በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ድክመቶቼ የአምላክ ኃይል እንዲታይ አድርገዋል

ድክመቶቼ የአምላክ ኃይል እንዲታይ አድርገዋል

እኔና ባለቤቴ በ1985 ኮሎምቢያ ስንደርስ አገሪቱ በዓመፅ እየታመሰች ነበር። መንግሥት በከተሞች ውስጥ ከዕፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች ጋር፣ በተራራማዎቹ አካባቢዎች ደግሞ ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ይዋጋ ነበር። ከጊዜ በኋላ ባገለገልንበት በሜደሊን፣ የታጠቁ ወሮበላ ወጣቶችን በየመንገዱ ላይ ማየት የተለመደ ነገር ነው። ዕፅ ይሸጡ፣ አስፈራርተው ገንዘብ ይቀበሉ እንዲሁም ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ ሆነው ይሠሩ ነበር። ሁሉም ዕድሜያቸው በአጭሩ ይቀጭ ነበር። ይህን ስናይ ሌላ ዓለም ውስጥ እንደገባን ተሰማን።

በምድር ሰሜናዊ ጫፍ ከሚገኙት አገሮች አንዷ የሆነችው የፊንላንድ ተወላጅ የሆኑ ሁለት ሰዎች ወደ ደቡብ አሜሪካ ሊመጡ የቻሉት እንዴት ነው? ያሳለፍኩት ሕይወትስ የትኞቹን ትምህርቶች አስተምሮኛል?

በፊንላንድ ያሳለፍኩት የወጣትነት ሕይወት

የተወለድኩት በ1955 ሲሆን ከሦስት ወንዶች ልጆች መካከል የመጨረሻው ነኝ። ያደግኩት በፊንላንድ ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ነው፤ ይህ አካባቢ አሁን ቫንታ ከተማ ተብሎ ይጠራል።

እኔ ከመወለዴ ከጥቂት ዓመታት በፊት እናቴ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። አባቴ ግን እውነትን ይቃወም ነበር። እናቴ እንድታስጠናንም ሆነ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች እንድትወስደን አልፈቀደላትም። ስለዚህ አባቴ ቤት በማይኖርበት ጊዜ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ታስተምረን ነበር።

በሰባት ዓመቴ ይሖዋን ለመታዘዝ ወስኜ ነበር

ከልጅነቴ አንስቶ ይሖዋን ለመታዘዝ ወስኜ ነበር። ለምሳሌ የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ ቬሪሌትያ የተባለ ደም ያለው የፊንላንድ ምግብ ለመብላት ፈቃደኛ ባለመሆኔ አስተማሪዬ በጣም ተበሳጨችብኝ። በአንድ እጇ ጉንጮቼን ጭምቅ አድርጋ ይዛ አፌን ለመክፈት እየታገለች በሌላኛው እጇ ያንን ምግብ በሹካ ወደ አፌ ውስጥ ለማስገባት ሞከረች። እኔ ግን ሹካውን ከእጇ አስጣልኳት።

የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ሞተ። ከዚያ በኋላ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ቻልኩ። በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞች ትኩረት ይሰጡኝ እንዲሁም ደግነት ያሳዩኝ ነበር፤ ይህም መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ አነሳሳኝ። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን በትጋት ማጥናት ጀመርኩ። እንዲህ ያለ ጥሩ የጥናት ልማድ ማዳበሬ ነሐሴ 8, 1969 በ14 ዓመቴ እንድጠመቅ አስችሎኛል።

ትምህርት ከጨረስኩ ብዙም ሳይቆይ የዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ስል በማዕከላዊ ፊንላንድ ወደምትገኘው ወደ ፔላቬሲ ተዛወርኩ።

ከውዷ ባለቤቴ ከሲርካ ጋር የተዋወቅነው ፔላቬሲ እያለሁ ነው። ትሑትና ጥልቅ መንፈሳዊነት ያላት መሆኗ ማረከኝ። ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ወይም የተደላደለ ሕይወት የመምራት ፍላጎት አልነበራትም። ሁለታችንም በተሰጠን በማንኛውም የአገልግሎት ምድብ ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ የማገልገል ፍላጎት ነበረን። መጋቢት 23, 1974 ተጋባን። ከዚያም ወደ ጫጉላ ሽርሽር ከመሄድ ይልቅ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት በካርቱላ ለማገልገል ሄድን።

በካርቱላ፣ ፊንላንድ የተከራየነው ቤት

ይሖዋ ተንከባክቦናል

ወንድሜ የሰጠን መኪና

ከተጋባንበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ መንግሥቱን እስካስቀደምን ድረስ በቁሳዊ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያሟላልን አሳይቶናል። (ማቴ. 6:33) ለምሳሌ በካርቱላ ስናገለግል መኪና አልነበረንም። መጀመሪያ ላይ ከቦታ ቦታ የምንጓዘው በብስክሌት ነበር። ሆኖም የቅዝቃዜው ወቅት በጣም ከባድ ነበር። ሰፊ በሆነው የጉባኤው ክልል ውስጥ ለማገልገል መኪና ያስፈልገን ነበር። ሆኖም መኪና ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ አልነበረንም።

ታላቅ ወንድሜ ባልጠበቅነው ጊዜ ሊጠይቀን መጣ። እሱም መኪናውን እንደሚሰጠን ነገረን። የመኪናው የኢንሹራንስ ክፍያ ተጠናቅቆ ነበር። ከእኛ የሚጠበቀው ነዳጅ መሙላት ብቻ ነበር። በዚህ መንገድ የሚያስፈልገንን መኪና አገኘን።

ይሖዋ በቁሳዊ የሚያስፈልገንን ነገር የማሟላቱን ኃላፊነት እንደተሸከመልን አሳይቶናል። የእኛ ድርሻ መንግሥቱን ማስቀደም ነው።

የጊልያድ ትምህርት ቤት

በ1978 የተካፈልንበት የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት

በ1978 በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት እየተካፈልን ሳለ አስተማሪያችን የሆነው ወንድም ሪሞ ክዎካነን a በጊልያድ ትምህርት ቤት ለመማር እንድናመለክት አበረታታን። ስለዚህ ይህን ግብ በአእምሯችን ይዘን እንግሊዝኛ መማር ጀመርን። ሆኖም ማመልከት ከመቻላችን በፊት በ1980 በፊንላንድ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንድናገለግል ተጋበዝን። በወቅቱ ቤቴላውያን በጊልያድ ትምህርት ቤት ለመማር ማመልከት አይችሉም ነበር። ነገር ግን እኛ በመረጥነው ቦታ ሳይሆን ይሖዋ በመረጠልን ቦታ ማገልገል እንፈልግ ነበር። ስለዚህ ግብዣውን ተቀበልን። ሆኖም ምናልባት አንድ ቀን በጊልያድ ልንማር እንችል ይሆናል ብለን ስላሰብን እንግሊዝኛ መማራችንን ቀጠልን።

ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ፣ የበላይ አካሉ ቤቴላውያንም በጊልያድ ትምህርት ቤት ለመማር ማመልከት እንደሚችሉ ገለጸ። ስለዚህ ወዲያውኑ ማመልከቻ ሞላን። ሆኖም ይህን ያደረግነው በቤቴል አገልግሎታችን ደስተኛ ስላልነበርን አይደለም። ከዚህ ይልቅ፣ ብቃቱን ካሟላን ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ለማገልገል ራሳችንን ማቅረብ ስለፈለግን ብቻ ነው። በጊልያድ ለመማር ያስገባነው ማመልከቻ ተቀባይነት አገኘ። ከዚያም መስከረም 1985 ከ79ኛው ክፍል ተመርቀን ኮሎምቢያ እንድናገለግል ተመደብን።

የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ምድባችን

ኮሎምቢያ ስንደርስ መጀመሪያ የተመደብነው በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ እንድናገለግል ነበር። የተሰጠኝን ኃላፊነት ለመወጣት የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ። ሆኖም በቅርንጫፍ ቢሮው ለአንድ ዓመት ያህል ካገለገልን በኋላ ለውጥ እንደሚያስፈልገን ተሰማኝ። ስለዚህ የአገልግሎት ምድቤ እንዲለወጥልኝ ጠየቅኩ፤ እንዲህ ያለ ጥያቄ ያቀረብኩት በሕይወቴ ለመጀመሪያም ሆነ ለመጨረሻ ጊዜ ነው። ከዚያም በህዊላ ክልል በምትገኘው በኔቫ ከተማ የመስክ ሚስዮናውያን ሆነን እንድናገለግል ተመደብን።

በፊትም ቢሆን አገልግሎት በጣም ያስደስተኛል። ከማግባቴ በፊት ፊንላንድ ውስጥ አቅኚ እያለሁ ከማለዳ አንስቶ እስከ ምሽት ድረስ አገለግል ነበር። ከሲርካ ጋር አዲስ ተጋቢዎች እያለንም ቀኑን ሙሉ የምናገለግልባቸው ጊዜያት ነበሩ። ርቀው በሚገኙ ክልሎች ውስጥ ስናገለግል አንዳንድ ጊዜ መኪና ውስጥ እናድር ነበር። ይህም በጉዞ ላይ የምናጠፋውን ጊዜ ለመቀነስና በማግስቱ አገልግሎታችንን በማለዳ ለመጀመር ይረዳናል።

የመስክ ሚስዮናውያን ስንሆን ቀደም ሲል ለአገልግሎት የነበረን ቅንዓት መልሶ ተቀጣጠለ። ጉባኤያችን እያደገ ሄደ። በኮሎምቢያ የነበሩት ወንድሞችና እህቶችም ሰው አክባሪ፣ አፍቃሪና አድናቂ ነበሩ።

የጸሎት ኃይል

እኛ ከተመደብንባት ከኔቫ ብዙም ሳይርቅ አንድም የይሖዋ ምሥክር የሌለባቸው ከተሞች ነበሩ። ምሥራቹ ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሚደርሰው እንዴት እንደሆነ በጣም ያሳስበኝ ነበር። ሆኖም በዚያ አካባቢ ጦርነት ስላለ የአካባቢው ተወላጅ ላልሆኑ ሰዎች ወደዚያ መሄድ አስጊ ነበር። ስለዚህ በእነዚህ ከተሞች የሚኖር አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር እንዲሆን ጸለይኩ። እንዲህ ያለው ሰው እውነትን መማር እንዲችል በኔቫ መኖር እንደሚያስፈልገው ተሰምቶኝ ነበር። ስለዚህ እውነትን ሰምቶ ከተጠመቀ በኋላ መንፈሳዊ እድገት አድርጎ ወደ ትውልድ ከተማው እንዲመለስና በዚያ እንዲሰብክ መጸለይ ጀመርኩ። ይሖዋ ከእኔ በጣም የተሻለ መፍትሔ እንዳዘጋጀ በወቅቱ አላወቅኩም ነበር።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ ፈርናንዶ ጎንዛሌዝ የተባለን አንድ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ጀመርኩ። እሱ የሚኖረው የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሉባቸው ከተሞች አንዷ በሆነችው በአልሄሲራስ ነበር። ፈርናንዶ ለሥራ በየሳምንቱ 50 ኪሎ ሜትር ተጉዞ ወደ ኔቫ ይመጣል። ለእያንዳንዱ ጥናት በሚገባ ይዘጋጅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ወዲያውኑ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ፈርናንዶ ማጥናት ከጀመረበት ሳምንት አንስቶ በትውልድ ከተማው ያሉ ሰዎችን ሰብስቦ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ላይ የተማረውን ነገር ያስተምራቸው ነበር።

በ1993 ከፈርናንዶ ጋር

ፈርናንዶ ጥናት ከጀመረ ከስድስት ወር በኋላ ጥር 1990 ተጠመቀ። ከዚያም የዘወትር አቅኚ ሆነ። አሁን የአልሄሲራስ ተወላጅ የሆነ አንድ አስፋፊ ስላለ ቅርንጫፍ ቢሮው ልዩ አቅኚዎችን ወደዚያ አካባቢ መላክ ቻለ። የካቲት 1992 በዚያ ከተማ ጉባኤ ተቋቋመ።

የፈርናንዶ አገልግሎት በትውልድ ከተማው ብቻ የተወሰነ ነበር? አልነበረም! ትዳር ከመሠረተ በኋላ እሱና ባለቤቱ ወደ ሳን ቪሴንቲ ዴል ካኋን ተዛወሩ። በዚያም አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። በዚያ ከተማ ጉባኤ እንዲቋቋም ረድተዋል። በ2002 ፈርናንዶ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ። እሱና ባለቤቱ ኦልጋ አሁንም ድረስ በወረዳ ሥራ እየተካፈሉ ነው።

ይህ ተሞክሮ፣ ከቲኦክራሲያዊ ኃላፊነታችን ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮችን አስመልክቶ መጸለይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝቦኛል። ይሖዋ እኛ ማድረግ የማንችለውን ነገር ያደርጋል። ደግሞም መከሩ የእሱ ነው እንጂ የእኛ አይደለም።—ማቴ. 9:38

ይሖዋ ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎትም ሆነ ኃይል’ ይሰጠናል

በ1990 በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ እንድንካፈል ተመደብን። የመጀመሪያው ወረዳችን የሚገኘው ዋና ከተማ በሆነችው በቦጎታ ነበር። ይህ ምድብ አስፈርቶን ነበር። ምክንያቱም እኔና ባለቤቴ ምንም የተለየ ተሰጥኦ የለንም። ደግሞም በትልቅ ከተማ ውስጥ መኖር አልለመድንም። ሆኖም ይሖዋ በፊልጵስዩስ 2:13 ላይ የገባውን ቃል ፈጽሞልናል፦ “ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ኃይል እንድታገኙ በማድረግ እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ብርታት የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።”

ከጊዜ በኋላ በመግቢያው ላይ በጠቀስኳት በሜደሊን ከተማ በሚገኝ ወረዳ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያ የሚኖሩ ሰዎች በመንገድ ላይ ዓመፅ ማየት ከመልመዳቸው የተነሳ ምንም አያስደነግጣቸውም ነበር። ለምሳሌ በአንድ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየመራሁ ሳለሁ ከማስጠናበት ቤት ውጭ ተኩስ ተከፈተ። እኔ ደንግጬ መሬት ላይ ልወድቅ ነበር፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ግን ተረጋግቶ አንቀጹን ማንበቡን ቀጠለ። አንቀጹን አንብቦ ሲጨርስ ወደ ውጭ ወጣ። ትንሽ ቆይቶ ሁለት ትናንሽ ልጆች ይዞ መጣና ተረጋግቶ “ይቅርታ፣ ልጆቼን ማምጣት ስለነበረብኝ ነው” አለኝ።

ሌሎችም አደገኛ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። በአንድ ወቅት ከቤት ወደ ቤት እያገለገልን ሳለ ባለቤቴ በድንጋጤ ፊቷ ገርጥቶ እየሮጠች ወደ እኔ መጣች። የሆነ ሰው ተኩሶ እንደሳታት ነገረችኝ። ይህም በጣም አስደነገጠኝ። ይሁንና በኋላ እንደተረዳነው ሰውየው መተኮስ የፈለገው በሲርካ ላይ ሳይሆን ከእሷ አጠገብ እያለፈ በነበረ ሰው ላይ ነው።

ውሎ አድሮ ዓመፁን እንዴት መቋቋም እንዳለብን ተማርን። እንዲህ ያሉና ከዚህም የከፉ ሁኔታዎችን በጽናት የሚቋቋሙት የአካባቢው ወንድሞች ያላቸው ጥንካሬ አበረታታን። ይሖዋ እነሱን እየረዳቸው ከሆነ እኛንም ይረዳናል ብለን ደመደምን። ምንጊዜም የሽማግሌዎችን ምክር እንከተልና የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንወስድ ነበር፤ የቀረውን ደግሞ በይሖዋ እጅ እንተወዋለን።

እርግጥ አንዳንድ ሁኔታዎች የፈራነውን ያህል አደገኛ አልነበሩም። በአንድ ወቅት አንድ ቤት ውስጥ ሰው እያነጋገርኩ ሳለ ከውጭ የሁለት ሴቶች ጭቅጭቅ የሚመስል ድምፅ ተሰማኝ። እርግጥ እኔ ጭቅጭቅ የማየት ፍላጎት አልነበረኝም። ሆኖም የማነጋግራት ሴት ወደ በረንዳው እንድወጣ ጎተጎተችኝ። ለካስ “እየተጨቃጨቁ” ያሉት ሁለት በቀቀኖች ናቸው፤ የጎረቤቶቿን ድምፅ እያስመሰሉ ነበር።

ተጨማሪ ኃላፊነቶችና ትግሎች

በ1997 የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት b አስተማሪ ሆኜ ተመደብኩ። በፊትም ቢሆን በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች መካፈል በጣም ያስደስተኛል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የማስተማር ልዩ መብት አገኛለሁ ብዬ ግን አስቤ አላውቅም ነበር።

ከጊዜ በኋላም የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ። ይህ ዝግጅት ካቆመ በኋላ ወደ ወረዳ ሥራ ተመለስኩ። ስለዚህ ከ30 ዓመት በላይ አስተማሪና ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ። እነዚህ የአገልግሎት ምድቦች ብዙ በረከት አስገኝተውልኛል። ሆኖም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። እንዲህ ስል ምን ማለቴ እንደሆነ ልንገራችሁ።

በባሕርዬ ቆራጥ ሰው ነኝ። ይህም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ረድቶኛል። ይሁንና በጉባኤ ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን ለማስተካከል ከመጠን ያለፈ ቅንዓት ያሳየሁባቸው ጊዜያት አሉ። ሌሎች አፍቃሪና ምክንያታዊ እንዲሆኑ ጠንከር ያለ ምክር ሰጥቼ አውቃለሁ። የሚገርመው ግን በዚያው ወቅት እኔ ራሴ እነዚህን ባሕርያት ማሳየት ይጠበቅብኝ ነበር።—ሮም 7:21-23

በድክመቶቼ የተነሳ በጣም ተስፋ የቆረጥኩባቸው ጊዜያት አሉ። (ሮም 7:24) በአንድ ወቅት የሚስዮናዊነት አገልግሎቴን አቁሜ ወደ ፊንላንድ ብመለስ እንደሚሻል ለይሖዋ በጸሎት ነገርኩት። በዚያ ምሽት በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። እዚያ ያገኘሁት ማበረታቻ በአገልግሎት ምድቤ መቀጠልና ድክመቶቼን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ እንዳለብኝ አሳመነኝ። ይሖዋ ለጸሎቴ የሰጠኝ ግልጽ መልስ አሁንም ድረስ ልቤን ይነካዋል። ከዚህም ሌላ ድክመቶቼን እንዳሸንፍ በደግነት ስለረዳኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።

የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ

እኔና ሲርካ አብዛኛውን ሕይወታችንን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድናሳልፍ ስለፈቀደልን ይሖዋን በጣም እናመሰግነዋለን። በተጨማሪም ይሖዋ ለእነዚህ ሁሉ ዓመታት እንዲህ ያለች አፍቃሪና ታማኝ ሚስት ስለሰጠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።

በቅርቡ 70 ዓመት ስለሚሞላኝ የመስክ አስተማሪና ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገሌን አቆማለሁ። ሆኖም ይህ መሆኑ አያሳዝነኝም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋን ማስከበር የምንችለው ልካችንን አውቀን እሱን በማገልገል እንዲሁም በፍቅርና በአመስጋኝነት በተሞላ ልብ ተነሳስተን እሱን በማወደስ እንደሆነ ጠንካራ እምነት አለኝ። (ሚክ. 6:8፤ ማር. 12:32-34) ይሖዋን ለማስከበር ልዩ የአገልግሎት መብት ሊኖረን አያስፈልግም።

ያገኘኋቸውን የአገልግሎት መብቶች መለስ ብዬ ሳስብ እነዚህን መብቶች ያገኘሁት ከሌሎች የተሻለ ብቃት ወይም ለየት ያለ ችሎታ ስላለኝ እንዳልሆነ እገነዘባለሁ። ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋ እነዚህን የአገልግሎት መብቶች የሰጠኝ በጸጋው ነው። ድክመቶች ቢኖሩብኝም እንኳ ይሖዋ እነዚህን መብቶች ሰጥቶኛል። እነዚህን ኃላፊነቶች መወጣት የቻልኩት ይሖዋ ስለረዳኝ ብቻ እንደሆነ አውቃለሁ። በዚህ መንገድ ድክመቶቼ የአምላክ ኃይል እንዲታይ አድርገዋል።—2 ቆሮ. 12:9

a የሪሞ ክዎካነን የሕይወት ታሪክ በሚያዝያ 1, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ይሖዋን ለማገልገል ቆርጠናል” በሚል ርዕስ ወጥቷል።

b ይህ ትምህርት ቤት በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተተክቷል።