በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 3

ይሖዋ ስኬታማ እንድትሆኑ ይረዳችኋል

ይሖዋ ስኬታማ እንድትሆኑ ይረዳችኋል

“ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ነበር። የሚሠራውንም ነገር ሁሉ [ያሳካለት ነበር]።”—ዘፍ. 39:2, 3

መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ

ማስተዋወቂያ a

1-2. (ሀ) ፈተናዎች የሚያጋጥሙን መሆኑ የማያስገርመን ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ፈተናዎች የሚያጋጥሙን መሆኑ አያስገርመንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “በብዙ መከራ አልፈን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት” እንዳለብን እንገነዘባለን። (ሥራ 14:22) በተጨማሪም የሚያጋጥሙን አንዳንዶቹ ችግሮች ሙሉ በሙሉ የሚፈቱት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን። በዚያ ጊዜ “ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:4

2 ይሖዋ ምንም ዓይነት ፈተና እንዳይደርስብን አይከላከልልንም። ሆኖም ፈተናዎቹን በጽናት እንድንቋቋማቸው ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን እንዳላቸው ልብ እንበል። በመጀመሪያ እሱና ወንድሞቹ ያጋጠሟቸውን የተለያዩ ፈተናዎች ዘረዘረ። ከዚያም “በወደደን በእሱ አማካኝነት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በድል አድራጊነት እንወጣለን” አለ። (ሮም 8:35-37) ከዚህ እንደምንረዳው፣ የሚደርስብን ፈተና ገና ባያበቃም እንኳ ይሖዋ ስኬታማ እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። ይሖዋ ዮሴፍ ስኬታማ እንዲሆን የረዳው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም እኛን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ሁኔታዎች በድንገት ሲቀየሩ

3. የዮሴፍ ሕይወት በድንገት የተቀየረው እንዴት ነው?

3 ያዕቆብ ልጁን ዮሴፍን በጣም ይወደው ነበር። (ዘፍ. 37:3, 4) ትላልቆቹ የያዕቆብ ልጆች ይህን ሲያዩ በወንድማቸው ቀኑበት። ከዚያም አጋጣሚ ሲያገኙ ዮሴፍን ለምድያማውያን ነጋዴዎች ሸጡት። እነዚህ ነጋዴዎች ደግሞ ዮሴፍን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ወደምትገኘው ወደ ግብፅ ወስደው የፈርዖን የዘቦች አለቃ ለሆነው ለጶጢፋር ሸጡት። በአባቱ የተወደደ ልጅ የነበረው ዮሴፍ ሕይወቱ በቅጽበት ተቀይሮ የአንድ ግብፃዊ ባሪያ ሆነ።—ዘፍ. 39:1

4. እንደ ዮሴፍ ዓይነት ፈተና ሊያጋጥመን የሚችለው እንዴት ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰው መጥፎ ነገር እንደሚያጋጥመው ይናገራል። (መክ. 9:11) አንዳንድ ጊዜ “በሰው ሁሉ ላይ” የሚደርሰው ዓይነት መከራ ያጋጥመናል። (1 ቆሮ. 10:13) ወይም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆናችን ምክንያት ችግር ሊደርስብን ይችላል። ለምሳሌ በእምነታችን ምክንያት ፌዝ፣ ተቃውሞ አልፎ ተርፎም ስደት ሊያጋጥመን ይችላል። (2 ጢሞ. 3:12) ያጋጠመህ ፈተና ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ ስኬታማ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል። ታዲያ ዮሴፍን የረዳው እንዴት ነው?

ዮሴፍ በግብፅ የጶጢፋር ባሪያ እንዲሆን በተሸጠበት ጊዜም ይሖዋ ስኬታማ እንዲሆን ረድቶታል (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)

5. ጶጢፋር፣ ዮሴፍ ስላገኘው ስኬት ምን ተገንዝቧል? (ዘፍጥረት 39:2-6)

5 ዘፍጥረት 39:2-6ን አንብብ። ጶጢፋር፣ ዮሴፍ ጥሩ ችሎታ እንዳለውና ታታሪ ሠራተኛ እንደሆነ አስተዋለ። እንዲህ ሊሆን የቻለበትን ምክንያትም ተገንዝቧል። ጶጢፋር፣ ዮሴፍ ‘የሚሠራውን ነገር ሁሉ ይሖዋ እንደሚያሳካለት አይቷል።’ b ውሎ አድሮ ይህ ግብፃዊ ዮሴፍን የቅርብ አገልጋዩ አደረገው። በተጨማሪም በቤቱ ላይ ሾመው። ውጤቱስ ምን ሆነ? ጶጢፋር በለጸገ።

6. ዮሴፍ ስላለበት ሁኔታ ምን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል?

6 እስቲ ራስህን በዮሴፍ ቦታ ለማስቀመጥ ሞክር። ዮሴፍ ከምንም በላይ የሚፈልገው ምን ነበር? ጶጢፋር ሥራውን እንዲያስተውልና ሹመት እንዲሰጠው ነው? ዮሴፍ በዋነኝነት የሚፈልገው ነፃነት አግኝቶ ወደ አባቱ መመለስ መሆን አለበት። ደግሞም ዮሴፍ በጶጢፋር ቤት ውስጥ ብዙ ሥልጣን ቢኖረውም ይሖዋን ለማያመልክ ጌታ የሚገዛ ባሪያ ነበር። ይሖዋ፣ ጶጢፋር ዮሴፍን ነፃ እንዲያወጣው አላደረገም። የዮሴፍ መከራ ግን በዚህም አላበቃም።

ሁኔታው ሲባባስ

7. የዮሴፍ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ የሄደው እንዴት ነው? (ዘፍጥረት 39:14, 15)

7 ዘፍጥረት ምዕራፍ 39 እንደሚገልጸው የጶጢፋር ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይኗን ጣለችበት፤ አብሯት እንዲተኛ ለማግባባትም በተደጋጋሚ ሞከረች። ሆኖም ዮሴፍ ፈቃደኛ አልሆነም። በመጨረሻም በጣም ስለተበሳጨች ዮሴፍ አስገድዶ ሊደፍራት እንደሞከረ በመግለጽ ከሰሰችው። (ዘፍጥረት 39:14, 15ን አንብብ።) ጶጢፋር ይህን ሲሰማ ዮሴፍን ወደ እስር ቤት ጣለው፤ ዮሴፍም ለተወሰኑ ዓመታት በእስር ቆየ። (ዘፍ. 39:19, 20) እስር ቤቱ ምን ዓይነት ነበር? ዮሴፍ እስር ቤቱን ለመግለጽ የተጠቀመበት የዕብራይስጥ ቃል “የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል፤ ይህም እስር ቤቱ ጨለማ እንደሆነና ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ እንደነበር ይጠቁማል። (ዘፍ. 40:15 ግርጌ) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዮሴፍ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እግሮቹ በእግር ብረት እንደታሰሩና አንገቱም ብረት ውስጥ እንደገባ ይገልጻል። (መዝ. 105:17, 18) የዮሴፍ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ሄዶ ነበር። የጌታውን አመኔታ ያተረፈ ባሪያ የነበረው ዮሴፍ አሁን ደግሞ እስረኛ ሆነ።

8. ያጋጠመን ችግር ቢባባስም ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

8 ያለህበትን አስጨናቂ ሁኔታ አስመልክቶ ልባዊ ጸሎት ብታቀርብም እንኳ ሁኔታው ተባብሶ ያውቃል? ይህ ሊያጋጥም ይችላል። የምንኖረው በሰይጣን ዓለም ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ ፈተናዎች እንዳይደርሱብን አይከላከልልንም። (1 ዮሐ. 5:19) ያም ቢሆን ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ ይሖዋ የሚያጋጥመንን መከራ በሚገባ ያውቃል፤ እንዲሁም ያስብልናል። (ማቴ. 10:29-31፤ 1 ጴጥ. 5:6, 7) በተጨማሪም “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” የሚል ቃል ገብቶልናል። (ዕብ. 13:5) ያለንበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ቢመስልም እንኳ ይሖዋ ያጋጠመንን ፈተና በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። ዮሴፍን በዚህ መልኩ የረዳው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ዮሴፍ እስር ቤት ሆኖ በሌሎቹ እስረኞች ላይ ኃላፊ ተደርጎ በተሾመበት ጊዜም ይሖዋ አብሮት ነበር (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)

9. ዮሴፍ እስር ቤት በነበረበት ወቅት ይሖዋ አብሮት እንደነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ዘፍጥረት 39:21-23)

9 ዘፍጥረት 39:21-23ን አንብብ። ዮሴፍ ታስሮ እየማቀቀ በነበረበት ጊዜም ይሖዋ ስኬታማ እንዲሆን ረድቶታል። እንዴት? የጶጢፋርን አመኔታ እንዳተረፈው ሁሉ ውሎ አድሮ የእስር ቤቱን አለቃ አመኔታና አክብሮት አተረፈ። ብዙም ሳይቆይ የእስር ቤቱ አለቃ በሌሎቹ እስረኞች ላይ ኃላፊ አድርጎ ሾመው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የእስር ቤቱ አለቃ በዮሴፍ ኃላፊነት ሥር ስላለው ስለ ማንኛውም ነገር ምንም አይጨነቅም ነበር” ይላል። አሁን ዮሴፍ አእምሮውን የሚይዝለት ፍሬያማ ሥራ አገኘ። ይህ ያልተጠበቀ ለውጥ ነው! የአንድን ባለሥልጣን ሚስት አስገድዶ በመድፈር ሙከራ የተከሰሰ እስረኛ እንዲህ ያለ ሹመት ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? መልሱ ግልጽ ነው። ዘፍጥረት 39:23 እንደሚለው ‘ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ የሚያደርገውንም ነገር ሁሉ ይሖዋ ያሳካለት ነበር።’

10. ዮሴፍ ሁሉም ነገር እንደተሳካለት ተሰምቶት ነበር? አብራራ።

10 እስቲ አሁንም ራስህን በዮሴፍ ቦታ ለማስቀመጥ ሞክር። ዮሴፍ በሐሰት ተከሶ ከታሰረ በኋላ ሁሉም ነገር እንደተሳካለት የሚሰማው ይመስልሃል? ዮሴፍ ከምንም ነገር በላይ የሚፈልገው ምንድን ነው? የእስር ቤቱን አለቃ ሞገስ ማግኘት ነው? ዮሴፍ በዋነኝነት የሚፈልገው ከተወነጀለበት ክስ ነፃ መሆንና ከእስር መለቀቅ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። እንዲያውም ሊፈታ የተቃረበን አንድ እስረኛ ስለ እሱ ለፈርዖን በመንገር ከዚያ አስከፊ እስር ቤት እንዲያስወጣው ጠይቆታል። (ዘፍ. 40:14) ሆኖም ሰውየው ወዲያውኑ ፈርዖንን አላናገረለትም። በመሆኑም ዮሴፍ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በእስር ቆየ። (ዘፍ. 40:23፤ 41:1, 14) ያም ቢሆን ይሖዋ ዮሴፍን ስኬታማ ማድረጉን ቀጥሏል። እንዴት?

11. ይሖዋ ለዮሴፍ ምን ልዩ ችሎታ ሰጠው? ይህስ የይሖዋን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ምን ሚና ተጫውቷል?

11 ዮሴፍ እስር ቤት በነበረበት ወቅት ይሖዋ የግብፅ ንጉሥ ሁለት አስጨናቂ ሕልሞችን እንዲያይ አደረገ። ፈርዖን የሕልሞቹን ትርጉም ለማወቅ በጣም ፈለገ። ፈርዖን፣ ዮሴፍ ሕልም የመተርጎም ችሎታ እንዳለው ሲሰማ ሰው ልኮ አስጠራው። በይሖዋ እርዳታ ዮሴፍ ሕልሞቹን ፈታ፤ እንዲሁም ጠቃሚ ምክር በመስጠት ፈርዖንን አስደመመው። ፈርዖን፣ ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር እንዳለ ስለተገነዘበ የምግብ አቅርቦቱን እንዲቆጣጠር በመላው የግብፅ ምድር ላይ አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመው። (ዘፍ. 41:38, 41-44) ከጊዜ በኋላ ከባድ ረሃብ ተከሰተ፤ ረሃቡ የተከሰተው በግብፅ ብቻ ሳይሆን የዮሴፍ ቤተሰቦች በሚኖሩበት በከነአንም ጭምር ነበር። አሁን ዮሴፍ የቤተሰቡን ሕይወት መታደግ እንዲሁም መሲሑ የሚመጣበትን የትውልድ መስመር ጠብቆ ማቆየት ቻለ።

12. ይሖዋ ዮሴፍን ስኬታማ ያደረገው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

12 በዮሴፍ ሕይወት ውስጥ የተከሰቱትን ያልተጠበቁ ክንውኖች እስቲ መለስ ብለህ አስብ። ጶጢፋር፣ ተራ ባሪያ የሆነውን ዮሴፍን ልብ ብሎ እንዲመለከተው ያደረገው ማን ነው? የእስር ቤቱ አለቃ፣ ምስኪን እስረኛ ለሆነው ለዮሴፍ ሞገስ እንዲያሳየው ያደረገው ማን ነው? ለፈርዖን የሚያስጨንቁ ሕልሞችን ያሳየው እንዲሁም ለዮሴፍ ሕልሞችን የመፍታት ችሎታ የሰጠው ማን ነው? ዮሴፍ በግብፅ የምግብ አቅርቦት ላይ ኃላፊ ሆኖ እንዲሾም ያደረገው ማን ነው? (ዘፍ. 45:5) ዮሴፍ ያደረገውን ነገር ሁሉ ያሳካለት ይሖዋ እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል። በእርግጥም ይሖዋ የዮሴፍ ወንድሞች በጭካኔ የሸረቡትን ሴራ ተጠቅሞ በስተ መጨረሻ ዓላማውን ማስፈጸም ችሏል።

ይሖዋ አንተንም ስኬታማ ያደርግሃል

13. ይሖዋ በሕይወታችን በሚያጋጥሙን ነገሮች ሁሉ ጣልቃ ይገባል? አብራራ።

13 ከዮሴፍ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ በሕይወታችን በሚያጋጥሙን ነገሮች ሁሉ ላይ ጣልቃ ይገባል? የሚያጋጥመንን እያንዳንዱን ነገር በመቆጣጠር፣ የሚደርሱብን ነገሮች ሁሉ ለበጎ እንዲሆኑ ያደርጋል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም። (መክ. 8:9፤ 9:11) ሆኖም የምናውቀው አንድ ነገር አለ፦ ፈተና ሲያጋጥመን ይሖዋ ሁኔታችንን ይረዳልናል፤ እንዲሁም እርዳታ ለማግኘት የምናሰማውን ጩኸት ያዳምጣል። (መዝ. 34:15፤ 55:22፤ ኢሳ. 59:1) ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ እንድንወጣ ይረዳናል። እንዴት?

14. ይሖዋ ችግሮች ሲያጋጥሙን የሚረዳን እንዴት ነው?

14 ይሖዋ እኛን የሚረዳበት አንዱ መንገድ ማጽናኛና ማበረታቻ በመስጠት ነው፤ በአብዛኛው ይህን የሚያደርገው ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ነው። (2 ቆሮ. 1:3, 4) በቱርክሜኒስታን የሚኖረው ኤዚዝ ይህ እውነት መሆኑን ተመልክቷል። ኤዚዝ በእምነቱ ምክንያት የሁለት ዓመት እስራት ተፈርዶበት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ለፍርድ በቀረብኩበት ቀን አንድ ወንድም ኢሳይያስ 30:15⁠ን አሳየኝ፤ ጥቅሱ ‘ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ’ ይላል። ይህ ጥቅስ ሳልረበሽ እንድኖርና በማንኛውም ጉዳይ በይሖዋ እንድታመን ረድቶኛል። በዚህ ጥቅስ ላይ ማሰላሰሌ በእስር በቆየሁበት ጊዜ ሁሉ ረድቶኛል።” አንተስ ይሖዋ ልክ በሚያስፈልግህ ወቅት ማጽናኛና ማበረታቻ በመስጠት የረዳህን ጊዜ ታስታውሳለህ?

15-16. ከቶሪ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?

15 ብዙውን ጊዜ፣ ይሖዋ አንድን ችግር ለመቋቋም እንዴት እንደረዳን የምናስተውለው ችግሩ ካለፈ በኋላ ነው። ቶሪ የተባለች እህት ይህ ሐሳብ እውነት መሆኑን በሕይወቷ ተመልክታለች። ልጇ ሜሰን ለስድስት ዓመታት ከካንሰር ጋር ሲታገል ከቆየ በኋላ ሞተ። በዚህ ጊዜ ቶሪ በከፍተኛ ሐዘን ተዋጠች። እንዲህ ብላለች፦ “መቼም አንዲት እናት ከዚህ የከፋ መከራ ሊደርስባት አይችልም። ልጄ ሲሠቃይ ከማይ እኔ ራሴ ብሠቃይ እመርጣለሁ፤ ሌሎች ወላጆችም በዚህ እንደሚስማሙ እርግጠኛ ነኝ።”

16 ቶሪ የደረሰባት መከራ በጣም ከባድ ቢሆንም ይሖዋ መከራውን እንድትቋቋም እንዴት እንደረዳት ከጊዜ በኋላ ማስተዋል ችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “መለስ ብዬ ሳስበው፣ ልጄ በታመመበት ጊዜ ሁሉ የይሖዋን እጅ እያየን ነበር። ለምሳሌ ሜሰን በጣም በመታመሙ ማንም እንዲጠይቀው በማይፈቀድበት ጊዜም ጭምር ወንድሞችና እህቶች ለሁለት ሰዓት በመኪና ተጉዘው ወደ ሆስፒታሉ ይመጡ ነበር። ምንጊዜም በሆስፒታሉ የእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ እኛን ለመርዳት የተዘጋጀ ሰው አይጠፋም። የሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮችም ተሟልተውልናል። ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ በነበረበት ጊዜም እንኳ የሚያስፈልገንን ነገር አላጣንም።” ይሖዋ ለቶሪም ሆነ ለሜሰን ሁኔታውን በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ሰጥቷቸዋል።—“ ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ሰጥቶናል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በረከቶቻችሁን አስታውሱ

17-18. በፈተና ውስጥ ስንሆን ይሖዋ እየደገፈን እንዳለ ለማስተዋል የሚረዳን ምንድን ነው? (መዝ. 40:5)

17 መዝሙር 40:5ን አንብብ። ተራራ የሚወጣ ሰው ዋነኛ ግቡ የተራራው ጫፍ ላይ መድረስ ነው። ይሁንና በመንገዱ ላይ ቆም እያለ የአካባቢውን መልክዓ ምድር ማድነቅ የሚችልበት ብዙ አጋጣሚ ይኖረዋል። አንተም በተመሳሳይ በመከራ ውስጥ ብትሆንም እንኳ ይሖዋ ስኬታማ እንድትሆን እየረዳህ ያለው እንዴት እንደሆነ አልፎ አልፎ ቆም እያልክ አስብ። በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ዛሬ የይሖዋን በረከት ያየሁት በምን መንገድ ነው? የደረሰብኝ ፈተና ገና ባያበቃም ይሖዋ ለመጽናት እየረዳኝ ያለው እንዴት ነው?’ ይሖዋ ስኬታማ እንድትሆን ለመርዳት ያደረገልህን ቢያንስ አንድ ነገር ለማስተዋል ሞክር።

18 እርግጥ ፈተናው እንዲያበቃ እየጸለይክ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ማድረግህ ምንም ስህተት የለውም። (ፊልጵ. 4:6) ሆኖም አሁን ያሉህን በረከቶችም ማስተዋል ይኖርብሃል። ደግሞም ይሖዋ ቃል የገባልን ብርታት እንደሚሰጠንና ለመጽናት እንደሚረዳን ነው። ስለዚህ ይሖዋ እያደረገልህ ላለው ድጋፍ ምንጊዜም አመስጋኝ ሁን። እንዲህ ካደረግክ፣ በፈተና ውስጥ ብትሆንም እንኳ ይሖዋ እንደ ዮሴፍ ስኬታማ እንድትሆን እየረዳህ ያለው እንዴት እንደሆነ ማየት ትችላለህ።—ዘፍ. 41:51, 52

መዝሙር 32 ከይሖዋ ጎን ቁም!

a ከባድ መከራ ሲደርስብን ‘ስኬታማ’ እንደሆንን ላይሰማን ይችላል። ስኬታማ ልንባል የምንችለው መከራው ካለፈ በኋላ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ይሁንና ዮሴፍ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠሙት ነገሮች ወሳኝ ትምህርት ይሰጡናል፤ በመከራ ውስጥ ብንሆንም እንኳ ይሖዋ ስኬታማ እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። ይሖዋ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

b መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ ባሪያ ሆኖ ከተሸጠበት ጊዜ አንስቶ በጶጢፋር ቤት ላይ እስከተሾመበት ጊዜ ያሉትን ክንውኖች በጥቂት ቁጥሮች ውስጥ ይገልጻቸዋል። ሆኖም እነዚህ ክንውኖች የተፈጸሙት በዓመታት ውስጥ ሊሆን ይችላል።