በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 35

ትዕግሥት ማሳየታችሁን ቀጥሉ

ትዕግሥት ማሳየታችሁን ቀጥሉ

“ትዕግሥትን ልበሱ።”—ቆላ. 3:12

መዝሙር 114 “በትዕግሥት ጠብቁ”

ማስተዋወቂያ a

1. ትዕግሥተኛ የሆኑ ሰዎችን የምታደንቀው ለምንድን ነው?

 ሁላችንም ትዕግሥተኛ የሆኑ ሰዎችን እናደንቃለን። ለምን? ሳይበሳጩ አንድን ነገር መጠበቅ ለሚችሉ ሰዎች አክብሮት አለን። ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ሌሎች በትዕግሥት ሲይዙን ደስ ይለናል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለመረዳት፣ ለመቀበል ወይም በሥራ ላይ ለማዋል በተቸገርንበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናን ሰው ትዕግሥት ስላሳየን አመስጋኞች ነን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ አምላክ በትዕግሥት ስለሚይዘን ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ሮም 2:4

2. ትዕግሥት ማሳየት ከባድ የሚሆንብን በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ሊሆን ይችላል?

2 ትዕግሥተኛ የሆኑ ሰዎችን ብናደንቅም እንኳ እኛ ራሳችን ትዕግሥት ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል ላይሆንልን ይችላል። ለምሳሌ በተለይ ሰዓት ረፍዶብን እያለ የትራፊክ መጨናነቅ ቢያጋጥመን ወይም ለረጅም ሰዓት ለመሰለፍ ብንገደድ ተረጋግተን መጠበቅ ሊከብደን ይችላል። ሌሎች የሚያበሳጭ ነገር ሲያደርጉብን እንቆጣ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይሖዋ ቃል የገባውን አዲስ ዓለም መጠበቅ ሊከብደን ይችላል። አንተስ ይበልጥ ትዕግሥተኛ መሆን ትፈልጋለህ? በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ትዕግሥተኛ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም ይህ ባሕርይ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ይበልጥ ትዕግሥተኛ ለመሆን ምን ሊረዳን እንደሚችል እናያለን።

ትዕግሥተኛ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

3. ትዕግሥተኛ ሰው የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመው ምን ያደርጋል?

3 ትዕግሥት ማሳየት የምንችልባቸውን አራት መንገዶች እስቲ እንመልከት። አንደኛ፣ ትዕግሥተኛ ሰው ለቁጣ ይዘገያል። የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመው ወይም ውጥረት ውስጥ ሲሆን ለመረጋጋት ይሞክራል፤ እንዲሁም አጸፋ ከመመለስ ይቆጠባል። “ለቁጣ የዘገየ” የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ስለ ይሖዋ ባሕርያት በሚገልጽ ጥቅስ ላይ ነው፤ ጥቅሱ “ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ . . .፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ እንደሆነ ይናገራል።—ዘፀ. 34:6

4. ትዕግሥተኛ ሰው መጠበቅ ሲያስፈልገው ምን ያደርጋል?

4 ሁለተኛ፣ ትዕግሥተኛ ሰው ተረጋግቶ መጠበቅ ይችላል። እንዲህ ያለው ሰው፣ አንድ ነገር ከጠበቀው በላይ ረጅም ጊዜ ቢወስድም እንኳ ላለመበሳጨት ጥረት ያደርጋል። (ማቴ. 18:26, 27) በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ በትዕግሥት መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ሰው ሲናገር ሳናቋርጠው በትዕግሥት ማዳመጥ ይኖርብናል። (ኢዮብ 36:2) ጥናታችን አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲረዳ ወይም አንድን መጥፎ ልማድ እንዲያስወግድ በምንረዳበት ጊዜም ትዕግሥት ሊያስፈልገን ይችላል።

5. ትዕግሥት ማሳየት የሚቻልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

5 ሦስተኛ፣ ትዕግሥተኛ ሰው አይቸኩልም። እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ሊኖርብን ይችላል። ያም ቢሆን፣ ትዕግሥተኛ ሰው አስፈላጊ ሥራ በሚያከናውንበት ወቅት ሥራውን ተጣድፎ አይጀምርም፤ ወይም ሥራውን ለመጨረስ አይቸኩልም። ከዚህ ይልቅ ሥራውን በምን መንገድ እንደሚያከናውን ለማቀድ የተወሰነ ጊዜ ይመድባል። ከዚያም በቂ ጊዜ ሰጥቶ ሥራውን ያከናውናል።

6. ትዕግሥተኛ ሰው ፈተና ወይም መከራ ሲያጋጥመው ምን ያደርጋል?

6 አራተኛ፣ ትዕግሥተኛ ሰው ሳያጉረመርም ፈተናዎችን ለመቋቋም ጥረት ያደርጋል። ከዚህ አንጻር ትዕግሥት ከጽናት ጋር የቅርብ ተዛማጅነት አለው። እርግጥ ነው፣ የደረሰብንን መከራ አስመልክቶ ለምንቀርበው ወዳጃችን ስሜታችንን አውጥተን መናገራችን ስህተት አይደለም። ያም ቢሆን ትዕግሥተኛ ሰው አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ለመጽናት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል። (ቆላ. 1:11) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሁሉንም የትዕግሥት ገጽታዎች ማንጸባረቅ ያስፈልገናል። ለምን? አንዳንድ ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት።

ትዕግሥት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አንድ ገበሬ ጊዜው ሲደርስ ሰብሉን እንደሚያጭድ በመተማመን በትዕግሥት እንደሚጠባበቅ ሁሉ እኛም ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች በትክክለኛው ጊዜ እንደሚፈጽም በመተማመን በትዕግሥት እንጠብቃለን (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. በያዕቆብ 5:7, 8 መሠረት ትዕግሥት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ትዕግሥት ለመዳናችን ወሳኝ ነው። በጥንት ዘመን እንደነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ እኛም አምላካችን ቃል የገባቸውን ነገሮች እስኪፈጽም በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልገናል። (ዕብ. 6:11, 12) መጽሐፍ ቅዱስ የእኛን ሁኔታ ከአንድ ገበሬ ሁኔታ ጋር ያመሳስለዋል። (ያዕቆብ 5:7, 8ን አንብብ።) አንድ ገበሬ ዘር ለመዝራትና ውኃ ለማጠጣት ተግቶ ይሠራል፤ ሆኖም ተክሉ የሚያድግበትን ትክክለኛ ጊዜ አያውቅም። በመሆኑም ገበሬው እህል እንደሚያጭድ ተማምኖ በትዕግሥት ይጠብቃል። እኛም በተመሳሳይ ‘ጌታችን በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ባናውቅም’ እንኳ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በቅንዓት መካፈላችንን እንቀጥላለን። (ማቴ. 24:42) ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች በሙሉ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚፈጽም በመተማመን በትዕግሥት እንጠብቃለን። ትዕግሥት ካጣን ግን መጠበቅ ሊሰለቸንና ቀስ በቀስ ከእውነት መራቅ ልንጀምር እንችላለን። ወይም ደግሞ ቅጽበታዊ ደስታ የሚያስገኙ ነገሮችን ማሳደድ እንጀምር ይሆናል። ትዕግሥተኛ ከሆንን ግን እስከ መጨረሻው መጽናትና መዳን እንችላለን።—ሚክ. 7:7፤ ማቴ. 24:13

8. ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ትዕግሥት የሚረዳን እንዴት ነው? (ቆላስይስ 3:12, 13)

8 ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ትዕግሥት ይረዳናል። ሌሎች በሚናገሩበት ጊዜ በጥሞና እንድናዳምጥ ያግዘናል። (ያዕ. 1:19) በተጨማሪም ትዕግሥት ሰላም ለማስፈን ይረዳናል። ውጥረት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ በችኮላ ምላሽ ከመስጠትና ደግነት የጎደለው ነገር ከመናገር ይጠብቀናል። በተጨማሪም ትዕግሥተኛ ከሆንን አንድ ሰው ስሜታችንን ሲጎዳን ለቁጣ የዘገየን እንሆናለን። አጸፋ ከመመለስ ይልቅ ‘እርስ በርስ መቻቻላችንንና በነፃ ይቅር መባባላችንን እንቀጥላለን።’—ቆላስይስ 3:12, 13ን አንብብ።

9. ውሳኔ በምናደርግበት ወቅት ትዕግሥት የሚረዳን እንዴት ነው? (ምሳሌ 21:5)

9 ትዕግሥት ጥሩ ውሳኔ ለማድረግም ይረዳናል። በችኮላ ወይም በስሜት ተነድተን ከመወሰን ይልቅ ያሉንን አማራጮች በተመለከተ ጊዜ ወስደን ምርምር እናደርጋለን፤ እንዲሁም የተሻለው አማራጭ የትኛው እንደሆነ እንገመግማለን። (ምሳሌ 21:5ን አንብብ።) ለምሳሌ ሥራ እየፈለግን ከሆነ ሥራው ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ የሚነካብን ቢሆንም እንኳ ያገኘነውን የመጀመሪያ ሥራ ለመቀጠር እንፈተን ይሆናል። ትዕግሥተኛ ከሆንን ግን ስለ ቦታው፣ ስለ ሥራ ሰዓቱ፣ ሥራው በቤተሰባችንና በመንፈሳዊነታችን ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዲሁም ስለ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጊዜ ወስደን እናስባለን። ትዕግሥተኛ መሆናችን መጥፎ ውሳኔ ከማድረግ ሊጠብቀን ይችላል።

ይበልጥ ትዕግሥተኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

10. አንድ ክርስቲያን ትዕግሥት ማዳበርና ይህን ባሕርይ ይዞ መቀጠል የሚችለው እንዴት ነው?

10 ይበልጥ ትዕግሥተኛ ለመሆን ጸልይ። ትዕግሥት ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። (ገላ. 5:22, 23) በመሆኑም ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን እንዲሁም የመንፈስ ፍሬ ለማፍራት እንዲረዳን መጸለይ እንችላለን። ትዕግሥታችንን የሚፈትን ሁኔታ ሲያጋጥመን ትዕግሥተኛ ለመሆን የሚረዳንን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ይሖዋን ‘ደጋግመን እንለምነዋለን።’ (ሉቃስ 11:9, 13) በተጨማሪም ይሖዋ ሁኔታውን ከእሱ አመለካከት አንጻር ለማየት እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን። ከጸለይን በኋላ ደግሞ በየዕለቱ ትዕግሥተኛ ለመሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። ትዕግሥት ለማዳበር በጸለይን እንዲሁም ትዕግሥተኛ ለመሆን ጥረት ባደረግን መጠን ይህ ባሕርይ በልባችን ውስጥ ይበልጥ ሥር በመስደድ የማንነታችን ክፍል እየሆነ ይሄዳል።

11-12. ይሖዋ ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው?

11 በመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ላይ አሰላስል። መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥት ያሳዩ በርካታ ሰዎችን ምሳሌ ይዟል። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ማሰላሰላችን ትዕግሥት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች ለማወቅ ይረዳናል። የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ከመመርመራችን በፊት፣ ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው አምላካችን ይሖዋ የተወውን ምሳሌ እንመልከት።

12 በኤደን ገነት ውስጥ ሰይጣን የይሖዋን ስም አጥፍቷል፤ እንዲሁም እሱ ፍትሐዊና አፍቃሪ ገዢ በመሆኑ ላይ ጥያቄ አስነስቷል። ይሖዋ ስም አጥፊውን ወዲያውኑ ከማጥፋት ይልቅ የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ መሆኑን ለማረጋገጥ ጊዜ እንደሚወስድ በመገንዘብ ትዕግሥትና ራስን መግዛት አሳይቷል። ያ ጊዜ እስኪደርስ በሚጠብቅበት ወቅትም በስሙ ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ በትዕግሥት ችሎ አልፏል። በተጨማሪም ይሖዋ ብዙ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ሲል በትዕግሥት ሲጠብቅ ቆይቷል። (2 ጴጥ. 3:9, 15) በውጤቱም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እሱን ማወቅ ችለዋል። የይሖዋ ትዕግሥት በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ ካተኮርን ይህን ሥርዓት ለማጥፋት የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ቀላል ይሆንልናል።

ትዕግሥት የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመን ለቁጣ የዘገየን እንድንሆን ይረዳናል (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. ኢየሱስ የአባቱን ትዕግሥት ፍጹም በሆነ መንገድ የኮረጀው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 ኢየሱስ የአባቱን ትዕግሥት ፍጹም በሆነ መንገድ ኮርጇል፤ እንዲሁም በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ይህን ባሕርይ አንጸባርቋል። በተለይ ግብዝ ለሆኑት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ትዕግሥት ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል እንዳልነበር ጥያቄ የለውም። (ዮሐ. 8:25-27) ያም ቢሆን ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ ለቁጣ የዘገየ ነበር። ሰዎች ሲሰድቡት ወይም የሚያበሳጭ ነገር ሲያደርጉበት አጸፋውን አልመለሰም። (1 ጴጥ. 2:23) ኢየሱስ መከራ ቢደርስበትም ሳያጉረመርም በትዕግሥት ጸንቷል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአተኞች . . . የሚያሰሙትን እንዲህ ዓይነቱን የተቃውሞ ንግግር በጽናት የተቋቋመውን እሱን በጥሞና አስቡ” የሚል ምክር የሚሰጠን መሆኑ አያስገርምም! (ዕብ. 12:2, 3) እኛም በይሖዋ እርዳታ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በትዕግሥት ጸንተን ማሳለፍ እንችላለን።

የአብርሃምን ትዕግሥት ከኮረጅን ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ወሮታችንን እንደሚከፍለን፣ አዲሱ ዓለም ሲመጣ ደግሞ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያፈስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. ከአብርሃም ትዕግሥት ምን ትምህርት እናገኛለን? (ዕብራውያን 6:15) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 መጨረሻውን በተመለከተ የጠበቅነው ነገር እስካሁን አልተፈጸመ ይሆናል። ምናልባት መጨረሻው ይመጣል ብለን ያሰብነው ከረጅም ጊዜ በፊት ሊሆን ይችላል። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የሕይወታችን ማብቂያ እንዳይቀድም እንሰጋ ይሆናል። ታዲያ በትዕግሥት መጠበቃችንን እንድንቀጥል ምን ይረዳናል? የአብርሃምን ምሳሌ እንመልከት። አብርሃም ገና ልጅ ከመውለዱ በፊት ይሖዋ “ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ” የሚል ቃል ገባለት፤ በወቅቱ አብርሃም 75 ዓመቱ ነበር። (ዘፍ. 12:1-4) ታዲያ አብርሃም ይህ ቃል ሲፈጸም ተመልክቷል? በመጠኑ። አብርሃም ኤፍራጥስ ወንዝን ከተሻገረና 25 ዓመት ከጠበቀ በኋላ በተአምራዊ መንገድ ይስሐቅን ወለደ፤ ከ60 ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ የልጅ ልጆቹ የሆኑት ኤሳውና ያዕቆብ ሲወለዱ ተመልክቷል። (ዕብራውያን 6:15ን አንብብ።) ሆኖም አብርሃም ዘሮቹ ታላቅ ብሔር ሲሆኑና ተስፋይቱን ምድር ሲወርሱ አልተመለከተም። ያም ቢሆን ይህ ታማኝ ሰው ከፈጣሪው ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት ችሏል። (ያዕ. 2:23) ወደፊት አብርሃም ከሞት ሲነሳ ደግሞ እምነትና ትዕግሥት ማሳየቱ ለሁሉም ብሔራት በረከት ያስገኘው እንዴት እንደሆነ ሲገነዘብ በጣም መደሰቱ አይቀርም። (ዘፍ. 22:18) እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች በሙሉ ሲፈጸሙ በዚህ ዘመን አናይ ይሆናል። ያም ቢሆን እንደ አብርሃም ትዕግሥት ካሳየን ይሖዋ በአሁኑ ወቅት ወሮታችንን እንደሚከፍለን፣ አዲሱ ዓለም ሲመጣ ደግሞ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያፈስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማር. 10:29, 30

15. በግል ጥናታችን ላይ ስለ ምን ጉዳይ ማጥናት እንችላለን?

15 መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥት ያሳዩ ሌሎች በርካታ ሰዎችን ምሳሌ ይዟል። (ያዕ. 5:10) በግል ጥናትህ ላይ የእነዚህን ሰዎች ምሳሌ ለመመርመር ለምን አትሞክርም? b ለአብነት ያህል፣ ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው ገና በልጅነቱ ቢሆንም ንግሥናውን እስኪቀበል ድረስ ለበርካታ ዓመታት መጠበቅ አስፈልጎታል። ስምዖን እና ሐና፣ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ እስኪመጣ በሚጠባበቁበት ወቅት ይሖዋን በታማኝነት ያገለግሉ ነበር። (ሉቃስ 2:25, 36-38) እንዲህ ያሉትን ዘገባዎች በምታጠናበት ወቅት የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለመፈለግ ጥረት አድርግ፦ ይህ ሰው ትዕግሥት እንዲያሳይ የረዳው ምን ሊሆን ይችላል? ትዕግሥተኛ መሆኑ የጠቀመው እንዴት ነው? የእሱን ምሳሌ መከተል የምችለው እንዴት ነው? ትዕግሥት ስላላሳዩ ሰዎች ማጥናትህም ሊጠቅምህ ይችላል። (1 ሳሙ. 13:8-14) የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልታነሳ ትችላለህ፦ ‘ትዕግሥት እንዳያሳይ ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል? ትዕግሥት አለማሳየቱ ምን መዘዝ አስከትሎበታል?’

16. ትዕግሥት ማሳየት የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች የትኞቹ ናቸው?

16 ትዕግሥት ማሳየት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች አስብ። ትዕግሥተኛ ከሆንን ይበልጥ ደስተኛና የተረጋጋን ሰዎች እንሆናለን። በመሆኑም ትዕግሥት አእምሯዊና አካላዊ ጤንነታችንን ሊያሻሽለው ይችላል። ሌሎችን በትዕግሥት የምንይዝ ከሆነ ከእነሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖረናል። ጉባኤያችን ይበልጥ አንድነት ያለው ይሆናል። አንድ ሰው ቢያበሳጨን ለቁጣ የዘገየን መሆናችን ሁኔታው እንዳይባባስ ያደርጋል። (መዝ. 37:8 ግርጌ፤ ምሳሌ 14:29) ከሁሉ በላይ ደግሞ ትዕግሥተኛ መሆናችን የሰማዩን አባታችንን ለመምሰልና ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳናል።

17. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

17 በእርግጥም ትዕግሥት በጣም ማራኪና ጠቃሚ ባሕርይ ነው! መታገሥ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆንልን ቢችልም በይሖዋ እርዳታ ይህን ባሕርይ ማዳበራችንን መቀጠል እንችላለን። በተጨማሪም አዲሱን ዓለም በትዕግሥት በምንጠባበቅበት ወቅት “የይሖዋ ዓይን የሚፈሩትን፣ ደግሞም ታማኝ ፍቅሩን የሚጠባበቁትን በትኩረት” እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 33:18) እንግዲያው ሁላችንም ትዕግሥትን መልበሳችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ

a በሰይጣን ዓለም ውስጥ ትዕግሥተኛ ሰው ማግኘት ከባድ ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥትን እንድንለብስ ይነግረናል። ይህ ርዕስ፣ ትዕግሥት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይበልጥ ትዕግሥተኛ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

b ከትዕግሥት ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ለማግኘት የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች ላይ “ስሜት፣ ባሕርያት እና ጠባይ” በሚለው ሥር የሚገኘውን “ትዕግሥት” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከት።