በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 8

“የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ!”

“የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ!”

“የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ!”—1 ጴጥ. 5:8

መዝሙር 144 ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ያተኩር!

ማስተዋወቂያ a

1. ኢየሱስ መጨረሻው የሚመጣበትን ጊዜ አስመልክቶ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ነገራቸው? ምን ማስጠንቀቂያስ ሰጣቸው?

 ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አራቱ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ [ምልክት] ምንድን ነው?” በማለት ጠይቀውት ነበር። (ማቴ. 24:3) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት የአይሁድ ሥርዓት የሚያበቃበትን ጊዜ ማወቅ ስለፈለጉ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ጥያቄያቸውን ሲመልስ ስለ አይሁድ ሥርዓት መጨረሻ ብቻ ሳይሆን እኛ ስለምንኖርበት ‘ስለዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ጭምር ተናገረ። ኢየሱስ መጨረሻው የሚመጣበትን ጊዜ አስመልክቶ እንዲህ አለ፦ “ስለዚያ ቀን ወይም ሰዓት ከአብ በቀር በሰማይ ያሉ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም።” ከዚያም ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ‘ዘወትር ነቅተው መጠበቅ’ እንዳለባቸው አሳሰበ።—ማር. 13:32-37

2. በአይሁድ ሥርዓት ሥር ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ነቅተው መጠበቅ ያስፈለጋቸው ለምን ነበር?

2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የሆኑ ክርስቲያኖች ነቅተው መጠበቅ ነበረባቸው፤ ይህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነበር። ኢየሱስ ተከታዮቹ የአይሁድ ሥርዓት የሚያበቃበት ጊዜ መቅረቡን ለማወቅ የትኞቹን ነገሮች ነቅተው መከታተል እንዳለባቸው ነግሯቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ።” ክርስቲያኖች ልክ ይህን ሲያዩ የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ በመስማት “ወደ ተራሮች መሸሽ” ነበረባቸው። (ሉቃስ 21:20, 21) ለዚህ ማስጠንቀቂያ ትኩረት የሰጡ ሰዎች ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ባጠፉበት ጊዜ ሕይወታቸውን ማትረፍ ችለዋል።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ዛሬ የምንኖረው የዚህ ክፉ ሥርዓት ማብቂያ በተቃረበበት ጊዜ ላይ ነው። ስለዚህ እኛም የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅና ንቁ ሆነን መኖር ያስፈልገናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ በዓለም ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች በቅርበት ስንከታተል ሚዛናችንን መጠበቅ፣ ለራሳችን ትኩረት መስጠትና ቀሪውን ጊዜ በተሻለ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

የዓለምን ክስተቶች ስትከታተሉ ሚዛናዊ ሁኑ

4. በዓለማችን ላይ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ መከታተል ያለብን ለምንድን ነው?

4 በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ የምንከታተልበት በቂ ምክንያት አለን። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የሰይጣን ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ መቃረቡን ለማወቅ የሚረዱንን ዝርዝር ክንውኖች ነግሮናል። (ማቴ. 24:3-14) በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ እምነታችን ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለግን የትንቢቶችን ፍጻሜ በትኩረት እንድንከታተል አበረታቶናል። (2 ጴጥ. 1:19-21) የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍም የሚጀምረው በሚከተሉት ቃላት ነው፦ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና እሱ የገለጠው ራእይ ይህ ነው።” (ራእይ 1:1) ስለዚህ በዓለማችን ላይ እየተከናወኑ ስላሉት ነገሮች እንዲሁም እነዚህ ክንውኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እንዲያገኝ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን። ከዚህም በላይ ስለ እነዚህ ክንውኖች ከሌሎች ጋር መወያየት ሊያስደስተን ይችላል።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ስንጨዋወት ምን ከማድረግ ልንቆጠብ ይገባል? ምን ማድረግስ ይኖርብናል? (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት) b

5. ምን ከማድረግ ልንቆጠብ ይገባል? ምን ማድረግስ ይኖርብናል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

5 ሆኖም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ከሌሎች ጋር ስንወያይ ግምታዊ ሐሳቦችን ከመሰንዘር መቆጠብ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም በጉባኤ ውስጥ ክፍፍል እንዲፈጠር የሚያደርግ ምንም ነገር መናገር አንፈልግም። ለምሳሌ ያህል፣ የዓለም መሪዎች እንዴት አንድን ግጭት ፈተው ሰላምና ደህንነት እንደሚያሰፍኑ ሲያወሩ ልንሰማ እንችላለን። እንዲህ ያሉት ንግግሮች በ1 ተሰሎንቄ 5:3 ላይ ያለው ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ ግምታዊ ሐሳብ ከመሰንዘር ይልቅ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የወጣውን ወቅታዊ መረጃ ልንከታተል ይገባል። የይሖዋ ድርጅት ባቀረበው መረጃ ላይ ተመሥርተን ከሌሎች ጋር የምንወያይ ከሆነ ጉባኤው ‘በአስተሳሰብ አንድነት እንዲኖረው’ አስተዋጽኦ እናደርጋለን።—1 ቆሮ. 1:10፤ 4:6

6. ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:11-13 ላይ ካለው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:11-13ን አንብብ። ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠው ምክር የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ስንመረምር ሚዛናዊ እንድንሆን ይረዳናል። ጴጥሮስ ‘የይሖዋን ቀን መምጣት በአእምሯችን አቅርበን እንድንመለከት’ አሳስቦናል። ለምን? እንዲህ የምናደርገው ይሖዋ አርማጌዶንን የሚያመጣበትን “ቀንና ሰዓት” ለማስላት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የቀረንን ጊዜ ‘ቅዱስ ሥነ ምግባር ለመከተልና ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮች ለመፈጸም’ ልንጠቀምበት ስለምንፈልግ ነው። (ማቴ. 24:36፤ ሉቃስ 12:40) በሌላ አባባል ንጹሕ ምግባር ይዘን መቀጠልና ይሖዋን ለማገልገል የምናደርገው ጥረት ለእሱ ያለንን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን። እንዲህ ለማድረግ ደግሞ ለራሳችን ምንጊዜም ትኩረት መስጠት ያስፈልገናል።

ለራሳችን ትኩረት መስጠት ሲባል ምን ማለት ነው?

7. ለራሳችን ትኩረት እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ሉቃስ 21:34)

7 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በዓለም ላይ ለሚከናወኑ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ትኩረት እንዲሰጡ ነግሯቸዋል። በሉቃስ 21:34 ላይ የሚገኘው ማስጠንቀቂያ ይህን ነጥብ ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ጥቅሱን አንብብ።) እዚያ ላይ ኢየሱስ “ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” በማለት ተናግሯል። ለራሱ የሚጠነቀቅ ወይም ትኩረት የሚሰጥ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ሊያበላሹበት የሚችሉ አደጋዎችን በንቃት ይከታተላል፤ ከእነዚህ አደጋዎች ለመራቅም አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል። እንዲህ በማድረግ ከአምላክ ፍቅር ሳይወጣ መኖር ይችላል።—ምሳሌ 22:3፤ ይሁዳ 20, 21

8. ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷል?

8 ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቲያኖችን ለራሳቸው ትኩረት እንዲሰጡ አሳስቧቸዋል። ለምሳሌ በኤፌሶን ያሉትን ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ።” (ኤፌ. 5:15, 16) ሰይጣን በመንፈሳዊነታችን ላይ የማያባራ ጥቃት ይሰነዝራል፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰነዘርብንን ማንኛውንም ጥቃት መቋቋም እንድንችል “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ” የሚል ምክር የሚሰጠን ለዚህ ነው።—ኤፌ. 5:17

9. ይሖዋ ለእኛ ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው?

9 መጽሐፍ ቅዱስ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ሊያበላሹ የሚችሉ አደጋዎችን በሙሉ በዝርዝር አይጠቅስም። ብዙ ጊዜ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በቀጥታ ካልተጠቀሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልገናል። ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ‘የይሖዋን ፈቃድ’ ማስተዋል ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው የአምላክን ቃል አዘውትረን በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ነው። የይሖዋን ፈቃድ ይበልጥ በተረዳንና ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ባዳበርን መጠን ‘እንደ ጥበበኛ ሰዎች መመላለስ’ ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል፤ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚገልጽ ቀጥተኛ ሕግ ባይኖርም እንኳ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እናደርጋለን። (1 ቆሮ. 2:14-16) አንዳንድ አደጋዎችን በቀላሉ መለየት ይቻላል፤ አንዳንዶቹ ግን ስውር ናቸው።

10. ልንርቃቸው የሚገቡ አንዳንድ አደጋዎች የትኞቹ ናቸው?

10 ልንርቃቸው ከሚገቡ አደጋዎች መካከል ማሽኮርመም፣ ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት እንዲሁም ጎጂ ንግግር ይገኙበታል፤ ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን መዝናኛዎች፣ የብልግና ምስሎችንና የመሳሰሉትን ማየትም በዚህ ውስጥ ይካተታል። (መዝ. 101:3) ጠላታችን ዲያብሎስ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማበላሸት የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች በንቃት ይከታተላል። (1 ጴጥ. 5:8) ንቁ ካልሆንን ሰይጣን በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ የምቀኝነት፣ የውሸት፣ የስግብግብነት፣ የጥላቻ፣ የኩራትና የምሬት ዘር ሊዘራ ይችላል። (ገላ. 5:19-21) መጀመሪያ ላይ እነዚህ ስሜቶች ያን ያህል አደገኛ እንዳልሆኑ ሊሰማን ይችላል። ከሥራቸው ነቅለን ለመጣል አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰድን ግን እንደ መርዛማ ተክል ማደጋቸውን ሊቀጥሉና ችግር ላይ ሊጥሉን ይችላሉ።—ያዕ. 1:14, 15

11. ልንርቃቸው ከሚገቡ ስውር አደጋዎች መካከል አንዱ ምንድን ነው? አደገኛ የሆነውስ ለምንድን ነው?

11 ስውር ከሆኑት አደጋዎች መካከል አንዱ መጥፎ ባልንጀርነት ነው። እስቲ ይህን ሁኔታ ለማሰብ ሞክሩ። የምትሠሩት የይሖዋ ምሥክር ካልሆነ ሰው ጋር ነው እንበል። የሥራ ባልደረባችሁ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት እንዲኖረው ስለምትፈልጉ ደግነት ታሳዩታላችሁ። አልፎ አልፎም ከዚህ ሰው ጋር ምሳ ትበላላችሁ። ብዙም ሳይቆይ አዘውትራችሁ ምሳ መብላት ትጀምራላችሁ። አንዳንድ ጊዜ ይህ ሰው በጭውውታችሁ መሃል ሥነ ምግባር የጎደላቸው ነገሮች ያወራል፤ መጀመሪያ ላይ እንዲህ ያሉትን ወሬዎች ችላ ብላችሁ ለማለፍ ትሞክራላችሁ። በጊዜ ሂደት ግን እንዲህ ያለውን ወሬ ከመልመዳችሁ የተነሳ ቅር መሰኘት ታቆማላችሁ። ከዚያም አንድ ቀን የሥራ ባልደረባችሁ ከሥራ በኋላ አብራችሁት እንድትጠጡ ይጋብዛችኋል፤ እናንተም ግብዣውን ትቀበላላችሁ። ቀስ በቀስ የሥራ ባልደረባችሁን አመለካከት መጋራት ትጀምራላችሁ። ታዲያ ከዚህ በኋላ እሱ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ማድረግ ለመጀመር ብዙ ጊዜ የሚወስድባችሁ ይመስላችኋል? እርግጥ ነው፣ ለሁሉም ሰዎች ደግነትና አክብሮት ማሳየት እንፈልጋለን፤ ሆኖም አብረናቸው ጊዜ የምናሳልፋቸው ሰዎች ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን እንደሚችሉ መዘንጋት አይኖርብንም። (1 ቆሮ. 15:33) ኢየሱስ እንዳሳሰበን ለራሳችን የምንጠነቀቅ ወይም ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ በይሖዋ መሥፈርቶች ከማይመሩ ሰዎች ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ ከመፍጠር እንርቃለን። (2 ቆሮ. 6:15) አደጋውን አስቀድመን አይተን ከዚያ እንሸሻለን።

ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት

12. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሥርዓቱን መደምደሚያ የተጠባበቁት የትኛውን ሥራ እያከናወኑ ነበር?

12 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሥርዓቱን መደምደሚያ የሚጠባበቁት እጃቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ አልነበረም። ኢየሱስ የሚሠሩት ሥራ ሰጥቷቸዋል። ምሥራቹን “በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ” እንዲሰብኩ አዟቸዋል። (ሥራ 1:6-8) የኢየሱስ ተከታዮች የተሰጣቸው ሥራ በጣም ሰፊ ነው! በዚህ ሥራ ራሳቸውን በማስጠመድ ጊዜያቸውን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቅመውበታል።

13. ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ መጠቀም ያለብን ለምንድን ነው? (ቆላስይስ 4:5)

13 ቆላስይስ 4:5ን አንብብ። ለራሳችን ትኩረት የምንሰጥበት አንዱ አቅጣጫ የጊዜ አጠቃቀማችንን ቆም ብለን ማሰብ ነው። ማናችንም ብንሆን “ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሊያጋጥሙን ይችላሉ። (መክ. 9:11) ሕይወታችን ድንገት ሊቀጭ ይችላል።

ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 14-15⁠ን ተመልከት)

14-15. ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? (ዕብራውያን 6:11, 12) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 የይሖዋን ፈቃድ በማድረግና ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት በማጠናከር ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። (ዮሐ. 14:21) “ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ . . . ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል። (1 ቆሮ. 15:58) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ መጨረሻው ማለትም የሕይወታችን ወይም የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ መቼም ይምጣ መቼ ምንም የሚቆጨን ነገር አይኖርም።—ማቴ. 24:13፤ ሮም 14:8

15 ኢየሱስ በመላው ምድር ላይ ስለ አምላክ መንግሥት ለሚሰብኩ ደቀ መዛሙርቱ መመሪያ መስጠቱን ቀጥሏል። እሱ የበኩሉን አድርጓል። በይሖዋ ድርጅት አማካኝነት እንዴት እንደምንሰብክ ያሠለጥነናል፤ እንዲሁም ምሥራቹን ለማስፋፋት የሚያስፈልጉንን መሣሪያዎች ያቀርብልናል። (ማቴ. 28:18-20) እኛም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ትጉ በመሆን እንዲሁም ይሖዋ ይህን ሥርዓት የሚያጠፋበትን ጊዜ በንቃት በመጠባበቅ የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። በዕብራውያን 6:11, 12 ላይ በሚገኘው ምክር መሠረት ተስፋችንን “እስከ መጨረሻው” አጥብቀን እንይዛለን።—ጥቅሱን አንብብ።

16. ቁርጥ ውሳኔያችን ምንድን ነው?

16 ይሖዋ የሰይጣንን ሥርዓት የሚያጠፋበትን ቀንና ሰዓት ወስኗል። ያ ጊዜ ሲመጣ ይሖዋ በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ ያደረጋቸው ትንቢቶች በሙሉ ያለአንዳች ጥርጥር እንዲፈጸሙ ያደርጋል። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ የሥርዓቱ ፍጻሜ እንደዘገየ ሊሰማን ይችላል። ሆኖም የይሖዋ ቀን “አይዘገይም!” (ዕን. 2:3) እንግዲያው ‘የሚያድነንን አምላክ በትዕግሥት’ እንዲሁም ‘በጉጉት ለመጠባበቅ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ሚክ. 7:7

መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ

a በዚህ ርዕስ ውስጥ መንፈሳዊ ሚዛናችንን መጠበቅና ንቁ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ለራሳችን ትኩረት መስጠትና ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ (ከላይ) አንድ ባልና ሚስት ዜና እያዩ ነው። በኋላ ላይ የጉባኤ ስብሰባ ሄደው ስብሰባው ካበቃ በኋላ ዜና ላይ ያዩት ነገር ስላለው ትርጉም ለሌሎች በስሜት ይናገራሉ። (ከታች) አንድ ባልና ሚስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን አረዳድ በተመለከተ ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት የበላይ አካሉን ሪፖርት እያዩ ነው። በኋላም ታማኙ ባሪያ ያዘጋጃቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ለሌሎች ሲያበረክቱ።