በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 27

“ይሖዋን ተስፋ አድርግ”

“ይሖዋን ተስፋ አድርግ”

“ይሖዋን ተስፋ አድርግ፤ ደፋር ሁን፤ ልብህም ይጽና።”—መዝ. 27:14

መዝሙር 128 እስከ መጨረሻው መጽናት

ማስተዋወቂያ *

1. (ሀ) ይሖዋ ምን ተስፋ ሰጥቶናል? (ለ) ‘ይሖዋን ተስፋ ማድረግ’ ሲባል ምን ማለት ነው? (“ተጨማሪ ማብራሪያ” የሚለውን ተመልከት።)

 ይሖዋ እሱን ለሚወዱት ሁሉ ግሩም ተስፋ ዘርግቶላቸዋል። በቅርቡ ሕመምን፣ ሐዘንንና ሞትን ያስወግዳል። (ራእይ 21:3, 4) እሱን ተስፋ የሚያደርጉ “የዋሆች” ምድርን ገነት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። (መዝ. 37:9-11) በተጨማሪም ከአሁኑ እጅግ በላቀ ሁኔታ እያንዳንዳችን ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረን ይረዳናል። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! ይሁንና ይሖዋ የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም ለማመን የሚያበቃ ምን ምክንያት አለን? ይሖዋ መቼም ቢሆን ቃሉን አያጥፍም። በመሆኑም ‘ይሖዋን ተስፋ ለማድረግ’ የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አለን። * (መዝ. 27:14) አምላካችን ዓላማውን እስኪፈጽም ድረስ በትዕግሥትና በደስታ በመጠባበቅ ይሖዋን ተስፋ እንደምናደርግ እናሳያለን።—ኢሳ. 55:10, 11

2. ይሖዋ ምን አድርጓል?

2 ይሖዋ ቃሉን እንደሚጠብቅ በተግባር አሳይቷል። ይህን የሚያሳይ አንድ ግሩም ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ በራእይ መጽሐፍ ላይ፣ በዘመናችን ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶችና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሰዎችን በንጹሕ አምልኮ አንድ እንደሚያደርጋቸው ቃል ገብቶ ነበር። ይህ አስደናቂ ቡድን በዛሬው ጊዜ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተብሎ ይጠራል። (ራእይ 7:9, 10) በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉት ሰዎች ከተለያየ ዘር፣ ቋንቋና ባሕል የተውጣጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ቢሆኑም ሰላምና አንድነት ያለው ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር መሥርተዋል። (መዝ. 133:1፤ ዮሐ. 10:16) በተጨማሪም የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ቀናተኛ ሰባኪዎች ናቸው። ወደፊት የተሻለ ዓለም እንደሚመጣ የሚገልጸውን ተስፋ ሰሚ ጆሮ ላላቸው ሁሉ ለመናገር ምንጊዜም ዝግጁ ናቸው። (ማቴ. 28:19, 20፤ ራእይ 14:6, 7፤ 22:17) አንተም የእጅግ ብዙ ሕዝብ ክፍል ከሆንክ ወደፊት የተሻለ ዓለም እንደሚመጣ የሚገልጸውን ተስፋ ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተው ምንም ጥያቄ የለውም።

3. የሰይጣን ዓላማ ምንድን ነው?

3 ዲያብሎስ ተስፋህን ሊያጨልምብህ ይፈልጋል። የእሱ ዓላማ ይሖዋ እንደማያስብልህና ቃሉን እንደማይጠብቅ እንድታምን ማድረግ ነው። ሰይጣን ተስፋችንን ማጨለም ከቻለ ድፍረት እናጣለን፤ ይባስ ብሎም ይሖዋን ማገልገላችንን ልናቆም እንችላለን። ቀጥሎ እንደምንመለከተው ዲያብሎስ የኢዮብን ተስፋ ለማጨለምና ይሖዋን ማገልገሉን እንዲያቆም ለማድረግ ሞክሮ ነበር።

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን? (ኢዮብ 1:9-12)

4 ሰይጣን፣ ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ ለማድረግ የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። (ኢዮብ 1:9-12ን አንብብ።) በተጨማሪም ከኢዮብ ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንዲሁም አምላክ እንደሚወደንና ቃሉን እንደሚጠብቅ ማስታወስ ያለብን ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

ሰይጣን የኢዮብን ተስፋ ሊያጨልምበት ሞከረ

5-6. ኢዮብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምን ደረሰበት?

5 ኢዮብ አስደሳች ሕይወት ይመራ ነበር። ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው። በተጨማሪም ደስታ የሰፈነበት ትልቅ ቤተሰብ ነበረው፤ እጅግ ባለጸጋም ነበር። (ኢዮብ 1:1-5) ሆኖም በአንድ ቀን ውስጥ ሁሉንም ነገር ተነጠቀ። በመጀመሪያ ንብረቱን አጣ። (ኢዮብ 1:13-17) ከዚያም የሚወዳቸው ልጆቹ በሙሉ ሞቱበት። እስቲ አስበው! ወላጆች ከልጆቻቸው አንዱን እንኳ በሞት ሲያጡ በከፍተኛ ሐዘን ይዋጣሉ። ከዚህ አንጻር ኢዮብና ሚስቱ አሥሩም ልጆቻቸው እንደሞቱ ሲሰሙ በከፍተኛ ድንጋጤ፣ ሐዘንና ተስፋ መቁረጥ ተውጠው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም! ኢዮብ በሐዘን ልብሱን መቅደዱና መሬት ላይ መደፋቱ ምንም አያስገርምም!—ኢዮብ 1:18-20

6 ቀጥሎም ሰይጣን ከኢዮብ ጤንነቱንና ክብሩን ነጠቀው። (ኢዮብ 2:6-8፤ 7:5) በአንድ ወቅት ኢዮብ በማኅበረሰቡ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ነበር። ሰዎች መጥተው ምክር ይጠይቁት ነበር። (ኢዮብ 31:18) አሁን ግን ሰዎች ራቁት። የገዛ ወንድሞቹ፣ የቅርብ ወዳጆቹ እና አገልጋዮቹ እንኳ አገለሉት!—ኢዮብ 19:13, 14, 16

በዘመናችን ያሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ኢዮብ መከራ ባጋጠመው ወቅት የተሰማው ስሜት ይገባቸዋል (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት) *

7. (ሀ) ኢዮብ ስለ መከራው ምንጭ ምን መደምደሚያ ላይ ደረሰ? ሆኖም ምን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም? (ለ) አንድ ክርስቲያን በሥዕላዊ መግለጫው ላይ የሚታየው ዓይነት ፈተና ሊደርስበት የሚችለው እንዴት ነው?

7 ሰይጣን፣ ኢዮብ መከራ የደረሰበት የይሖዋን ሞገስ ስላጣ እንደሆነ እንዲያስብ ፈልጎ ነበር። ለምሳሌ ሰይጣን አሥሩም የኢዮብ ልጆች አንድ ላይ እየተመገቡ በነበረበት ወቅት ኃይለኛ ነፋስ አምጥቶ ቤቱን አፈረሰው። (ኢዮብ 1:18, 19) በተጨማሪም ከሰማይ እሳት አውርዶ የኢዮብን መንጎችና መንጎቹን እየጠበቁ የነበሩትን አገልጋዮቹን ገደላቸው። (ኢዮብ 1:16) ነፋሱና እሳቱ የመጡት ከሰብዓዊ ምንጭ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ ኢዮብ የእነዚህ አደጋዎች ምንጭ ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ደመደመ። በመሆኑም ኢዮብ ይሖዋ በሆነ ምክንያት እንዳዘነበት አሰበ። ያም ቢሆን ኢዮብ የሰማዩን አባቱን ለመርገም ፈቃደኛ አልሆነም። ኢዮብ ላለፉት ዓመታት ከይሖዋ ብዙ መልካም ነገሮችን እንደተቀበለ ያውቃል። ስለዚህ ከይሖዋ መልካም ነገሮችን ከተቀበለ ክፉውንም ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን እንዳለበት ተናገረ። በመሆኑም “የይሖዋ ስም ምንጊዜም ይወደስ” አለ። (ኢዮብ 1:20, 21፤ 2:10) ኢዮብ ንብረቱን፣ ልጆቹንና ጤንነቱን ቢያጣም አሁንም ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት አላጓደለም። ሰይጣን በኢዮብ ላይ ያደረሰው ፈተና ግን በዚህ አላበቃም።

8. ሰይጣን ኢዮብን ለማጥቃት ምን ሌላ ዘዴ ተጠቀመ?

8 ሰይጣን ኢዮብን ለማጥቃት አንድ ተጨማሪ ዘዴ ቀየሰ። ሦስት ወዳጅ ተብዬዎችን በመጠቀም ኢዮብ የከንቱነት ስሜት እንዲሰማው ለማድረግ ሞከረ። እነዚህ ሰዎች፣ ኢዮብ መከራ የደረሰበት መሆኑ ብዙ ኃጢአቶችን መፈጸሙን እንደሚያሳይ ተናገሩ። (ኢዮብ 22:5-9) በተጨማሪም እሱ ክፉ ሰው ባይሆን እንኳ አምላክን ለማስደሰት ያደረገው ጥረት ምንም ዋጋ እንደሌለው ሊያሳምኑት ሞከሩ። (ኢዮብ 4:18፤ 22:2, 3፤ 25:4) አምላክ እንደማይወደው፣ እንደማይንከባከበው እንዲሁም አምላክን ማገልገሉ ምንም ዋጋ እንደሌለው ኢዮብን ሊያሳምኑት ሞክረው ነበር። እነዚህ ሰዎች የተናገሩት ነገር ኢዮብ ሁኔታው ምንም ተስፋ እንደሌለው እንዲያስብ ሊያደርገው ይችል ነበር።

9. ኢዮብ ደፋርና ብርቱ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?

9 እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። ኢዮብ አመድ ላይ ተቀምጧል፤ ሕመሙ በኃይል እያሠቃየው ነው። (ኢዮብ 2:8) ሦስቱ ወዳጅ ተብዬዎች የማያባራ ክስ እየሰነዘሩበትና ስሙን ለማጠልሸት እየሞከሩ ነው። የደረሰበት መከራ እንደ ከባድ ሸክም ተጭኖታል፤ ልጆቹን ማጣቱ ያስከተለበት ሐዘን ውስጥ ውስጡን እየበላው ነው። መጀመሪያ ላይ ኢዮብ ምንም አልተናገረም። (ኢዮብ 2:13 እስከ 3:1) ወዳጅ ተብዬዎቹ የኢዮብ ዝምታ ለፈጣሪው ጀርባውን እንደሰጠ የሚያሳይ እንደሆነ ከተሰማቸው በእጅጉ ተሳስተዋል። በአንድ ወቅት ኢዮብ፣ ሦስቱን ሰዎች ቀና ብሎ ዓይን ዓይናቸውን እያየ ሳይሆን አይቀርም “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” አላቸው። (ኢዮብ 27:5) ኢዮብ ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም ደፋርና ብርቱ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? በሐዘን በተዋጠበት ጊዜም እንኳ፣ የሚወደው አባቱ ይዋል ይደር እንጂ ከሥቃዩ እንደሚገላግለው ተስፋ ያደርግ ነበር። ቢሞት እንኳ ይሖዋ እንደሚያስነሳው ያውቅ ነበር።—ኢዮብ 14:13-15

ኢዮብን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

10. የኢዮብ ታሪክ ምን ያስተምረናል?

10 የኢዮብ ታሪክ፣ ሰይጣን ይሖዋን እንድንተው ሊያስገድደን እንደማይችል እንዲሁም ይሖዋ የሚያጋጥመንን ሁኔታ በሙሉ እንደሚያውቅ ያስተምረናል። በተጨማሪም የኢዮብ ታሪክ፣ ከሚያጋጥመን መከራ በስተ ጀርባ ያሉትን ጉዳዮች በተሻለ መንገድ እንድንረዳ ያስችለናል። ከኢዮብ የምናገኛቸውን አንዳንድ ትምህርቶች እስቲ እንመልከት።

11. በይሖዋ መታመናችንን ከቀጠልን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ያዕቆብ 4:7)

11 የኢዮብ ታሪክ፣ በይሖዋ መታመናችንን ከቀጠልን የትኛውንም መከራ በጽናት መቋቋምና ሰይጣንን በተሳካ ሁኔታ መቃወም እንደምንችል ያረጋግጣል። ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ካደረግን ዲያብሎስ ከእኛ እንደሚሸሽ ዋስትና ይሰጠናል።ያዕቆብ 4:7ን አንብብ።

12. የትንሣኤ ተስፋ ለኢዮብ ብርታት የሰጠው እንዴት ነው?

12 በትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል። ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ሰይጣን ንጹሕ አቋማችንን እንድናጎድፍ ለማድረግ የሞት ፍርሃትን ብዙ ጊዜ ይጠቀማል። ሰይጣን ስለ ኢዮብ ሲናገር ኢዮብ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ንጹሕ አቋሙን ማጉደፍን ጨምሮ ምንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለስ ገልጾ ነበር። ሰይጣን ምንኛ ተሳስቷል! ኢዮብ ሞት አፋፍ እንደደረሰ በተሰማው ጊዜም እንኳ አቋሙን አላላላም። ይሖዋ ጥሩ እንደሆነ እንዲሁም ይዋል ይደር እንጂ ሁሉንም ነገር እንደሚያስተካክል ያለው ጠንካራ እምነት እንዲጸና ረድቶታል። ኢዮብ በሕይወት እያለ ነገሮች ባይስተካከሉ እንኳ ወደፊት አምላክ ከሞት እንደሚያስነሳው እምነት ነበረው። የትንሣኤ ተስፋ ለኢዮብ እውን ነበር። ይህ ተስፋ ለእኛም እውን ከሆነልን ከሞት ጋር ብንፋጠጥ እንኳ ንጹሕ አቋማችንን አናጎድፍም።

13. ሰይጣን ኢዮብን ለማጥቃት የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች ልብ ማለት ያለብን ለምንድን ነው?

13 ሰይጣን ኢዮብን ለማጥቃት የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች ልብ ልንላቸው ይገባል። ምክንያቱም ሰይጣን በዛሬው ጊዜም እኛን ለማጥቃት ተመሳሳይ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ሰይጣን ክስ የሰነዘረው በኢዮብ ላይ ብቻ እንዳልሆነ ልብ በል፤ “[ሰው] ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል” ብሏል። (ኢዮብ 2:4, 5) በሌላ አነጋገር ሰይጣን፣ ይሖዋ አምላክን ከልባችን እንደማንወደው እንዲሁም ሕይወታችንን ለማትረፍ ስንል እሱን እንደምንተወው መግለጹ ነው። በተጨማሪም ሰይጣን፣ አምላክ እንደማይወደን እንዲሁም እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት ከቁብ እንደማይቆጥረው ገልጿል። ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች የሰይጣንን መሠሪ ዘዴዎች ስለሚያውቁ በእሱ ውሸቶች አይታለሉም።

14. የሚደርሱብን መከራዎች ምን እንድናስተውል ይረዱናል? በምሳሌ አስረዳ።

14 የሚደርሱብንን መከራዎች ስለ ራሳችን ይበልጥ ለማወቅ እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። ኢዮብ የደረሰበት መከራ ያለበትን ድክመት ለማወቅና ለማስተካከል አጋጣሚ ሰጥቶታል። ለምሳሌ ይበልጥ ትሕትና ማዳበር እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። (ኢዮብ 42:3) እኛም መከራ ሲደርስብን ስለ ራሳችን ብዙ ነገር ማወቅ እንችላለን። ኒኮላይ * የተባለ አንድ ወንድም ከባድ የጤና እክል ቢኖርበትም እስር ቤት ገብቶ ነበር፤ እንዲህ ብሏል፦ “እስር ቤት እንደ ራጅ ማሽን ነው፤ የአንድን ክርስቲያን ውስጣዊ ማንነት አውጥቶ ያሳያል።” ድክመቶቻችንን ለይተን ካወቅን በኋላ ደግሞ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ እንችላለን።

15. ማዳመጥ ያለብን ማንን ነው? ለምንስ?

15 ጠላቶቻችንን ሳይሆን ይሖዋን ልናዳምጥ ይገባል። ኢዮብ ይሖዋ ሲያነጋግረው በጥሞና አዳምጧል። አምላክ ኢዮብን በጉዳዩ ላይ እንዲያመዛዝን ረድቶታል፤ እንዲህ ያለው ያህል ነው፦ ‘በፈጠርኳቸው ነገሮች ላይ የተንጸባረቀውን ኃይሌን ታያለህ? የደረሰብህን ነገር በሙሉ አውቃለሁ። አንተን መንከባከብ የሚያቅተኝ ይመስልሃል?’ ኢዮብ ለይሖዋ ጥሩነት ያለውን ጥልቅ አድናቆት የሚያሳይና ትሕትና የሚንጸባረቅበት መልስ ሰጥቷል። “ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን በገዛ ዓይኔ አየሁህ” ብሏል። (ኢዮብ 42:5) ኢዮብ ይህን የተናገረው እዚያው አመድ ላይ እንደተቀመጠ ሳይሆን አይቀርም፤ ሰውነቱን ቁስል ወርሶታል፤ እንዲሁም ልጆቹን በማጣቱ በሐዘን እንደተዋጠ ነው። ያም ቢሆን ይሖዋ ኢዮብን እንደሚወደውና ሞገሱን እንደሚያሳየው አረጋገጠለት።—ኢዮብ 42:7, 8

16. በኢሳይያስ 49:15, 16 መሠረት መከራ ሲያጋጥመን ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

16 በዛሬው ጊዜም ሰዎች ሊሰድቡን ወይም ሊያንቋሽሹን ይችላሉ። የእኛን ወይም የድርጅቱን ስም ሊያጠፉ እንዲሁም ‘ክፉውን ሁሉ በውሸት ሊያስወሩብን’ ይችላሉ። (ማቴ. 5:11) ይሖዋ መከራ ቢደርስብንም ታማኝነታችንን እንደማናጓድል እንደሚተማመንብን ከኢዮብ ታሪክ እንማራለን። ይሖዋ ይወደናል፤ እሱን ተስፋ የሚያደርጉትን መቼም ቢሆን አይተዋቸውም። (ኢሳይያስ 49:15, 16ን አንብብ።) የአምላክ ጠላቶች ለሚናገሯቸው ውሸቶች ጆሮ አትስጥ። በቱርክ የሚኖረው ጄምስ የተባለ ወንድምና ቤተሰቦቹ ብዙ መከራ አጋጥሟቸዋል፤ ጄምስ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ አምላክ ሕዝቦች የሚነገሩ ውሸቶችን መስማታችን ተስፋ እንደሚያስቆርጠን ተገነዘብን። ስለዚህ ትኩረታችንን በመንግሥቱ ተስፋ ላይ አሳረፍን። እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት በቅንዓት መካፈላችንን ቀጠልን። ይህም ደስታችንን እንዳናጣ ረድቶናል።” እኛም እንደ ኢዮብ ይሖዋን እናዳምጣለን። ጠላቶቻችን የሚናገሯቸው ውሸቶች ተስፋችንን አያጨልሙብንም።

ተስፋችን ያጸናናል

ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ ተባርኳል። እሱና ሚስቱ ለረጅም ዘመናት የይሖዋን በረከት ማጣጣም ችለዋል (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት) *

17. በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ ከተጠቀሱት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

17 ኢዮብ ከባድ መከራ ቢያጋጥማቸውም ደፋርና ብርቱ መሆናቸውን ካሳዩ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል አንዱ ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሌሎች በርካታ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችን ጠቅሷል፤ እነዚህን ሰዎች “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” በማለት ጠርቷቸዋል። (ዕብ. 12:1) ሁሉም ከባድ መከራ አጋጥሟቸው ነበር፤ ሆኖም ዕድሜያቸውን በሙሉ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ኖረዋል። (ዕብ. 11:36-40) ታዲያ ጽናታቸውና ትጋታቸው ከንቱ ሆኗል? በጭራሽ! አምላክ የገባቸው ቃሎች በሙሉ ሲፈጸሙ በሕይወት ዘመናቸው ማየት ባይችሉም እንኳ ይሖዋን ተስፋ ማድረጋቸውን ቀጥለው ነበር። ደግሞም የይሖዋን ሞገስ እንዳገኙ እርግጠኞች ስለነበሩ ይሖዋ የገባቸው ቃሎች ሲፈጸሙ ማየታቸው እንደማይቀር ቅንጣት ታክል አልተጠራጠሩም። (ዕብ. 11:4, 5) የእነሱ ምሳሌ ይሖዋን ተስፋ ማድረጋችንን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል።

18. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው? (ዕብራውያን 11:6)

18 የምንኖርበት ዓለም ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ ነው። (2 ጢሞ. 3:13) ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች መፈተኑን አላቆመም። ከፊታችን የሚጠብቀን ፈተና ምንም ይሁን ምን ‘ተስፋችንን የጣልነው ሕያው በሆነው አምላክ ላይ’ እንደሆነ በመተማመን ይሖዋን በትጋት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (1 ጢሞ. 4:10) አምላክ ለኢዮብ የሰጠው በረከት “ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ” እንደሚያረጋግጥ ልንዘነጋ አይገባም። (ያዕ. 5:11) እኛም ይሖዋ “ከልብ ለሚፈልጉት” ወሮታቸውን እንደሚከፍላቸው በመተማመን ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንጽና።—ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።

መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ

^ ከባድ መከራን በጽናት ስለተቋቋሙ ሰዎች ስናስብ መጀመሪያ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ኢዮብ መሆን አለበት። ከዚያ ታማኝ ሰው ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሰይጣን ይሖዋን እንድንተው ሊያስገድደን እንደማይችል እንማራለን። ይሖዋ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ሁኔታ እንደሚያውቅም እንማራለን። በተጨማሪም ይሖዋ የኢዮብ መከራ እንዲያበቃ እንዳደረገ ሁሉ አንድ ቀን እኛንም ከመከራችን ሁሉ ይገላግለናል። በእነዚህ እውነታዎች ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለን በተግባር ካሳየን ‘ይሖዋን ተስፋ አድርገናል’ ሊባል ይችላል።

^ ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “ተስፋ” ማድረግ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አንድን ነገር በጉጉት “መጠባበቅ” የሚል ትርጉም አለው። አንድን አካል ማመንን ወይም በእሱ ላይ መታመንንም ሊያመለክት ይችላል።—መዝ. 25:2, 3፤ 62:5

^ አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢዮብና ሚስቱ ልጆቻቸውን በሞት በማጣታቸው በከባድ ሐዘን ተዋጡ።

^ የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢዮብ መከራው እስከሚያበቃበት ጊዜ ድረስ ጸንቷል። እሱና ሚስቱ ይሖዋ ለእነሱና ለቤተሰባቸው በሰጠው በረከት ላይ ሲያሰላስሉ።