በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 24

የይሖዋ ይቅርታ ወደር የለውም

የይሖዋ ይቅርታ ወደር የለውም

“ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ፤ አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም።”—መዝ. 86:5

መዝሙር 42 የአምላክ አገልጋይ ጸሎት

ማስተዋወቂያ *

1. በመክብብ 7:20 ላይ ንጉሥ ሰለሞን የትኛውን እውነታ ገልጿል?

 ንጉሥ ሰለሞን “ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኃጢአት የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” ብሏል። (መክ. 7:20) ይህ ምንኛ እውነት ነው! ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። (1 ዮሐ. 1:8) በመሆኑም ሁላችንም የአምላክና የሰዎች ይቅርታ ያስፈልገናል።

2. የቅርብ ጓደኛችን ይቅር ሲለን ምን ይሰማናል?

2 የቅርብ ጓደኛህን ያስቀየምክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? ችግሩን መፍታትና ወዳጅነታችሁን ማደስ ስለፈለግክ ከልብህ ይቅርታ ጠየቅከው። ታዲያ ጓደኛህ በነፃ ይቅር ሲልህ ምን ተሰማህ? እፎይ አላልክም? በጣም እንደተደሰትክ ጥያቄ የለውም!

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ይሖዋ የቅርብ ጓደኛችን እንዲሆን እንፈልጋለን፤ ሆኖም እሱን ቅር የሚያሰኝ ነገር መናገራችን ወይም ማድረጋችን አይቀርም። ታዲያ ይሖዋ ይቅር ሊለን እንደሚጓጓ እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ በሚያሳየው ይቅርታና እኛ በምናሳየው ይቅርታ መካከል ምን ልዩነት አለ? በተጨማሪም የይሖዋን ይቅርታ ማግኘት የሚችሉት እነማን ናቸው?

ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው

4. ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

4 የአምላክ ቃል ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ እንደሆነ ያረጋግጥልናል። ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ ራሱን ለሙሴ በገለጠበት ወቅት በአንድ መልአክ አማካኝነት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ፣ ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል።” (ዘፀ. 34:6, 7) ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ምንጊዜም ዝግጁ የሆነ ደግና መሐሪ አምላክ ነው።—ነህ. 9:17፤ መዝ. 86:15

ይሖዋ ማንነታችንን የቀረጹትን ነገሮች በሙሉ ያውቃል (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)

5. በመዝሙር 103:13, 14 መሠረት ይሖዋ ሰዎችን በጥልቀት ማወቁ ምን እንዲያደርግ ያነሳሳዋል?

5 ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ ስለ እኛ ሁሉንም ነገር ያውቃል። እስቲ አስበው! በምድር ላይ ስላለው ስለ እያንዳንዱ ሰው እያንዳንዷን ዝርዝር ነገር ያውቃል። (መዝ. 139:15-17) ስለዚህ ከወላጆቻችን የወረስነውን አለፍጽምና በሙሉ ማየት ይችላል። በተጨማሪም በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን ነገሮች ባሕርያችንን የቀረጹት እንዴት እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ የሰው ልጆችን እንዲህ በጥልቀት ማወቁ ምን እንዲያደርግ ያነሳሳዋል? በምሕረት እንዲይዘን ያነሳሳዋል።—መዝ. 78:39፤ መዝሙር 103:13, 14ን አንብብ።

6. ይሖዋ እኛን ይቅር የማለት ጉጉት እንዳለው በተግባር ያሳየው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ ይቅር ለማለት እንደሚጓጓ በተግባር አሳይቷል። የመጀመሪያው ሰው አዳም በሠራው ኃጢአት የተነሳ ሁላችንም በኃጢአትና በሞት እርግማን ሥር እንደወደቅን ያውቃል። (ሮም 5:12) ራሳችንንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ሰው ከዚህ እርግማን ማላቀቅ የምንችልበት ምንም መንገድ አልነበረም። (መዝ. 49:7-9) ያም ቢሆን አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ነፃ የምንወጣበትን መንገድ በማዘጋጀት ርኅራኄ አሳይቶናል። በምን መንገድ? ዮሐንስ 3:16 እንደሚገልጸው ይሖዋ አንድያ ልጁን ለእኛ ሲል እንዲሞት ላከልን። (ማቴ. 20:28፤ ሮም 5:19) ኢየሱስ በእሱ የሚያምን ሁሉ ነፃ መውጣት እንዲችል በእኛ ምትክ የሞትን ቅጣት ተቀበለ። (ዕብ. 2:9) ይሖዋ የሚወደው ልጁ ተሠቃይቶና ተዋርዶ ሲሞት ሲያይ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ይሖዋ እኛን ይቅር የማለት ፍላጎት ባይኖረው ኖሮ ልጁ እንዲሞት አይፈቅድም ነበር።

7. ይሖዋ በነፃ ይቅር ካላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ።

7 ይሖዋ በነፃ ይቅር ያላቸው በርካታ ሰዎች ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። (ኤፌ. 4:32) የማንን ታሪክ ታስታውሳለህ? ንጉሥ ምናሴን ታስታውስ ይሆናል። ይህ ክፉ ሰው ዘግናኝ ኃጢአቶችን በመሥራት ይሖዋን አሳዝኗል። የሐሰት አምልኮን አስፋፍቷል። የገዛ ልጆቹን እንኳ ለሐሰት አማልክት መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። ይባስ ብሎም ቅዱስ በሆነው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ጣዖት አቁሟል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ ሲናገር “ይሖዋን ያስቆጣው ዘንድ በእሱ ፊት በጣም ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሠራ” ይላል። (2 ዜና 33:2-7) ሆኖም ምናሴ ከልቡ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ በነፃ ይቅር ብሎታል። እንዲያውም ወደ ንግሥናው እንዲመለስ አድርጎታል። (2 ዜና 33:12, 13) ምናልባት የንጉሥ ዳዊትን ታሪክም ታስታውስ ይሆናል። ንጉሥ ዳዊት እንደ ምንዝርና ነፍስ ግድያ ያሉ ከባድ ኃጢአቶችን በመሥራት ይሖዋን አሳዝኗል። ሆኖም ዳዊት ኃጢአቱን አምኖ ተቀብሎ ከልቡ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ በነፃ ይቅር ብሎታል። (2 ሳሙ. 12:9, 10, 13, 14) በእርግጥም ይሖዋ ይቅር ለማለት እንደሚጓጓ መተማመን እንችላለን። ደግሞም ቀጥሎ እንደምንመለከተው ይሖዋ የሚያሳየው ይቅርታ ሰዎች ከሚያሳዩት ይቅርታ በእጅጉ የተለየ ነው።

የይሖዋ ይቅርታ በዓይነቱ ልዩ ነው

8. ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ዳኛ መሆኑ ከይቅር ባይነቱ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ “የምድር ሁሉ ዳኛ” ነው። (ዘፍ. 18:25) አንድ ጥሩ ዳኛ ሕጉን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል። ይሖዋ ዳኛችን ብቻ ሳይሆን ሕግ ሰጪያችንም ስለሆነ ሕጉን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ምንም ጥያቄ የለውም። (ኢሳ. 33:22) ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ የይሖዋን ያህል እውቀት ያለው ማንም የለም። ከአንድ ጥሩ ዳኛ ሌላስ ምን ይጠበቃል? ብይን ከማስተላለፉ በፊት ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በሙሉ ከግምት ማስገባት አለበት። በዚህ ረገድም ቢሆን ይሖዋን የሚተካከለው ዳኛ የለም።

9. ይሖዋ ይቅር ለማለት ወይም ላለማለት ሲወስን የትኞቹን መረጃዎች ግምት ውስጥ ያስገባል?

9 ከሰብዓዊ ዳኞች በተለየ መልኩ ይሖዋ ከየትኛውም ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተሟላ መረጃ አለው። (ዘፍ. 18:20, 21፤ መዝ. 90:8) የእሱ ፍርድ በዓይን በሚታየው ወይም በጆሮ በሚሰማው ነገር ብቻ የተገደበ አይደለም። አንድ ሰው በዘር የወረሰው ነገር፣ አስተዳደጉ፣ ማኅበረሰቡ እንዲሁም ስሜታዊና አእምሯዊ ጤንነቱ በድርጊቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የሰዎችን ልብ ያነብባል። የእያንዳንዱን ሰው ውስጣዊ ግፊት፣ የልብ ዝንባሌና ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ይረዳል። ከይሖዋ ዓይን ሊሰወር የሚችል አንድም ነገር የለም። (ዕብ. 4:13) በመሆኑም ይሖዋ ይቅር የሚለው ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ስለሚያውቅ ነው።

ይሖዋ ፍትሐዊና ከአድልዎ ነፃ ነው። በጉቦ ሊደለል አይችልም (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. የይሖዋ ፍርድ ምንጊዜም ፍትሐዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ዘዳግም 32:4)

10 ይሖዋ የሚያስተላልፈው ፍርድ ምንጊዜም ፍትሐዊ ነው። ይሖዋ ፈጽሞ አያዳላም። ይቅርታው የተመካው በሰዎች መልክ፣ ሀብት፣ ታዋቂነት ወይም ችሎታ ላይ አይደለም። (1 ሳሙ. 16:7፤ ያዕ. 2:1-4) ማንም ሰው በይሖዋ ላይ ጫና ሊያሳድርበት ወይም በጉቦ ሊደልለው አይችልም። (2 ዜና 19:7) በተጨማሪም ውሳኔ የሚያደርገው በስሜት ተገፋፍቶ አይደለም። (ዘፀ. 34:7) ይሖዋ ከፍተኛ እውቀትና ጥልቅ ማስተዋል ያለው በመሆኑ ከሁሉ የላቀ ዳኛ ነው።ዘዳግም 32:4ን አንብብ።

11. የይሖዋን ይቅርታ በዓይነቱ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

11 የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች የይሖዋ ይቅርታ በዓይነቱ ልዩ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። በአንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ላይ እንደተገለጸው እነዚህ ጸሐፊዎች በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተጠቀሙበት የዕብራይስጥ ቃል “አምላክ ለኃጢአተኞች የሚያሳየውን ይቅርታ ብቻ የሚያመለክት ነው። ይህ ቃል ሰዎች የሚያሳዩትን ውስን ይቅርታ ለማመልከት ተሠርቶበት አያውቅም።” ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ሙሉ በሙሉ ይቅር ማለት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። ታዲያ የይሖዋ ይቅርታ ምን ውጤት ያስገኛል?

12-13. (ሀ) ይሖዋ ይቅር ሲለን ምን ጥቅም እናገኛለን? (ለ) የይሖዋ ይቅርታ ለምን ያህል ጊዜ ይዘልቃል?

12 ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን ስንቀበል “የመታደስ ዘመን” ይመጣልናል፤ በመሆኑም የአእምሮ ሰላምና ንጹሕ ሕሊና እናገኛለን። እንዲህ ያለው ይቅርታ ሊመጣ የሚችለው ከሰዎች ሳይሆን ‘ከይሖዋ ዘንድ’ ብቻ ነው። (ሥራ 3:19) ይሖዋ ይቅር ሲለን፣ ኃጢአቱ ያልተፈጸመ ያህል ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ሙሉ በሙሉ ያድሰዋል።

13 ይሖዋ አንዴ ይቅር ካለን በኋላ በዚያ ኃጢአት ድጋሚ አይጠይቀንም ወይም አይቀጣንም። (ኢሳ. 43:25፤ ኤር. 31:34) “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ” ይሖዋ ኃጢአታችንን ከእኛ ያርቃል። * (መዝ. 103:12) የይሖዋ ይቅርታ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ስናሰላስል በአመስጋኝነትና በአድናቆት ስሜት እንሞላለን። (መዝ. 130:4) ሆኖም የይሖዋን ይቅርታ በዚህ መልኩ ማግኘት የሚችሉት እነማን ናቸው?

ይሖዋ ይቅር የሚለው እነማንን ነው?

14. ይሖዋ ይቅር ለማለት የሚወስንበትን መንገድ በተመለከተ እስካሁን ምን ተምረናል?

14 ይሖዋ ይቅር ለማለት የሚወስነው የኃጢአቱን ክብደት መሠረት አድርጎ እንዳልሆነ ተመልክተናል። በተጨማሪም ይሖዋ አንድን ሰው ይቅር ለማለት የሚወስነው ፈጣሪ፣ ሕግ ሰጪ እና ዳኛ በመሆኑ ያለውን እውቀት መሠረት አድርጎ እንደሆነ ተመልክተናል። ለመሆኑ ይሖዋ ይቅር ለማለት ሲወስን ከግምት የሚያስገባው የትኞቹን ጉዳዮች ነው?

15. በሉቃስ 12:47, 48 መሠረት ይሖዋ ግምት ውስጥ የሚያስገባው የመጀመሪያው ነጥብ ምንድን ነው?

15 ይሖዋ ከግምት የሚያስገባው አንደኛው ነጥብ ‘ኃጢአተኛው ድርጊቱን የፈጸመው ስህተት መሆኑን እያወቀ ነው ወይ’ የሚለው ነው። ኢየሱስ በሉቃስ 12:47, 48 ላይ ይህን ነጥብ በግልጽ ተናግሯል። (ጥቅሱን አንብብ።) በክፋት ተነሳስቶ፣ ድርጊቱ ይሖዋን እንደሚያሳዝን እያወቀ ኃጢአት የሚፈጽም ሰው ኃጢአቱ ከባድ ይሆንበታል። እንዲህ ያለው ሰው ይቅር ላይባል ይችላል። (ማር. 3:29፤ ዮሐ. 9:41) ያም ቢሆን ሐቁን ለመናገር፣ አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት የምንሠራው ድርጊቱ ኃጢአት መሆኑን እያወቅን ነው። ታዲያ እንዲህ ካደረግን ይቅር ልንባል አንችልም ማለት ነው? በፍጹም! ምክንያቱም ይሖዋ ግምት ውስጥ የሚያስገባው ሌላም ነገር አለ።

ከልብ ንስሐ ከገባን ይሖዋ ይቅር እንደሚለን መተማመን እንችላለን (ከአንቀጽ 16-17⁠ን ተመልከት)

16. ንስሐ ምንድን ነው? ንስሐ መግባት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

16 ይሖዋ ግምት ውስጥ የሚያስገባው ሌላኛው ነጥብ ‘ኃጢአተኛው ከልቡ ንስሐ ገብቷል ወይ’ የሚለው ነው። ንስሐ መግባት ሲባል ምን ማለት ነው? ንስሐ መግባት ሲባል “ሐሳብን፣ አመለካከትን ወይም ዓላማን መቀየር” ማለት ነው። መጥፎ ነገር በመፈጸማችን ወይም ትክክለኛውን ነገር ሳናደርግ በመቅረታችን ምክንያት የሚሰማንን የጸጸት ወይም የሐዘን ስሜት ያካትታል። ንስሐ የገባ ሰው የሚያዝነው በፈጸመው መጥፎ ድርጊት የተነሳ ብቻ ሳይሆን እንደዚያ ያለ ኃጢአት እስኪፈጽም ድረስ መንፈሳዊነቱ በመዳከሙም ጭምር ነው። ምናሴና ዳዊት የፈጸሙት ኃጢአት ከባድ ቢሆንም ከልብ ንስሐ በመግባታቸው ይሖዋ ይቅር እንዳላቸው እናስታውስ። (1 ነገ. 14:8) በእርግጥም ይሖዋ ይቅር ከማለቱ በፊት ንስሐ መግባታችንን ማየት ይፈልጋል። ሆኖም በፈጸምነው ኃጢአት መጸጸታችን ብቻውን በቂ አይደለም። እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። * ይህ ደግሞ ይሖዋ ግምት ውስጥ ወደሚያስገባው ሌላኛው ነጥብ ይወስደናል።

17. መለወጥ ምንድን ነው? መለወጥ ቀደም ሲል የሠራነውን ኃጢአት ላለመድገም የሚረዳንስ እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 55:7)

17 ይሖዋ ግምት ውስጥ የሚያስገባው ሌላው ነጥብ ደግሞ መለወጣችን ነው። መለወጥ ማለት “መመለስ” ማለት ነው። በሌላ አባባል ግለሰቡ መጥፎ አካሄዱን መተውና የይሖዋን መንገድ መከተል ይኖርበታል። (ኢሳይያስ 55:7ን አንብብ።) እንዲሁም አእምሮውን ለውጦ በይሖዋ አስተሳሰብ መመራት ይኖርበታል። (ሮም 12:2፤ ኤፌ. 4:23) መጥፎ አስተሳሰቡንና ድርጊቱን ወደ ኋላ ለመተው ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለበት። (ቆላ. 3:7-10) እርግጥ ይሖዋ ይቅር እንዲለንና ከኃጢአታችን እንዲያነጻን መሠረት የሚሆነው ዋነኛው ነገር በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ ያለን እምነት ነው። ይሖዋ መጥፎ ምግባራችንን ለማስተካከል ልባዊ ጥረት እያደረግን እንዳለን ሲያይ የልጁን መሥዋዕት መሠረት አድርጎ ይቅር ይለናል።—1 ዮሐ. 1:7

ይሖዋ ይቅር እንደሚልህ ተማመን

18. ስለ ይሖዋ ይቅር ባይነት ምን ተምረናል?

18 እስካሁን የተመለከትናቸውን ቁልፍ ነጥቦች በአጭሩ እንከልስ። ይሖዋ ይቅር በማለት ረገድ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የለውም። ይህን የምንለው ከምን ተነስተን ነው? አንደኛ፣ ምንጊዜም ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። ሁለተኛ፣ ሁላችንንም አብጠርጥሮ ያውቀናል። ስለ እኛ ሁሉንም ነገር ስለሚያውቅ እውነተኛ ንስሐ መግባታችንን ከማንም በተሻለ ማወቅ የሚችለው እሱ ነው። ሦስተኛ ደግሞ ይሖዋ ይቅር ሲለን ኃጢአታችንን ሙሉ በሙሉ ይሰርዘዋል። ይህም ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረንና የእሱን ሞገስ እንድናገኝ ይረዳናል።

19. ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት ኃጢአት መሥራታችን ባይቀርም በምን ልንደሰት እንችላለን?

19 እርግጥ ነው፣ ፍጹም እስካልሆንን ድረስ ኃጢአት መሥራታችንን መቀጠላችን አይቀርም። ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 771 ላይ ያለው ሐሳብ በእጅጉ ያጽናናናል፤ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ የአገልጋዮቹን ሥጋዊ ድክመት በምሕረት ስለሚመለከት በወረሱት አለፍጽምና የተነሳ በሠሯቸው ስህተቶች ዕድሜ ልካቸውን ሲጸጸቱ መኖር አያስፈልጋቸውም። (መዝ 103:8-14፤ 130:3) በአምላክ መንገድ ለመጓዝ ልባዊ ጥረት እስካደረጉ ድረስ መደሰት ይችላሉ። (ፊልጵ 4:4-6፤ 1ዮሐ 3:19-22)” እንዴት ያለ የሚያበረታታ ሐሳብ ነው!

20. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

20 በፈጸምነው ኃጢአት ከልባችን ከተጸጸትን ይሖዋ ይቅር ሊለን ዝግጁ በመሆኑ አመስጋኞች ነን። ሆኖም ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ሰዎች የሚያሳዩት ይቅርታ ከይሖዋ ይቅርታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? የሚለያየውስ በየትኞቹ መንገዶች ነው? ይህን ልዩነት መረዳታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

መዝሙር 45 በልቤ የማሰላስለው ነገር

^ ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ በቃሉ አማካኝነት አረጋግጦልናል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ይቅርታው እንደማይገባን ሊሰማን ይችላል። በሠራነው ኃጢአት ከልባችን ከተጸጸትን አምላካችን ይቅር ሊለን ምንጊዜም ዝግጁ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን የምንችልበትን ምክንያት በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን።

^ ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “ንስሐ” አንድ ሰው በቀድሞ አካሄዱ፣ በፈጸመው መጥፎ ድርጊት ወይም ሳያደርግ በቀረው ነገር ከልብ ተጸጽቶ የአመለካከት ለውጥ ማድረጉን ያመለክታል። እውነተኛ ንስሐ ፍሬ ያፈራል፤ ማለትም ግለሰቡ በአካሄዱ ላይ ለውጥ እንዳደረገ በግልጽ ይታያል።