በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ስላለው የወደፊቱን ጊዜ የማወቅ ችሎታ ምን ያስተምራል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ የመናገር ችሎታ እንዳለው በግልጽ ይናገራል። (ኢሳ. 45:21) ሆኖም የወደፊቱን ጊዜ የሚያውቀው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ለማወቅ የሚመርጠው መቼ እና ምን ያህል እንደሆነ በዝርዝር አይነግረንም። ስለዚህ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ያም ቢሆን ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ።

ይሖዋ የፈለገውን ነገር ማድረግ ይችላል፤ ሆኖም በራሱ ላይ አንዳንድ ገደቦችን ያበጃል። ገደብ የለሽ ጥበብ ስላለው የፈለገውን ነገር አስቀድሞ ማወቅ ይችላል። (ሮም 11:33) ሆኖም ፍጹም የሆነ ራሱን የመቆጣጠር ችሎታ ስላለው ወደፊት የሚከናወነውን ነገር ላለማወቅ መምረጥ ይችላል።—ከኢሳይያስ 42:14 ጋር አወዳድር።

ይሖዋ ፈቃዱ እንዲፈጸም ያደርጋል። ይህ እውነታ፣ የወደፊቱን ጊዜ አስቀድሞ ከመናገር ችሎታው ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? ኢሳይያስ 46:10 እንዲህ ይላል፦ “ከመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ገና ያልተከናወኑትንም ነገሮች ከረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሜ እናገራለሁ። እኔ ‘ውሳኔዬ ይጸናል፤ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ሁሉ አደርጋለሁ’ እላለሁ።”

ስለዚህ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ መናገር የሚችልበት አንዱ ምክንያት ማንኛውንም ነገር ለማከናወን የሚያስችል ኃይል ስላለው ነው። ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ የሚያውቅበት መንገድ አንድን ፊልም ወደፊት አሳልፈን መጨረሻውን ማየት ከምንችልበት መንገድ የተለየ ነው፤ ወደፊት የሚከናወኑት ነገሮች በሙሉ በሆነ መልኩ ተቀርጸው የተቀመጡ ይመስል ይሖዋ ወደፊት አሳልፎ መመልከት አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ አንድ ነገር በሆነ ወቅት እንዲከናወን አስቀድሞ መወሰን ከዚያም ያ ጊዜ ሲደርስ ክንውኑ እንዲፈጸም ማድረግ ይችላል።—ዘፀ. 9:5, 6፤ ማቴ. 24:36፤ ሥራ 17:31

በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ወደፊት ከሚከናወኑ አንዳንድ ነገሮች ጋር በተያያዘ ምን እንደሚያደርግ ሲገልጽ “አስቤአለሁ” እና “ሠርቻለሁ” እንደሚሉት ያሉ ቃላትን ይጠቀማል። (2 ነገ. 19:25 ግርጌ፤ ኢሳ. 46:11) እነዚህ ቃላት በበኩረ ጽሑፉ ላይ “ሸክላ ሠሪ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል ጋር ዝምድና አላቸው። (ኤር. 18:4) ጥሩ ችሎታ ያለው ሸክላ ሠሪ አንድን የሸክላ ጭቃ ቅርጽ አስይዞ ውብ የሆነ የአበባ ማስቀመጫ መሥራት እንደሚችል ሁሉ ይሖዋም ፈቃዱን ለማስፈጸም ሲል ሁኔታዎችን ማመቻቸት ወይም ቅርጽ ማስያዝ ይችላል።—ኤፌ. 1:11

ይሖዋ ሰዎች ያላቸውን የመምረጥ ነፃነት ያከብራል። የሰዎችን ዕጣ ፈንታ አይወስንም፤ ወይም ደግሞ ጥሩ ሰዎች ወደ ጥፋት የሚያመራ ነገር እንዲፈጽሙ አያደርግም። ሁሉም ሰዎች የሚፈልጉትን የሕይወት ጎዳና እንዲመርጡ ይፈቅድላቸዋል። እንዲሁም ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና እንዲመርጡ ያበረታታቸዋል።

ሁለት ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። የመጀመሪያው ምሳሌ ከነነዌ ነዋሪዎች ጋር የተያያዘ ነው። ይሖዋ የነነዌ ሰዎች ክፉዎች በመሆናቸው የተነሳ ከተማዋ እንደምትጠፋ ትንቢት ተናገረ። ሆኖም የነነዌ ሰዎች ንስሐ ሲገቡ ይሖዋ “[በእነሱ] ላይ አመጣዋለሁ ያለውን ነገር መልሶ በማጤን ጥፋቱን ከማምጣት ተቆጠበ።” (ዮናስ 3:1-10) የነነዌ ሰዎች የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመው ይሖዋ የላከላቸውን የማስጠንቀቂያ መልእክት ለመስማትና ንስሐ ለመግባት በመወሰናቸው ይሖዋ ከተናገረው ትንቢት ጋር በተያያዘ ሐሳቡን ቀየረ።

ሁለተኛው ምሳሌ፣ ቂሮስ የተባለ ተዋጊ አይሁዳውያንን ከግዞት ነፃ እንደሚያወጣቸውና የይሖዋ ቤተ መቅደስ መልሶ እንዲገነባ እንደሚያዝዝ የሚገልጸው ትንቢት ነው። (ኢሳ. 44:26–45:4) የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ይህ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። (ዕዝራ 1:1-4) ይሁንና ቂሮስ እውነተኛውን አምላክ አላመለከም። ይሖዋ ቂሮስ ያለውን ማንን እንደሚያመልክ የመምረጥ መብት ሳይነካ ቂሮስ ትንቢቱን እንዲፈጽም አድርጓል።—ምሳሌ 21:1

እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ የማወቅ ችሎታውን ከሚጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ ከግምት መግባት ያለባቸው ነገሮች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ሰዎች የይሖዋን መንገዶች ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማይችሉ ግልጽ ነው። (ኢሳ. 55:8, 9) ይሁንና ስለ ይሖዋ ከምናውቀው ነገር በመነሳት ምንጊዜም ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ትንቢት በሚናገርበት ጊዜም ትክክለኛውን ነገር ያደርጋል።