በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 21

መዝሙር 107 መለኮታዊው የፍቅር መንገድ

የትዳር ጓደኛ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

የትዳር ጓደኛ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

“ባለሙያ ሚስትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከዛጎል እጅግ ይበልጣል።”ምሳሌ 31:10

ዓላማ

ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት የሚረዱት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ትዳር መመሥረት የሚፈልጉ ወንድሞችንና እህቶችን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

1-2. (ሀ) ያላገቡ ክርስቲያኖች መጠናናት ከመጀመራቸው በፊት የትኞቹን ነገሮች ከግምት ማስገባት ይኖርባቸዋል? (ለ) “መጠናናት” ስንል ምን ማለታችን ነው? (“ተጨማሪ ማብራሪያ” የሚለውን ተመልከት።)

 ማግባት ትፈልጋለህ? a ደስተኛ ለመሆን ትዳር መመሥረት የግድ አስፈላጊ ባይሆንም ወጣትም ሆኑ አረጋውያን በርካታ ያላገቡ ክርስቲያኖች ማግባት ይፈልጋሉ። እርግጥ ነው፣ መጠናናት ከመጀመርህ በፊት በኢኮኖሚ፣ በመንፈሳዊና በስሜታዊ ለትዳር ዝግጁ መሆን ይኖርብሃል። b (1 ቆሮ. 7:36) እንዲህ ማድረግህ የሰመረ ትዳር የመመሥረት አጋጣሚህን ከፍ ያደርገዋል።

2 ያም ቢሆን፣ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ማግኘት ቀላል ላይሆን ይችላል። (ምሳሌ 31:10) በደንብ ልታውቃት የምትፈልጋት እህት ካገኘህ በኋላም እንኳ መጠናናት መጀመር ቀላል ላይሆንልህ ይችላል። c በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ያላገቡ ክርስቲያኖች ለትዳር የሚሆናቸው ሰው ለማግኘትና መጠናናት ለመጀመር ምን ሊረዳቸው እንደሚችል እንመለከታለን። በተጨማሪም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ማግባት የሚፈልጉ ክርስቲያኖችን መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንማራለን።

ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ማግኘት

3. አንድ ያላገባ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛ ሲፈልግ የትኞቹን ነገሮች ከግምት ማስገባት አለበት?

3 ማግባት የምትፈልግ ከሆነ መጠናናት ከመጀመርህ በፊት ምን ዓይነት የትዳር ጓደኛ እንደምትፈልግ ቆም ብለህ ማሰብህ ጠቃሚ ነው። እንዲህ ካላደረግክ፣ ጥሩ የትዳር አጋር ልትሆንህ የምትችልን ሴት ችላ ብለህ ልታልፍ ወይም ከማትሆንህ ሴት ጋር መጠናናት ልትጀምር ትችላለህ። እርግጥ ነው፣ ለትዳር የምታስባት ሴት የተጠመቀች ክርስቲያን መሆን አለባት። (1 ቆሮ. 7:39) ያም ቢሆን ሁሉም የተጠመቁ እህቶች ጥሩ የትዳር አጋር ይሆኑሃል ማለት አይደለም። ስለዚህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ግቤ ምንድን ነው? ላገባት የማስባት እህት የግድ እንዲኖሯት የምፈልጋቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? የምጠብቀው ነገር ምክንያታዊ ነው?’

4. አንዳንዶች በጸሎታቸው ላይ ምን ይጠቅሳሉ?

4 ማግባት የምትፈልግ ከሆነ፣ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልየህ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። (ፊልጵ. 4:6) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ለማንም ሰው የትዳር አጋር እንደሚሰጥ ቃል አልገባም። ያም ቢሆን የሚያስፈልግህ ነገርና ስሜትህ ያሳስበዋል፤ እንዲሁም የትዳር ጓደኛ ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ሊረዳህ ይችላል። ስለዚህ ፍላጎትህንና ስሜትህን ለእሱ መንገርህን ቀጥል። (መዝ. 62:8) ትዕግሥትና ጥበብ እንዲሰጥህ ጸልይ። (ያዕ. 1:5) በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ጆን d የተባለ ያላገባ ወንድም በጸሎቱ ውስጥ ምን እንደሚያካትት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከማገባት እህት የምፈልጋቸውን ባሕርያት ለይሖዋ እነግረዋለሁ። የትዳር ጓደኛ የምትሆነኝን ሴት ማግኘት የምችልበት አጋጣሚ እንዲፈጠርልኝ እጸልያለሁ። በተጨማሪም ጥሩ ባል እንድሆን የሚረዱኝን ባሕርያት ለማዳበር እንዲረዳኝ ይሖዋን እጠይቀዋለሁ።” በስሪ ላንካ የምትኖር ታንያ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “የትዳር ጓደኛ በምፈልግበት ጊዜ ታማኝ፣ አዎንታዊና ደስተኛ እንድሆን እንዲረዳኝ ይሖዋን እጠይቀዋለሁ።” ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ወዲያውኑ ባታገኝም እንኳ ይሖዋ አካላዊና ስሜታዊ ፍላጎቶችህን ማሟላቱን እንደሚቀጥል ቃል ገብቶልሃል።—መዝ. 55:22

5. ያላገቡ ክርስቲያኖች ይሖዋን የሚወዱ ሌሎች ያላገቡ ክርስቲያኖችን ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? (1 ቆሮንቶስ 15:58) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ” የሚል ማበረታቻ ይሰጠናል። (1 ቆሮንቶስ 15:58ን አንብብ።) በይሖዋ አገልግሎት ስትጠመድና ከተለያዩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ጊዜ ስታሳልፍ ጥሩ ወዳጆች የምታገኝ ከመሆኑም ሌላ እንደ አንተ ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮሩ ያላገቡ ክርስቲያኖችን ለማግኘት አጋጣሚ ይከፈትልሃል። በተጨማሪም ይሖዋን ለማስደሰት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ስታደርግ እውነተኛ ደስታ ታገኛለህ።

በይሖዋ አገልግሎት ከተጠመድክና ከተለያዩ የእምነት አጋሮችህ ጋር ጊዜ ካሳለፍክ ማግባት የሚፈልጉ ሌሎች ክርስቲያኖችን ልታገኝ ትችላለህ (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)


6. ያላገቡ ክርስቲያኖች የትዳር ጓደኛ በሚፈልጉበት ጊዜ ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል?

6 ሆኖም አንድ መጠንቀቅ ያለብህ ነገር አለ፤ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ሕይወትህን እንዲቆጣጠረው አትፍቀድ። (ፊልጵ. 1:10) እውነተኛ ደስታ ማግኘትህ የተመካው በማግባትህ ወይም ባለማግባትህ ላይ ሳይሆን ከይሖዋ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ነው። (ማቴ. 5:3) ደግሞም ነጠላ መሆንህ አገልግሎትህን ለማስፋት የሚያስችል ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጥህ ይችላል። (1 ቆሮ. 7:32, 33) ይህን ጊዜ ጥሩ አድርገህ ተጠቀምበት። በ30ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ ትዳር የመሠረተች ጄሲካ የተባለች በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር እህት እንዲህ ብላለች፦ “በአገልግሎት ሰፊ ጊዜ አሳልፍ ነበር፤ ይህ ደግሞ ትዳር መመሥረት ብፈልግም እንኳ በሕይወቴ ደስተኛ እንድሆን ረድቶኛል።”

ጊዜ ወስደህ ተመልከታት

7. ለትዳር ላሰብካት እህት ስሜትህን ከመንገርህ በፊት እሷን ለተወሰነ ጊዜ መመልከትህ ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 13:16)

7 አንዲት እህት ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ልትሆንህ እንደምትችል ከተሰማህስ? ስሜትህን ወዲያውኑ ልትነግራት ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጥበበኛ ሰው እርምጃ ከመውሰዱ በፊት እውቀት ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራል። (ምሳሌ 13:16ን አንብብ።) ስለዚህ ስሜትህን ለእሷ ከመንገርህ በፊት ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከርቀት ብትመለከታት የተሻለ ነው። በኔዘርላንድስ የሚኖረው አሽዊን እንዲህ ብሏል፦ “የፍቅር ስሜት ወዲያውኑ ሊመጣ ይችላል፤ ግን ወዲያውኑ ሊጠፋም ይችላል። ስለዚህ መጀመሪያ ጊዜ ወስደህ መመልከትህ በጊዜያዊ ስሜት ላይ ተመሥርተህ ወደ መጠናናት እንዳትገባ ይረዳሃል።” ከዚህም ሌላ፣ እህትን እየተመለከትካት ስትሄድ ለአንተ እንደማትሆንህ ትገነዘብ ይሆናል።

8. አንድ ወንድም ለትዳር የሚያስባትን እህት መመልከት የሚችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

8 ለትዳር የምታስባትን እህት ከርቀት መመልከት የምትችለው እንዴት ነው? በጉባኤ ስብሰባዎች ወይም በማኅበራዊ ግብዣዎች ላይ ስለ መንፈሳዊነቷ፣ ስለ ባሕርይዋ እና ስለ ምግባሯ የሚጠቁሙ ነገሮችን ትመለከት ይሆናል። ጓደኞቿ እነማን ናቸው? ስለ ምን ጉዳይ ማውራት ትወዳለች? (ሉቃስ 6:45) ግባችሁ ተመሳሳይ ነው? የጉባኤ ሽማግሌዎቿን ወይም እሷን በደንብ የሚያውቁ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ማነጋገር ትችል ይሆናል። (ምሳሌ 20:18) ስላተረፈችው ስምና ስለ ባሕርያቷ መጠየቅ ትችላለህ። (ሩት 2:11) ሆኖም እህትን በምትመለከትበት ጊዜ ምቾቷን የሚነሳ ነገር አታድርግ። ለስሜቷ አክብሮት ይኑርህ፤ እንዲሁም እሷ ባለችበት ሁሉ ለመገኘት ወይም ስለ እሷ ሁሉንም ነገር ለማወቅ ጥረት አታድርግ።

ስሜትን ከመግለጽ በፊት ግለሰቡን ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከርቀት መመልከት ጠቃሚ ነው (ከአንቀጽ 7-8⁠ን ተመልከት)


9. ለትዳር ያሰብካትን እህት ከማነጋገርህ በፊት ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ልትሆን ይገባል?

9 ስሜትህን ከመናገርህ በፊት ለምን ያህል ጊዜ ልትመለከታት ይገባል? ስሜትህን ቶሎ ከነገርካት በችኮላ ውሳኔ እንዳደረግክ ሊሰማት ይችላል። (ምሳሌ 29:20) በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተለይ ስሜትህን ካስተዋለች በኋላ ረጅም ጊዜ ከወሰድክ ውሳኔ ማድረግ እንደምትቸገር ሊሰማት ይችላል። (መክ. 11:4) እሷን ከመጠየቅህ በፊት እንደምታገባት እርግጠኛ መሆን እንደማያስፈልግህ አስታውስ። ሆኖም ለትዳር ዝግጁ መሆንህን እንዲሁም እሷ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ልትሆንህ እንደምትችል እርግጠኛ መሆን ይኖርብሃል።

10. አንዲት እህት ለትዳር እያሰበችህ እንደሆነ ብትገነዘብና አንተ ግን እንደዚያ ባይሰማህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

10 ሆኖም አንዲት እህት አንተን ለትዳር እያሰበችህ እንደሆነ ብትገነዘብስ? ከእሷ ጋር ለመጠናናት የማታስብ ከሆነ ይህን በድርጊትህ በግልጽ ለማሳየት ሞክር። አንተ የመጠናናት ሐሳብ ሳይኖርህ ለእሷ ተስፋ መስጠት ደግነት አይደለም።—1 ቆሮ. 10:24፤ ኤፌ. 4:25

11. ባለትዳሮችን የሚያገናኙት ሌሎች ሰዎች በሆኑባቸው አገሮች ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል?

11 በአንዳንድ አገሮች ላላገቡ ሰዎች የትዳር ጓደኛ የሚመርጡት ወላጆች ወይም ሌሎች አዋቂዎች ናቸው። በሌሎች አገሮች ደግሞ ቤተሰቦች ወይም ጓደኞች ላላገቡ ሰዎች የትዳር ጓደኛ ከፈለጉላቸው በኋላ ግለሰቦቹ ይጣጣሙ እንደሆነ ለማየት ተገናኝተው እንዲነጋገሩ አጋጣሚ ይፈጥሩላቸዋል። ለአንድ ሰው የትዳር ጓደኛ እንድትፈልግ ከተጠየቅክ ወንዱም ሆነ ሴቷ የሚፈልጓቸውን ነገሮች ከግምት አስገባ። ሊሆናቸው የሚችል ሰው ካገኘህላቸው በኋላ ስለ ግለሰቡ ወይም ስለ ግለሰቧ ማንነት፣ ባሕርይ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ መንፈሳዊነት የቻልከውን ያህል ለማወቅ ጥረት አድርግ። ከገንዘብ፣ ከትምህርት ደረጃ ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ካላቸው ቦታ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ከይሖዋ ጋር ያላቸው የቅርብ ዝምድና ነው። ያም ቢሆን፣ ትዳር ከመመሥረት ጋር በተያያዘ የመጨረሻውን ውሳኔ ማድረግ ያለባቸው የሚጋቡት ወንድምና እህት እንደሆኑ አስታውስ።—ገላ. 6:5

መጠናናት መጀመር

12. ከአንዲት እህት ጋር ለመጠናናት እያሰብክ ከሆነ እንዴት ብለህ ልትነግራት ትችላለህ?

12 ከአንዲት እህት ጋር ለመጠናናት ካሰብክ እንዴት ብለህ ልትነግራት ትችላለህ? e ለማውራት በሚያመች ግልጽ ቦታ ላይ ተገናኝታችሁ ወይም በስልክ ልታነጋግራት ትችላለህ። ሐሳብህን በግልጽ ንገራት። (1 ቆሮ. 14:9) አስፈላጊ ከሆነ ስለ ጉዳዩ አስባበት መልስ እንድትሰጥህ ጊዜ ስጣት። (ምሳሌ 15:28) እህት ከአንተ ጋር መጠናናት ካልፈለገች ደግሞ ስሜቷን አክብርላት።

13. አንዲት እህት ከአንተ ጋር መጠናናት እንደምትፈልግ ብትነግርህ ምን ማድረግ ትችላለህ? (ቆላስይስ 4:6)

13 አንዲት እህት ከአንተ ጋር ለመጠናናት እንደምትፈልግ ብትነግርህስ? አንተን ለማነጋገር ድፍረት ጠይቆባት እንደሚሆን ጥያቄ የለውም፤ ስለዚህ በደግነትና በአክብሮት አነጋግራት። (ቆላስይስ 4:6ን አንብብ።) ስለ ጉዳዩ ለማሰብ ጊዜ የሚያስፈልግህ ከሆነ በግልጽ ንገራት። ያም ቢሆን በተቻለ ፍጥነት መልስ ለመስጠት ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 13:12) ከእሷ ጋር ለመጠናናት ፍላጎት ከሌለህ ይህን በደግነትና በግልጽ ንገራት። በኦስትሪያ የሚኖር ሃንስ የተባለ ወንድም አንዲት እህት ስትጠይቀው ምን ዓይነት መልስ እንደሰጣት እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “ውሳኔዬን በደግነት ሆኖም በግልጽ ነገርኳት። የውሸት ተስፋ ልሰጣት ስላልፈለግኩ መልሴን የነገርኳት ወዲያውኑ ነው። ከዚያ በኋላ ከእሷ ጋር ባለኝ ግንኙነትም ጠንቃቃ ነበርኩ።” በሌላ በኩል ግን ከእሷ ጋር ለመጠናናት ካሰብክ ስሜትህን ንገራት፤ እንዲሁም የመጠናናቱ ሂደት እንዴት እንዲቀጥል እንደምትፈልጉ በግልጽ ተነጋገሩ። በባሕላችሁ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ አንተ የምታስበው ነገር እሷ ከምታስበው የተለየ ሊሆን ይችላል።

ሌሎቻችን ያላገቡ ክርስቲያኖችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?

14. ያላገቡ ክርስቲያኖችን በንግግራችን መደገፍ የምንችለው እንዴት ነው?

14 ትዳር መመሥረት የሚፈልጉ ክርስቲያኖችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ስለምንናገረው ነገር ጠንቃቆች በመሆን ነው። (ኤፌ. 4:29) ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፦ ‘ማግባት በሚፈልጉ ክርስቲያኖች ላይ አጉል ቀልድ እቀልድባቸዋለሁ? አንድ ነጠላ ወንድምና አንዲት ነጠላ እህት ሲያወሩ ስላየሁ ብቻ በመካከላቸው የሆነ ነገር እንዳለ ይሰማኛል?’ (1 ጢሞ. 5:13) ከዚህም በተጨማሪ ያላገቡ ክርስቲያኖች ትዳር ባለመመሥረታቸው የተነሳ የሆነ የጎደላቸው ነገር እንዳለ እንዲሰማቸው ማድረግ አንፈልግም። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሃንስ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ወንድሞች ‘የማታገባው ለምንድን ነው? አሁን እኮ ልጅ አይደለህም’ ይሉኛል። እንዲህ ያለው ሐሳብ ያላገቡ ክርስቲያኖች እንደማይደነቁ እንዲሰማቸው ያደርጋል፤ እንዲሁም እንዲያገቡ አላስፈላጊ ጫና ያሳድርባቸዋል።” እንዲህ ከምናደርግ ይልቅ፣ ያላገቡ ክርስቲያኖችን የምናመሰግንባቸውን አጋጣሚዎች ብንፈልግ ምንኛ የተሻለ ነው!—1 ተሰ. 5:11

15. (ሀ) በሮም 15:2 ላይ ባለው መሠረታዊ ሥርዓት መሠረት አንድ ሰው የትዳር ጓደኛ እንዲያገኝ ከመርዳታችን በፊት ምን ማሰብ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) ከቪዲዮው ምን ትምህርት አግኝታችኋል?

15 አንድ ወንድምና አንዲት እህት ጥሩ ባልና ሚስት ሊወጣቸው እንደሚችል ቢሰማህስ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሌሎች ስሜት እንድናስብ ይመክረናል። (ሮም 15:2ን አንብብ።) በርካታ ያላገቡ ክርስቲያኖች ሌሎች ለትዳር የሚሆን ሰው እንዲያስተዋውቋቸው አይፈልጉም፤ ደግሞም ፍላጎታቸውን ልናከብርላቸው ይገባል። (2 ተሰ. 3:11) ሌሎች ግን እገዛ ቢያገኙ ደስ ይላቸው ይሆናል፤ ሆኖም ሳንጠየቅ ለመርዳት መሞከር የለብንም። f (ምሳሌ 3:27) አንዳንድ ያላገቡ ክርስቲያኖች ደግሞ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ቢያገናኟቸው ይመርጡ ይሆናል። በጀርመን የምትኖር ሊዲያ የተባለች ያላገባች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ወንድምና እህትን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር አብራችሁ መጋበዝ ትችላላችሁ። ሁለቱ እንዲገናኙ አጋጣሚ ከፈጠራችሁላቸው በቂ ነው፤ የቀረውን ለእነሱ ተዉት።”

ሰብሰብ ብሎ መጨዋወት ያላገቡ ክርስቲያኖች የሚገናኙበት አጋጣሚ ይፈጥራል (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)


16. ያላገቡ ክርስቲያኖች ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል?

16 ያገባን ሆንንም ያላገባን፣ ሁላችንም ደስተኛና አርኪ ሕይወት መምራት እንችላለን! (መዝ. 128:1) በመሆኑም ማግባት ብትፈልግም እስካሁን የሚሆንህ ሰው ካላገኘህ ለይሖዋ በምታቀርበው አገልግሎት ላይ ትኩረት ማድረግህን ቀጥል። ሲን ዪ የተባለች በማካው የምትኖር እህት እንዲህ ብላለች፦ “በገነት ውስጥ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ልታሳልፉ ከምትችሉት ጊዜ አንጻር በነጠላነት የምታሳልፉት ጊዜ አጭር ነው። ይህን ጊዜ አጣጥሙት፤ እንዲሁም ጥሩ አድርጋችሁ ተጠቀሙበት።” ይሁንና የትዳር ጓደኛ ልትሆንህ የምትችል ሴት አግኝተህ መጠናናት ጀምረህ ከሆነስ? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በተሳካ ሁኔታ መጠናናት የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

መዝሙር 137 ታማኝ ሴቶች፣ ክርስቲያን እህቶች

a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ ርዕስ ውስጥ ትዳር የሚፈልገውን ሰው በወንድ ፆታ ገልጸነዋል። ሆኖም ሐሳቦቹ ለእህቶችም በእኩል መጠን ይሠራሉ።

b ለጋብቻ ዝግጁ መሆን አለመሆንህን ለማወቅ jw.org ላይ የሚገኘውን “የፍቅር ጓደኝነት—ክፍል 1፦ የፍቅር ጓደኛ ለመያዝ ደርሻለሁ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ “መጠናናት” የሚለው ቃል አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለጋብቻ የሚጣጣሙ መሆናቸውን ለመወሰን ሲሉ ይበልጥ ለመተዋወቅ የሚያሳልፉትን ጊዜ ያመለክታል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ መተዋወቅ ወይም የፍቅር ጓደኝነት ተብሎም ይጠራል። መጠናናት የሚጀምረው አንድ ወንድና አንዲት ሴት የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት እንደሚፈልጉ በግልጽ ከተነጋገሩ በኋላ ሲሆን የሚያበቃው ደግሞ ለመጋባት ወይም ግንኙነቱን ለማቆም ሲወስኑ ነው።

d አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

e በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ብዙውን ጊዜ መጠናናት ለመጀመር የሚጠይቁት ወንድሞች ናቸው። ሆኖም እህቶችም ለወንድሞች ጥያቄ ቢያቀርቡ ምንም ችግር የለውም። (ሩት 3:1-13) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በኅዳር 2004 ንቁ! ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . እንደማፈቅረው እንዴት ብዬ ልገልጽለት እችላለሁ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።