በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 25

ይሖዋ ይቅር ባዮችን ይባርካል

ይሖዋ ይቅር ባዮችን ይባርካል

“ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”—ቆላ. 3:13

መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ

ማስተዋወቂያ *

1. ይሖዋ ንስሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች ምን ዋስትና ሰጥቷል?

 ይሖዋ ፈጣሪያችን፣ ሕግ ሰጪያችንና ዳኛችን ብቻ ሳይሆን አፍቃሪ አባታችንም ነው። (መዝ. 100:3፤ ኢሳ. 33:22) በእሱ ላይ ኃጢአት ብንሠራም እንኳ ከልባችን ንስሐ ከገባን እኛን ይቅር ለማለት ሥልጣኑ ብቻ ሳይሆን ፍላጎቱም አለው። (መዝ. 86:5) ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት “ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል” የሚል የሚያጽናና ዋስትና ሰጥቶናል።—ኢሳ. 1:18

2. ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

2 ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን ሌሎችን የሚያሳዝን ነገር መናገራችን ወይም ማድረጋችን አይቀርም። (ያዕ. 3:2) ይህ ሲባል ግን ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም ማለት አይደለም። ይቅር ባዮች ከሆንን ከሌሎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን። (ምሳሌ 17:9፤ 19:11፤ ማቴ. 18:21, 22) ትናንሽ ቅሬታዎች በመካከላችን ሲፈጠሩ ይሖዋ ይቅር እንድንል ይፈልጋል። (ቆላ. 3:13) ደግሞም እንዲህ ማድረጋችን ተገቢ ነው። ምክንያቱም ይሖዋ “ብዙ” ጊዜ በነፃ ይቅር ይለናል።—ኢሳ. 55:7

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። ለሽማግሌዎች ማሳወቅ ያለብን የትኞቹን ኃጢአቶች ነው? ይሖዋ ሌሎችን ይቅር እንድንል የሚፈልገው ለምንድን ነው? በተጨማሪም በሌሎች ኃጢአት ምክንያት ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ቢፈጽም

4. (ሀ) አንድ የይሖዋ አገልጋይ ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ ምን ማድረግ አለበት? (ለ) ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን በሚያነጋግሩበት ጊዜ ኃላፊነታቸው ምንድን ነው?

4 አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች ማሳወቅ ይኖርብናል። ከእነዚህ ኃጢአቶች አንዳንዶቹ በ1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 ላይ ተዘርዝረዋል። ከባድ ኃጢአት የሚባለው ከአምላክ ሕግ ጋር በእጅጉ የሚቃረን ድርጊት ነው። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ኃጢአት ከፈጸመ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፤ እንዲሁም የጉባኤውን ሽማግሌዎች ሊያነጋግር ይገባል። (መዝ. 32:5፤ ያዕ. 5:14) የሽማግሌዎች ሚና ምንድን ነው? ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ይቅር የማለት ሥልጣን ያለው ይሖዋ ብቻ ነው፤ ይህን የሚያደርገው ደግሞ የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ነው። * ሆኖም ‘ኃጢአተኛው በጉባኤው ውስጥ ይቀጥል ወይ’ የሚለውን ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው እንዲወስኑ ይሖዋ ለሽማግሌዎች ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (1 ቆሮ. 5:12) ሽማግሌዎች ይህን ጉዳይ በሚወስኑበት ጊዜ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ያደርጋሉ፦ ግለሰቡ ኃጢአት የሠራው አስቀድሞ አሲሮ ነው? ኃጢአቱን ከሌሎች ለመደበቅ ሞክሯል? ኃጢአቱን ረዘም ላለ ጊዜ ሲፈጽም ቆይቷል? በዋነኝነት ደግሞ፣ ኃጢአተኛው ከልቡ ንስሐ እንደገባ የሚያሳይ ማስረጃ አለ? ይሖዋ ይቅር እንዳለው የሚጠቁም ነገር አለ?—ሥራ 3:19

5. ሽማግሌዎች የሚያከናውኑት ሥራ ምን ጥቅም ያስገኛል?

5 ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን በሚያነጋግሩበት ጊዜ ግባቸው ቀድሞውኑ በሰማይ ከተደረገው ውሳኔ ጋር የሚስማማ ውሳኔ በምድር ላይ ማድረግ ነው። (ማቴ. 18:18) ይህ ዝግጅት ጉባኤውን የሚጠቅመው እንዴት ነው? የይሖዋን ውድ በጎች ሊጎዱ የሚችሉ ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤው እንዲወገዱ ያደርጋል። (1 ቆሮ. 5:6, 7, 11-13፤ ቲቶ 3:10, 11) ኃጢአተኛውም ንስሐ ገብቶ የይሖዋን ይቅርታ እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል። (ሉቃስ 5:32) ግለሰቡ ንስሐ ከገባ ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ እንዲያገግም ይሖዋ እንዲረዳው ይጸልዩለታል።—ያዕ. 5:15

6. አንድ ሰው ከተወገደ በኋላም ይሖዋ ይቅር ሊለው ይችላል? አብራራ።

6 ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን በሚያነጋግሩበት ጊዜ ግለሰቡ የንስሐ ፍሬ ባያሳይስ? ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ግለሰቡ ከጉባኤ ይወገዳል። ግለሰቡ የሠራው ኃጢአት ወንጀል ከሆነ ደግሞ ሽማግሌዎች የሚገባውን ቅጣት እንዳያገኝ አይከላከሉለትም። የመንግሥት ባለሥልጣናት ሕግ በሚጥስ በማንኛውም ሰው ላይ እንዲፈርዱና ቅጣት እንዲበይኑ ይሖዋ ፈቅዶላቸዋል፤ ግለሰቡ ንስሐ ገባም አልገባ ማለት ነው። (ሮም 13:4) ይሁንና ግለሰቡ ከጊዜ በኋላ ወደ ልቦናው ተመልሶ ከልቡ ንስሐ ከገባና ከተለወጠ ይሖዋ ይቅር ሊለው ፈቃደኛ ነው። (ሉቃስ 15:17-24) የፈጸመው ኃጢአት በጣም ከባድ ቢሆንም ይሖዋ ይቅር ይለዋል።—2 ዜና 33:9, 12, 13፤ 1 ጢሞ. 1:15

7. የበደለንን ሰው ይቅር እንላለን ሲባል ምን ማለት ነው?

7 ይሖዋ አንድን ኃጢአተኛ ይቅር ይለዋል ወይስ አይለውም የሚለውን መወሰን የእኛ ኃላፊነት አለመሆኑ ትልቅ እፎይታ ነው። ያም ቢሆን የእኛን ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር አለ። ምንድን ነው? ምናልባትም አንድ ሰው ከባድ በደል አድርሶብን ይሆናል። ከጊዜ በኋላ ግለሰቡ ይቅርታ ሊጠይቀን ይችላል፤ ላይጠይቀንም ይችላል። ያም ቢሆን ግለሰቡን ይቅር ለማለት መምረጥ እንችላለን። ይህም ሲባል በግለሰቡ ላይ ያደረብንን ቅሬታና ብስጭት ለመተው እንመርጣለን ማለት ነው። በተለይ ግለሰቡ ያደረሰብን ጉዳት ከባድ ከሆነ ጉዳዩን መተው ጊዜ እንደሚወስድና ጥረት እንደሚጠይቅብን የታወቀ ነው። የመስከረም 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ይላል፦ “አንድን በደለኛ ይቅር ስትለው በደሉን ተቀብለኸዋል ማለት [አይደለም]። አንድ ክርስቲያን ይቅር አለ ሲባል ጉዳዩን በእምነት ለይሖዋ ተወው ማለት ነው። ይሖዋ የመላው ጽንፈ ዓለም ጻድቅ ፈራጅ ነው፤ ፍትሕንም በተገቢው ጊዜ ላይ ይሰጣል።” ይሁንና ይሖዋ የበደሉንን ሰዎች ይቅር እንድንል እና ፍርድ የመስጠቱን ጉዳይ በእሱ እጅ እንድንተወው የሚፈልገው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ሌሎችን ይቅር እንድንል የሚፈልገው ለምንድን ነው?

8. ሌሎችን ይቅር ማለታችን ለይሖዋ ምሕረት አድናቆት እንዳለን የሚያሳየው እንዴት ነው?

8 ሌሎችን ይቅር ማለት አድናቆት እንዳለን ያሳያል። ኢየሱስ በአንድ ምሳሌ ላይ ይሖዋን የባሪያውን ዕዳ ከሰረዘ ንጉሥ ጋር አመሳስሎታል፤ ይህ ባሪያ ከፍሎ ሊጨርሰው የማይችለው እጅግ ብዙ ዕዳ ነበረበት። ሆኖም ዕዳው የተሰረዘለት ባሪያ ከእሱ በጣም ያነሰ ገንዘብ ለተበደረው ባሪያ ምሕረት ሳያሳይ ቀርቷል። (ማቴ. 18:23-35) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ምን ሊያስተምረን ፈልጎ ነው? ይሖዋ ያሳየንን ታላቅ ምሕረት የምናደንቅ ከሆነ ሌሎችን ይቅር ለማለት እንነሳሳለን። (መዝ. 103:9) አንድ መጠበቂያ ግንብ ከበርካታ ዓመታት በፊት የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቶ ነበር፦ “ሌሎችን ምንም ያህል ጊዜ ይቅር ብንል አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ካሳየን ምሕረትና ይቅር ባይነት ጋር ጨርሶ ሊተካከል አይችልም።”

9. ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ለእነማን ነው? (ማቴዎስ 6:14, 15)

9 ሌሎችን ይቅር ካልን ይሖዋ ይቅር ይለናል። ይሖዋ ለመሐሪዎች ምሕረት ያደርጋል። (ማቴ. 5:7፤ ያዕ. 2:13) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንደሚጸልዩ ባስተማራቸው ወቅት ይህን ግልጽ አድርጓል። (ማቴዎስ 6:14, 15ን አንብብ።) ከዚያ በፊትም ይሖዋ ለአገልጋዩ ለኢዮብ የነገረው ነገር ይህን ነጥብ ያስተምረናል። ይህ ታማኝ ሰው ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር የተባሉ ሦስት ሰዎች በተናገሩት ጎጂ ንግግር ስሜቱ እጅግ ተጎድቶ ነበር። ሆኖም ይሖዋ ኢዮብን ለእነዚህ ሰዎች እንዲጸልይላቸው አዘዘው። ይሖዋ ኢዮብን የባረከው እንዲህ ካደረገ በኋላ ነው።—ኢዮብ 42:8-10

10. ቂም መያዝ የሚጎዳን እንዴት ነው? (ኤፌሶን 4:31, 32)

10 ቂም መያዝ ራሳችንን ይጎዳናል። ቂም ከባድ ሸክም ነው፤ ይሖዋ ይህን ሸክም ከላያችን አውርደን እፎይ እንድንል ይፈልጋል። (ኤፌሶን 4:31, 32ን አንብብ።) “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው” የሚል ምክር ሰጥቶናል። (መዝ. 37:8) ይህን ምክር መከተል በጣም ጠቃሚ ነው። ቂም መያዝ አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጤንነታችንን ሊጎዳው ይችላል። (ምሳሌ 14:30) ደግሞም ቂም ይዘን የበደለን ሰው እንዲጎዳ መጠበቅ እኛ መርዝ እየጠጣን የበደለን ሰው እንዲጎዳ ከመጠበቅ ተለይቶ አይታይም። ሌሎችን ይቅር ስንል ለራሳችን ስጦታ እየሰጠን ነው ሊባል ይችላል። (ምሳሌ 11:17) አእምሯችንና ልባችን ሰላም ያገኛል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ወደፊት መግፋት እንችላለን።

11. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መበቀል ምን ይላል? (ሮም 12:19-21)

11 በቀል የይሖዋ ነው። ይሖዋ የበደሉንን እንድንበቀል አልፈቀደልንም። (ሮም 12:19-21ን አንብብ።) እይታችን የተዛባና የተገደበ ስለሆነ እንደ አምላክ ትክክለኛ ፍርድ ማስተላለፍ አንችልም። (ዕብ. 4:13) ደግሞም አንዳንድ ጊዜ ስሜታችን የማመዛዘን ችሎታችንን ይጋርደዋል። ያዕቆብ በይሖዋ መንፈስ ተመርቶ “የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግም” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 1:20) ይሖዋ ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግና ፍትሕን ፍጹም በሆነ መንገድ እንደሚያስፈጽም እርግጠኛ መሆን እንችላለን።

ቁጣንና ቂምን ከልብህ አስወግድ። ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ተወው። ይሖዋ ኃጢአት ያስከተላቸውን ጉዳቶች በሙሉ ያስተካክላል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. በይሖዋ ፍትሕ እንደምንተማመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

12 ይቅር ማለታችን በይሖዋ ፍትሕ እንደምንተማመን ያሳያል። ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ስንተወው ይሖዋ ኃጢአት ያስከተለውን ጉዳት በሙሉ እንደሚያስተካክል እምነት እንዳለን እናሳያለን። አምላክ እንደሚያመጣ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ፣ የስሜት ቁስል ያስከተሉብን ነገሮች ጨርሶ “አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም።” (ኢሳ. 65:17) ይሁንና የደረሰብን ጉዳት ከባድ ከሆነ በልባችን ውስጥ ያደረውን ቁጣና ቂም በእርግጥ ማስወገድ እንችላለን? አንዳንዶች ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ይቅር ማለት የሚያስገኛቸው በረከቶች

13-14. ከቶኒና ከሆሴ ተሞክሮ ስለ ይቅር ባይነት ምን ትምህርት አግኝተሃል?

13 በርካታ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሌሎች ከባድ በደል ቢያደርሱባቸውም እንኳ ይቅር ለማለት መርጠዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ምን በረከት አስገኝቶላቸዋል?

14 በፊሊፒንስ የሚኖረው ቶኒ * እውነትን ከመስማቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ሆሴ የተባለ ሰው ታላቅ ወንድሙን እንደገደለው አወቀ። በወቅቱ ቶኒ ዓመፀኛና ብስጩ ሰው ነበር፤ ሆሴን ለመበቀልም ቆርጦ ተነሳ። ሆሴ በፈጸመው ወንጀል ምክንያት ታሰረ። ሆሴ ከእስር ቤት ከተለቀቀ በኋላ ቶኒ ሆሴን የገባበት ገብቶ እንደሚገድለው ዝቶ ነበር። ለዚህም ሲል ሽጉጥ ገዛ። በኋላ ግን ቶኒ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ይህም ቂሜን መተውን ይጨምር ነበር።” ከጊዜ በኋላ ቶኒ ተጠመቀ፤ በኋላም የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ። ቶኒ ሆሴም የተጠመቀ የይሖዋ አገልጋይ እንደሆነ ሲሰማ ምን ያህል ተደንቆ ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስቡት! ቶኒና ሆሴ ሲገናኙ ተቃቀፉ። ቶኒም ሆሴን ይቅር እንዳለው ነገረው። ቶኒ ሆሴን ይቅር ማለቱ በቃላት ሊገልጸው የማይችል ታላቅ ደስታ እንዳስገኘለት ተናግሯል። በእርግጥም ቶኒ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ በመሆኑ ይሖዋ ባርኮታል።

የፒተር እና የሱ ምሳሌ ቁጣንና ቂምን ማስወገድ እንደምንችል ያሳያል (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት)

15-16. ከፒተር እና ከሱ ተሞክሮ ስለ ይቅር ባይነት ምን ትምህርት አግኝተሃል?

15 በ1985 ፒተር እና ሱ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ሳሉ ከባድ ፍንዳታ ተከሰተ። አንድ ሰው በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ፈንጂ አጥምዶ ነበር። ሱ በፍንዳታው ምክንያት በማየትና በመስማት ችሎታዋ ላይ ዘላቂ ጉዳት ደረሰባት። የማሽተት ችሎታዋንም አጥታለች። * ፒተር እና ሱ ‘እንዴት ሰው እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ያደርጋል?’ ብለው በተደጋጋሚ ራሳቸውን ይጠይቁ ነበር። እርግጥ ፈንጂውን ያጠመደው ሰው የይሖዋ አገልጋይ አይደለም። ይህ ሰው ከበርካታ ዓመታት በኋላ በቁጥጥር ሥር ውሎ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት። ፒተር እና ሱ ሰውየውን ይቅር ብለውት እንደሆነ ሲጠየቁ እንዲህ ብለዋል፦ “ይሖዋ ቂም መያዝ አካላዊ፣ ስሜታዊና አእምሯዊ ጉዳት እንደሚያስከትልብን አስተምሮናል። ስለዚህ ፍንዳታው ከተከሰተ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ቁጣንና ቂምን ከልባችን አውጥተን ሕይወታችንን በሰላም እንድንቀጥል እንዲረዳን ለመንነው።”

16 ሰውየውን ይቅር ማለት ቀላል ነበር? እንደዚያ ለማለት ይከብዳል። ፒተር እና ሱ እንዲህ ብለዋል፦ “ሱ በአደጋው ምክንያት የደረሰባት ጉዳት በሕይወታችን ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ አልፎ አልፎ እንደ አዲስ እናስተውላለን። በዚህ ጊዜ ልባችን በቁጣ ይሞላል። ግን ስለ ጉዳዩ እየተብሰለሰልን ስለማንቆይ ስሜቱ ቶሎ ይጠፋል። እንዲያውም ፈንጂውን ያጠመደው ሰውዬ አንድ ቀን ወንድማችን ከሆነ በደስታ እንደምንቀበለው አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። ያጋጠመን ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በእርግጥም ነፃ እንደሚያወጡን አስተምሮናል፤ ከምናስበው በላይ በተለያዩ መንገዶች ነፃነት ይሰጡናል! ይሖዋ የደረሰብንን ጉዳት በሙሉ በቅርቡ እንደሚያስተካክለው ማወቃችንም ያጽናናናል።”

17. ከማይራ ተሞክሮ ስለ ይቅር ባይነት ምን ትምህርት አግኝተሃል?

17 ማይራ እውነትን በሰማችበት ወቅት ባለትዳርና የሁለት ትናንሽ ልጆች እናት ነበረች። ባለቤቷ እውነትን አልተቀበለም። ከጊዜ በኋላ ባለቤቷ ምንዝር ፈጽሞ ቤተሰቡን ትቶ ሄደ። ማይራ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ እኔንና ሁለት ልጆቻችንን ትቶን ሲሄድ በሚወዱት ሰው የተከዱ ብዙ ሰዎች የሚሰማቸው ዓይነት ስሜት ተሰማኝ። ደነገጥኩ፤ ሁኔታውን ማመን ከበደኝ፤ በሐዘንና በቁጭት ተዋጥኩ፤ ራሴን ወቀስኩ፤ እንዲሁም ተበሳጨሁ።” ማይራ ትዳሯ ከፈረሰም በኋላ የባለቤቷ ክህደት ያሳደረባት ቁስል አልጠፋም። ማይራ እንዲህ ብላለች፦ “ያ ስሜት ለወራት ቀጠለ። ይህም ከይሖዋና ከሌሎች ጋር የነበረኝን ግንኙነት እንደጎዳው አስተዋልኩ።” አሁን ማይራ በቀድሞ ባለቤቷ መበሳጨቷን አቁማለች፤ ለእሱም ምንም ዓይነት የጥላቻ ስሜት የላትም። አንድ ቀን የይሖዋ አገልጋይ እንደሚሆን ተስፋ ታደርጋለች። ማይራ በወደፊቱ ጊዜ ላይ ትኩረት ማድረግ ችላለች። ነጠላ እናት ሆና ሁለት ልጆቿን የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት ችላለች። በአሁኑ ወቅት ማይራ ከልጆቿና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይሖዋን የማገልገል መብት አግኝታለች።

የይሖዋ ፍጹም ፍትሕ

18. የጽንፈ ዓለሙ ዳኛ የሆነው ይሖዋ ምን እንደሚያደርግ መተማመን እንችላለን?

18 ሰዎች ምን ዓይነት ፍርድ ሊፈረድባቸው እንደሚገባ መወሰን የእኛ ኃላፊነት አለመሆኑ ትልቅ እፎይታ ነው! ይህን ወሳኝ ሥራ ማከናወን የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ዳኛ የሆነው የይሖዋ ኃላፊነት ነው። (ሮም 14:10-12) ይሖዋ ምንጊዜም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ካወጣው ፍጹም መሥፈርት ጋር የሚስማማ ፍርድ እንደሚያስተላልፍ መተማመን እንችላለን። (ዘፍ. 18:25፤ 1 ነገ. 8:32) ይሖዋ መቼም ቢሆን ፍትሕ አያዛባም!

19. የይሖዋ ፍጹም ፍትሕ ምን ውጤት ያስገኛል?

19 ይሖዋ አለፍጽምና እና ኃጢአት ያስከተሏቸውን መጥፎ ውጤቶች በሙሉ የሚያስተካክልበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። በዚያ ጊዜ ያሉብን አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ቁስሎች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይሻራሉ። (መዝ. 72:12-14፤ ራእይ 21:3, 4) ጨርሶ አይታወሱም። ያ አስደሳች ጊዜ እስኪመጣ በምንጠባበቅበት ወቅት ይሖዋ በይቅር ባይነት ረገድ እሱን የመምሰል ችሎታ ስለሰጠን በጣም አመስጋኞች ነን።

መዝሙር 18 ለቤዛው አመስጋኝ መሆን

^ ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ይጓጓል። እኛ ክርስቲያኖችም አንድ ሰው ሲበድለን የይሖዋን ምሳሌ መከተል አለብን። እኛ በራሳችን ይቅር ብለን ልናልፍ ስለምንችላቸው ኃጢአቶች እንዲሁም ለሽማግሌዎች መናገር ስላለብን ኃጢአቶች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። ይሖዋ እርስ በርስ ይቅር እንድንባባል የሚፈልገው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ሌሎችን ይቅር ስንል ምን በረከቶችን እንደምናገኝም እንመለከታለን።

^ በሚያዝያ 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

^ አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ የጥር 8, 1992 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 9-13⁠ን ተመልከት። በተጨማሪም በ​JW ብሮድካስቲንግ ላይ የወጣውን ፒተር እና ሱ ሹልትስ፦ አስፈሪ ትዝታዎችን ማሸነፍ ይቻላል (እንግሊዝኛ) የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።