በምንዝርና ድጋሚ በማግባቱ ምክንያት የቀድሞ ትዳሩ ፈርሷል።”

በግንዛቤያችን ላይ ማስተካከያ አድርገናል ሲባል የትዳርን ቅድስና አቅልለን እንመለከታለን ወይም ምንዝርን እንደ ከባድ ኃጢአት አድርገን አንመለከተውም ማለት አይደለም። ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ሳይኖረው ሚስቱን የሚፈታ ከዚያም ቅዱስ ጽሑፋዊ ነፃነት ሳይኖረው ሌላ ሴት የሚያገባ ሰው በምንዝር ተከሶ የፍርድ እርምጃ ይወሰድበታል። (አዲሷ ሚስቱ ክርስቲያን ከሆነች እሷም በምንዝር ተከሳ የፍርድ እርምጃ ይወሰድባታል።) አዲሱ ትዳር የምንዝር ጋብቻ ተደርጎ ባይቆጠርም ግለሰቡ ለበርካታ ዓመታት በጉባኤ ውስጥ ልዩ የአገልግሎት መብቶችን ለመቀበል ብቃት አይኖረውም፤ በተጨማሪም ብቃቱን የሚያሟላው በበደሉ ምክንያት የደረሰው ቅሬታ ከጠራ እና ግለሰቡ የሌሎችን አክብሮት መልሶ ማትረፍ ከቻለ በኋላ ነው። ይህም ክህደት የተፈጸመባት የቀድሞ ሚስቱ እንዲሁም ትቷቸው የሄደው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቹ ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባትን ይጨምራል።—ሚል. 2:14-16

ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌለው ፍቺ ፈጽሞ ሌላ ማግባት ከሚያስከትላቸው አስከፊ መዘዞች አንጻር ክርስቲያኖች የይሖዋን አመለካከት በማዳበር የትዳርን ቅድስና ማክበራቸው የጥበብ እርምጃ ነው።—መክ. 5:4, 5፤ ዕብ. 13:4

a በዚህ ርዕስ ውስጥ ባልየው ምንዝር እንደፈጸመ፣ ሚስትየዋ ደግሞ ተበዳይ እንደሆነች ተደርጎ የተገለጸው ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል ነው። በማርቆስ 10:11, 12 ላይ ኢየሱስ፣ በዚህ ረገድ የሰጠው ምክር ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች በእኩል መጠን እንደሚሠራ በግልጽ ተናግሯል።

b ይህ ሐሳብ ቀደም ሲል የነበረንን አመለካከት የሚያስተካክል ነው። ቀደም ሲል ተበዳዩ ወገን እስካልሞተ፣ ድጋሚ እስካላገባ ወይም የፆታ ብልግና እስካልፈጸመ ድረስ አዲሱ ጋብቻ የምንዝር ጋብቻ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።