በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 6

መዝሙር 10 ይሖዋ አምላካችንን አወድሱ!

“የይሖዋን ስም አወድሱ”

“የይሖዋን ስም አወድሱ”

“እናንተ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ውዳሴ አቅርቡ፤ የይሖዋን ስም አወድሱ።”መዝ. 113:1

ዓላማ

በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ የይሖዋን ቅዱስ ስም ለማወደስ የሚያነሳሳን ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

1-2. ይሖዋ ስሙ በመጥፋቱ የተሰማውን ስሜት ለመረዳት የሚያግዘን ምንድን ነው?

 አንድ የምትቀርበው ሰው ስለ አንተ መጥፎ ነገር ተናገረ እንበል። አንተ ወሬው ውሸት እንደሆነ ታውቃለህ፤ አንዳንዶች ግን አመኑት። ይባስ ብሎ ደግሞ ያንን ውሸት ማሰራጨት ጀመሩ። በዚህም የተነሳ ሌሎች ብዙ ሰዎች ውሸቱን አመኑ። በዚህ ጊዜ ምን ይሰማሃል? ስለ ሰዎችና ስለ መልካም ስምህ የምታስብ ከሆነ ስምህ መጥፋቱ እንደሚያናድድህ ጥያቄ የለውም።—ምሳሌ 22:1

2 ይህ ሁኔታ ይሖዋ ስሙ በጠፋ ጊዜ ምን እንደተሰማው እንድንረዳ ያግዘናል። ከመንፈሳዊ ልጆቹ አንዱ ለመጀመሪያዋ ሴት ለሔዋን ይሖዋን በተመለከተ ውሸት ነገራት። እሷም ይህን ውሸት አመነች። ይህ ውሸት የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን በይሖዋ ላይ እንዲያምፁ አደረጋቸው። በዚህም የተነሳ የሰው ልጆች በኃጢአትና በሞት ቀንበር ሥር ወደቁ። (ዘፍ. 3:1-6፤ ሮም 5:12) ሞትን፣ ጦርነትንና መከራን ጨምሮ በዓለም ላይ የምናያቸው ችግሮች በሙሉ የጀመሩት ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ ይህን ውሸት በመናገሩ ነው። ይሖዋ ስሙ በመጥፋቱና በዚህም የተነሳ በሰው ልጆች ላይ መከራ በመምጣቱ ምን ተሰማው? በጣም እንዳዘነ ምንም ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን ይሖዋ ብስጩ አልሆነም። እንዲያውም አሁንም ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው።—1 ጢሞ. 1:11

3. ምን ልዩ መብት አለን?

3 “የይሖዋን ስም አወድሱ” የሚለውን ቀላል ትእዛዝ ከታዘዝን ለይሖዋ ስም መቀደስ የበኩላችንን አስተዋጽኦ የማበርከት ልዩ መብት እናገኛለን። (መዝ. 113:1) እንዲህ የምናደርገው በዚህ ቅዱስ ስም ስለሚጠራው አምላክ መልካም ነገር በመናገር ነው። አንተስ እንዲህ ታደርጋለህ? የአምላካችንን ስም በሙሉ ልብ ለማወደስ የሚያነሳሱንን ሦስት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ ስሙን ስናወድስ ይደሰታል

4. ይሖዋ ስናወድሰው የሚደሰተው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 የሰማዩ አባታችን ስሙን ስናወድስ ይደሰታል። (መዝ. 119:108) ታዲያ ይህ ሲባል፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የበታችነት ስሜት እንደሚሰማቸው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ውዳሴ ያስፈልገዋል ማለት ነው? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንዲት ትንሽ ልጅ አባቷ ላይ ጥምጥም ብላ “እንደ አንተ ዓይነት አባት የትም የለም!” ብትለው አባትየው ይደሰታል፤ እንዲያውም ባደረገችው ነገር ልቡ ይነካል። ለምን? ከልጁ ውዳሴ መቀበል የሚያስፈልገው የበታችነት ስሜት የሚሰማው ሰው ስለሆነ ነው? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ የልጁን ፍቅርና አድናቆት ሲመለከት የሚደሰት ጥሩ አባት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን። ልጁ አፍቃሪና አመስጋኝ መሆኗ እያደገች ስትሄድ ደስተኛ እንድትሆን እንደሚረዳት ያውቃል። ታላቁ አባታችን ይሖዋም ስናወድሰው የሚደሰተው ለዚህ ነው።

አንድ አባት ልጆቹ ፍቅራቸውንና አድናቆታቸውን ሲገልጹለት እንደሚደሰት ሁሉ ይሖዋም ስሙን ስናወድስ ይደሰታል (አንቀጽ 4⁠ን ተመልከት)


5. የአምላክን ስም በማወደስ የትኛውን ውሸት ማጋለጥ እንችላለን?

5 የሰማዩን አባታችንን ስናወድስ እኛን የሚመለከትን አንድ ውሸት ለማጋለጥ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። ሰይጣን ማንም ሰው በታማኝነት ለአምላክ ስም ጥብቅና አይቆምም ብሎ ተከራክሯል። እንደ እሱ አባባል ከሆነ ማናችንም ንጹሕ አቋማችንን አንጠብቅም። ለአምላክ ጀርባችንን መስጠት ጥቅም እንደሚያስገኝልን እስከተሰማን ድረስ ማናችንም ብንሆን ይህን ከማድረግ ወደኋላ እንደማንል ተናግሯል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4) ሆኖም ታማኙ ኢዮብ፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አጋልጧል። አንተስ? እያንዳንዳችን ለአባታችን ስም ጥብቅና የመቆምና እሱን በታማኝነት በማገልገል ልቡን የማስደሰት ውድ መብት አለን። (ምሳሌ 27:11) በእርግጥም ይህ ታላቅ ክብር ነው።

6. ንጉሥ ዳዊትንና ሌዋውያኑን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? (ነህምያ 9:5)

6 የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ለእሱ ያላቸው ፍቅር ስሙን በሙሉ ልባቸው እንዲያወድሱት ያነሳሳቸዋል። ንጉሥ ዳዊት “ይሖዋን ላወድስ፤ ሁለንተናዬ ቅዱስ ስሙን ያወድስ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 103:1) ዳዊት የይሖዋን ስም ማወደስ ይሖዋን ራሱን ማወደስ እንደሆነ ተገንዝቧል። የይሖዋ ስም ማንነቱን ማለትም ያሉትን ግሩም ባሕርያትና ያከናወናቸውን አስደናቂ ሥራዎች ያካትታል። ዳዊት የአባቱን ስም እንደ ቅዱስ ለመመልከትና ለማወደስ ተነሳስቷል። ይህን ማድረግ የፈለገው ደግሞ ‘በሁለንተናው’ ማለትም በሙሉ ልቡ ነው። በተመሳሳይም ሌዋውያን ግንባር ቀደም ሆነው ይሖዋን አወድሰዋል። የይሖዋ ቅዱስ ስም የሚገባውን ውዳሴ በቃላት ሊገልጹት እንደማይችሉ በትሕትና ተናግረዋል። (ነህምያ 9:5ን አንብብ።) ይሖዋ እንዲህ ባለው ትሕትና የተንጸባረቀበት ልባዊ ውዳሴ እንደተደሰተ ምንም ጥያቄ የለውም።

7. በአገልግሎታችንና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ይሖዋን ማወደስ የምንችለው እንዴት ነው?

7 በዛሬው ጊዜም ቅንዓት፣ አመስጋኝነትና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ስለ ይሖዋ በመናገር እሱን ማስደሰት እንችላለን። አገልግሎት ስንወጣ ዋነኛው ዓላማችን ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ እንዲሁም ለሰማዩ አባታችን የእኛ ዓይነት አመለካከት እንዲያዳብሩ መርዳት እንደሆነ አንዘነጋም። (ያዕ. 4:8) ለሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚል ማለትም እንደ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ኃይል ያሉትን ባሕርያቱን እንዴት አድርጎ እንደሚገልጽ ስናሳያቸው ደስ ይለናል። በተጨማሪም ይሖዋን ለመምሰል የቻልነውን ሁሉ በማድረግ እሱን ማወደስና ማስደሰት እንችላለን። (ኤፌ. 5:1) እንዲህ ስናደርግ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ካሉት ሰዎች የተለየን እንደሆንን ይታያል። (ማቴ. 5:14-16) ሰዎች የተለየን መሆናችንን ሲያስተውሉ ምክንያቱን ማወቅ ይፈልጉ ይሆናል። በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከሰዎች ጋር ስንገናኝ የተለየን የሆንበትን ምክንያት ልናብራራላቸው እንችላለን። በዚህም የተነሳ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ አምላካችን ለመቅረብ ይነሳሳሉ። በእነዚህ መንገዶች ይሖዋን ስናወድስ ልቡን እናስደስታለን።—1 ጢሞ. 2:3, 4

የይሖዋን ስም ስናወድስ ኢየሱስን እናስደስተዋለን

8. ኢየሱስ የይሖዋን ስም በማወደስ ረገድ ግንባር ቀደም የሆነው እንዴት ነው?

8 በሰማይም ሆነ በምድር ካሉት ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታት መካከል የወልድን ያህል አብን የሚያውቅ ማንም የለም። (ማቴ. 11:27) ኢየሱስ አባቱን ይወደዋል፤ እንዲሁም የአባቱን ስም በማወደስ ረገድ ግንባር ቀደም ሆኗል። (ዮሐ. 14:31) ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ ምድራዊ አገልግሎቱን ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ “ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ” ብሏል። (ዮሐ. 17:26) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር?

9. ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ በግልጽ ለማሳየት የትኛውን ምሳሌ ተጠቅሟል?

9 ኢየሱስ ለሰዎች የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ከማሳወቅ ያለፈ ነገር አድርጓል። ኢየሱስ ያስተማራቸው አይሁዳውያን ቀድሞውንም የአምላክን ስም ያውቃሉ። ሆኖም ኢየሱስ ግንባር ቀደም ሆኖ ስለ እሱ ‘ገልጿል።’ (ዮሐ. 1:17, 18) ለምሳሌ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ መሐሪና ሩኅሩኅ እንደሆነ ይናገራሉ። (ዘፀ. 34:5-7) ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅና ስለ አባቱ የሚገልጸውን ምሳሌ በተናገረበት ወቅት ይህንን እውነት ይበልጥ ግልጽ አድርጎታል። አባትየው ንስሐ የገባውን ልጁን ‘ገና ሩቅ ሳለ እንዳየው፣’ ሮጦ ሄዶ እንደተቀበለው፣ እንዳቀፈው እንዲሁም በሙሉ ልቡ ይቅር እንዳለው ስናነብ የይሖዋ ምሕረትና ርኅራኄ ግልጽ ሆኖ ይታየናል። (ሉቃስ 15:11-32) በእርግጥም ኢየሱስ የአባቱን እውነተኛ ማንነት ገልጦልናል።

10. (ሀ) ኢየሱስ የአባቱን የግል ስም እንደተጠቀመና ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ ይፈልግ እንደነበረ እንዴት እናውቃለን? (ማርቆስ 5:19) (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?

10 ኢየሱስ ሌሎች ሰዎችስ የአባቱን የግል ስም እንዲጠቀሙ ይፈልግ ነበር? ምንም ጥያቄ የለውም። በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ አክራሪ የሃይማኖት መሪዎች ‘የአምላክ ስም በጣም ቅዱስ ከመሆኑ የተነሳ ሊጠራ አይገባም’ የሚል አመለካከት ሳይኖራቸው አይቀርም። ኢየሱስ ግን እንዲህ ያሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች የአባቱን ስም ከማክበር እንዲያግዱት አልፈቀደም። ለምሳሌ ኢየሱስ በጌርጌሴኖን ክልል አጋንንት የያዘውን ሰው በፈወሰ ጊዜ የሆነውን ነገር እንመልከት። ሰዎቹ በጣም ስለፈሩ ኢየሱስ አካባቢያቸውን ለቆ እንዲሄድ ተማጸኑት፤ በመሆኑም ኢየሱስ እዚያ አልቆየም። (ማር. 5:16, 17) ያም ቢሆን ኢየሱስ በዚያ አካባቢ የይሖዋ ስም እንዲታወቅ ፈልጎ ነበር። በመሆኑም የፈወሰውን ሰው፣ እሱ ያደረገለትን ሳይሆን ይሖዋ ያደረገለትን ነገር ለሌሎች እንዲናገር አዘዘው። (ማርቆስ 5:19ን አንብብ።) a በዛሬው ጊዜም ይህንኑ እንድናደርግ ማለትም የአባቱን ስም ለመላው ዓለም እንድናሳውቅ ይፈልጋል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ይህን ስናደርግ ንጉሣችንን ኢየሱስን እናስደስተዋለን።

ኢየሱስ፣ አጋንንት ያስወጣለትን ሰው ይሖዋ ያደረገለትን ነገር ለሰዎች እንዲናገር አዞታል (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)


11. ኢየሱስ ተከታዮቹን ምን ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ሕዝቅኤል 36:23)

11 ኢየሱስ፣ የይሖዋ ዓላማ ስሙን መቀደስ ማለትም ከማንኛውም ነቀፋ ነፃ እንዲሆን ማድረግ እንደሆነ ያውቃል። ጌታችን፣ ተከታዮቹ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ለዚህ ነው። (ማቴ. 6:9) ኢየሱስ ሁሉንም ፍጥረታት የሚመለከተው ወሳኝ ጉዳይ ይህ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ሕዝቅኤል 36:23ን አንብብ።) በጽንፈ ዓለም ውስጥ ካሉ ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታት መካከል የኢየሱስን ያህል የይሖዋን ስም ለማስቀደስ ጥረት ያደረገ ማንም የለም። ሆኖም ኢየሱስ በታሰረ ጊዜ ጠላቶቹ የከሰሱት ምን ብለው ነው? አምላክን ተሳድቧል ብለው ነው! ኢየሱስ የአባቱን ቅዱስ ስም መሳደብ ከኃጢአቶች ሁሉ የከፋው እንደሆነ እንደሚሰማው ምንም ጥያቄ የለውም። በዚህ ኃጢአት መከሰሱ በጣም ረብሾት ነበር። ኢየሱስ ከመያዙ በፊት በነበሩት ሰዓታት “በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ” የነበረው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።—ሉቃስ 22:41-44

12. ኢየሱስ ከሁሉ በላቀ መንገድ የአባቱን ስም ያስቀደሰው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ የአባቱን ስም ለማስቀደስ ሲል የደረሰበትን ስድብ፣ ሥቃይና የሐሰት ክስ በጽናት ተቋቁሟል። አባቱን ሙሉ በሙሉ እንደታዘዘ ስለሚያውቅ የሚያፍርበት ነገር አልነበረውም። (ዕብ. 12:2) በእነዚያ አስጨናቂ ሰዓታት በቀጥታ ጥቃት እየሰነዘረበት ያለው ሰይጣን እንደሆነም ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 22:2-4፤ 23:33, 34) ሰይጣን፣ ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን ያላላል ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር። ሆኖም የሰይጣን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል! ኢየሱስ፣ ሰይጣን የለየለት ውሸታም እንደሆነና ይሖዋ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ታማኝ አገልጋዮች እንዳሉት በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል።

13. ንጉሣችንን ማስደሰት የምትችለው እንዴት ነው?

13 አንተስ ንጉሣችንን ማስደሰት ትፈልጋለህ? ከሆነ የይሖዋን ስም ማወደስህን ቀጥል። ሰዎች የአምላካችንን አስደናቂ ማንነት እንዲያውቁ እርዳቸው። እንዲህ በማድረግ የኢየሱስን ፈለግ ትከተላለህ። (1 ጴጥ. 2:21) እንደ ኢየሱስ ይሖዋን ታስደስተዋለህ፤ እንዲሁም ጠላቱ ሰይጣን ውሸታም እንደሆነ ታጋልጣለህ።

የይሖዋን ስም ስናወድስ የሰዎችን ሕይወት እናድናለን

14-15. ሰዎችን ስለ ይሖዋ ስናስተምር የትኞቹ አስደናቂ ውጤቶች ይገኛሉ?

14 የይሖዋን ስም ስናወድስ የሰዎችን ሕይወት እናድናለን። እንዴት? ሰይጣን “የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል።” (2 ቆሮ. 4:4) በዚህም የተነሳ እነዚህ ሰዎች እንደሚከተሉት ያሉትን ሰይጣናዊ ውሸቶች ያምናሉ፦ አምላክ የለም፤ አምላክ ከእኛ የራቀ ነው፤ ለሰው ልጆችም አያስብም፤ አምላክ ጨካኝ ነው፤ ኃጢአተኞችን ለዘላለም ያሠቃያል። እንዲህ ያሉት ውሸቶች ዓላማቸው የአምላክን ስም በመሰወር ወይም በማጠልሸት ሰዎች ወደ እሱ ለመቅረብ ምንም ፍላጎት እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው። ይሁንና ሥራችን የሰይጣን ዓላማ እንዳይሳካ ያደርጋል። ለሰዎች ስለ አባታችን እውነቱን በማስተማር የአምላካችንን ቅዱስ ስም እናወድሳለን። ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል?

15 በአምላክ ቃል ውስጥ ያለው እውነት ትልቅ ኃይል አለው። ሰዎችን ስለ ይሖዋና ስለ ባሕርያቱ ስናስተምራቸው አስደናቂ ውጤት እናያለን። በሰይጣናዊ ውሸት የታወረው ዓይናቸው ቀስ በቀስ ይበራል፤ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ውድ የሆነውን አባታችንን እኛ በምናየው መንገድ ማየት ይጀምራሉ። ገደብ የለሽ ኃይሉ ያስደምማቸዋል። (ኢሳ. 40:26) ፍጹም የሆነው ፍትሑ እንዲተማመኑበት ያደርጋቸዋል። (ዘዳ. 32:4) ጥልቅ ከሆነው ጥበቡ ብዙ ትምህርት ያገኛሉ። (ኢሳ. 55:9፤ ሮም 11:33) እንዲሁም እሱ ፍቅር መሆኑን ማወቃቸው ያጽናናቸዋል። (1 ዮሐ. 4:8) ወደ ይሖዋ ሲቀርቡ ልጆቹ ሆነው ለዘላለም የመኖር ተስፋቸው የተረጋገጠ ይሆናል። ሰዎች ወደ አባታቸው እንዲቀርቡ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የሥራ ባልደረቦቹ አድርጎ ይመለከተናል።—1 ቆሮ. 3:5, 9

16. አንዳንዶች የአምላክን ስም ሲማሩ ምን ይሰማቸዋል? ምሳሌ ስጥ።

16 ለሰዎች መጀመሪያ ላይ የምናስተምራቸው የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ብቻ ሊሆን ይችላል። ይህ በራሱ ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። ክርስቲያን ባልሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያደገችውን አሊያ b የተባለች ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሃይማኖቷ አላረካትም ነበር፤ ከአምላክ ጋርም ምንም ዓይነት ዝምድና አልነበራትም። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ከጀመረች በኋላ ግን ሁኔታዎች ተቀየሩ። አምላክን እንደ ወዳጇ አድርጋ ማየት ጀመረች። የአምላክ ስም ከብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ እንደወጣና እንደ ጌታ ባሉት የማዕረግ ስሞች እንደተተካ ስታውቅ በጣም ተገረመች። የይሖዋን ስም ስትማር ሕይወቷ ተቀየረ። “የቅርብ ወዳጄን ስም አወቅኩት!” ብላ በደስታ ተናግራለች። ውጤቱስ ምን ሆነ? እንዲህ ብላለች፦ “አሁን ውስጣዊ ሰላም አለኝ። ትልቅ መብት እንዳገኘሁ ይሰማኛል።” ስቲቭ የተባለ አንድ ሙዚቀኛ ደግሞ ቤተሰቦቹ አክራሪ አይሁዳውያን ነበሩ። ሆኖም በሃይማኖቶች ውስጥ ብዙ ግብዝነት ስላየ የየትኛውም ሃይማኖት አባል አልነበረም። በአንድ ወቅት ግን ሐዘን አጋጠመው፤ በዚህ ጊዜ በአንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ተገኘ። የአምላክን ስም ሲያውቅ ልቡ በጥልቅ ተነካ። “የአምላክን ስም ጨርሶ ሰምቼ አላውቅም ነበር” ብሏል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ በእርግጥ እንዳለ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ተረዳሁ። አምላክ እውን ሆነልኝ። ወዳጅ እንዳገኘሁ ገባኝ።”

17. የይሖዋን ስም ማወደስህን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

17 በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ስትካፈል ለሰዎች “ይሖዋ” የተባለውን ቅዱስ ስም ትነግራቸዋለህ? የአምላካችንን ባሕርያት እንዲያውቁስ ትረዳቸዋለህ? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የአምላክን ስም ታወድሳለህ። ሰዎች ይሖዋ በሚለው ስም የሚጠራውን አምላክ እንዲያውቁ በመርዳት የይሖዋን ቅዱስ ስም ማወደስህን እንድትቀጥል ምኞታችን ነው። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የሰዎችን ሕይወት ታድናለህ። የንጉሣችንን የክርስቶስ ኢየሱስን ፈለግ ትከተላለህ። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ አፍቃሪውን አባታችንን ይሖዋን ታስደስታለህ። እንግዲያው ‘ለዘላለም ስሙን አወድስ!’—መዝ. 145:2

ለሰዎች የይሖዋን ስም በመንገርና እሱ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ በማስተማር ስሙን እናወድሳለን (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

የአምላክን ስም ማወደሳችን . . .

  • ይሖዋን የሚያስደስተው እንዴት ነው?

  • ክርስቶስ ኢየሱስን የሚያስደስተው እንዴት ነው?

  • የሰዎችን ሕይወት የሚያድነው እንዴት ነው?

መዝሙር 2 ስምህ ይሖዋ ነው

a ማርቆስ፣ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ሲጽፍ መለኮታዊውን ስም እንደተጠቀመ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አለ። በመሆኑም አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ጥቅስ ላይ “ይሖዋ” የሚለውን ስም ይጠቀማል።

b ስሞቹ ተቀይረዋል።