በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 19

መዝሙር 22 በሰማይ የተቋቋመው መንግሥት ይምጣልን!

ይሖዋ ወደፊት ስለሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ምን እናውቃለን?

ይሖዋ ወደፊት ስለሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ምን እናውቃለን?

“ይሖዋ . . . ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።”—2 ጴጥ. 3:9

ዓላማ

ይሖዋ ወደፊት የሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደሚሆኑ መተማመን እንችላለን።

1. የምንኖረው አስደናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

 የምንኖርበት ዘመን አስደናቂ ነው። በየዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ በዓይናችን እንመለከታለን። ለምሳሌ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እና “የደቡቡ ንጉሥ” ዓለምን ለመቆጣጠር እርስ በርሳቸው ሲታገሉ እናያለን። (ዳን. 11:40 ግርጌ) የአምላክ መንግሥት ምሥራች ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እየተሰበከ ነው፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው። (ኢሳ. 60:22፤ ማቴ. 24:14) በተጨማሪም “በተገቢው ጊዜ” የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እየቀረበልን ነው።—ማቴ. 24:45-47

2. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ሆኖም የትኛውን ሐቅ አምነን መቀበል ይኖርብናል?

2 ይሖዋ በቅርቡ ስለሚከሰቱ ጉልህ ክንውኖች ይበልጥ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖረን እየረዳን ነው። (ምሳሌ 4:18፤ ዳን. 2:28) ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ወቅት፣ ያንን አስቸጋሪ ጊዜ በታማኝነት ለማለፍና በመንፈሳዊ ለማበብ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ እንደምናውቅ መተማመን እንችላለን። ይሁንና በቅርቡ ከሚከሰቱት ነገሮች ጋር በተያያዘ የማናውቃቸው ነገሮች መኖራቸውን አምነን መቀበል ይኖርብናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ መጀመሪያ ላይ ከእነዚህ ክንውኖች ጋር በተያያዘ ያለንን ግንዛቤ ያስተካከልንበትን ምክንያት እንመለከታለን። ቀጥሎ ደግሞ የወደፊቱን ጊዜ እንዲሁም የሰማዩ አባታችን የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ የምናውቃቸውን አንዳንድ ነገሮች እንመለከታለን።

የማናውቀው ነገር

3. ሰዎች ከይሖዋ ጎን መቆም የሚችሉበት አጋጣሚ ከሚያበቃበት ጊዜ ጋር በተያያዘ ምን እንል ነበር? እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረስነውስ ለምንድን ነው?

3 ቀደም ሲል፣ ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ከይሖዋ ጎን መቆምና ከአርማጌዶን መትረፍ እንደማይችሉ እንናገር ነበር። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረስነው ስለ ጥፋት ውኃው የሚናገረው ዘገባ ትንቢታዊ ጥላ እንደሆነ እናምን ስለነበር ነው። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ የጥፋት ውኃው ከመጀመሩ በፊት የመርከቡን በር እንደዘጋው ሁሉ ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ በሰይጣን ሥርዓት ላይ በሩን እንደሚዘጋበትና ተጨማሪ ሰዎች መዳን እንደማይችሉ እናምን ነበር።—ማቴ. 24:37-39

4. ስለ ጥፋት ውኃው የሚናገረው ዘገባ ትንቢታዊ ጥላነት አለው ማለት ያቆምነው ለምንድን ነው?

4 ስለ ጥፋት ውኃው የሚገልጸውን ዘገባ እንደ ትንቢታዊ ጥላ ልንመለከተው ይገባል? አይገባም። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ለማለት የሚያበቃ ቀጥተኛ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የለም። a ኢየሱስ ‘የኖኅን ዘመን’ ከእሱ መገኘት ጋር አመሳስሎታል። ሆኖም የጥፋት ውኃው ትንቢታዊ ጥላ እንደሆነ ማለትም በዘገባው ውስጥ የተካተተው እያንዳንዱ ግለሰብና እያንዳንዱ ክስተት የሚያመለክተው ነገር እንዳለ አልገለጸም፤ በተጨማሪም የመርከቡ በር መዘጋት ትንቢታዊ ጥላነት እንዳለው አልተናገረም። ያም ቢሆን ስለ ኖኅና ስለ ጥፋት ውኃው ከሚናገረው ዘገባ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።

5. (ሀ) ኖኅ ከጥፋት ውኃው በፊት ምን አድርጓል? (ዕብራውያን 11:7፤ 1 ጴጥሮስ 3:20) (ለ) ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ በዛሬው ጊዜ ያለንበት ሁኔታ ከኖኅ ዘመን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

5 ኖኅ የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክት ሲሰማ መርከብ በመሥራት እምነት እንዳለው አሳይቷል። (ዕብራውያን 11:7ን እና 1 ጴጥሮስ 3:20ን አንብብ።) በተመሳሳይም የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰሙ ሰዎች በሰሙት ነገር ላይ ተመሥርተው እርምጃ መውሰድ አለባቸው። (ሥራ 3:17-20) ጴጥሮስ ኖኅን “የጽድቅ ሰባኪ” በማለት ጠርቶታል። (2 ጴጥ. 2:5) ያም ቢሆን ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ ኖኅ የጥፋት ውኃው ከመድረሱ በፊት በምድር ላይ ያሉትን ሰዎች በሙሉ ለማግኘት የስብከት ዘመቻ አካሂዶ እንደሆነ አናውቅም። በዛሬው ጊዜ ዓለም አቀፍ የስብከት ዘመቻ እየተካሄደ ነው፤ እኛም በዚህ ሥራ በቅንዓት ለመካፈል የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ያም ቢሆን ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምድር ላይ ላለ ሰው ሁሉ ምሥራቹን ማዳረስ አንችልም። ለምን?

6-7. መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት በምድር ላይ ለሚኖር ለእያንዳንዱ ሰው ምሥራቹን መስበክ አንችልም የምንለው ለምንድን ነው? አብራራ።

6 ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ ስለሚኖረው ስፋት ምን እንዳለ ልብ በል። ምሥራቹ “ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” እንደሚሰበክ ትንቢት ተናግሯል። (ማቴ. 24:14) ይህ ትንቢት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። የመንግሥቱ መልእክት ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይዘጋጃል፤ እንዲሁም በ​jw.org ድረ ገጽ አማካኝነት አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ምሥራቹን ማግኘት ይችላል።

7 ይሁንና ኢየሱስ፣ እሱ ከመምጣቱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ ሁሉንም “ከተሞችና መንደሮች” ፈጽሞ እንደማያዳርሱ፣ በሌላ አባባል ለሁሉም ሰው እንደማይሰብኩ ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 10:23፤ 25:31-33) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ በዛሬው ጊዜም እውነት ነው። በዛሬው ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚኖሩት በነፃነት መስበክ በማንችልባቸው አካባቢዎች ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በየደቂቃው በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጆች ይወለዳሉ። ምሥራቹን “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” ለማዳረስ የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። (ራእይ 14:6) ሆኖም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምድር ላይ ላለ ለእያንዳንዱ ሰው ምሥራቹን መስበክ እንደማንችል የታወቀ ነው።

8. ይሖዋ ወደፊት ከሚወስደው የፍርድ እርምጃ ጋር በተያያዘ ምን ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

8 ይህ አንድ ጥያቄ ያስነሳል፦ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ ስለማያገኙ ሰዎች ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ እና የመፍረድ ሥልጣን የሰጠው ልጁ በእነዚህ ሰዎች ላይ ምን ዓይነት እርምጃ ይወስዳሉ? (ዮሐ. 5:19, 22, 27፤ ሥራ 17:31) ይህ የጥናት ርዕስ የተመሠረተበት ጥቅስ ይሖዋ ‘ማንም እንዲጠፋ እንደማይፈልግ’ ይናገራል። ከዚህ ይልቅ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ” ይፈልጋል። (2 ጴጥ. 3:9፤ 1 ጢሞ. 2:4) ስለ ይሖዋ ይህን ብናውቅም፣ ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ ባላገኙ ሰዎች ላይ ምን ዓይነት ፍርድ እንደሚያስተላልፍ ይሖዋ አልገለጠልንም። ደግሞም ይሖዋ ከዚህ በፊት ስላደረገውም ሆነ ወደፊት ስለሚያደርገው ነገር ለእኛ ምንም ነገር የመናገር ግዴታ የለበትም።

ይሖዋ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ምሥራቹን ለመስማት አጋጣሚ ባላገኙ ሰዎች ላይ የሚፈርደው እንዴት ነው? (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት) c


9. ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ምን ገልጦልናል?

9 ይሖዋ ወደፊት የሚያደርጋቸውን አንዳንድ ነገሮች በቃሉ ውስጥ ገልጦልናል። ለምሳሌ ይሖዋ ምሥራቹን ሰምተው በሕይወታቸው ላይ ማስተካከያ ለማድረግ አጋጣሚ ያላገኙ ‘ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎችን’ ከሞት እንደሚያስነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ሥራ 24:15፤ ሉቃስ 23:42, 43) ይህ ሌሎች ወሳኝ ጥያቄዎችን ያስነሳል።

10. የትኞቹ ተጨማሪ ጥያቄዎች ይነሳሉ?

10 ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ የሞቱ ሁሉ ትንሣኤ ላያገኙ ለዘላለም ይጠፋሉ? ይሖዋና ሠራዊቱ በአርማጌዶን ጦርነት ላይ የሚያጠፏቸው ተቃዋሚዎች ከሞት እንደማይነሱ ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ይናገራሉ። (2 ተሰ. 1:6-10) ሆኖም ስለ ሌሎቹ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ለምሳሌ በዚያ ወቅት በተፈጥሯዊ ምክንያት፣ በአደጋ ወይም በሰው እጅ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ምን ይሆናሉ? (መክ. 9:11፤ ዘካ. 14:13) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከሚነሱት “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” መካከል ይገኙ ይሆን? የዚህን ጥያቄ መልስ አናውቀውም።

የምናውቀው ነገር

11. በአርማጌዶን ወቅት ሰዎች የሚፈረድባቸው በምን መሠረት ነው?

11 ወደፊት ከሚከናወኑት ነገሮች ጋር በተያያዘ የምናውቃቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ በአርማጌዶን ወቅት ሰዎች የሚፈረድባቸው ለክርስቶስ ወንድሞች ባደረጉት ነገር መሠረት እንደሆነ እናውቃለን። (ማቴ. 25:40) “በጎች” ተብለው የሚፈረድላቸው ለቅቡዓኑና ለክርስቶስ ድጋፍ ያደረጉ ሰዎች ናቸው። ከዚህም ሌላ፣ ከክርስቶስ ወንድሞች መካከል አንዳንዶቹ ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ በምድር ላይ እንደሚኖሩና አርማጌዶን ሊጀምር ትንሽ እስኪቀረው ድረስ ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ እናውቃለን። የክርስቶስ ወንድሞች ምድር ላይ እስካሉ ድረስ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እነሱንና ሥራቸውን ለመደገፍ አጋጣሚ ሊያገኙ ይችላሉ። (ማቴ. 25:31, 32፤ ራእይ 12:17) እነዚህ ነጥቦች ትኩረታችንን የሚስቡት ለምንድን ነው?

12-13. አንዳንዶች ‘የታላቂቱ ባቢሎንን’ ጥፋት ከተመለከቱ በኋላ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

12 ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላም እንኳ፣ ‘የታላቂቱ ባቢሎንን’ ጥፋት ያዩ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ከረጅም ጊዜ በፊት ስለዚህ ክንውን ይናገሩ እንደነበር ያስታውሱ ይሆናል። እነዚህን ክንውኖች የሚያዩ አንዳንድ ሰዎች አቋማቸውን ያስተካክሉ ይሆን?—ራእይ 17:5፤ ሕዝ. 33:33

13 እንዲህ ከሆነ፣ በሙሴ ዘመን በግብፅ ከተፈጠረው ነገር ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በወቅቱ ከእስራኤላውያን ጋር አብሮ የወጣ “እጅግ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” እንደነበር አስታውስ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ ሙሴ ስለ አሥሩ መቅሰፍቶች የተናገረው ማስጠንቀቂያ መፈጸሙን ሲያዩ እምነት ማዳበር ጀምረው ሊሆን ይችላል። (ዘፀ. 12:38) የታላቂቱን ባቢሎን ጥፋት ተከትሎ እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመ፣ መጨረሻው ልክ ሊደርስ ሲል ከእኛ ጋር የተቀላቀሉ ሰዎች በመኖራቸው እናዝናለን? በፍጹም! “መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን መምሰል እንፈልጋለን። bዘፀ. 34:6

የታላቂቱን ባቢሎን ጥፋት የሚመለከቱ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ከረጅም ጊዜ በፊት ስለዚህ ክንውን ይናገሩ እንደነበር ያስታውሳሉ (ከአንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት) d


14-15. አንድ ሰው የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚው የተመካው በሚሞትበት ጊዜ ወይም በሚኖርበት አካባቢ ላይ ነው? አብራራ። (መዝሙር 33:4, 5)

14 አንዳንድ ክርስቲያኖች ዘመዶቻቸውን በተመለከተ እንዲህ ሲሉ እንሰማ ይሆናል፦ “ትንሣኤ እንዲያገኝ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ቢሞት ሳይሻል አይቀርም።” እንዲህ የሚሉት በደግነት ተነሳስተው እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ሆኖም ሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘታቸው አጋጣሚ የተመካው በሚሞቱበት ጊዜ ላይ አይደለም። ይሖዋ ፍጹም የሆነ ዳኛ ስለሆነ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ትክክለኛና ፍትሐዊ ናቸው። (መዝሙር 33:4, 5ን አንብብ።) “የምድር ሁሉ ዳኛ” ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ መተማመን እንችላለን።—ዘፍ. 18:25

15 በተጨማሪም ሰዎች የዘላለም ሕይወት የማግኘታቸው አጋጣሚ በሚኖሩበት አካባቢ ላይ የተመካ አይደለም ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው። ይሖዋ በሚኖሩበት አገር የተነሳ ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ ለመስጠት አጋጣሚ ያላገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን እዚያ አካባቢ በመኖራቸው ብቻ ‘ፍየል ናቸው’ ብሎ ይፈርድባቸዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። (ማቴ. 25:46) ጻድቅ የሆነው የምድር ሁሉ ዳኛ ከማናችንም በላይ ለእነዚህ ሰዎች ያስባል። ይሖዋ በታላቁ መከራ ወቅት ሁኔታዎችን እንዴት እንደሚያመቻች አናውቅም። ምናልባትም ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ስለ ይሖዋ የመማር፣ በእሱ የማመን እንዲሁም በብሔራት ሁሉ መካከል ራሱን በሚቀድስበት ጊዜ ከእሱ ጎን የመሰለፍ አጋጣሚ ያገኙ ይሆናል።—ሕዝ. 38:16

ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላም እንኳ . . . እነዚህን ክንውኖች የሚያዩ አንዳንድ ሰዎች አቋማቸውን ያስተካክሉ ይሆን?

16. ስለ ይሖዋ የትኞቹን ነገሮች እናውቃለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ይሖዋ የሰዎችን ሕይወት ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ተምረናል። ሁላችንም የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ እንዲኖረን ሲል ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 3:16) ሁላችንም የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ አጣጥመናል። (ኢሳ. 49:15) እያንዳንዳችንን በስም ያውቀናል። እንዲያውም ማንነታችንን የሚገነቡትን ትዝታዎች ጨምሮ ስለ እኛ እያንዳንዱን ዝርዝር ነገር ስለሚያውቅ ብንሞት ድጋሚ ሊፈጥረን ይችላል! (ማቴ. 10:29-31) በእርግጥም አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ፍጹም ሚዛናዊ፣ ፍትሐዊና ምሕረት የሚንጸባረቅበት ፍርድ እንደሚያስተላልፍ መተማመን እንችላለን።—ያዕ. 2:13

ይሖዋ በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ፍጹም ሚዛናዊ፣ ፍትሐዊና ምሕረት የሚንጸባረቅበት ፍርድ እንደሚያስተላልፍ መተማመን እንችላለን (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)


17. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

17 እነዚህ ማስተካከያዎች የስብከቱ ሥራችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጣዳፊ እንደሆነ እንድንገነዘብ ያደርጉናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምሥራቹን ያለማሰለስ ለመስበክ የሚያነሳሳንስ ምንድን ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በዝርዝር እንመለከታለን።

መዝሙር 76 ምን ይሰማሃል?

a ይህ ማስተካከያ የተደረገው ለምን እንደሆነ ማብራሪያ ለማግኘት በመጋቢት 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 7-11 ላይ ያለውን “ይህ የአንተ ፈቃድ ነው” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ የማጎጉ ጎግ ጥቃት ሲሰነዝር ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ይፈተናሉ። ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ ከይሖዋ ሕዝቦች ጎን የተሰለፉ ሰዎችም አብረው ይፈተናሉ።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ ዓለም አቀፉ የስብከት ዘመቻችን አንዳንድ ሰዎች ጋ ላይደርስ የሚችለው ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ ሦስት ሁኔታዎች፦ (1) በአካባቢው ዋነኛ ሃይማኖት የተነሳ መስበክ አደገኛ በሆነበት አካባቢ የምትኖር ሴት፣ (2) በፖለቲካው ሥርዓት የተነሳ መስበክ ሕገ ወጥና አደገኛ በሆነበት አካባቢ የሚኖሩ ባልና ሚስት እንዲሁም (3) በጣም ሩቅና ገለልተኛ በሆነ አካባቢ ከመኖሩ የተነሳ ምሥራቹን መስማት ያልቻለ ሰው።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ እውነትን የተወች አንዲት ወጣት ሴት ስለ “ታላቂቱ ባቢሎን” ጥፋት የተማረችውን ነገር ታስታውሳለች። አመለካከቷን አስተካክላ ወደ ክርስቲያን ወላጆቿ ተመለሰች። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን ባሕርይ በመኮረጅ ኃጢአተኛው በመመለሱ ልንደሰት ይገባል።