በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሴቶች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አለህ?

ለሴቶች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አለህ?

ከበርካታ ታማኝ ሴቶች ጋር አንድ ላይ የማገልገል ውድ መብት አለን። እነዚህን ታማኝና ታታሪ እህቶች a እንወዳቸዋለን፤ እንዲሁም በጣም እናደንቃቸዋለን! በመሆኑም ወንድሞች፣ እህቶቻችንን በደግነት፣ በፍትሕና በአክብሮት ለመያዝ ጥረት አድርጉ። ሆኖም ፍጽምና ስለሚጎድለን አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ማድረግ ሊከብደን ይችላል። አንዳንድ ወንድሞች ደግሞ እንቅፋት የሚሆንባቸው ሌላም ነገር አለ።

አንዳንዶች ያደጉት፣ ወንዶች ሴቶችን ዝቅ አድርገው በሚመለከቱባቸው ባሕሎች ውስጥ ነው። ለምሳሌ በቦሊቪያ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግለው ሃንስ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ወንዶች ያደጉት፣ ወንዶች ከፍ ተደርገው በሚታዩበት ባሕል ውስጥ ነው። እነዚህ ወንዶች ከሴቶች እንደሚበልጡ ስለሚሰማቸው ብዙውን ጊዜ ሴቶችን የሚይዙት አክብሮት በጎደለው መንገድ ነው።” ታይዋን ውስጥ በሽማግሌነት የሚያገለግለው ሸንግሺየን እንዲህ ብሏል፦ “ብዙዎቹ ወንዶች፣ ሴቶች በእነሱ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው ይሰማቸዋል። አንድ ወንድ፣ አንዲት ሴት የሰጠችውን ሐሳብ ካስተጋባ ሌሎች ወንዶች ሊንቁት ይችላሉ።” ሌሎች ወንዶች ደግሞ ለሴቶች ያላቸውን ንቀት የሚያሳዩት ስውር በሆኑ መንገዶች ነው። ለምሳሌ ሴቶችን የሚያቃልል ቀልድ ይናገሩ ይሆናል።

ደስ የሚለው፣ ማንኛውም ሰው ከባሕል ተጽዕኖ መላቀቅ ይችላል። ወንዶች ከሴቶች ይበልጣሉ የሚለውን ስሜትም ማሸነፍ ይችላል። (ኤፌ. 4:22-24) የይሖዋን ምሳሌ መከተላችን ይህን ለማድረግ ያግዘናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ይሖዋ ሴቶችን የሚይዘው እንዴት እንደሆነ፣ ወንድሞች ለሴቶች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ሽማግሌዎች ለእህቶች አክብሮት በማሳየት ረገድ ግንባር ቀደም መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ይሖዋ ሴቶችን የሚይዘው እንዴት ነው?

ይሖዋ ሴቶችን የሚይዝበት መንገድ ፍጹም ምሳሌ ይሆነናል። ሩኅሩኅ አባት ስለሆነ ሁሉንም ልጆቹን ይወዳቸዋል። (ዮሐ. 3:16) ታማኝ እህቶችንም እንደ ውድ ልጆቹ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ይሖዋ ሴቶችን በአክብሮት እንደሚይዝ ያሳየባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ ይይዛቸዋል። ይሖዋ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን የፈጠረው በራሱ መልክ ነው። (ዘፍ. 1:27) ወንዶችን የፈጠራቸው ከሴቶች የበለጠ ጥበብና ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጎ አይደለም፤ ከዚህም ሌላ ለወንዶች አያዳላም። (2 ዜና 19:7) ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመረዳትና ግሩም የሆኑትን ባሕርያቱን ለማንጸባረቅ የሚያስችል ተመሳሳይ አእምሯዊ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም ይሖዋ የወንዶችንም ሆነ የሴቶችን እምነት የሚመለከተው በእኩል ዓይን ነው፤ ሁለቱም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር እንዲሁም በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው የማገልገል መብት አላቸው። (2 ጴጥ. 1:1) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ ለወንዶች አያዳላም።

ይሰማቸዋል። ይሖዋ የሴቶች ስሜትና ጭንቀት ያሳስበዋል። ለምሳሌ ራሔልና ሐና ያቀረቡትን ጸሎት ሰምቶ መልሶላቸዋል። (ዘፍ. 30:22፤ 1 ሳሙ. 1:10, 11, 19, 20) ከዚህም ሌላ ይሖዋ፣ ሴቶችን ስላዳመጡ ወንዶች የሚገልጹ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጻፉ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም የይሖዋን መመሪያ በመከተል ሚስቱን ሣራን ሰምቷታል። (ዘፍ. 21:12-14) ንጉሥ ዳዊትም አቢጋኤልን ሰምቷታል። እንዲያውም እሱን እንድታነጋግረው የላካት ይሖዋ እንደሆነ ተሰምቶታል። (1 ሳሙ. 25:32-35) የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀው ኢየሱስ እናቱን ማርያምን ሰምቷታል። (ዮሐ. 2:3-10) እነዚህ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ይሖዋ ሴቶችን በአክብሮት እንደሚይዝ ያሳየበት አንዱ መንገድ እነሱን በመስማት ነው።

ይተማመንባቸዋል። ለምሳሌ ይሖዋ በሔዋን ስለተማመነባት ምድርን በማስተዳደሩ ሥራ እንድትካፈል ኃላፊነት ሰጥቷታል። (ዘፍ. 1:28) እንዲህ ማድረጉ ከባሏ ከአዳም እንደምታንስ አድርጎ ሳይሆን እንደ ማሟያ አድርጎ እንደተመለከታት ያሳያል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ነቢይቷ ዲቦራ እና ነቢይቷ ሕልዳና አንድን መስፍን እና አንድን ንጉሥ ጨምሮ ለሕዝቡ ምክር እንዲሰጡ ኃላፊነት የሰጣቸው መሆኑ እንደተማመነባቸው ያሳያል። (መሳ. 4:4-9፤ 2 ነገ. 22:14-20) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሴቶችም የሰጣቸውን ሥራ እንደሚያከናውኑ ይተማመንባቸዋል። እነዚህ ታማኝ እህቶች አስፋፊዎች፣ አቅኚዎችና ሚስዮናውያን ሆነው ያገለግላሉ። የስብሰባ አዳራሾችንና የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎችን ንድፍ በማውጣት፣ በመገንባትና በመጠገን ሥራ ይካፈላሉ። አንዳንዶቹ በቤቴል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በርቀት የትርጉም ቢሮዎች ውስጥ ያገለግላሉ። እነዚህ እህቶች፣ ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጠቀምባቸው ታላቅ ሠራዊት ናቸው። (መዝ. 68:11) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ ሴቶች ደካማ እንደሆኑ ወይም ብቃት እንደሌላቸው አይሰማውም።

ወንድሞች ለሴቶች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበር የሚችሉት እንዴት ነው?

እኛ ወንድሞች፣ ለክርስቲያን እህቶቻችን የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ያለን መሆኑን ለማረጋገጥ አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። እንዲህ ለማድረግ እርዳታ ያስፈልገናል። የራጅ ማሽን በልባችን ውስጥ ያለን በሽታ ለማወቅ እንደሚያስችል ሁሉ ጓደኞቻችንና የአምላክ ቃል ስለ ሴቶች በውስጣችን ተደብቆ ያለ አሉታዊ ስሜት ካለ ለማወቅ ይረዱናል። ታዲያ እንዲህ ያለውን እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

የቅርብ ወዳጅህን ጠይቅ። (ምሳሌ 18:17) ደግና ሚዛናዊ በመሆኑ የሚታወቅ የቅርብ ጓደኛችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቀው እንችላለን፦ “እህቶችን ስለምይዝበት መንገድ ምን ይሰማሃል? እንደማከብራቸው ይሰማቸዋል? እነሱን የምይዝበትን መንገድ ማሻሻል እንዳለብኝ ይሰማሃል?” ጓደኛህ ማሻሻል የምትችላቸውን ነገሮች ከጠቆመህ ሰበብ አስባብ አትደርድር። ከዚህ ይልቅ፣ አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ ሁን።

የአምላክን ቃል አጥና። እህቶቻችንን የምንይዝበት መንገድ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የሚያስችለን ከሁሉ የተሻለው መንገድ አመለካከታችንንና ድርጊታችንን ከአምላክ ቃል አንጻር መመዘን ነው። (ዕብ. 4:12) መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ሴቶችን በተገቢው መንገድ ስለያዙና ስላልያዙ ወንዶች እናነባለን። ከዚያም የእነሱን ድርጊት ከእኛ ጋር ማወዳደር እንችላለን። በተጨማሪም አንድ ጥቅስ ለሴቶች ያለንን ተገቢ ያልሆነ አመለካከት እንደሚደግፍልን አድርገን በተሳሳተ መንገድ እንዳንረዳው የተለያዩ ጥቅሶችን ማወዳደራችን ይጠቅመናል። ለምሳሌ 1 ጴጥሮስ 3:7 ሚስቶች “እንደ ተሰባሪ ዕቃ” b ሊከበሩ እንደሚገባ ይገልጻል። ታዲያ ይህ ሲባል የሴቶች ችሎታና ጥበብ ከወንዶች ያንሳል ማለት ነው? በፍጹም! ጴጥሮስ የጻፈውን ሐሳብ ከገላትያ 3:26-29 ጋር ማወዳደር እንችላለን። ጥቅሱ፣ ይሖዋ ሴቶችን ልክ እንደ ወንዶች በሰማይ ከኢየሱስ ጋር አብረው እንዲገዙ እንደመረጣቸው ይገልጻል። የአምላክን ቃል ካጠናንና ሴቶችን የምንይዝበትን መንገድ በተመለከተ የቅርብ ወዳጃችንን ከጠየቅን ለሴቶች ተገቢውን አክብሮት ማሳየት እንችላለን።

ሽማግሌዎች ለእህቶች አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች ለእህቶች አክብሮት ማሳየትን መማር የሚችሉበት ሌላው መንገድ አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎች የሚተዉትን ምሳሌ መከተል ነው። ሽማግሌዎች ለእህቶች አክብሮት በማሳየት ረገድ ግንባር ቀደም መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ መንገዶችን እስቲ እንመልከት።

እህቶችን ያመሰግናሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሽማግሌዎች ግሩም ምሳሌ ትቷል። በሮም ላለው ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በርካታ እህቶችን በይፋ አመስግኗል። (ሮም 16:12) የጳውሎስ ደብዳቤ ለጉባኤው በተነበበበት ወቅት እነዚህ እህቶች ምንኛ ተደስተው ይሆን! በተመሳሳይም ሽማግሌዎች፣ እህቶች ስላሏቸው መልካም ባሕርያት እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ስለሚያከናውኑት ሥራ ሊያመሰግኗቸው ይገባል። እንዲህ ማድረጋቸው እህቶች ምን ያህል እንደሚከበሩና እንደሚወደዱ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። ሽማግሌዎች የሚናገሩት የሚያበረታታ ቃል እህቶች ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ሊረዳቸው ይችላል።—ምሳሌ 15:23

አመስግኑ

ሽማግሌዎች ለእህቶች የሚሰጡት ምስጋና ከልብ የመነጨ ሊሆን ይገባል፤ እንዲሁም የሚያመሰግኑበትን ነጥብ ለይተው መጥቀስ ይኖርባቸዋል። ለምን? ጄሲካ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንዲት እህት ወንድሞች ‘እናመሰግናለን’ ሲሏት ደስ ይላታል። ሆኖም ወንድሞች የሚያመሰግኑበትን ነጥብ ለይተው ሲጠቅሱ ይበልጥ ደስ ይለናል። ለምሳሌ ልጆቻችን በስብሰባ ላይ ጸጥ ብለው እንዲያዳምጡ በማስተማራችን ወይም መሥዋዕት ከፍለን አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወደ ስብሰባ ይዘን በመምጣታችን ሲያመሰግኑን ደስ ይለናል።” ሽማግሌዎች አንድን ነጥብ ለይተው በመጥቀስ እህቶችን ሲያመሰግኑ እህቶች በጉባኤው ውስጥ እንደሚፈለጉና ከፍ ያለ ቦታ እንደሚሰጣቸው ይሰማቸዋል።

እህቶችን ይሰማሉ። ትሑት የሆኑ ሽማግሌዎች፣ ጥሩ ሐሳብ የሚያመነጩት እነሱ ብቻ እንደሆኑ አይሰማቸውም። እንዲህ ያሉት ሽማግሌዎች፣ እህቶች ምክረ ሐሳብ እንዲሰጡ ይጋብዛሉ፤ በሚናገሩበት ጊዜም በጥሞና ያዳምጧቸዋል። ሽማግሌዎች እንዲህ ማድረጋቸው እህቶችን ያበረታታል፤ እነሱንም ይጠቅማቸዋል። እንዴት? በቤቴል የሚያገለግል ሄራርዶ የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “እህቶችን አስተያየት መጠየቄ ሥራዬን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን ረድቶኛል። ብዙውን ጊዜ እህቶች በሥራው ላይ ከወንድሞች የበለጠ ተሞክሮ አላቸው።” በጉባኤ ውስጥ ደግሞ ብዙ እህቶች በአቅኚነት ስለሚያገለግሉ በክልላቸው ውስጥ ስላሉት ሰዎች ብዙ ነገር ያውቃሉ። ብራያን የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “እህቶቻችን ለድርጅቱ ማበርከት የሚችሉት ብዙ ነገር አለ። ስለዚህ ከተሞክሯቸው ተጠቀሙ!”

ስሙ

ጥበበኛ የሆኑ ሽማግሌዎች የእህቶችን ምክረ ሐሳብ ችላ አይሉም። ለምን? ኤድዋርድ የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “የእህቶች አመለካከትና ተሞክሮ አንድ ወንድም ጉዳዩን ሰፋ ባለ ዓይን እንዲያይ ሊረዳው ይችላል፤ ከዚህም በተጨማሪ የሌሎችን ስሜት የመረዳት ችሎታ እንዲያዳብር ያግዘዋል።” (ምሳሌ 1:5) አንድ ሽማግሌ አንዲት እህት የሰጠችውን ሐሳብ በሥራ ላይ ማዋል ባይችል እንኳ ሐሳብ ለመስጠትና ተሞክሮዋን ለማካፈል ፈቃደኛ በመሆኗ ሊያመሰግናት ይችላል።

እህቶችን ያሠለጥናሉ። አስተዋይ ሽማግሌዎች እህቶችን ለማሠልጠን አጋጣሚ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ የተጠመቀ ወንድም በማይኖርበት ጊዜ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን እንዲመሩ እህቶችን ሊያሠለጥኑ ይችላሉ። በቲኦክራሲያዊ የግንባታና የጥገና ፕሮጀክቶች መካፈል እንዲችሉ አንዳንድ መሣሪያዎችን መጠቀምና ማሽኖችን ማንቀሳቀስ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ሊያሠለጥኗቸው ይችላሉ። ቤቴል ውስጥ ደግሞ የበላይ ተመልካቾች፣ እህቶች የተለያዩ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ አሠልጥነዋል፤ ከእነዚህ መካከል ጥገና፣ ዕቃ ግዢ፣ የሒሳብ አያያዝ እንዲሁም የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ይገኙበታል። ሽማግሌዎች እህቶችን ማሠልጠናቸው እህቶችን ብቃት እንዳላቸውና እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ያሳያል።

አሠልጥኑ

በርካታ እህቶች ከሽማግሌዎች ያገኙትን ሥልጠና ሌሎችን ለመርዳት ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ እህቶች ከግንባታ ሥራ ጋር በተያያዘ ያገኙትን ሥልጠና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ቤታቸው የፈረሰባቸውን ወንድሞች ለመርዳት ይጠቀሙበታል። አንዳንድ እህቶች ደግሞ ከአደባባይ ምሥክርነት ጋር በተያያዘ ያገኙትን ሥልጠና በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ የሚካፈሉ ተጨማሪ እህቶችን ለማሠልጠን ይጠቀሙበታል። እህቶች ስለሚያሠለጥኗቸው ሽማግሌዎች ምን ይሰማቸዋል? ጄኒፈር የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ስካፈል የበላይ ተመልካቹ ጊዜ ወስዶ አሠለጠነኝ። ያከናወንኩትን ሥራ በማስተዋል አመሰገነኝ። እንደምፈለግና እንደምታመን ስለተሰማኝ ከእሱ ጋር መሥራት ያስደስተኝ ነበር።”

እህቶችን እንደ ቤተሰብ መያዝ ያለው ጥቅም

ልክ እንደ ይሖዋ እኛም ታማኝ እህቶቻችንን እንወዳቸዋለን! በመሆኑም እንደ ቤተሰባችን አድርገን እንይዛቸዋለን። (1 ጢሞ. 5:1, 2) ከእነሱ ጋር አብረን በማገልገላችን ክብርና ኩራት ይሰማናል። እንደምንወዳቸውና እንደምንደግፋቸው ሲሰማቸው እንደሰታለን። ቫኔሳ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የድርጅቱ ክፍል እንድሆን ስለፈቀደልኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ድርጅቱ መንፈስን በሚያድሱ ወንድሞች የተሞላ ነው።” በታይዋን የምትኖር አንዲት እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋና ድርጅቱ ለእኛ ለሴቶችና ለስሜታችን ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ይህ መሆኑ እምነቴን ያጠናክርልኛል፤ እንዲሁም የይሖዋ ድርጅት ክፍል የመሆን መብቴን ይበልጥ እንዳደንቀው ያደርገኛል።”

ይሖዋ፣ ታማኝ የሆኑ ክርስቲያን ወንዶች ለሴቶች የእሱ ዓይነት አመለካከት ለማዳበርና እሱ በሚይዛቸው መንገድ ለመያዝ ጥረት ሲያደርጉ በጣም ይኮራባቸዋል። (ምሳሌ 27:11) በስኮትላንድ የሚኖር ቤንጃሚን የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ዓለም ለሴቶች ያለው አመለካከት በጣም ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ ሴቶች ወደ ስብሰባ አዳራሻችን ሲገቡ ለውጡ እንዲታወቃቸው እንፈልጋለን።” ሁላችንም ለውድ እህቶቻችን የሚገባቸውን ፍቅርና አክብሮት በማሳየት ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል።—ሮም 12:10

a በዚህ ርዕስ ውስጥ “እህቶች” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የሥጋ እህቶቻችንን ሳይሆን ክርስቲያን እህቶቻችንን ነው።

b “ተሰባሪ ዕቃ” የሚለውን አገላለጽ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በግንቦት 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ከፍተኛ ዋጋ ያለው ‘ተሰባሪ ዕቃ’” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም በመጋቢት 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ለባለ ትዳሮች የሚሆን ጥበብ ያዘለ መመሪያ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።