በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 2

መዝሙር 19 የጌታ ራት

በዓመቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ቀን ተዘጋጅታችኋል?

በዓመቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ቀን ተዘጋጅታችኋል?

“ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።”ሉቃስ 22:19

ዓላማ

የመታሰቢያውን በዓል በጣም ልዩ የሚያደርገው ምን እንደሆነ፣ ለበዓሉ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ሌሎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

1. የመታሰቢያው በዓል በዓመቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቀን የሆነው ለምንድን ነው? (ሉቃስ 22:19, 20)

 የይሖዋ ሕዝቦች በዓመቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ቀን የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲያከብሩት በቀጥታ ያዘዘው ብቸኛው በዓል ይሄ ነው። (ሉቃስ 22:19, 20ን አንብብ።) የመታሰቢያውን በዓል በጉጉት የምንጠባበቅባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

2. የመታሰቢያውን በዓል በጉጉት እንድንጠባበቅ የሚያደርጉን አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

2 የመታሰቢያው በዓል ቤዛው ባለው ዋጋ ላይ እንድናሰላስል ይረዳናል። ለኢየሱስ መሥዋዕት ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች ያስታውሰናል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) በተጨማሪም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር “እርስ በርሳችን እንድንበረታታ” አጋጣሚ ይሰጠናል። (ሮም 1:12) በየዓመቱ በርካታ የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ፣ የተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ አነሳስቷቸዋል። ከዚህም ሌላ፣ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች በዚያ ዕለት የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር በሕይወት መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ ያነሳሳቸዋል። የመታሰቢያውን በዓል በጣም ከፍ አድርገን የምንመለከተው ለዚህ ነው!

3. የመታሰቢያው በዓል ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበራችንን አንድ የሚያደርገው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

3 የመታሰቢያው በዓል ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበራችንን አንድ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነም ለማሰብ ሞክር። በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እነሱ በሚኖሩበት አካባቢ ፀሐይ ስትጠልቅ ይሰበሰባሉ። ሁላችንም የቤዛውን አስፈላጊነት የሚያጎላ ንግግር ሲቀርብ እናዳምጣለን። ሁለት የውዳሴ መዝሙሮች እንዘምራለን፤ ቂጣውና የወይን ጠጁ በፊታችን እንዲያልፍ ይደረጋል፤ እንዲሁም አራት ጸሎቶች ሲቀርቡ በሙሉ ልብ “አሜን” እንላለን። በ24 ሰዓት ውስጥ ሁሉም ጉባኤዎች በተመሳሳይ መንገድ በዓሉን ያከብራሉ። ይሖዋና ኢየሱስ በዚህ መልኩ አንድ ሆነን ስናከብራቸው ምን ያህል እንደሚደሰቱ መገመት ትችላለህ?

የመታሰቢያው በዓል ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበራችንን አንድ ያደርጋል (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት) f


4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ ለመታሰቢያው በዓል ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? ሌሎች ከበዓሉ እንዲጠቀሙ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? የቀዘቀዙትን መርዳት የምንችለውስ እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ መመርመራችን ለዚህ ቅዱስ በዓል ዝግጁ እንድንሆን ይረዳናል።

ለመታሰቢያው በዓል ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

5. (ሀ) ቤዛው ባለው ዋጋ ላይ ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው? (መዝሙር 49:7, 8) (ለ) ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው? ከሚለው ቪዲዮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

5 ለመታሰቢያው በዓል ልባችንን ማዘጋጀት ከምንችልባቸው ወሳኝ መንገዶች አንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ባለው ዋጋ ላይ ማሰላሰል ነው። በራሳችን ጥረት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ መውጣት የምንችልበት ምንም መንገድ የለም። (መዝሙር 49:7, 8ን አንብብ፤ ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮም ተመልከት።) a በመሆኑም ይሖዋ፣ ኢየሱስ ሕይወቱን ለእኛ ሲል እንዲሰጠን አደረገ፤ ይህም ይሖዋንም ሆነ ውድ ልጁን ትልቅ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። (ሮም 6:23) ይሖዋና ኢየሱስ በከፈሉልን መሥዋዕት ላይ ባሰላሰልን መጠን ለቤዛው ያለን አድናቆት እያደገ ይሄዳል። ከዚህ በመቀጠል፣ ይሖዋና ኢየሱስ ቤዛውን ለማዘጋጀት ከከፈሏቸው መሥዋዕቶች የተወሰኑትን እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን ቤዛው የተከፈለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

6. ቤዛው የተከፈለው እንዴት ነው?

6 ቤዛ አንድን ነገር መልሶ ለመግዛት የሚከፈል ዋጋ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም ሲፈጠር ፍጹም ነበር። አዳም ኃጢአት ሲሠራ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚውን አጣ፤ ልጆቹም ይህን አጋጣሚ እንዲያጡ አደረገ። ኢየሱስ፣ አዳም ያጣውን ነገር መልሶ ለመግዛት ሲል ፍጹም ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ “ምንም ኃጢአት አልሠራም፤ በአንደበቱም የማታለያ ቃል አልተገኘም።” (1 ጴጥ. 2:22) ኢየሱስ በሞተበት ወቅት ልክ እንደ አዳም ፍጹም ሰው ነበር፤ በመሆኑም ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረግ አዳም ያጣውን ሕይወት መልሶ መግዛት ችሏል።—1 ቆሮ. 15:45፤ 1 ጢሞ. 2:6

7. ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የትኞቹ ፈተናዎች አጋጥመውታል?

7 ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም በሰማይ ላለው አባቱ ፍጹም ታዛዥ ሆኗል። ኢየሱስ ሲወለድ ጀምሮ ፍጹም የነበረ ቢሆንም ልጅ ሳለ ፍጹማን ላልሆኑት ወላጆቹ መገዛት ነበረበት። (ሉቃስ 2:51) ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ሲገባ ደግሞ ታዛዥነቱን ወይም ታማኝነቱን እንዲያጓድል የሚደረግበትን ማንኛውንም ጫና መቋቋም ነበረበት። ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ ደግሞ ሰይጣን ዲያብሎስ ያደረሰበትን ፈተና መቋቋም ነበረበት። ሰይጣን፣ ኢየሱስ ለአምላክ ያለውን ታማኝነት እንዲያጓድል ለማድረግ ቀጥተኛ ጥቃት ሰንዝሮበታል። (ማቴ. 4:1-11) ሰይጣን፣ ኢየሱስ ቤዛውን መክፈል እንዳይችል ለማድረግ ሲል ኃጢአት ሊያሠራው ቆርጦ ተነስቶ ነበር።

8. ኢየሱስ የትኞቹን ሌሎች ፈተናዎች መቋቋም ነበረበት?

8 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሌሎች ፈተናዎችንም በጽናት ተቋቁሟል። ስደት ደርሶበታል፤ ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀባቸው ጊዜያትም ነበሩ። (ሉቃስ 4:28, 29፤ 13:31) የተከታዮቹን አለፍጽምና መቻል ነበረበት። (ማር. 9:33, 34) ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ከፍተኛ ሥቃይና ፌዝ ደርሶበታል። ከዚያም እጅግ በሚያሠቃይና በሚያዋርድ መንገድ ተገደለ። (ዕብ. 12:1-3) የመጨረሻውን ፈተና የተቋቋመው ደግሞ ያለይሖዋ ጥበቃ ብቻውን ነው። bማቴ. 27:46

9. ስለ ኢየሱስ መሥዋዕት ምን ይሰማናል? (1 ጴጥሮስ 1:8)

9 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ቤዛው ኢየሱስን ትልቅ ዋጋ አስከፍሎታል። ኢየሱስ ለእኛ ሲል ይህን ሁሉ መሥዋዕት በፈቃደኝነት እንደከፈለልን ስናስብ ልባችን ለእሱ ባለን ፍቅር አይሞላም?—1 ጴጥሮስ 1:8ን አንብብ።

10. ቤዛው ይሖዋን ምን ዋጋ አስከፍሎታል?

10 ኢየሱስ ቤዛ እንዲሆን ይሖዋስ ምን መሥዋዕት መክፈል አስፈልጎታል? ይሖዋና ኢየሱስ ከየትኛውም አባትና ልጅ ይበልጥ ይቀራረባሉ። (ምሳሌ 8:30) ስለዚህ ኢየሱስ ምድር ላይ ያ ሁሉ መከራ ሲፈራረቅበት ይሖዋ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው። ይሖዋ ልጁ ሲንገላታ፣ ሲጠላ እና ፈተና ሲደርስበት ሲያይ በጣም አዝኖ መሆን አለበት።

11. ይሖዋ፣ ኢየሱስ በተገደለበት ወቅት ምን እንደተሰማው በምሳሌ አስረዳ።

11 ልጃቸውን በሞት ያጡ ወላጆች እንዲህ ያለው ሁኔታ መሪር ሐዘን እንደሚያስከትል ያውቃሉ። በትንሣኤ ላይ ጠንካራ እምነት አለን። ሆኖም ይህ እምነታችን የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ የሚደርስብንን ሐዘን አያስቀርልንም። ይህ ምሳሌ፣ ይሖዋ ውድ ልጁ በ33 ዓ.ም. ተሠቃይቶ ሲገደል የተሰማውን ስሜት ለመረዳት ያስችለናል። cማቴ. 3:17

12. የመታሰቢያው በዓል እስኪደርስ ድረስ ምን ማድረግ ትችላለህ?

12 የመታሰቢያው በዓል እስኪደርስ ድረስ በቤዛው ላይ ያተኮረ የግል ጥናት ወይም የቤተሰብ አምልኮ ፕሮጀክት ለማካሄድ ለምን አትሞክርም? የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮችን ወይም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መሣሪያዎችን ተጠቅመህ ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጥልቀት ያለው ምርምር ማድረግ ትችላለህ። d በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ ላይ የወጣውን የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አንብብ። በመታሰቢያው በዓል ዕለት ደግሞ ለዚያ ቀን የተዘጋጀውን ልዩ የማለዳ አምልኮ ፕሮግራም መመልከትህን አትርሳ። ለመታሰቢያው በዓል ልባችንን ካዘጋጀን ሌሎችም ከዚህ በዓል እንዲጠቀሙ መርዳት እንችላለን።—ዕዝራ 7:10

ሌሎች ከበዓሉ እንዲጠቀሙ መርዳት

13. ሌሎች ከመታሰቢያው በዓል እንዲጠቀሙ ለመርዳት በመጀመሪያ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 ሌሎች ከመታሰቢያው በዓል እንዲጠቀሙ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ልንጋብዛቸው ይገባል። በመደበኛው አገልግሎታችን ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች ከመጋበዝ በተጨማሪ ልንጋብዛቸው የምንችላቸውን ሌሎች ሰዎች ዘርዝረን መጻፍ እንችላለን። ከእነዚህ መካከል ዘመዶቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን የሚማሩ ልጆች እንዲሁም ሌሎች ይገኙበታል። በወረቀት የታተመው መጋበዣ በበቂ መጠን ባይኖረንም እንኳ መጋበዣው የሚገኝበትን ሊንክ መላክ እንችላለን። ምን ያህል ሰዎች ግብዣችንን እንደሚቀበሉ ማን ያውቃል?—መክ. 11:6

14. ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ መጋበዝ የሚያመጣውን ለውጥ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

14 ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ መጋበዝ የሚያመጣውን ለውጥ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የምትኖር አንዲት እህት፣ አንድ ቀን ባለቤቷ የመታሰቢያው በዓል ላይ አብሯት እንደሚገኝ በኩራት ሲነግራት በጣም ተደነቀች። የተደነቀችው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከዚያ ቀደም በበዓሉ ላይ እንዲገኝ ብዙ ጊዜ አበረታታው ነበር፤ እሱ ግን ተገኝቶ አያውቅም። ታዲያ አሁን ለመገኘት የወሰነው ለምንድን ነው? በግለሰብ ደረጃ የመጋበዣ ወረቀት ስለተሰጠው ነው፤ መጋበዣውን የሰጠው አንድ የሚያውቀው የጉባኤ ሽማግሌ ነው። ሰውየው በዚያ ዓመት ብቻ ሳይሆን በቀጣዮቹ ዓመታትም በበዓሉ ላይ ተገኝቷል።

15. ሰዎችን ለመታሰቢያው በዓል ስንጋብዝ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

15 የጋበዝናቸው ሰዎች፣ በተለይ በስብሰባዎቻችን ላይ ተገኝተው የማያውቁ ከሆነ ጥያቄ ሊኖራቸው እንደሚችል ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ምን ዓይነት ጥያቄ ሊያነሱ እንደሚችሉ ማሰብና መልስ ለመስጠት መዘጋጀት ይኖርብናል። (ቆላ. 4:6) ለምሳሌ አንዳንዶች እንዲህ ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ፦ ‘ፕሮግራሙ ምን ይመስላል?’ ‘ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?’ ‘ምን ዓይነት ልብስ መልበስ ይኖርብኛል?’ ‘የመግቢያ ክፍያ አለው?’ ‘ሙዳየ ምጽዋት ይዞራል?’ አንድን ሰው በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኝ ስንጋብዝ “ጥያቄ አለህ?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን፤ ከዚያም የሚያነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ ልንመልስለት እንችላለን። በተጨማሪም የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ እና በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የተባሉትን ቪዲዮዎች በመጠቀም ግለሰቡ ስብሰባዎቻችን ምን እንደሚመስሉ እንዲገነዘብ ልንረዳው እንችላለን። ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 28 ላይ የሚገኙትን ጠቃሚ ነጥቦችም ልናካፍለው እንችላለን።

16. በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙ ሰዎች ምን ተጨማሪ ጥያቄዎች ሊፈጠሩባቸው ይችላሉ?

16 እንግዶቻችን በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኙ በኋላ ተጨማሪ ጥያቄዎች ሊኖሯቸው ይችላሉ። ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የተካፈለ ሰው የሌለው ወይም ደግሞ የተካፈሉት ሰዎች ጥቂት ብቻ የሆኑት ለምን እንደሆነ ሊጠይቁ ይችላሉ። ከዚህም ሌላ የመታሰቢያውን በዓል የምናከብረው በየስንት ጊዜው እንደሆነ ይጠይቁ ይሆናል። ወይም ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉንም ስብሰባዎቻቸውን የሚያካሂዱት በዚህ መንገድ እንደሆነ ሊጠይቁ ይችላሉ። አብዛኞቹ ነጥቦች በመታሰቢያው በዓል ንግግር ላይ የሚብራሩ ቢሆንም እንግዶች ተጨማሪ ማብራሪያ ሊፈልጉ ይችላሉ። “የይሖዋ ምሥክሮች የጌታ ራትን የሚያከብሩበት መንገድ ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?” የሚለው በ​jw.org ላይ የሚገኘው ርዕስ አንዳንዶቹን ጥያቄዎች ለመመለስ ይረዳናል። “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ከመታሰቢያው በዓል የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ ከበዓሉ በፊት፣ በበዓሉ ወቅትም ሆነ ከበዓሉ በኋላ የቻልነውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።—ሥራ 13:48

የቀዘቀዙትን መርዳት

17. ሽማግሌዎች የቀዘቀዙትን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? (ሕዝቅኤል 34:12, 16)

17 በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ሽማግሌዎች የቀዘቀዙትን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? ፍቅራዊ አሳቢነት አሳዩአቸው። (ሕዝቅኤል 34:12, 16ን አንብብ።) ከመታሰቢያው በዓል በፊት በተቻለ መጠን ብዙ የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን ለማግኘት ሞክሩ። እንደምትወዷቸውና በማንኛውም መንገድ ልትረዷቸው እንደምትፈልጉ አረጋግጡላቸው። በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸው። በዓሉ ላይ ከተገኙ ደግሞ ሞቅ ያለ አቀባበል አድርጉላቸው። ከመታሰቢያው በዓል በኋላ ከእነዚህ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር መገናኘታችሁን ቀጥሉ። እንዲሁም ወደ ይሖዋ ለመመለስ የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውንም ድጋፍ አድርጉላቸው።—1 ጴጥ. 2:25

18. ሁላችንም የቀዘቀዙትን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (ሮም 12:10)

18 በጉባኤው ውስጥ ያሉ በሙሉ በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙትን የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች መርዳት ይችላሉ። እንዴት? እነሱን በፍቅር፣ በደግነትና በአክብሮት በመያዝ ነው። (ሮም 12:10ን አንብብ።) እነዚህ ውድ የይሖዋ በጎች በስብሰባው ላይ መገኘት ከብዷቸው ሊሆን እንደሚችል አትዘንጉ። ምናልባትም እነዚህ ሰዎች ጥሩ አቀባበል እንደማይደረግላቸው ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። e ስለዚህ የሚያሸማቅቁ ጥያቄዎች በመጠየቅ ወይም ስሜት የሚጎዳ ነገር በመናገር አታስጨንቋቸው። (1 ተሰ. 5:11) እነዚህ ወንድሞችና እህቶች የእምነት አጋሮቻችን ናቸው። አብረውን በድጋሚ ይሖዋን እንዲያገለግሉ እንመኛለን።—መዝ. 119:176፤ ሥራ 20:35

19. የመታሰቢያውን በዓል በማክበር ምን ጥቅም እናገኛለን?

19 ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በየዓመቱ እንድናከብር ማዘዙ ምን ያስገርማል? በዓሉን ስናከብር ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን በተለያዩ መንገዶች እንጠቅማለን። (ኢሳ. 48:17, 18) ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለን ፍቅር ያድጋል። ላደረጉልን ነገር ያለንን አድናቆት እናሳያለን። ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለንን አንድነት እናጠናክራለን። እንዲሁም ሌሎችም ቤዛው የሚያስገኛቸውን በረከቶች ማጣጣም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲማሩ መርዳት እንችል ይሆናል። እንግዲያው በዚህ ዓመት ውስጥ ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው ቀን፣ ይኸውም ለመታሰቢያው በዓል ዝግጁ ለመሆን የቻልነውን ሁሉ እናድርግ!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ለመታሰቢያው በዓል ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

  • ሌሎች ከመታሰቢያው በዓል እንዲጠቀሙ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

  • የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 18 ለቤዛው አመስጋኝ መሆን

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ርዕሶችና ቪዲዮዎች ለማግኘት በ​jw.org ላይ የሚገኘውን መፈለጊያ ተጠቀም።

b በሚያዝያ 2021 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

d ለምርምር የሚረዱ ሐሳቦች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

e ሥዕሎቹንና “ የጉባኤው አቀባበል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት። አንድ የቀዘቀዘ ወንድም ወደ ስብሰባ አዳራሹ ለመግባት ቢያመነታም ፍርሃቱን ያሸንፋል። ወንድሞች ሞቅ ያለ አቀባበል ያደርጉለታል፤ እሱም ከእነሱ ጋር ጥሩ ጊዜ ያሳልፋል።

f የሥዕሉ መግለጫ፦ በአንድ የዓለም ክፍል ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች የመታሰቢያውን በዓል ሲያከብሩ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለዚህ ልዩ በዓል ይዘጋጃሉ።