በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ጎዳናዬን እንዲመራልኝ ፈቅጃለሁ

ይሖዋ ጎዳናዬን እንዲመራልኝ ፈቅጃለሁ

በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ የራሴን የሕይወት ጎዳና መርጬ ነበር፤ በጣም የምወደው ሥራ ነበረኝ። ይሖዋ ግን የተለየ ጎዳና እንድከተል ግብዣ አቀረበልኝ፤ “ጥልቅ ማስተዋል እሰጥሃለሁ፤ ልትሄድበት የሚገባውንም መንገድ አስተምርሃለሁ” ያለኝ ያህል ነበር። (መዝ. 32:8) ይሖዋ ጎዳናዬን እንዲመራልኝ መፍቀዴ በእሱ አገልግሎት ግሩም መብቶችና በረከቶች እንዳገኝ አስችሎኛል፤ ከዚህም መካከል በአፍሪካ ያሳለፍኩት 52 ዓመት ይገኝበታል።

ከእንግሊዝ ወደ አፍሪካ

የተወለድኩት በ1935 እንግሊዝ ውስጥ በብላክ ካንትሪ በሚገኘው በዳርለስተን ነው። ይህ አካባቢ ብላክ ካንትሪ ተብሎ የተጠራው አየሩ በዚያ ከሚገኙት በርካታ የብረት ማቅለጫዎችና ሌሎች ፋብሪካዎች በሚወጣው ጥቁር ጭስ የተሞላ ስለነበር ነው። አራት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ወላጆቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ሳለሁ እውነትን እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ። ከዚያም በ1952 በ16 ዓመቴ ተጠመቅኩ።

በዚያው ጊዜ አካባቢ፣ የእጅ መሣሪያዎችና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች በሚያመርት ትልቅ ፋብሪካ ውስጥ አፓረንት ወጣሁ። የድርጅቱ ጸሐፊ ለመሆን ሥልጠና ጀመርኩ፤ ሥራውን በጣም እወደው ነበር።

አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በዊለንሆል በሚገኘው ጉባኤዬ በሳምንቱ መሃል የሚካሄደውን የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት እንድመራ ሲጋብዘኝ ከባድ ውሳኔ ከፊቴ ተደቀነ። በዚህ ጊዜ አጣብቂኝ ውስጥ ገባሁ። በወቅቱ የምሰበሰበው ሁለት ጉባኤዎች ውስጥ ነበር። የሳምንቱን መሃል ስብሰባ የምካፈለው ለሥራ ቦታዬ ቅርብ በሆነ ጉባኤ ውስጥ ነበር። ምክንያቱም የምሠራው ከቤተሰቦቼ ቤት 32 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ በሚገኘው በብሮምስግሮቭ ነበር። በሳምንቱ መጨረሻ ደግሞ ወደ ወላጆቼ ቤት ስለምሄድ በዊለንሆል በሚገኘው ጉባኤ እሰበሰባለሁ።

የይሖዋን ድርጅት የመደገፍ ፍላጎት ስለነበረኝ ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ያቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። እርግጥ ይህ በጣም የምወደውን ሥራ መልቀቅ ጠይቆብኛል። በዚያ ወቅት ይሖዋ ጎዳናዬን እንዲመራልኝ መፍቀዴ ፈጽሞ የማያስቆጭ ሕይወት እንድመራ መንገድ ከፍቶልኛል።

በብሮምስግሮቭ በሚገኘው ጉባኤ እሰበሰብ በነበረበት ወቅት አን የተባለች ቆንጆ እና መንፈሳዊ እህት ተዋወቅኩ። በ1957 ተጋባን። አብረን ሆነን በዘወትር አቅኚነት፣ በልዩ አቅኚነት፣ በጉብኝት ሥራ እንዲሁም በቤቴል አገልግሎት ተካፍለናል። አን በመላ ሕይወቴ የደስታ ምንጭ ሆናልኛለች።

በ1966 በጊልያድ ትምህርት ቤት 42ኛ ክፍል መማር በመቻላችን በጣም ተደሰትን። ከዚያም በማላዊ እንድናገለግል ተመደብን። ማላዊ ደግና እንግዳ ተቀባይ በሆኑት ሕዝቦቿ ትታወቃለች። ሆኖም እዚያ ብዙ መቆየት እንደማንችል አላወቅንም ነበር።

በማላዊ በአስቸጋሪ ጊዜ ማገልገል

በማላዊ በጉብኝት ሥራ ስንካፈል የተጠቀምንበት ጂፕ መኪና

የካቲት 1, 1967 ማላዊ ደረስን። ለአንድ ወር ያህል ቋንቋውን ከተማርን በኋላ በአውራጃ የበላይ ተመልካችነት ሥራ መካፈል ጀመርን። መኪናችን የትም ቦታ፣ ወንዝ ውስጥም እንኳ ሳይቀር መሄድ እንደሚችል የሚታመነው ጂፕ መኪና ነበር። የሚያሳዝነው ግን መኪናችን ማቋረጥ የሚችለው ጥልቀት የሌላቸውን ወንዞች ብቻ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የምናርፈው በጎጆ ቤቶች ውስጥ ነበር። ቤቶቹ በክረምት ወቅት ዝናብ ሲዘንብ ውኃ ስለሚያስገቡ ከጣሪያው ሥር ሸራ ይዘረጋላቸዋል። የሚስዮናዊነት አገልግሎትን የጀመርንበት መንገድ አስቸጋሪ ቢሆንም በጣም ወደድነው።

በሚያዝያ ወር በአገሪቱ ውስጥ ችግር እየተጠነሰሰ እንደሆነ ተገነዘብኩ። የማላዊ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ሄስቲንግስ ባንዳ የሰጡትን ንግግር በሬዲዮ ሰማሁ። የይሖዋ ምሥክሮች ግብር እንደማይከፍሉና በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ እንደሚገቡ ገለጹ። እነዚህ ክሶች ውሸት እንደሆኑ ግልጽ ነው። ያበሳጫቸው ነገር ገለልተኛ መሆናችን፣ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲ የአባልነት ካርድ ለመግዛት ፈቃደኛ አለመሆናችን እንደሆነ አውቀን ነበር።

መስከረም ወር ላይ ፕሬዚዳንቱ የይሖዋ ምሥክሮች በሁሉም ቦታ ችግር እንደሚፈጥሩ መግለጻቸውን ጋዜጣ ላይ አነበብን። በአንድ የፖለቲካ ስብሰባ ላይ፣ መንግሥታቸው በቅርቡ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲታገዱ እንደሚያደርግ ተናገሩ። ጥቅምት 20, 1967 እገዳው ተጣለ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ፖሊሶችና የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው መጥተው ቢሮውን ዘጉት፤ ሚስዮናውያኑንም ከአገሪቱ አባረሩ።

በ1967 ተይዘን አብረውን በሚስዮናዊነት ከሚያገለግሉት ከጃክ እና ከሊንዳ ዮሃንሰን ጋር ከማላዊ ስንባረር

ለሦስት ቀናት እስር ቤት ውስጥ ከቆየን በኋላ በብሪታንያ ቁጥጥር ሥር ወደነበረችው ወደ ሞሪሸስ ተላክን። ሆኖም የሞሪሸስ ባለሥልጣናት እዚያ ሚስዮናውያን ሆነን እንድንቀጥል አልፈቀዱልንም። ስለዚህ በሮዴዥያ (የአሁኗ ዚምባብዌ) እንድናገለግል ተመደብን። እዚያ ስንደርስ አንድ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን እንዲህ በማለት እንዳንገባ ከለከለን፦ “ማላዊ እንዳትቆዩ ተከለከላችሁ። ሞሪሸስም እንድትቆዩ አልተፈቀደላችሁም። ስለተመቻችሁ ብቻ ነው እዚህ የመጣችሁት።” በዚህ ጊዜ አን ማልቀስ ጀመረች። የትም እንደማንፈለግ ተሰማን። በዚያ ሰዓት ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቼ ወደ እንግሊዝ መመለስ አሰኝቶኝ ነበር። በመጨረሻ ግን የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናቱ በቅርንጫፍ ቢሮው እንድናድር ፈቀዱልን። ሆኖም በማግስቱ ቢሯቸው መምጣት እንዳለብን አስጠነቀቁን። በጣም ዝለን ነበር፤ ግን ሁሉንም ነገር በይሖዋ እጅ ለመተው ወሰንን። በማግስቱ ከሰዓት በኋላ ጨርሶ ባልጠበቅነው መንገድ በዚምባብዌ እንደ ጎብኚዎች ሆነን እንድንቆይ ተፈቀደልን። በዚያ ቀን የተሰማኝን ስሜት መቼም አልረሳውም። ይሖዋ ጎዳናችንን እየመራልን እንደሆነ እርግጠኛ ሆኜ ነበር።

አዲስ ምድብ—ከዚምባብዌ ሆኖ ማላዊ ማገልገል

ከአን ጋር በዚምባብዌ ቤቴል፣ 1968

በዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ በአገልግሎት ዘርፍ እንዳገለግል ተመደብኩ። በማላዊና በሞዛምቢክ የሚካሄደውን ሥራ እከታተል ነበር። በወቅቱ የማላዊ ወንድሞቻችን አስከፊ ስደት እየደረሰባቸው ነበር። ሥራዬ የማላዊ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሚልኳቸውን ሪፖርቶች መተርጎምን ያካትት ነበር። አንድ ቀን አንድ ሪፖርት ለማጠናቀር አምሽቼ እየሠራሁ ሳለ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እየደረሰባቸው ያለውን አሰቃቂ ግፍ ሳነብ አለቀስኩ። * በተጨማሪም ታማኝነታቸው፣ እምነታቸውና ጽናታቸው ልቤን በጥልቅ ነካው።—2 ቆሮ. 6:4, 5

በማላዊ ለቀሩት እንዲሁም ወደ ሞዛምቢክ ለሸሹት ወንድሞች መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርግ ነበር። ማላዊ ውስጥ በስፋት የሚነገረው የቺቼዋ ቋንቋ የትርጉም ቡድን በዚምባብዌ ወደሚገኝ የአንድ ወንድም ትልቅ እርሻ ተዛወረ። ወንድማችን ለተርጓሚዎቹ ቤትና ቢሮ ሠርቶላቸው ነበር። እዚያ ሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የመተርጎሙን ወሳኝ ሥራ ማከናወናቸውን ቀጠሉ።

በማላዊ የሚያገለግሉት የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በየዓመቱ በዚምባብዌ በሚካሄደው የቺቼዋ የአውራጃ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ዝግጅት አደረግን። ለስብሰባ ሲመጡ የአውራጃ ስብሰባው የንግግር አስተዋጽኦዎች ይሰጧቸዋል። ከዚያም ወደ ማላዊ ሲመለሱ ሐሳቡን በዚያ ለሚገኙት ወንድሞች ለማካፈል የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። አንድ ዓመት ላይ ወደ ዚምባብዌ ሲመጡ እነዚህን ደፋር የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ለማበረታታት የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት አዘጋጀንላቸው።

በዚምባብዌ በቺቼዋ እና በሾና በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በቺቼዋ ንግግር ሳቀርብ

የካቲት 1975 በሞዛምቢክ ወደሚገኙ ካምፖች የሸሹ የማላዊ ወንድሞችን ለመጠየቅ ሄድኩ። እነዚህ ወንድሞች ከዓለም አቀፉ የይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል እየሄዱ ነበር፤ የሽማግሌዎች አካል እንዲኖር የተደረገውን አዲስ ዝግጅትም ተግባራዊ አድርገዋል። አዲሶቹ ሽማግሌዎች የሕዝብ ንግግር ማቅረብን፣ በዕለቱ ጥቅስና በመጠበቂያ ግንብ ላይ መወያየትን አልፎ ተርፎም ትላልቅ ስብሰባዎችን ማካሄድን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን አደራጅተው ነበር። ካምፖቹን ያደራጇቸው ልክ እንደ ትልቅ ስብሰባ ነበር፤ የጽዳት፣ የምግብ አቅርቦት እንዲሁም የጥበቃ ዲፓርትመንት ነበራቸው። እነዚያ ታማኝ ወንድሞች በይሖዋ በረከት ብዙ ነገር አከናውነዋል። እኔም እነሱን በማየቴ እጅግ ተበረታታሁ።

በ1970ዎቹ መጨረሻ ላይ የዛምቢያ ቅርንጫፍ ቢሮ በማላዊ የሚከናወነውን ሥራ መከታተል ጀመረ። ያም ቢሆን ስለ ማላዊ ወንድሞች ማሰቤንና መጸለዬን አላቋረጥኩም፤ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች እንዲሁ አድርገዋል። የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኜ ሳገለግል ከዋናው መሥሪያ ቤት ተወካዮች እንዲሁም ከማላዊ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከዛምቢያ ከመጡ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ጋር በተደጋጋሚ ተገናኝቻለሁ። ሁሌም ስንገናኝ የምናነሳው ጥያቄ ተመሳሳይ ነበር፦ “የማላዊን ወንድሞች ይበልጥ ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?”

በጊዜ ሂደት ስደቱ በረድ አለ። ከአገሪቱ ሸሽተው የነበሩ ወንድሞች ወደ ማላዊ መመለስ ጀመሩ። በዚያ የቀሩት ወንድሞችም ቀስ በቀስ ከሚደርስባቸው ስደት እፎይ አሉ። አጎራባች አገሮች ለይሖዋ ሕዝቦች ሕጋዊ እውቅና መስጠትና የጣሉባቸውን እገዳ ማንሳት ጀመሩ። በ1991 ሞዛምቢክም እንደዚያው አደረገች። ሆኖም ‘በማላዊ ያሉት ወንድሞች ነፃነት የሚያገኙት መቼ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስበን ነበር።

ወደ ማላዊ መመለስ

ውሎ አድሮ የማላዊ የፖለቲካ ሁኔታ ተቀየረ፤ መንግሥትም በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለውን እገዳ በ1993 አነሳ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከአንድ ሚስዮናዊ ጋር እየተነጋገርኩ ሳለሁ ሚስዮናዊው “ወደ ማላዊ ትመለሳለህ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም በወቅቱ 59 ዓመቴ ስለነበር “አይ፣ አሁንማ አርጅቻለሁ” አልኩት። ሆኖም በዚያው ዕለት ከበላይ አካሉ ፋክስ ደረሰን፤ መልእክቱ ወደ ማላዊ እንድንመለስ ግብዣ የሚያቀርብ ነበር።

የዚምባብዌ ምድባችንን በጣም ስለምንወደው ይህ ለእኛ ከባድ ውሳኔ ነበር። በአገልግሎታችን ደስተኞች የነበርን ከመሆኑም ሌላ የረጅም ጊዜ ወዳጆች አፍርተን ነበር። እርግጥ የበላይ አካሉ፣ ከፈለግን ዚምባብዌ መቀጠል እንደምንችል በመግለጽ ደግነት አሳይቶናል። ስለዚህ የራሳችንን ጎዳና በመምረጥ ዚምባብዌ መቅረት እንችል ነበር። ሆኖም አብርሃምና ሣራ ይሖዋን ለመታዘዝ ሲሉ በስተ እርጅናቸው የተመቻቸ ቤታቸውን ለቀው እንደሄዱ አስታወስኩ።—ዘፍ. 12:1-5

በመሆኑም የይሖዋ ድርጅት የሰጠንን መመሪያ ለመከተል ወሰንን። የካቲት 1, 1995 ማለትም ለመጀመሪያ ጊዜ ማላዊ በሄድን ልክ በ28ኛ ዓመታችን እዚያ ደረስን። በዚያም እኔንና ሌሎች ሁለት ወንድሞችን ያቀፈ የቅርንጫፍ ኮሚቴ ተቋቋመ። ወዲያውኑ የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ በድጋሚ ለማደራጀት ጥረት ማድረግ ጀመርን።

የሚያሳድገው ይሖዋ ነው

ይሖዋ ሥራውን በፍጥነት ሲያሳድገው መመልከት በጣም ያስደስታል። በ1993 30,000 ገደማ የነበረው የአስፋፊዎች ቁጥር በ1998 ከ42,000 አለፈ። * በመስኩ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ እድገት ለማስተናገድ የበላይ አካሉ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲገነባ ፈቃድ ሰጠ። ሊሎንግዌ ውስጥ 12 ሄክታር መሬት ገዛን። እኔም በግንባታ ኮሚቴው ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ።

የበላይ አካል አባል የነበረው ወንድም ጋይ ፒርስ ግንቦት 2001 የአዲሱን ቅርንጫፍ ቢሮ የውሰና ንግግር አቀረበ። ከሁለት ሺህ የሚበልጡ የማላዊ ወንድሞችና እህቶች በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል። ከእነሱ መካከል አብዛኞቹ ከተጠመቁ 40 ዓመት ያለፋቸው ናቸው። እነዚህ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች በእገዳው ሥር ለበርካታ ዓመታት በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግት ስደት ደርሶባቸዋል። በቁሳዊ ድሆች ቢሆኑም በመንፈሳዊ የናጠጡ ሀብታሞች ናቸው። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች አዲሱን ቤቴል የመጎብኘት መብት በማግኘታቸው በጣም ተደሰቱ። ቤቴል ውስጥ በሄዱበት ሁሉ የመንግሥቱን መዝሙሮች በአፍሪካዊ ቃና ሲዘምሩ ይሰማ ነበር። በሕይወቴ ከተገኘሁባቸው ዝግጅቶች ሁሉ የዚህን ያህል ልቤን የነካው የለም። ፈተናዎችን በታማኝነት የሚወጡ ክርስቲያኖችን ይሖዋ እንደሚባርካቸው የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነበር።

የቅርንጫፍ ቢሮው ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ በስብሰባ አዳራሽ ውሰናዎች ላይ እንድካፈል በተደጋጋሚ መጋበዝ ጀመርኩ። በማላዊ የሚገኙ ጉባኤዎች፣ የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች አዳራሾችን በፍጥነት ለመገንባት ከተደረገው ዝግጅት ተጠቃሚ ሆኑ። ቀደም ሲል አንዳንድ ጉባኤዎች የሚሰበሰቡት ከባሕር ዛፍ በተሠሩ ዳሶች ውስጥ ነበር። ጣሪያው ላይ ሰሌን ይዘረጋሉ፤ ለመቀመጥ ደግሞ ከጭቃ የተሠሩ አግዳሚዎችን ይጠቀማሉ። አሁን ግን በገነቧቸው የሸክላ ምድጃዎች ውስጥ ጡብ እየተኮሱ ውብ የስብሰባ አዳራሾችን መገንባት ጀመሩ። ሆኖም የሚመርጡት አግዳሚ ወንበሮችን ነበር፤ ምክንያቱም አግዳሚ ወንበር ላይ ሁሌም አጠጋግቶ ሰው መጨመር ይቻላል።

ይሖዋ ሰዎችን በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ሲረዳቸው በመመልከቴም ተደስቻለሁ። ወጣት አፍሪካውያን ወንድሞች ራሳቸውን በፈቃደኝነት ሲያቀርቡ እንዲሁም ባገኙት መለኮታዊ ትምህርትና ሥልጠና ተጠቅመው ተሞክሮ ሲያካብቱ ማየት በጣም ያስደስታል። በቤቴልም ሆነ በጉባኤዎቻቸው ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን መቀበል ችለዋል። የአገሪቱ ተወላጅ የሆኑ አዳዲስ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች መሾማቸውም ጉባኤዎቹ ይበልጥ እንዲጠናከሩ አድርጓል። አብዛኞቹ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ባለትዳሮች ናቸው። እነዚህ ባለትዳሮች ከማኅበረሰቡ፣ አልፎ ተርፎም ከቤተሰቦቻቸው ጫና ቢደርስባቸውም ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ሲሉ ልጅ መውለድ የሚያስገኘውን ደስታ መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነዋል።

ባደረግኳቸው ውሳኔዎች ደስተኛ ነኝ

ከአን ጋር በብሪታንያ ቤቴል

ለ52 ዓመታት አፍሪካ ውስጥ ከቆየን በኋላ የጤና እክል አጋጠመኝ። ቅርንጫፍ ቢሮው በብሪታንያ እንድናገለግል ያቀረበውን ሐሳብ የበላይ አካሉ አጸደቀው። የምንወደውን የአገልግሎት ምድብ ትተን በመሄዳችን ብናዝንም የብሪታንያ ቤቴል ቤተሰብ አባላት በእርጅና ዘመናችን ጥሩ አድርገው እየተንከባከቡን ነው።

ይሖዋ ጎዳናዬን እንዲመራልኝ መፍቀዴ በሕይወቴ ውስጥ ካደረግኳቸው ውሳኔዎች ሁሉ የተሻለው እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። በገዛ ራሴ ማስተዋል ተመክቼ በሥራው ዓለም ቀጥዬ ቢሆን ኖሮ ሕይወቴ ከዚህ በጣም የተለየ ይሆን ነበር። ለካ ‘ጎዳናዬን ቀና ለማድረግ’ የሚያስፈልገኝ ምን እንደሆነ ይሖዋ ምንጊዜም ያውቃል! (ምሳሌ 3:5, 6) በወጣትነቴ አንድ ትልቅ ድርጅት የሚሠራበትን መንገድ መማር በመቻሌ በጣም ተደስቼ ነበር። ሆኖም የይሖዋ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት የሰጠኝ መንፈሳዊ ሥራ ከዚህ ጋር ሊወዳደር የማይችል ደስታ አስገኝቶልኛል። ያኔም ሆነ ዛሬ ይሖዋን ማገልገሌ እጅግ አርኪ የሆነ ሕይወት ለመምራት አስችሎኛል!

^ በአሁኑ ወቅት ማላዊ ውስጥ ከ100,000 በላይ አስፋፊዎች አሉ።