በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

1923—የዛሬ መቶ ዓመት

1923—የዛሬ መቶ ዓመት

የጥር 1, 1923 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “1923 አስደሳች ዓመት እንደሚሆን እንጠብቃለን። ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ለተጨቆኑ ሰዎች መናገር ታላቅ መብት ነው።” በ1923 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ስብሰባዎቻቸውንና አገልግሎታቸውን በሚያከናውኑበት መንገድ ላይ አስደናቂ ለውጦችን አድርገዋል። ይህም ይበልጥ አንድነት እንዲኖራቸው ረድቷቸዋል።

አንድነት በስብሰባዎች

ጥቅሶችንና የመዝሙር ቁጥሮችን የያዘ የቀን መቁጠሪያ

በዚያ ዓመት ድርጅቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ መካከል ያለውን አንድነት የሚያጠናክሩ አንዳንድ ለውጦችን አድርጎ ነበር። መጠበቂያ ግንብ በሳምንታዊው “የጸሎት፣ የውዳሴ እና የምሥክርነት ስብሰባ” ላይ የሚጠቀሙበትን ጥቅስ የሚያብራሩ ሐሳቦች ይዞ መውጣት ጀመረ። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ለእያንዳንዱ ሳምንት የተዘጋጀውን ጥቅስ እንዲሁም በግል ጥናትና በቤተሰብ አምልኮ ወቅት የሚዘምሯቸውን መዝሙሮች የያዘ የቀን መቁጠሪያ አዘጋጁ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በስብሰባዎቻቸው ላይ “ምሥክርነት” ይሰጡ ነበር፤ “ምሥክርነት” የሚባለው የመስክ አገልግሎት ተሞክሮ፣ ለይሖዋ የሚቀርብ ምስጋና፣ መዝሙር አልፎ ተርፎም ጸሎት ሊሆን ይችላል። በ1923 በ15 ዓመቷ የተጠመቀችው ኢቫ ባርኒ እንዲህ ብላለች፦ “ምሥክርነት መስጠት ከፈለጋችሁ ትቆሙና ‘ጌታ ላሳየኝ ጥሩነት ሁሉ ላመሰግነው እፈልጋለሁ’ ብላችሁ ትጀምራላችሁ።” አንዳንድ ወንድሞች ምሥክርነት መስጠት በጣም ይወዱ ነበር። እህት ባርኒ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “አረጋዊው ወንድም ጎድዊን ስለተለያዩ ነገሮች ጌታን ማመስገን ይወድ ነበር። ሆኖም ባለቤቱ፣ ስብሰባውን የሚመራው ወንድም ሲቁነጠነጥ ስታይ ኮቱን ጎተት ታደርገዋለች። በዚህ ጊዜ ይቀመጣል።”

እያንዳንዱ ጉባኤ በወር አንድ ጊዜ ለየት ያለ “የጸሎት፣ የውዳሴ እና የምሥክርነት ስብሰባ” ያካሂድ ነበር። የሚያዝያ 1, 1923 መጠበቂያ ግንብ ይህን ስብሰባ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “የስብሰባው ግማሽ ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ ምሥክርነቶችን ለመስጠትና ሠራተኞቹን ለማበረታታት ሊውል ይገባል። . . . ይህ የአምልኮ አንድነት ወንድሞችን ይበልጥ እንደሚያቀራርባቸው እንተማመናለን።”

በቫንኩቨር፣ ካናዳ ውስጥ በአስፋፊነት ያገለግል የነበረው የ19 ዓመቱ ቻርልስ ማርቲን ከእነዚህ ስብሰባዎች በእጅጉ ተጠቅሟል። እንዲህ ብሏል፡- “ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ምን ማለት እንዳለብኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተማርኩት በዚህ ስብሰባ ላይ ነበር። ብዙውን ጊዜ ወንድሞች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ ያገኟቸውን ተሞክሮዎች ይናገሩ ነበር። ይህም አገልግሎት ላይ ምን ማለት እንዳለብኝ እንዲሁም የተለያየ ዓይነት ተቃውሞ ሲያጋጥመኝ ምን ምላሽ መስጠት እንደምችል አስተምሮኛል።”

አንድነት በአገልግሎት

የግንቦት 1, 1923 ቡለቲን

የተመደቡ “የአገልግሎት ቀናት” መኖራቸውም በድርጅቱ ውስጥ ላለው አንድነት አስተዋጽኦ አበርክቷል። የሚያዝያ 1, 1923 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ማስታወቂያ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “በአንድነት በሥራው መካፈል እንድንችል . . . ማክሰኞ፣ ግንቦት 1, 1923 አጠቃላይ የአገልግሎት ቀን ተብሎ ተመድቧል። ከዚያ በኋላ ደግሞ የእያንዳንዱ ወር የመጀመሪያ ማክሰኞ የአገልግሎት ቀን ይሆናል። . . . የእያንዳንዱ ጉባኤ እያንዳንዱ አባል በሆነ መንገድ በሥራው መካፈል አለበት።”

ወጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም በሥራው ተካፍለዋል። በወቅቱ የ16 ዓመት ወጣት የነበረችው ሄዝል በርፎርድ እንዲህ ብላለች፦ “ቡለቲን በቃላችን እንድንይዛቸው መግቢያዎችን ይዞ ይወጣ ነበር። a ከአያቴ ጋር ሆኜ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች በቅንዓት እካፈል ነበር።” ይሁንና እህት በርፎርድ ካልተጠበቀ ምንጭ ተቃውሞ አጋጠማት። እንዲህ ብላለች፦ “አንድ አረጋዊ ወንድም ሰዎችን ማነጋገር እንደሌለብኝ ስለተሰማው አጥብቆ ተቃወመኝ። በወቅቱ አንዳንዶች ‘ወጣት ወንዶችንና ወጣት ሴቶችን’ ጨምሮ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ታላቁን ፈጣሪያችንን በማወደሱ ሥራ መካፈል እንዳለባቸው አልተገነዘቡም ነበር።” (መዝ. 148:12, 13) ሆኖም እህት በርፎርድ መስበኳን አላቆመችም። ከጊዜ በኋላ በጊልያድ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ክፍል ተምራ ፓናማ ውስጥ በሚስዮናዊነት ማገልገል ችላለች። ውሎ አድሮ እነዚህ ወንድሞች በአገልግሎት ከሚካፈሉ ወጣቶች ጋር በተያያዘ የነበራቸውን አመለካከት አስተካከሉ።

አንድነት በትላልቅ ስብሰባዎች

ትላልቅ ስብሰባዎችም በወንድሞች መካከል ላለው አንድነት አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ብዙዎቹ ስብሰባዎች የአገልግሎት ቀን ነበራቸው። ለምሳሌ በዊኒፔግ፣ ካናዳ ትልቅ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት ሁሉም ተሰብሳቢዎች መጋቢት 31 በተካሄደው ልዩ የስብከት ዘመቻ እንዲካፈሉ ግብዣ ቀርቦላቸው ነበር። እንዲህ ያሉት የአገልግሎት ቀኖች ሥራው እንዲስፋፋ መሠረት ጥለዋል። ነሐሴ 5 ቀን 7,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በዊኒፔግ በተካሄደ ሌላ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል። ከዚያ በፊት ካናዳ ውስጥ የዚህን ያህል ብዙ ሰው የተገኘበት ትልቅ ስብሰባ ተካሂዶ አያውቅም።

በ1923 ከተካሄዱት ስብሰባዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከነሐሴ 18-26 በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ የተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ነው። ከስብሰባው በፊት በነበሩት ሳምንታት ስለ ስብሰባው የሚናገሩ ማስታወቂያዎች በጋዜጣ ላይ ይወጡ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹም ከ500,000 በላይ የመጋበዣ ወረቀቶችን አሰራጭተዋል። በተጨማሪም የማስታወቂያ ፖስተሮች በሕዝብ መጓጓዣም ሆነ በግል መኪኖች ላይ ተሰቅለው ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በ1923 በሎስ አንጀለስ ያካሄዱት ትልቅ ስብሰባ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 25 ወንድም ራዘርፎርድ “በጎች እና ፍየሎች” በሚል ርዕስ ንግግር ያቀረበ ሲሆን ‘በጎቹ’ የሚያመለክቱት ገነት በሆነችው ምድር ላይ የሚኖሩትን ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች እንደሆነ በግልጽ ተናገረ። በተጨማሪም “ማስጠንቀቂያ” የሚል የአቋም መግለጫ አወጣ። የአቋም መግለጫው ሕዝበ ክርስትናን የሚያወግዝ እንዲሁም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ እንዲወጡ የሚያበረታታ ነበር። (ራእይ 18:2, 4) በዓለም ዙሪያ ያሉ ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከጊዜ በኋላ ይህን የአቋም መግለጫ የያዙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ትራክቶችን አሰራጭተዋል።

“ይህ የአምልኮ አንድነት ወንድሞችን ይበልጥ እንደሚያቀራርባቸው እንተማመናለን”

በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ላይ ከ30,000 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ወንድም ራዘርፎርድ “ብሔራት ሁሉ ወደ አርማጌዶን እየገሰገሱ ነው፤ ሆኖም ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” በሚል ርዕስ ንግግር ሲያቀርብ አዳመጡ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ፣ ብዙ ሰው በስብሰባው ላይ እንደሚገኝ ስለጠበቁ በቅርቡ የተገነባውን የሎስ አንጀለስ ስታዲየም ተከራይተው ነበር። ወንድሞች ሁሉም ሰው ንግግሩን በደንብ እንዲያዳምጥ ስለፈለጉ የስታዲየሙን ድምፅ ማጉያ ተጠቀሙ፤ ድምፅ ማጉያ በወቅቱ አዲስ ቴክኖሎጂ ነበር። ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በሬዲዮ ተከታትለዋል።

ዓለም አቀፋዊ እድገት

በ1923 በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በሕንድና በደቡብ አሜሪካ የስብከቱ ሥራ በእጅጉ ተስፋፍቶ ነበር። በሕንድ የሚኖረው ወንድም አዳቪማናቱ ጆሴፍ ባለቤቱንና ስድስት ልጆቹን እያስተዳደረ በሂንዲ፣ በታሚል፣ በቴሉጉ እና በኡርዱ ቋንቋዎች ጽሑፎቻችንን በማዘጋጀቱ ሥራ ይካፈል ነበር።

ዊልያም ብራውን እና ቤተሰቡ

በሴራ ሊዮን የሚኖሩት አልፍሬድ ጆሴፍ እና ሌነርድ ብላክማን የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት በመጻፍ የሚረዳቸው ሰው እንዲላክላቸው ጠየቁ። ሚያዝያ 14, 1923 ጥያቄያቸው መልስ አገኘ። አልፍሬድ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ቅዳሜ ምሽት ካልጠበቅኩት ቦታ ስልክ ተደወለልኝ።” አንድ ሰው በሚያስገመግም ድምፅ “ወደ መጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽፈህ ሰባኪ እንዲላክልህ የጠየቅከው አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው። አልፍሬድም “አዎ” ብሎ መለሰ። ሰውየውም “እኔን ልከውኛል” አለው። የደወለው ዊልያም ብራውን ነበር። ወንድም ብራውን ከባለቤቱ ከአንቶኒያ እና ከሁለት ትናንሽ ልጆቻቸው ከሉዊዝ እና ከሉሲ ጋር ከካሪቢያን ወደ ሴራ ሊዮን የደረሰው በዚያ ቀን ነበር። ወንድሞች አዲሶቹን ሰባኪዎች ለመተዋወቅ ብዙ መጠበቅ አላስፈለጋቸውም።

አልፍሬድ ታሪኩን ሲቀጥል እንዲህ ብሏል፦ “በቀጣዩ ቀን ጠዋት ላይ እኔና ሌነርድ ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን እያካሄድን ሳለን አንድ ግዙፍ ሰው ወደ በሩ መጣ። ሰውየው ወንድም ብራውን ነበር። ወንድም ብራውን ለእውነት ከፍተኛ ቅንዓት ስለነበረው በቀጣዩ ቀን የሕዝብ ንግግር ለማቅረብ ፈልጎ ነበር።” አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወንድም ብራውን ይዞ የመጣቸውን ጽሑፎች በሙሉ አበርክቶ ጨረሰ። ብዙም ሳይቆይ 5,000 መጻሕፍት ተላኩለት፤ ይሁንና እነሱንም ጨርሶ ተጨማሪ ጠየቀ። ያም ቢሆን ሰዎች ወንድም ብራውንን የሚያዩት እንደ መጽሐፍ ሻጭ አልነበረም። ይሖዋን በቅንዓት ባገለገለባቸው በርካታ ዓመታት በንግግሮቹ ላይ ቅዱሳን መጻሕፍትን አዘውትሮ ይጠቅስ ስለነበር “ባይብል ብራውን” ተብሎ ይጠራ ነበር።

የማግደበርግ ቤቴል በ1920ዎቹ

ይህ በእንዲህ እንዳለ በባርመን፣ ጀርመን የነበረው ቅርንጫፍ ቢሮ ለሠራተኞቹ ስለጠበባቸው ከዚያ ለመውጣት አሰቡ። በተጨማሪም ከተማዋ በፈረንሳይ ሠራዊት የመወረር አደጋ ተደቅኖባት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በማግደበርግ ለሕትመት ሥራቸው ተስማሚ የሆነ ሕንፃ አገኙ። ሰኔ 19 ወንድሞች የሕትመት መሣሪያዎቻቸውንና ሌሎች ዕቃዎቻቸውን ይዘው በማግደበርግ ወደሚገኘው አዲስ ቤቴል ተዛወሩ። ወንድሞች ወደ አዲሱ ቤቴል ተዛውረው መጨረሳቸውን ለዋናው መሥሪያ ቤት ባሳወቁ በቀጣዩ ቀን ፈረንሳይ የባርመን ከተማን እንደተቆጣጠረች የሚገልጽ ዜና በጋዜጦች ላይ ወጣ። ወንድሞች ሁኔታውን የይሖዋን በረከትና ጥበቃ እንደሚያሳይ ማስረጃ አድርገው ተመልክተውታል።

ጆርጅ ያንግ ከሣራ ፈርጉሰን (በስተ ቀኝ) እና ከእህቷ ጋር

ብራዚል ውስጥ ደግሞ፣ ምሥራቹን ለማስፋፋት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን የተጓዘው ጆርጅ ያንግ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ አቋቁሞ የፖርቱጋልኛ መጠበቂያ ግንብ ማተም ጀመረ። በጥቂት ወራት ውስጥ ከ7,000 የሚበልጡ ጽሑፎችን አበረከተ። ወንድም ያንግ ወደ ብራዚል መምጣቱ ለሣራ ፈርጉሰን ልዩ አጋጣሚ ከፍቶላታል። ከ1899 አንስቶ መጠበቂያ ግንብ ስታነብ የቆየች ቢሆንም ራሷን መወሰኗን በውኃ ጥምቀት የምታሳይበት አጋጣሚ አላገኘችም ነበር። ከተወሰኑ ወራት በኋላ እህት ፈርጉሰንና አራት ልጆቿ ይህን ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ቻሉ።

በቅንዓትና በደስታ አምላክን ማገልገል

በዓመቱ መገባደጃ ላይ የታኅሣሥ 15, 1923 መጠበቂያ ግንብ በስብሰባዎች፣ በአገልግሎትና በትላልቅ ስብሰባዎች ረገድ የተደረጉት ለውጦች በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ላይ ምን ተጽዕኖ እንዳሳደሩ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ጉባኤዎቹ በጥሩ መንፈሳዊ አቋም ላይ እንደሚገኙ በግልጽ ማየት ይቻላል። . . . ወገባችንን ለሥራ ታጥቀን በቀጣዩ ዓመትም አምላክን በቅንዓትና በደስታ ማገልገላችንን እንቀጥል።”

ቀጣዩ ዓመት ማለትም 1924 በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዓመት ነው። በቤቴል የሚያገለግሉት ወንድሞች በብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ብዙም ሳይርቅ በስታተን አይላንድ በገዙት መሬት ላይ ለበርካታ ወራት የዘለቀ የግንባታ ሥራ እያካሄዱ ነበር። የግንባታ ሥራው በ1924 መጀመሪያ አካባቢ ተጠናቀቀ። ይህ ሕንፃ ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን በወንድማማች ማኅበሩ መካከል ያለው አንድነት እንዲጠናከርና ምሥራቹ እንዲስፋፋ መንገድ ከፍቷል።

በስታተን አይላንድ የነበሩት የግንባታ ሠራተኞች

a አሁን ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ ተብሎ ይጠራል።