በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እንደ ጭንጋፍ የምቆጠር’ ሲል ምን ማለቱ ነበር? (1 ቆሮንቶስ 15:8)

በ1 ቆሮንቶስ 15:8 ላይ ጳውሎስ “በመጨረሻ ደግሞ እንደ ጭንጋፍ ለምቆጠር ለእኔ ተገለጠልኝ” ብሏል። ይህን ሐሳብ ቀደም ሲል የምንረዳው በዚህ መልኩ ነበር፦ ጳውሎስ ይህን ሐሳብ ሲናገር ኢየሱስን በሰማያዊ ግርማው ስላየበት ጊዜ ማመልከቱ ነበር። ጳውሎስ የኢየሱስን ሰማያዊ ክብር መመልከቱ፣ ጊዜው ከመድረሱ በፊት ማለትም መንፈሳዊ ትንሣኤ መከናወን ከመጀመሩ ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት ተወልዶ ወይም ትንሣኤ አግኝቶ መንፈሳዊ ሕይወት ያገኘ ያህል ነበር። ሆኖም በዚህ ጥቅስ ላይ የተደረገው ተጨማሪ ጥናት በዚህ ጥቅስ ማብራሪያ ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።

ጳውሎስ እዚህ ላይ የተናገረው ወደ ክርስትና በተለወጠበት ወቅት ስለሆነው ነገር መሆኑ እውነት ነው። ይሁንና “እንደ ጭንጋፍ” ወይም ያለጊዜው እንደተወለደ ፅንስ እንደሚቆጠር ሲገልጽ ምን ማለቱ ነበር? የተለያዩ አማራጮችን እንመልከት።

ለውጡ ድንገተኛና አስደንጋጭ ነበር። ብዙውን ጊዜ ፅንስ ያለጊዜው የሚወለደው በድንገት ነው። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ተብሎ የተጠራው ሳኦል በደማስቆ ያሉትን ክርስቲያኖች ለማሳደድ ወደዚያ ሲጓዝ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን በራእይ እንደሚያየው አልጠበቀም ነበር። ጳውሎስ ወደ ክርስትና መለወጡ ለእሱ ብቻ ሳይሆን በደማስቆ ሊያሳድዳቸው ላሰባቸው ክርስቲያኖችም ድንገተኛ ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ ያጋጠመው ነገር አስደንጋጭ ከመሆኑ የተነሳ ለጊዜው የማየት ችሎታውን አጥቶ ነበር።—ሥራ 9:1-9, 17-19

ጳውሎስ የተለወጠው “ያለጊዜው” ነው። “ጭንጋፍ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ያለጊዜው የተወለደ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ዘ ጀሩሳሌም ባይብል ጥቅሱን “ማንም ባልጠበቀበት ጊዜ የተወለድኩ ያህል ነው” በማለት ተርጉሞታል። ጳውሎስ በተለወጠበት ወቅት ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመልሷል። ቀደም ባሉት ቁጥሮች ላይ ከተጠቀሱት ሰዎች በተለየ መልኩ ጳውሎስ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት አላየውም። (1 ቆሮ. 15:4-8) ኢየሱስ ባልተጠበቀ መልኩ ለጳውሎስ መታየቱ፣ ለጳውሎስ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን የማየት አጋጣሚ ሰጥቶታል፤ እርግጥ ይህ የሆነው “ያለጊዜው” ነው ሊባል ይችላል።

ራሱን ዝቅ ማድረጉ ነበር። አንዳንድ ምሁራን እንደሚገልጹት፣ ጳውሎስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት አገላለጽ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ነው። ጳውሎስ ይህን ቃል የተጠቀመው በዚህ መንፈስ ከሆነ፣ የተሰጠው መብት እንደማይገባው መግለጹ ነበር። እንዲያውም ቀጥሎ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የአምላክን ጉባኤ አሳድድ ስለነበር ከሐዋርያት ሁሉ የማንስና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ። ሆኖም አሁን የሆንኩትን ለመሆን የበቃሁት በአምላክ ጸጋ ነው።”—1 ቆሮ. 15:9, 10

ከዚህ አንጻር ጳውሎስ፣ ኢየሱስ የተገለጠለት በድንገትና አስደንጋጭ በሆነ መልኩ መሆኑን፣ የተለወጠው ባልተጠበቀ ጊዜ መሆኑን ወይም እንዲህ ያለ አስደናቂ ራእይ ለማየት ብቁ አለመሆኑን መግለጹ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ ጳውሎስ ይህን አጋጣሚ ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው በግልጽ ማየት ይቻላል። ይህ አጋጣሚ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን በማያሻማ መንገድ አረጋግጦለታል። በእርግጥም ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ ለሌሎች ሰዎች ሲሰብክ ይህን ያልተጠበቀ ክንውን በተደጋጋሚ መጥቀሱ አያስገርምም።—ሥራ 22:6-11፤ 26:13-18