በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 7

መዝሙር 51 ራሳችንን ለአምላክ ወስነናል!

ከናዝራውያን የምናገኛቸው ትምህርቶች

ከናዝራውያን የምናገኛቸው ትምህርቶች

“ናዝራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ ለይሖዋ ቅዱስ ይሆናል።”ዘኁ. 6:8

ዓላማ

የናዝራውያን ምሳሌ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስና ድፍረት በማሳየት ይሖዋን ለማገልገል የሚረዳን እንዴት ነው?

1. የይሖዋ አገልጋዮች በታሪክ ዘመናት ሁሉ የትኛውን ግሩም ዝንባሌ አሳይተዋል?

 ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ከፍ አድርገህ ትመለከተዋለህ? እንደምትመለከተው ጥያቄ የለውም! እንደዚህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ከጥንት ዘመን አንስቶ እንዲህ የተሰማቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች አሉ። (መዝ. 104:33, 34) ብዙዎች ይሖዋን ለማምለክ መሥዋዕት ከፍለዋል። በጥንቷ እስራኤል የኖሩት ናዝራውያን ለዚህ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ናዝራውያን እነማን ነበሩ? ከእነሱ ምሳሌስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

2. (ሀ) ናዝራውያን እነማን ነበሩ? (ዘኁልቁ 6:1, 2) (ለ) አንዳንድ እስራኤላውያን የናዝራዊነት ስእለት ለመሳል የሚመርጡት ለምንድን ነው?

2 “ናዝራዊ” የሚለው ቃል “ተነጥሎ የወጣ፣” “ለአንድ ነገር የተወሰነ” ወይም “ለአንድ ዓላማ የተለየ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ ነው። ይህ ቃል፣ ይሖዋን ልዩ በሆነ መንገድ ለማገልገል ሲሉ አንዳንድ መሥዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኛ የነበሩትን ቀናተኛ እስራኤላውያን ጥሩ አድርጎ ይገልጻቸዋል። የሙሴ ሕግ፣ አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ለይሖዋ ልዩ ስእለት በመሳል ለተወሰነ ጊዜ ያህል ናዝራዊ ሆነው ለመኖር መምረጥ እንደሚችሉ ይናገራል። a (ዘኁልቁ 6:1, 2ን አንብብ።) አንድ ሰው እንዲህ ያለውን ስእለት ከተሳለ፣ ሌሎች እስራኤላውያን እንዲታዘዙ የማይጠበቅባቸውን አንዳንድ መመሪያዎች መታዘዝ ይጠበቅበታል። ታዲያ አንድ እስራኤላዊ የናዝራዊነት ስእለት ለመሳል የሚመርጠው ለምንድን ነው? እንዲህ ያለውን ስእለት ለመሳል የሚያነሳሳው ለይሖዋ ያለው ጥልቅ ፍቅርና ከእሱ ላገኛቸው በረከቶች ያለው ልባዊ አድናቆት እንደሆነ ግልጽ ነው።—ዘዳ. 6:5፤ 16:17

3. በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ከናዝራውያን ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

3 የሙሴ ሕግ ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሲተካ የናዝራዊነት ዝግጅት አበቃ። (ገላ. 6:2፤ ሮም 10:4) ሆኖም ልክ እንደ ናዝራውያን ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችም እሱን በሙሉ ልባቸው፣ በሙሉ ነፍሳቸው፣ በሙሉ አእምሯቸውና በሙሉ ኃይላቸው የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። (ማር. 12:30) ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን እንዲህ ለማድረግ በፈቃደኝነት እንሳላለን። ይህን ስእለት ለመፈጸም ለይሖዋ ፈቃድ ራሳችንን ማስገዛትና መሥዋዕት መክፈል ይኖርብናል። ናዝራውያን ስእለታቸውን ይፈጽሙ የነበረው እንዴት እንደሆነ በመመርመር እኛም የተሳልነውን ስእለት ለመፈጸም የሚረዱንን ጠቃሚ ትምህርቶች ማግኘት እንችላለን። b (ማቴ. 16:24) አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ አሳዩ

4. በዘኁልቁ 6:3, 4 መሠረት የናዝራውያን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚፈተነው እንዴት ነው?

4 ዘኁልቁ 6:3, 4ን አንብብ። ናዝራውያን ከማንኛውም ዓይነት የአልኮል መጠጥ እንዲሁም የወይን ፍሬንና ዘቢብን ጨምሮ ከወይን ተክል ከተዘጋጀ ከማንኛውም ነገር መራቅ ነበረባቸው። ሌሎች እስራኤላውያን እነዚህን ምግቦች ዘወትር መመገብ ይችላሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ምግቦችና መጠጦች በራሳቸው ምንም ችግር የለባቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ” የአምላክ ስጦታ እንደሆነ ይናገራል። (መዝ. 104:14, 15) ያም ቢሆን ናዝራውያን እንዲህ ባሉ ነገሮች የመደሰት መብታቸውን በፈቃደኝነት መሥዋዕት አድርገዋል። c

እንደ ናዝራውያን መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ነህ? (ከአንቀጽ 4-6⁠ን ተመልከት)


5. ማዲያን እና ማርሴላ ምን ዓይነት መሥዋዕት ለመክፈል መርጠዋል? ለምንስ?

5 እኛም ልክ እንደ ናዝራውያን ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለማገልገል ስንል አንዳንድ ነገሮችን መሥዋዕት እናደርጋለን። ማዲያን እና ማርሴላ ያደረጉትን ነገር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። d እነዚህ ክርስቲያን ባልና ሚስት የተመቻቸ ሕይወት ነበራቸው። ማዲያን ጥሩ ሥራ ስለነበረው በሚያምር አፓርታማ ውስጥ ይኖሩ ነበር። ሆኖም በይሖዋ አገልግሎት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማሳደግ ፈለጉ። እዚህ ግባቸው ላይ ለመድረስ ሲሉ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ወሰኑ። እንዲህ ብለዋል፦ “ወጪያችንን መቀነስ ጀመርን። አነስ ወዳለች አፓርታማ ተዛወርን፤ እንዲሁም መኪናችንን ሸጥን።” ማዲያን እና ማርሴላ እንዲህ ያለውን መሥዋዕት የመክፈል ግዴታ አልነበረባቸውም። ሆኖም አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ለመክፈል መርጠዋል። ውሳኔያቸው ደስታና እርካታ አስገኝቶላቸዋል።

6. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች መሥዋዕት የሚከፍሉት ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ አንዳንድ ነገሮችን በደስታ መሥዋዕት ያደርጋሉ። (1 ቆሮ. 9:3-6) ይሖዋ እንዲህ ያሉ መሥዋዕቶችን እንድንከፍል አይጠብቅብንም፤ እንዲሁም መሥዋዕት የምናደርጋቸው ነገሮች በራሳቸው ስህተት አይደሉም። ለምሳሌ አንዳንዶች የሚወዱትን ሥራ፣ ቤታቸውን ወይም የሚወዷቸውን ሌሎች ነገሮች መሥዋዕት ያደርጉ ይሆናል። ብዙዎች ለተወሰነ ጊዜ ያህል ትዳር ላለመመሥረት ወይም ልጆች ላለመውለድ መርጠዋል። ሌሎች ደግሞ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው መራቅ ቢጠይቅባቸውም እንኳ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ለመዛወር ወስነዋል። ብዙዎቻችን ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት ስለምንፈልግ እንዲህ ያሉ መሥዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኞች ነን። የምትከፍሉት መሥዋዕት ትንሽም ይሁን ትልቅ፣ ይሖዋ እሱን ለማገልገል ስትሉ የምትከፍሉትን ማንኛውንም መሥዋዕት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኞች ሁኑ።—ዕብ. 6:10

ከሌሎች የተለያችሁ ለመሆን ፈቃደኞች ሁኑ

7. አንድ ናዝራዊ ስእለቱን ለመፈጸም ሲሞክር ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችላል? (ዘኁልቁ 6:5) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ዘኁልቁ 6:5ን አንብብ። ናዝራውያን ፀጉራቸውን ላለመቆረጥ ይሳሉ ነበር። ይህም ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደሚገዙ የሚያሳይ ምልክት ነበር። አንድ እስራኤላዊ በናዝራዊነት የሚያሳልፈው ጊዜ ረዘም ያለ ከሆነ ፀጉሩን አለመቆረጡን ሌሎች እስራኤላውያን ማስተዋላቸው አይቀርም። በዙሪያው ያሉ ሰዎች የናዝራዊነት ስእለቱን ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት የሚደግፉለት ከሆነ ይህ ምንም ችግር አይፈጥርበትም። የሚያሳዝነው ግን በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ናዝራውያን አድናቆት ወይም ድጋፍ ያላገኙበት ጊዜ ነበር። በነቢዩ አሞጽ ዘመን ከሃዲ የሆኑ እስራኤላውያን ለናዝራውያን “የወይን ጠጅ እንዲጠጡ” ይሰጧቸው ነበር። እንዲህ የሚያደርጉት የወይን ጠጅ ላለመጠጣት የገቡትን ስእለት እንዲያፈርሱ ለማድረግ ሳይሆን አይቀርም። (አሞጽ 2:12) አንዳንድ ጊዜ፣ ናዝራውያን ስእለታቸውን መፈጸምና የተለዩ ሆነው መታየት ድፍረት ጠይቆባቸው ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ የለውም።

ስእለታቸውን ለመፈጸም የቆረጡ ናዝራውያን ከሌሎች የተለዩ ለመሆን ፈቃደኞች ነበሩ (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)


8. ከቤንጃሚን ተሞክሮ ምን የሚያበረታታ ሐሳብ አግኝታችኋል?

8 እኛም በተፈጥሯችን ዓይናፋር ብንሆንም እንኳ በይሖዋ እርዳታ ደፋር መሆንና ከሌሎች የተለየ አቋም መያዝ እንችላለን። በኖርዌይ የሚኖረውን ቤንጃሚን የተባለ የአሥር ዓመት ልጅ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በትምህርት ቤቱ ውስጥ፣ በጦርነት የምትታመሰውን ዩክሬንን ለመደገፍ አንድ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር። ተማሪዎቹ በዩክሬን ባንዲራ ላይ ያሉትን ቀለሞች ለብሰው መዝሙር እንዲዘምሩ ተጠየቁ። ቤንጃሚን ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅበት በዚህ ፕሮግራም ላይ መካፈል ስላልፈለገ ራቅ ብሎ ቆመ። ሆኖም አስተማሪው ስታየው ጮክ ብላ ጠራችውና “ና እንጂ። እየጠበቅንህ እኮ ነው” አለችው። ቤንጃሚን ወደ አስተማሪዋ ጠጋ ብሎ በድፍረት እንዲህ አላት፦ “እኔ ገለልተኛ ነኝ፤ በፖለቲካዊ ሰልፎች ላይ አልካፈልም። ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ለመዋጋት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ታስረዋል።” አስተማሪዋ ይህን ማብራሪያ ከሰማች በኋላ ቤንጃሚን በፕሮግራሙ ላይ መካፈል እንደማይጠበቅበት ነገረችው። ሆኖም አብረውት የሚማሩት ልጆች አብሯቸው የማይዘምረው ለምን እንደሆነ ይጠይቁት ጀመር። ቤንጃሚን በጣም ከመፍራቱ የተነሳ እንባው መጥቶ ነበር። ሆኖም ለአስተማሪው የነገራትን ነገር በሁሉም ተማሪዎች ፊት በድፍረት ተናገረ። በኋላ ላይ ቤንጃሚን፣ ለእምነቱ ጥብቅና ለመቆም የረዳው ይሖዋ እንደሆነ ለወላጆቹ ነግሯቸዋል።

9. የይሖዋን ልብ ማስደሰት የምንችለው በምን መንገድ ነው?

9 ለይሖዋ ፈቃድ ስለምንገዛ በዙሪያችን ካሉት ሰዎች የተለየን መሆናችን አይቀርም። በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለማሳወቅ ድፍረት ያስፈልገናል። በዓለም ያሉ ሰዎች ባሕርይና ምግባር እየከፋ ሲሄድ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራትና ምሥራቹን ለሌሎች ማወጅ ይበልጥ እየከበደን ሊሄድ ይችላል። (2 ጢሞ. 1:8፤ 3:13) ይሁንና ይሖዋ እሱን ከማያመልኩ ሰዎች በድፍረት የተለየ አቋም ስንይዝ ‘ልቡ እንደሚደሰት’ ምንጊዜም አስታውሱ።—ምሳሌ 27:11፤ ሚል. 3:18

በሕይወታችሁ ውስጥ ይሖዋን አስቀድሙ

10. በዘኁልቁ 6:6, 7 ላይ የሚገኘውን መመሪያ መጠበቅ ለናዝራውያን ተፈታታኝ የሚሆነው እንዴት ነው?

10 ዘኁልቁ 6:6, 7ን አንብብ። ናዝራውያን ወደ አስከሬን መቅረብ አይፈቀድላቸውም ነበር። ላይ ላዩን ሲታይ ይህ ከባድ መሥዋዕት ላይመስል ይችላል። ሆኖም ናዝራውያን የቅርብ ዘመዶቻቸው ሲሞቱ ይህን መመሪያ መታዘዝ ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። በዘመኑ የነበረው የቀብር ሥነ ሥርዓት ወደ ሟቹ አስከሬን መጠጋትን ይጠይቅ ነበር። (ዮሐ. 19:39, 40፤ ሥራ 9:36-40) የናዝራውያን ስእለት እንዲህ ባሉት ልማዶች እንዳይካፈሉ ያግዳቸዋል። የቤተሰባቸው አባል ሞቶ በከፍተኛ ሐዘን በሚዋጡበት ጊዜም ናዝራውያን ስእለታቸውን በመፈጸም ጠንካራ እምነት አሳይተዋል። ይሖዋ እነዚህ ታማኝ አገልጋዮቹ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲወጡ ብርታት እንደሰጣቸው ምንም ጥያቄ የለውም።

11. አንድ ክርስቲያን ከቤተሰብ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔው ምን ሊሆን ይገባል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

11 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ራሳችንን ስንወስን ለይሖዋ የገባነውን ስእለት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ይህ ደግሞ ከቤተሰብ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የምናደርጋቸውን ውሳኔዎችና የምንወስዳቸውን እርምጃዎች ይነካል። ከቤተሰቦቻችን ጋር በተያያዘ ያለብንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት በትጋት እንወጣለን፤ ሆኖም የቤተሰቦቻችንን ፍላጎት ይሖዋ ከሚጠብቅብን ነገር ፈጽሞ አናስቀድምም። (ማቴ. 10:35-37፤ 1 ጢሞ. 5:8) በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ይሖዋን ለማስደሰት ስንል ቤተሰቦቻችንን የሚያስከፋ ውሳኔ ልናደርግ እንችላለን።

በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥምህም የይሖዋን ፈቃድ ለማስቀደም ፈቃደኛ ነህ? (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት) e


12. አሌክሳንድሩ አስቸጋሪ የቤተሰብ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ምን አደረገ? ምንስ አላደረገም?

12 የአሌክሳንድሩን እና የባለቤቱን የዶሪናን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስን ለአንድ ዓመት ያህል ካጠኑ በኋላ ዶሪና ጥናቷን ለማቋረጥ ወሰነች፤ አሌክሳንድሩም ጥናቱን እንዲያቋርጥ ፈልጋ ነበር። ሆኖም ጥናቱን እንደሚቀጥል በእርጋታና በዘዴ ነገራት። ዶሪና በዚህ አልተደሰተችም፤ በመሆኑም ጥናቱን በግድ ልታስቆመው ሞከረች። አሌክሳንድሩ የባለቤቱን ስሜት ለመረዳት ጥረት ቢያደርግም ሁኔታው ለእሱ ቀላል እንዳልነበረ ተናግሯል። በዶሪና ትችት እና ኃይለ ቃል የተነሳ ጥናቱን ለማቋረጥ የተፈተነበት ጊዜ ነበር። ያም ቢሆን አሌክሳንድሩ ይሖዋን ማስቀደሙን ቀጥሏል፤ ለባለቤቱም ቢሆን ታላቅ ፍቅርና አክብሮት ማሳየቱን አላቆመም። በስተ መጨረሻ የእሱ መልካም ምሳሌነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን እንድትቀጥል አነሳሳት፤ ከዚያም እውነትን ተቀበለች።—“እውነት ሕይወትን ይለውጣል” በሚለው ዓምድ ሥር የሚገኘውን አሌክሳንድሩ እና ዶሪና ቫካር፦ ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው የሚለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።

13. ለይሖዋና ለቤተሰባችን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

13 የቤተሰብን ዝግጅት የመሠረተው ይሖዋ ነው፤ ደስተኛ ቤተሰብ እንዲኖረንም ይፈልጋል። (ኤፌ. 3:14, 15) እውነተኛ ደስታ ማግኘት ከፈለግን የይሖዋን መመሪያ መከተል ይኖርብናል። ይሖዋ ቤተሰቦቻችሁን እየተንከባከባችሁ እንዲሁም ለእነሱ ፍቅርና አክብሮት እያሳያችሁ እሱን ለማገልገል የምትከፍሉትን መሥዋዕት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ፈጽሞ አትጠራጠሩ።—ሮም 12:10

ሌሎች የናዝራዊነትን መንፈስ እንዲያሳዩ አበረታቱ

14. በንግግራችን በተለይ እነማንን ለማበረታታት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል?

14 በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ለማገልገል የሚመርጡ በሙሉ በፍቅር ተነሳስተው አንዳንድ መሥዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። ሆኖም እንዲህ ማድረግ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ታዲያ ሌሎች እንዲህ ያለ ዝንባሌ እንዲያሳዩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? እነሱን በንግግራችን በማበረታታት ነው። (ኢዮብ 16:5) በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ ሕይወታቸውን ቀላል ለማድረግ እየሞከሩ ያሉ አስፋፊዎች በጉባኤያችሁ ውስጥ አሉ? በጣም ተፈታታኝ ቢሆንባቸውም በትምህርት ቤት ከሌሎች የተለየ አቋም ለመያዝ የሚሞክሩ ደፋር ወጣቶች አሉ? የቤተሰብ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ታማኝ ለመሆን እየታገሉ ያሉ አስፋፊዎች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ታውቃላችሁ? እንዲህ ያሉ የእምነት አጋሮቻችን ለሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስና ድፍረት አድናቆታችንን በመግለጽ እነሱን ለማበረታታት ያገኘነውን አጋጣሚ ሁሉ እንጠቀም።—ፊልሞና 4, 5, 7

15. አንዳንዶች ለሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ምን ድጋፍ አድርገዋል?

15 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለሚካፈሉ የእምነት አጋሮቻችን ተግባራዊ እርዳታ ማበርከት እንችል ይሆናል። (ምሳሌ 19:17፤ ዕብ. 13:16) በስሪ ላንካ የምትኖር ታማኝ የሆነች አረጋዊት እህት እንዲህ ማድረግ ፈልጋ ነበር። እህታችን ጡረታዋ ሲጨመርላት በአስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወጣት አቅኚ እህቶችን ለመርዳት አሰበች። በመሆኑም ለስልክ ወጪ እንዲሆናቸው በየወሩ ለእነሱ የተወሰነ ገንዘብ ለመስጠት ወሰነች። እህታችን እንዴት ያለ ግሩም መንፈስ አሳይታለች!

16. በጥንት ዘመን ከነበረው የናዝራዊነት ዝግጅት ምን ትምህርት እናገኛለን?

16 በጥንት ዘመን የኖሩት ናዝራውያን ከተዉት ግሩም ምሳሌ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በተጨማሪም ይህ ዝግጅት ስለ ሰማዩ አባታችን ስለ ይሖዋ የሚያስተምረን ነገር አለ። ይሖዋ እሱን ለማስደሰት ልባዊ ፍላጎት እንዳለንና ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ስእለት ለመፈጸም ስንል አንዳንድ መሥዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኞች እንደሆንን እርግጠኛ ነው። ለእሱ ያለንን ፍቅር በፈቃደኝነት እንድናሳይ አጋጣሚ በመስጠት አክብሮናል። (ምሳሌ 23:15, 16፤ ማር. 10:28-30፤ 1 ዮሐ. 4:19) የናዝራዊነት ዝግጅት፣ ይሖዋ እሱን ለማገልገል ስንል የምንከፍላቸውን መሥዋዕቶች እንደሚያስተውልና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ያስተምረናል። እንግዲያው ለይሖዋ በፈቃደኝነት ምርጣችንን በመስጠት እሱን ማገልገላችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ናዝራውያን የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደረጉትና ድፍረት ያሳዩት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

  • በዛሬው ጊዜ ሌሎች የናዝራዊነት መንፈስ እንዲያሳዩ ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?

  • የናዝራዊነት ዝግጅት ይሖዋ በአገልጋዮቹ እንደሚተማመን የሚያሳየው እንዴት ነው?

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

a በይሖዋ የተሾሙ ጥቂት ናዝራውያን ቢኖሩም አብዛኞቹ ናዝራውያን ይህን ስእለት የሚሳሉት በራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው ሳይሆን አይቀርም።—“ በይሖዋ የተሾሙ ናዝራውያን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b አንዳንድ ጽሑፎቻችን ናዝራውያንን ከሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጋር አመሳስለዋቸዋል። ሆኖም ይህ ርዕስ የሚያተኩረው ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ የናዝራዊነት መንፈስ ማሳየት በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ነው።

c በጥቅሉ ሲታይ ናዝራውያን ከስእለታቸው ጋር የተያያዙ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ወይም የሥራ ምድቦች የነበሯቸው አይመስልም።

d “የይሖዋ ምሥክሮች ተሞክሮዎች” በሚለው ዓምድ ሥር የሚገኘውን “ኑሯችንን ቀላል ለማድረግ ወሰንን” የሚለውን ርዕስ jw.org ላይ ተመልከት።

e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ናዝራዊ የቤተሰቡን አባል የቀብር ሥነ ሥርዓት ከሰገነት ላይ ሆኖ ሲመለከት። በስእለቱ የተነሳ ቀረብ ብሎ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ መካፈል አይችልም።