በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 9

ከአምላክ ላገኘኸው የሕይወት ስጦታ አድናቆት ይኑርህ

ከአምላክ ላገኘኸው የሕይወት ስጦታ አድናቆት ይኑርህ

“ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።”—ሥራ 17:28

መዝሙር 141 ሕይወት ተአምር ነው

ማስተዋወቂያ a

1. ሕይወታችን በይሖዋ ዘንድ ምን ያህል ውድ ነው?

 አንድ ወዳጃችሁ በጣም የቆየ ሆኖም ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ሥዕል ሰጣችሁ እንበል። ሥዕሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ቀለሙ ለቋል፣ ቆሻሻ ነክቶታል፣ የተወሰነ መሰነጣጠቅም አለው። ያም ሆኖ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ያወጣል። ይህን ሥዕል ከፍ አድርጋችሁ እንደምትመለከቱትና በጥንቃቄ እንደምትይዙት የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ይሖዋ ውድ የሆነ ስጦታ ሰጥቶናል፤ ይህም የሕይወት ስጦታ ነው። እንዲያውም ይሖዋ ልጁን ለእኛ ቤዛ እንዲሆን በመስጠት ሕይወታችንን ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው አሳይቷል።—ዮሐ. 3:16

2. ሁለተኛ ቆሮንቶስ 7:1 ላይ በተገለጸው መሠረት ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል?

2 የሕይወት ምንጭ ይሖዋ ነው። (መዝ. 36:9) ሐዋርያው ጳውሎስም “ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው” በማለት ይህን እውነታ አረጋግጧል። (ሥራ 17:25, 28) ከዚህ አንጻር ሕይወት የአምላክ ስጦታ ነው ማለታችን ተገቢ ነው። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ በሕይወት ለመቀጠል የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሰጥቶናል። (ሥራ 14:15-17) ሆኖም ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሕይወታችንን አይጠብቅልንም። ከዚህ ይልቅ በተቻለን መጠን አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነታችንን እንድንንከባከብ ይጠብቅብናል። (2 ቆሮንቶስ 7:1ን አንብብ።) ጤንነታችንን ለመንከባከብና ሕይወታችንን ከአደጋ ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

ስጦታ ለሆነው ሕይወት አድናቆት ይኑራችሁ

3. ጤንነታችንን የምንንከባከብበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

3 ጤንነታችንን የምንንከባከብበት አንዱ ምክንያት በሙሉ አቅማችን ይሖዋን ማገልገል ስለምንፈልግ ነው። (ማር. 12:30) ሰውነታችንን “ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት” አድርገን ማቅረብ እንፈልጋለን፤ ስለዚህ ጤንነታችንን እንደሚጎዱ ከምናውቃቸው ነገሮች እንርቃለን። (ሮም 12:1) እርግጥ ጤንነታችንን ለመንከባከብ የፈለግነውን ያህል ጥረት ብናደርግም ሙሉ ጤንነት ላይኖረን ይችላል። ሆኖም በስጦታ ላገኘነው ሕይወት አድናቆት እንዳለን ለሰማዩ አባታችን ማሳየት እንፈልጋለን፤ ስለዚህ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን።

4. ንጉሥ ዳዊት ምን ለማድረግ ቆርጦ ነበር?

4 ንጉሥ ዳዊት ከአምላክ በስጦታ ያገኘውን ሕይወት ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “መሞቴና ወደ ጉድጓድ መውረዴ ምን የሚያስገኘው ጥቅም አለ? አፈር ያወድስሃል? የአንተንስ ታማኝነት ይናገራል?” (መዝ. 30:9) ዳዊት እነዚህን ቃላት የጻፈው በሕይወቱ ማብቂያ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም ይሖዋን ለማወደስ ሲል እስከቻለው ድረስ ጤናማ ሆኖ በሕይወት ለመቆየት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። የሁላችንም ልባዊ ፍላጎት ይህ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።

5. የቱንም ያህል ዕድሜያችን ቢገፋ ወይም ብንታመም ምን ማድረግ እንችላለን?

5 ሕመምና እርጅና በአንድ ወቅት እናከናውናቸው የነበሩ በርካታ ነገሮችን እንዳናከናውን ሊያግዱን ይችላሉ። በዚህም የተነሳ ቅስማችን ሊሰበርና ልናዝን እንችላለን። ሆኖም ተስፋ ቆርጠን ጤንነታችንን የመንከባከቡን ጉዳይ ፈጽሞ ችላ ልንል አይገባም። ለምን? ምክንያቱም ምንም ያህል ዕድሜያችን ቢገፋ ወይም ጤንነታችን ቢቃወስ ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን ማወደስ እንችላለን። ፍጹማን ባንሆንም አምላካችን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! (ማቴ. 10:29-31) አምላካችን ብንሞት እንኳ መልሶ ሊያስነሳን ይጓጓል። (ኢዮብ 14:14, 15) በሕይወት እስካለን ድረስ ጤንነታችንን መንከባከብና ሕይወታችንን ከአደጋ መጠበቅ እንፈልጋለን።

ጎጂ ልማዶችን አስወግዱ

6. ይሖዋ ከምግብና ከመጠጥ ልማዳችን ጋር በተያያዘ ምን ይጠብቅብናል?

6 ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ጤንነትን ለመንከባከብ ወይም የአመጋገብ መመሪያ ለመስጠት የተጻፈ መጽሐፍ ባይሆንም ይሖዋ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ ይረዳናል። ለምሳሌ ይሖዋ ‘ጎጂ ነገሮችን ከሰውነታችን እንድናርቅ’ አሳስቦናል። (መክ. 11:10) መጽሐፍ ቅዱስ ከልክ በላይ እንደ መብላትና እንደ መጠጣት ያሉ ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ልማዶችን ያወግዛል። (ምሳሌ 23:20) ይሖዋ የምንበላውንና የምንጠጣውን ነገር መጠን ስንወስን ራሳችንን እንድንገዛ ይጠብቅብናል።—1 ቆሮ. 6:12፤ 9:25

7. ምሳሌ 2:11 ላይ ያለው ምክር ከጤንነታችን ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?

7 አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ ከፍተኛ አድናቆት እንዳለን የሚያሳዩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የማመዛዘን ችሎታችንን ልንጠቀም ይገባል። (መዝ. 119:99, 100፤ ምሳሌ 2:11ን አንብብ።) ለምሳሌ የምንበላቸውን ምግቦች ስንመርጥ የማመዛዘን ችሎታችንን መጠቀም ያስፈልገናል። አንድ የምንወደው ምግብ እንደሚያሳምመን የምናውቅ ከሆነ ያን ምግብ ከመብላት እንቆጠባለን። በቂ እንቅልፍ ማግኘታችን፣ አዘውትረን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጋችን፣ የግል ንጽሕናችንን መጠበቃችንና ቤታችንን ማጽዳታችንም ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለን ያሳያል።

አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን በንቃት ተከታተሉ

8. መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ከደህንነት ጋር በተያያዘ ስላለው አመለካከት ምን ይጠቁመናል?

8 ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር የሰጠው ሕግ በቤትም ሆነ በሥራ ቦታ ከባድ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የሚረዱ መመሪያዎችን ይዟል። (ዘፀ. 21:28, 29፤ ዘዳ. 22:8) አንድ ሰው የሌላን ሰው ሕይወት ያጠፋው ሳያስበው ቢሆንም ድርጊቱ ከባድ መዘዝ ያስከትልበት ነበር። (ዘዳ. 19:4, 5) አንድ ሰው ሳያስበውም እንኳ በፅንስ ላይ ጉዳት ቢያደርስ ግለሰቡ እንዲቀጣ ሕጉ ያዛል። (ዘፀ. 21:22, 23) ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያሳዩት ይሖዋ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ለማስወገድ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ ይፈልጋል።

በእነዚህ ሁኔታዎች ሥር ለሕይወት አክብሮት እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው? (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)

9. አደጋዎችን ለማስወገድ የትኞቹን ቅድመ ጥንቃቄዎች መውሰድ እንችላለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

9 በቤትም ሆነ በሥራ ቦታ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። ለምሳሌ ስለት ያላቸው ነገሮችን፣ መርዛማ ኬሚካሎችን ወይም መድኃኒቶችን በተገቢው መንገድ እናስወግዳለን፤ በተጨማሪም እንዲህ ያሉትን ነገሮች ልጆች የማይደርሱበት ቦታ እናስቀምጣለን። እሳትን፣ ትኩስ ፈሳሾችንና የተለያዩ መሣሪያዎችን ስንጠቀም ጥንቃቄ እናደርጋለን፤ ደግሞም እነዚህን ነገሮች አደጋ ሊያደርሱ በሚችሉበት ሁኔታ ትተናቸው አንሄድም። በመድኃኒት፣ በመጠጥ ወይም በእንቅልፍ እጦት ምክንያት የማመዛዘን ችሎታችን በተዛባበት ሁኔታ መኪና አንነዳም፤ በተጨማሪም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በእጃችን ይዘን እየነካካን አናሽከረክርም።

አደጋ ሲከሰት

10. ለሕይወት አስጊ የሆነ አደጋ ከመከሰቱ በፊትና በሚከሰትበት ወቅት ምን ማድረግ እንችላለን?

10 አንዳንዴ ለሕይወት አስጊ የሆኑ አደጋዎች እንዳይከሰቱ መከላከል አንችልም። ለምሳሌ እንደ ተፈጥሮ አደጋ፣ ወረርሽኝና ሕዝባዊ ዓመፅ ያሉ ነገሮች ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ናቸው። ሆኖም እንዲህ ያሉ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት የሰዓት እላፊዎችን፣ አካባቢውን ለቀን እንድንወጣ የሚሰጡ መመሪያዎችንና የድንገተኛ ጊዜ ገደቦችን በመታዘዝ የሚደርስብንን አደጋ መቀነስ እንችላለን። (ሮም 13:1, 5-7) ለአንዳንዶቹ አደጋዎች አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል። እንዲህ ካሉት አደጋዎች ጋር በተያያዘ የአካባቢው ባለሥልጣናት አስቀድመን እንድንዘጋጅ በማሰብ የሚሰጡንን ማንኛውንም መመሪያ መከተላችን ተገቢ ነው። ለምሳሌ ውኃ፣ ቶሎ የማይበላሽ ምግብና የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ መስጫ ሣጥን ማዘጋጀታችን ተገቢ ሊሆን ይችላል።

11. በአካባቢያችን ወረርሽኝ ቢከሰት ምን ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን አለብን?

11 በምንኖርበት አካባቢ ወረርሽኝ ቢከሰት ምን ማድረግ ይኖርብናል? እጃችንን እንደ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀታችንን እንደ መጠበቅ፣ ማስክ እንደ ማድረግና የበሽታው ምልክት ከታየብን ተገልለን እንደ መቆየት ያሉ መመሪያዎችን ልንታዘዝ ይገባል። እነዚህን መመሪያዎች ለመታዘዝ ፈጣን መሆናችን አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ ምን ያህል አድናቆት እንዳለን ያሳያል።

12. ምሳሌ 14:15 ላይ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ከሚናፈሱት መረጃዎች ጋር በተያያዘ መራጮች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

12 ድንገተኛ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ወቅት ከወዳጆቻችን፣ ከጎረቤቶቻችንና ከመገናኛ ብዙኃን የተዛቡ መረጃዎችን ልንሰማ እንችላለን። በዚህ ጊዜ “ቃልን ሁሉ” ከማመን ይልቅ መንግሥትና የሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን የተሻለ ተአማኒነት ያለው መረጃ ማዳመጣችን ተገቢ ነው። (ምሳሌ 14:15ን አንብብ።) የበላይ አካሉና ቅርንጫፍ ቢሮዎች የጉባኤ ስብሰባዎችንና የስብከቱን ሥራ በተመለከተ መመሪያ ከመስጠታቸው በፊት ስለ ጉዳዩ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት የቻሉትን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ። (ዕብ. 13:17) እንዲህ ያሉ መመሪያዎችን መታዘዛችን ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ከአደጋ ይጠብቃል። በተጨማሪም ጉባኤው በማኅበረሰቡ ዘንድ ጥሩ ስም እንዲያተርፍ ያስችላል።—1 ጴጥ. 2:12

ከደም ለመራቅ አስቀድማችሁ ተዘጋጁ

13. ከደም ጋር በተያያዘ አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ አድናቆት እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው?

13 የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ደም ቅድስና ባላቸው አመለካከት በስፋት ይታወቃሉ። ድንገተኛ የሕክምና ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜም እንኳ ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆን ይሖዋ ስለ ደም የሰጠውን ሕግ እንደምናከብር እናሳያለን። (ሥራ 15:28, 29) ይህ ሲባል ግን መሞት እንፈልጋለን ማለት አይደለም። እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ ከፍተኛ አድናቆት አለን። ያለደም ጥራት ያለው ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችን ለማግኘት የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን።

14. ከባድ ቀዶ ሕክምና የሚጠይቁ ሁኔታዎችን መቀነስ የምንችለው እንዴት ነው?

14 ቀደም ሲል በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ጤንነትን ለመንከባከብ የሚረዱ ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ ከባድ ቀዶ ሕክምና የሚጠይቁ ሁኔታዎችን መቀነስ እንችላለን። ቀድሞውንም ጤንነታችንን የምንንከባከብ ከሆነ የግድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ቢያጋጥመን እንኳ በቀላሉ ማገገም እንችላለን። በተጨማሪም በቤትም ሆነ በሥራ ቦታ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን በማስወገድ እንዲሁም የትራፊክ ሕጎችን በጥብቅ በመከተል ድንገተኛ ቀዶ ሕክምና የሚጠይቁ ሁኔታዎችን መቀነስ እንችላለን።

በስጦታ ላገኘነው ሕይወት አድናቆት ስላለን የሕክምና መመሪያ ካርድ እንሞላለን እንዲሁም ሁሌም ይዘነው እንንቀሳቀሳለን (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት) c

15. (ሀ) የታደሰ የሕክምና መመሪያ ካርድ መያዛችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ቪዲዮው ላይ እንደተገለጸው ደምን ለሕክምና ከመጠቀም ጋር በተያያዘ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

15 የሕክምና መመሪያ ካርድ መሙላታችንና ሁሌም ይዘነው መንቀሳቀሳችን በስጦታ ላገኘነው ሕይወት አድናቆት እንዳለን ያሳያል። ይህ ሰነድ ደም መስጠትን ከሚጠይቁ ሕክምናዎችና ከአንዳንድ የሕክምና ዓይነቶች ጋር በተያያዘ ምን አቋም እንዳለን ያሳያል። የሕክምና መመሪያ ካርዳችሁ የታደሰና አሁን ያላችሁን አቋም የሚገልጽ ነው? ይህን ካርድ እንደ አዲስ መሙላትም ሆነ የነበራችሁን ማደስ የሚያስፈልጋችሁ ከሆነ ዛሬ ነገ አትበሉ። አቋማችንን በግልጽ በጽሑፍ ማስፈራችን ቶሎ ሕክምና ለማግኘት ይረዳናል። የሕክምና ባለሙያዎቹም በስህተት እኛን ሊጎዳ የሚችል ሕክምና እንዳይሰጡን ጥበቃ ያደርጋል። b

16. የሕክምና መመሪያ ካርዱን እንዴት እንደምንሞላ ካላወቅን ምን ማድረግ እንችላለን?

16 ዕድሜያችን ወይም የጤንነታችን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሁላችንም አደጋና ሕመም ሊያጋጥመን ይችላል። (መክ. 9:11) በመሆኑም የሕክምና መመሪያ ካርድ መሙላታችን ጥበብ ነው። ይህን ሰነድ እንዴት መሙላት እንዳለባችሁ የማታውቁ ከሆነ የጉባኤ ሽማግሌዎቻችሁን እንዲረዷችሁ ጠይቋቸው። ሽማግሌዎች ሰነዱን በደንብ ለማወቅ ጥረት ስለሚያደርጉ ሊረዷችሁ ይችላሉ፤ ግን ውሳኔ አያደርጉላችሁም። ይህ የእናንተ ኃላፊነት ነው። (ገላ. 6:4, 5) ሆኖም ያሏችሁን አማራጮች በደንብ እንድትረዱና አቋማችሁን በጽሑፍ እንድታሰፍሩ ይረዷችኋል።

ምክንያታዊ ሁኑ

17. ከጤንነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ምክንያታዊነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 ከጤናችንና ከምንመርጠው የሕክምና ዓይነት ጋር የተያያዙትን አብዛኞቹን ውሳኔዎች የምናደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችንን ተጠቅመን ነው። (ሥራ 24:16፤ 1 ጢሞ. 3:9) ውሳኔዎችን ስናደርግና ስላደረግነው ውሳኔ ከሌሎች ጋር ስንነጋገር በፊልጵስዩስ 4:5 ላይ የሚገኘውን “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት መከተላችን ተገቢ ነው። ምክንያታዊ ከሆንን ስለ አካላዊ ጤንነታችን ከልክ በላይ አንጨነቅም፤ ሌሎች የእኛን አመለካከት እንዲቀበሉም ጫና አናደርግም። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከእኛ የተለየ ውሳኔ ቢያደርጉም እንኳ እንወዳቸዋለን እንዲሁም እናከብራቸዋለን።—ሮም 14:10-12

18. በስጦታ ላገኘነው ሕይወት አድናቆታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ሕይወታችንን ከአደጋ በመጠበቅና ለይሖዋ ምርጣችንን በመስጠት የሕይወት ምንጭ ለሆነው ለእሱ አድናቆታችንን እናሳያለን። (ራእይ 4:11) በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ ከሕመምና ከአደጋ ማምለጥ አንችልም። የፈጣሪያችን ዓላማ ግን በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንድንኖር አይደለም። በቅርቡ ሥቃይና ሞት የሌለበት ዘላለማዊ ሕይወት ይሰጠናል። (ራእይ 21:4) እስከዚያው ግን በሕይወት ኖረን አፍቃሪውን አባታችንን ይሖዋን ማገልገላችን እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው!

መዝሙር 140 መጨረሻ የሌለው ሕይወት

a ይህ ርዕስ የአምላክ ስጦታ ለሆነው ለሕይወት ያለንን አድናቆት እንድናሳድግ ይረዳናል። አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ጤንነታችንን ለመጠበቅና ሕይወታችንን ለማትረፍ ምን ማድረግ እንዳለብን እንመለከታለን፤ በተጨማሪም ከባድ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለመቀነስ ምን እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለብን እናያለን። ለድንገተኛ የሕክምና ሁኔታዎች አስቀድመን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት እንደሆነም እንመለከታለን።

b jw.org ላይ የሚገኘውን ደምን በመጠቀም ከሚሰጡ ሕክምናዎች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወጣት ወንድም የሕክምና መመሪያ ካርድ ሲሞላና አስታውሶ የገንዘብ ቦርሳው ውስጥ ሲከት።