በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ስለ ይሖዋ መማርና ማስተማር በመቻሌ ደስተኛ ነኝ

ስለ ይሖዋ መማርና ማስተማር በመቻሌ ደስተኛ ነኝ

ያደግኩት በኢስተን፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነው፤ በልጅነቴ ስኬታማ የመሆን ምኞት ስለነበረኝ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ወሰንኩ። ትምህርት እወድ ነበር፤ በሒሳብና በሳይንስም ጥሩ ውጤት አገኝ ነበር። በ1956 አንድ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ከጥቁር ተማሪዎች መካከል ከፍተኛውን ውጤት በማግኘቴ 25 ዶላር ሸልሞኛል። በኋላ ግን ግቤ ተቀየረ። ለምን?

ስለ ይሖዋ የተማርኩበት መንገድ

በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወላጆቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። እርግጥ ጥናታቸውን አልቀጠሉም፤ ሆኖም እናቴ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን መውሰዷን ቀጠለች። በ1950 በኒው ዮርክ ሲቲ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፤ የእኛ ቤተሰብም በስብሰባው ላይ ተገኘ።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ወንድም ሎረንስ ጄፍሪስ ቤታችን መጥቶ ያነጋግረን ጀመር። እኔን ለመርዳት ጥረት አድርጓል። መጀመሪያ ላይ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካና በጦር ሠራዊት ውስጥ አለመግባታቸው ያከራክረን ነበር። ሁሉም የአሜሪካ ዜጋ አልዋጋም ካለ ጠላቶቻችን መጥተው አገራችንን ድል እንደሚያደርጓት በመግለጽ ተከራከርኩት። ወንድም ጄፍሪስ ግን እንዲህ በማለት በትዕግሥት አስረዳኝ፦ “ሁሉም የአሜሪካ ዜጎች ይሖዋ አምላክን የሚያገለግሉ ቢሆንና ጠላቶች መጥተው ጥቃት ቢሰነዝሩባቸው ይሖዋ ምን እርምጃ የሚወስድ ይመስልሃል?” ስለዚህና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች የሰጠኝ ማብራሪያ ተቃውሞዬ መሠረተ ቢስ እንደሆነ አስገነዘበኝ። ይህም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የመማር ጉጉቴን አነሳሳው።

የተጠመቅኩበት ዕለት

እናቴ ምድር ቤት ውስጥ ያስቀመጠቻቸውን የቆዩ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ለሰዓታት አነብ ነበር። ውሎ አድሮ እውነትን እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ። በመሆኑም ወንድም ጄፍሪስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድጀምር ያቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። በስብሰባዎችም ላይ አዘውትሬ መገኘት ጀመርኩ። የምማረውን ነገር ወደድኩት፤ በመሆኑም የምሥራቹ አስፋፊ ሆንኩ። “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቅርብ” መሆኑን ስገነዘብ ግቤ ተቀየረ። (ሶፎ. 1:14) ዩኒቨርሲቲ ከመግባት ይልቅ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ ለመርዳት ተነሳሳሁ።

ሰኔ 13, 1956 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀቅኩ፤ ከዚያም ከሦስት ቀን በኋላ በአንድ የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠመቅኩ። በመላ ሕይወቴ ስለ ይሖዋ ለመማርና ለማስተማር መወሰኔ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን በረከቶች እንደሚያስገኝልኝ በወቅቱ አልተገነዘብኩም ነበር።

በአቅኚነት አገልግሎት መማርና ማስተማር

ከተጠመቅኩ ከስድስት ወር በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። የታኅሣሥ 1956 የመንግሥት አገልግሎት “እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ተዛውረህ ማገልገል ትችል ይሆን?” የሚል ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር። ግብዣው እኔንም ይመለከተኛል። ብዙ የምሥራቹ ሰባኪዎች በሌሉበት ቦታ እርዳታ ማበርከት እፈልግ ነበር።—ማቴ. 24:14

ወደ ኤጅፊልድ፣ ሳውዝ ካሮላይና ተዛወርኩ። በዚያ ያለው ጉባኤ አራት አስፋፊዎች ብቻ ነበሩት። እኔ ስሄድ የአስፋፊዎች ቁጥር አምስት ሆነ። ስብሰባ የምናደርገው በአንድ ወንድም ሳሎን ውስጥ ነበር። በየወሩ በአገልግሎት 100 ሰዓት አሳልፍ ነበር። በአገልግሎት ግንባር ቀደም ሆኜ በመካፈልና የስብሰባ ክፍሎችን በማቅረብ ተጠመድኩ። የሚገርመው በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ በተካፈልኩ መጠን ስለ ይሖዋ ይበልጥ ተማርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናት አንዲት ሴት ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በጆንስተን የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ነበራት። በወቅቱ ሥራ በጣም ያስፈልገኝ ስለነበር በሳምንት የተወሰነ ቀን እንድሠራ ቀጠረችኝ፤ እንዲሁም የነበራትን አነስተኛ ሕንፃ እንደ ስብሰባ አዳራሽ እንድንጠቀምበት ፈቀደችልን።

የአስጠኚዬ ልጅ የሆነው ወንድም ጆሊ ጄፍሪስ ከብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ተዛውሮ አብሮኝ በአቅኚነት ማገልገል ጀመረ። የምንኖረው አንድ ወንድም ባዋሰን ትንሽዬ ተጎታች ቤት ውስጥ ነበር።

በደቡብ ዩናይትድ ስቴትስ ለሠራተኛ የሚከፈለው ደሞዝ አነስተኛ ነበር። ለአንድ ቀን ሥራ የሚከፈለን ሁለት ወይም ሦስት ዶላር ብቻ ነበር። አንድ ቀን ያሉኝን የመጨረሻ ሳንቲሞች ተጠቅሜ አስቤዛ ገዛሁ። ከሱቁ ስወጣ አንድ ሰው ወደ እኔ መጣና “ሥራ ትፈልጋለህ? በሰዓት አንድ ዶላር እከፍልሃለሁ” አለኝ። ለሦስት ቀናት አንድን የግንባታ ቦታ እንዳጸዳ ቀጠረኝ። ይሖዋ በኤጅፊልድ እንድቆይ እየረዳኝ እንዳለ ግልጽ ሆነልኝ። ገቢዬ ዝቅተኛ ቢሆንም በ1958 በኒው ዮርክ ሲቲ በተካሄደው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ መገኘት ችዬ ነበር።

በሠርጋችን ቀን

በስብሰባው ሁለተኛ ቀን ላይ አንድ ልዩ ነገር አጋጠመኝ። በጋላቲን፣ ቴነሲ በዘወትር አቅኚነት ከምታገለግለው ከሩቢ ዋድሊንግተን ጋር ተዋወቅን። ሁለታችንም ሚስዮናዊ ሆነን የማገልገል ፍላጎት ስለነበረን በጊልያድ መማር ለሚፈልጉ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተገኘን። በኋላም ደብዳቤ መጻጻፍ ጀመርን። ብዙም ሳይቆይ በጋላቲን የሕዝብ ንግግር እንድሰጥ ተጋበዝኩ። እኔም አጋጣሚውን ተጠቅሜ እንድታገባኝ ጠየቅኳት። ሩቢ ወዳለችበት ጉባኤ ተዛወርኩ። ከዚያም በ1959 ተጋባን።

በጉባኤ ውስጥ መማርና ማስተማር

የ23 ዓመት ወጣት ሳለሁ በጋላቲን የጉባኤ አገልጋይ (አሁን የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ተብሎ ይጠራል) ሆኜ ተሾምኩ። ቻርልስ ቶምሰን የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንደተሾመ የጎበኘው የመጀመሪያ ጉባኤ የእኛ ጉባኤ ነበር። ብዙ ተሞክሮ ቢኖረውም ወንድሞች ምን እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም ሌሎች የወረዳ የበላይ ተመልካቾች አንዳንድ ጉዳዮችን እንዴት እንደሚይዙ ሐሳብ እንድሰጠው ጠየቀኝ። እኔም ውሳኔ ከማድረጌ በፊት ጥያቄ መጠየቅና የተሟላ መረጃ ማግኘት ጠቃሚ መሆኑን ከእሱ ተምሬያለሁ።

ግንቦት 1964 በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ በተካሄደው አንድ ወር የሚፈጅ የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት እንድካፈል ተጋበዝኩ። የትምህርት ቤቱ አስተማሪዎች ይበልጥ ለመማርና መንፈሳዊነቴን ለማሳደግ ጥልቅ ፍላጎት እንዲያድርብኝ ረዱኝ።

በወረዳና በአውራጃ ሥራ መማርና ማስተማር

እኔና ሩቢ ጥር 1965 በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ግብዣ ቀረበልን። የተመደብንበት ወረዳ በጣም ሰፊ ነበር፤ ከኖክስቪል፣ ቴነሲ ተነስቶ እስከ ሪችመንድ፣ ቨርጂንያ አካባቢ ይደርሳል። በኖርዝ ካሮላይና፣ በኬንተኪና በዌስት ቨርጂንያ ያሉ ጉባኤዎችን ያካትታል። የምጎበኘው ጥቁሮች ያሉባቸውን ጉባኤዎች ብቻ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ ነጮችና ጥቁሮች አንድ ላይ መሰብሰብ አይፈቀድላቸውም። ወንድሞች ድሆች ስለነበሩ ያለንን ነገር ለተቸገሩ ሰዎች ማካፈልን ተምረናል። ለረጅም ጊዜ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ያገለገለ አንድ ወንድም ወሳኝ ትምህርት ሰጥቶኛል፦ “ወንድም ሁንላቸው። ወደ አንድ ጉባኤ ስትሄድ እንደ አለቃ አትሁን። ልትረዳቸው የምትችለው እንደ ወንድማቸው ካዩህ ብቻ ነው።”

አንድን ትንሽ ጉባኤ እየጎበኘን በነበረበት ወቅት ሩቢ የአንድ ዓመት ልጅ ያላትን አንዲት ወጣት ሴት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀመረች። በጉባኤው ውስጥ እሷን ሊያስጠናት የሚችል ሰው ባልነበረበት ወቅት ሩቢ በደብዳቤ ታስጠናት ነበር። በቀጣዩ ጉብኝታችን ወቅት ሴትየዋ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ተገኘች። ሁለት ልዩ አቅኚ እህቶች እዚያ ሲመደቡ ከእነሱ ጋር ማጥናቷን ቀጠለች፤ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀች። ከ30 ዓመት ገደማ በኋላ በ1995 በፓተርሰን ቤቴል ሳለን አንዲት ወጣት እህት መጥታ ሩቢን ተዋወቀቻት። ለካስ እህት፣ ሩቢ ያስጠናቻት ሴትዮ ልጅ ነች። ያቺ ልጅ አድጋ ከባለቤቷ ጋር በጊልያድ ትምህርት ቤት 100ኛ ክፍል ተምራለች።

ሁለተኛው ወረዳችን ማዕከላዊ ፍሎሪዳን ይሸፍን ነበር። በዚያ ወቅት መኪና ስላስፈለገን በርካሽ ዋጋ መኪና ገዛን። ሆኖም በመጀመሪያው ሳምንት የውኃ ፓምፑ ተበላሸ። ለማሠሪያ የሚሆን ገንዘብ ደግሞ አልነበረንም። አንድ ወንድም ሊረዳን እንደሚችል ስላሰብኩ ደወልኩለት። እሱም ከሠራተኞቹ አንዱን ልኮ መኪናችንን አሠራልን፤ ሆኖም ለጥገናው ገንዘብ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲሁ “ተከፍሏል” አለን። እንዲያውም የተወሰነ ገንዘብ በስጦታ መልክ ሰጠን! ይሖዋ አገልጋዮቹን እንዴት እንደሚንከባከባቸው የሚያሳይ ግሩም ተሞክሮ ነበር። እኛም ለሌሎች ልግስና ማሳየት እንዳለብን አስተማረን።

ጉባኤዎችን ስንጎበኝ የምናርፈው በወንድሞች ቤት ነበር። በመሆኑም በርካታ የረጅም ጊዜ ወዳጆች አፍርተናል። አንድ ቀን ስለ ጉባኤው ሪፖርት መጻፍ ከጀመርኩ በኋላ ወረቀቱን እዚያው ታይፕራይተሩ ላይ ትቼው ሄድኩ። በእንግድነት የተቀበሉን ቤተሰቦች የሦስት ዓመት ልጅ ነበራቸው። ማታ ስመለስ ልጁ ታይፕራይተሩን ነካክቶ ወረቀቱ ላይ እንደጻፈበት አየሁ። ያንን ሪፖርት ለመጨረስ “ስላገዘኝ” ለበርካታ ዓመታት እቀልድበት ነበር።

በ1971 በኒው ዮርክ ሲቲ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል የሚጋብዝ ደብዳቤ ደረሰኝ። በጣም ደነገጥን! እዚያ በሄድንበት ወቅት ገና 34 ዓመቴ ነበር። በዚያ የተመደብኩት የመጀመሪያው ጥቁር የአውራጃ የበላይ ተመልካች እኔ ነበርኩ። ወንድሞች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ።

የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሳገለግል በየሳምንቱ በወረዳ ስብሰባ ላይ ስለ ይሖዋ ማስተማር ያስደስተኝ ነበር። ብዙዎቹ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ከእኔ የበለጠ ተሞክሮ ነበራቸው። ከእነዚህ ወንድሞች መካከል አንዱ፣ በተጠመቅኩበት ወቅት የጥምቀት ንግግር ያቀረበው ወንድም ነበር። ሌላኛው የወረዳ የበላይ ተመልካች ደግሞ ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ቴዎዶር ጃራዝ ነው። በብሩክሊን ቤቴል የሚያገለግሉ ተሞክሮ ያላቸው ብዙ ወንድሞችም ነበሩ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾቹና ቤቴላውያኑ ነፃነት እንዲሰማኝ ስላደረጉኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። እነዚህ ወንድሞች በአምላክ ቃል የሚታመኑና ድርጅቱን በታማኝነት የሚደግፉ አፍቃሪ እረኞች መሆናቸውን በገዛ ዓይኔ ተመልክቻለሁ። ትሑት መሆናቸው የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ቀላል እንዲሆንልኝ አድርጓል።

ወደ ወረዳ ሥራ መመለስ

በ1974 የበላይ አካሉ ሌሎች የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በአውራጃ ሥራ እንዲካፈሉ መደበ፤ እኔ ደግሞ በድጋሚ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተመደብኩ። ይሄኛው ወረዳዬ የሚገኘው በሳውዝ ካሮላይና ነበር። ደስ የሚለው፣ በወቅቱ ጥቁሮችና ነጮች በወረዳና በጉባኤ ስብሰባ ላይ አብረው መሰብሰብ ተፈቅዶላቸው ነበር፤ ይህም ወንድሞችን በጣም አስደስቷቸዋል።

በ1976 መገባደጃ አካባቢ በጆርጂያ በሚገኝ ወረዳ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ ወረዳው ከአትላንታ እስከ ኮሎምበስ ያለውን ቦታ ይሸፍን ነበር። ለአምስት ጥቁር ልጆች የቀብር ንግግር ያቀረብኩበትን ጊዜ በደንብ አስታውሳለሁ። ልጆቹ የሞቱት ሰዎች በቤታቸው ላይ እሳት በመልቀቃቸው ነው። እናታቸው ቆስላ ሆስፒታል ገብታ ነበር። ነጭ ጥቁር ሳይል፣ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ወላጆቹን ለማጽናናት ወደ ሆስፒታሉ ይጎርፉ ነበር። ወንድሞች ያሳዩት ፍቅር በጣም አስደናቂ ነው። እንዲህ ያለው ርኅራኄ የአምላክ አገልጋዮች በጣም ከባድ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም እንኳ በጽናት እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል።

በቤቴል መማርና ማስተማር

በ1977 ለተወሰኑ ወራት ወደ ብሩክሊን ቤቴል መጥተን በአንድ ፕሮጀክት እንድንካፈል ተጠየቅን። ፕሮጀክቱ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ሁለት የበላይ አካል አባላት እኔና ሩቢ በቋሚነት በቤቴል ለማገልገል ፈቃደኞች መሆናችንን ጠየቁኝ። እኛም ግብዣውን ተቀበልን።

ለ24 ዓመታት በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ አገልግያለሁ፤ እዚያ የሚያገለግሉት ወንድሞች ብዙውን ጊዜ ውስብስብና ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች ያጋጥሟቸዋል። ባለፉት ዓመታት የበላይ አካሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማሙ መመሪያዎችን ሲሰጥ ቆይቷል። ጥያቄዎችን የምንመልሰው እነዚህን መመሪያዎች መሠረት አድርገን ነው። በተጨማሪም መመሪያዎቹ ለወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ ለሽማግሌዎችና ለአቅኚዎች ለሚሰጠው ሥልጠና መሠረት ሆነው ያገለግላሉ። ይህ ሥልጠና ብዙዎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ረድቷል። ይህ ደግሞ የይሖዋን ድርጅት አጠናክሮታል።

ከ1995 እስከ 2018 የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ ወይም በቀድሞ መጠሪያው የዞን የበላይ ተመልካች ሆኜ የተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ጎብኝቻለሁ። ከቅርንጫፍ ኮሚቴዎች፣ ከቤቴላውያን እንዲሁም ከሚስዮናውያን ጋር በመገናኘት እነሱን ለማበረታታትና የሚያሳስቧቸውን ችግሮች ለመፍታት ጥረት አደርግ ነበር። በምላሹም እኔና ሩቢ ወንድሞች በሚያካፍሉን ተሞክሮዎች በእጅጉ ታንጸናል። ለምሳሌ በ2000 ሩዋንዳን ጎብኝተን ነበር። የቤቴል ቤተሰብ አባላት በ1994 በተከሰተው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ወቅት ያሳለፉትን ሁኔታ ስንሰማ ልባችን በጥልቅ ተነካ። ብዙዎቹ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን አጥተዋል። እነዚህ ወንድሞች ብዙ መከራ ቢደርስባቸውም እምነት፣ ተስፋና ደስታ ነበራቸው።

በ50ኛ ዓመት የጋብቻ ክብረ በዓላችን ቀን

አሁን በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እንገኛለን። ላለፉት 20 ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ አገልግያለሁ። ዩኒቨርሲቲ ገብቼ አልተማርኩም፤ ሆኖም ይሖዋና ድርጅቱ የሚሰጡትን ከሁሉ የላቀ ትምህርት አግኝቻለሁ። ይህም ዘላለማዊ ጥቅም የሚያስገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሌሎች ለማስተማር ብቁ እንድሆን ረድቶኛል። (2 ቆሮ. 3:5፤ 2 ጢሞ. 2:2) የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት፣ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉና ከፈጣሪያቸው ጋር ዝምድና እንዲመሠርቱ እንደሚረዳቸው ተመልክቻለሁ። (ያዕ. 4:8) እኔና ሩቢ አሁንም ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ሌሎች ስለ ይሖዋ የመማርና የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን የማስተማር መብታቸውን ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት እናበረታታቸዋለን። ደግሞም አንድ የይሖዋ አገልጋይ ሊያገኝ የሚችለው ከሁሉ የላቀው መብት ይህ ነው!