በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 23

መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን

ይሖዋ እንግዶቹ እንድንሆን ጋብዞናል

ይሖዋ እንግዶቹ እንድንሆን ጋብዞናል

“ድንኳኔ ከእነሱ ጋር ይሆናል፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።”ሕዝ. 37:27

ዓላማ

ይሖዋ በምሳሌያዊ ድንኳኑ ውስጥ እንግዶቹ እንድንሆን ላቀረበልን ግብዣ እንዲሁም ለእንግዶቹ ለሚያደርገው እንክብካቤ ያለንን አድናቆት ማሳደግ።

1-2. ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ምን ግብዣ አቅርቧል?

 ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ ምን ዓይነት ቦታ አለው? ‘ይሖዋ አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ ነው’ ብለህ ትመልስ ይሆናል። ይሖዋን ለመግለጽ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ሌሎች የማዕረግ ስሞችም አሉ። ሆኖም እንደ ጋባዥህ አድርገህስ ትመለከተዋለህ?

2 ንጉሥ ዳዊት ይሖዋ ከታማኝ አገልጋዮቹ ጋር ያለውን ወዳጅነት አንድ ጋባዥ ከእንግዶቹ ጋር ካለው ዝምድና ጋር አመሳስሎታል። እንዲህ ሲል ጠይቋል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በድንኳንህ ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ማን ነው? በተቀደሰ ተራራህ የሚኖር ማን ነው?” (መዝ. 15:1) ዳዊት በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ቃላት የይሖዋ እንግዶች ወይም ወዳጆች መሆን እንደምንችል ያስገነዝቡናል። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ግብዣ ነው!

ይሖዋ እንግዶቹ እንድንሆን ይፈልጋል

3. የይሖዋ የመጀመሪያ እንግዳ ማን ነው? ይሖዋና እንግዳው አንዳቸው ስለ ሌላቸው ምን ይሰማቸው ነበር?

3 ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ብቻውን ነበር። ከዚያ ግን የበኩር ልጁን ፈጠረ። በዚህ መንገድ የመጀመሪያ እንግዳውን ወደ ምሳሌያዊ ድንኳኑ ጋበዘ። ይሖዋ እንግዶችን መቀበል በመጀመሩ በጣም ተደስቷል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በልጁ የተነሳ ‘ልዩ ደስታ ይሰማው’ እንደነበር ይናገራል። የመጀመሪያ እንግዳው የሆነው ልጁም ‘በይሖዋ ፊት ሁልጊዜ ሐሴት ያደርግ ነበር።’—ምሳሌ 8:30

4. ይሖዋ ቀስ በቀስ ድንኳኑን ያሰፋው እንዴት ነው?

4 ቀጥሎም ይሖዋ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታትን በመፍጠር እንግዶቹ እንዲሆኑ ጋበዛቸው። መላእክቱ ‘የአምላክ ልጆች’ ተብለው ተጠርተዋል፤ እነሱም ከይሖዋ ጋር በመሆናቸው ደስተኞች ናቸው። (ኢዮብ 38:7፤ ዳን. 7:10) ለተወሰነ ጊዜ ያህል ይሖዋ ወዳጆች የነበሩት እሱ በሚኖርበት በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ብቻ ነበር። በኋላ ግን ሰዎችን ፈጠረ። በዚህ መንገድ ድንኳኑን በማስፋት በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችንም እንዲያካትት አደረገ። ከይሖዋ እንግዶች መካከል ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃምና ኢዮብ ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች የአምላክ ወዳጆች እንደሆኑ ወይም ‘ከእውነተኛው አምላክ ጋር እንደሄዱ’ ተገልጿል።—ዘፍ. 5:24፤ 6:9፤ ኢዮብ 29:4፤ ኢሳ. 41:8

5. በሕዝቅኤል 37:26, 27 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ምን እንማራለን?

5 ባለፉት ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ወዳጆቹን ወደ ድንኳኑ ሲጋብዝ ቆይቷል። (ሕዝቅኤል 37:26, 27ን አንብብ።) ለምሳሌ የሕዝቅኤል ትንቢት፣ አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖራቸው እንደሚፈልግ ያሳያል። ከእነሱ ጋር ‘የሰላም ቃል ኪዳን እንደሚገባ’ ተናግሯል። ይህ ትንቢት ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች በምሳሌያዊ ድንኳኑ ውስጥ “አንድ መንጋ” የሚሆኑበት ጊዜ እንደሚመጣ ያሳያል። (ዮሐ. 10:16) ይህ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ነው።

የትም ብንሆን አምላክ ይንከባከበናል

6. አንድ ሰው በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንግዳ የሚሆነው እንዴት ነው? ድንኳኑስ የሚገኘው የት ነው?

6 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ድንኳን አንድ ሰው እረፍት የሚያገኝበት እንዲሁም ከዝናብና ከፀሐይ የሚጠለልበት ቦታ ነበር። ወደዚህ ድንኳን እንዲገባ የሚጋበዝ እንግዳ ጥሩ እንክብካቤ እንደሚደረግለት መጠበቅ ይችላል። ራሳችንን ወስነን የይሖዋ ወዳጆች ስንሆን በእሱ ምሳሌያዊ ድንኳን ውስጥ እንግዶቹ እንሆናለን። (መዝ. 61:4) የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እናገኛለን፤ እንዲሁም ከሌሎቹ የይሖዋ እንግዶች ጋር ጥሩ ወዳጅነት ይኖረናል። የይሖዋ ምሳሌያዊ ድንኳን በአንድ ቦታ የተወሰነ አይደለም። ወደ ሌላ አገር ስትጓዝ ምናልባትም በልዩ የክልል ስብሰባ ላይ ስትገኝ በአምላክ ድንኳን ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰዎችን አግኝተህ ይሆናል። የይሖዋ ታዛዥ አገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሁሉ ድንኳኑ አለ።—ራእይ 21:3

7. በሞት ያንቀላፉ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች አሁንም በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንግዶች ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 በሞት ስላንቀላፉ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችስ ምን ማለት ይቻላል? አሁንም በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንግዶች ናቸው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው? በሚገባ! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህን ሰዎች ይሖዋ ስለማይረሳቸው በእሱ ዘንድ ሕያው ናቸው። ኢየሱስ ሁኔታውን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “ሙሴም እንኳ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ ይሖዋን ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ’ ብሎ በጠራው ጊዜ ሙታን እንደሚነሡ አስታውቋል። እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸውና።”—ሉቃስ 20:37, 38

በሞት ያንቀላፉ ታማኝ ሰዎች እንኳ በአምላክ ድንኳን ውስጥ እንግዶች እንደሆኑ ሊቆጠር ይችላል (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)


የምናገኘው ጥቅምና ያለብን ኃላፊነት

8. የይሖዋ እንግዶች ድንኳኑ ውስጥ መሆናቸው ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?

8 ድንኳን የእረፍት ቦታና ጥላ ከለላ እንደሚሆን ሁሉ የይሖዋ ድንኳንም ለእንግዶቹ ከመንፈሳዊ ጉዳትና ከተስፋ መቁረጥ ጥበቃ ያስገኝላቸዋል። ይሖዋን የሙጥኝ ካልን ሰይጣን ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን አይችልም። (መዝ. 31:23፤ 1 ዮሐ. 3:8) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ደግሞ ይሖዋ ወዳጆቹን ከመንፈሳዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ከሞትም እንኳ ይጠብቃቸዋል።—ራእይ 21:4

9. ይሖዋ እንግዶቹ ምን ዓይነት ምግባር እንዲኖራቸው ይጠብቅባቸዋል?

9 በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንግዳ መሆን ይኸውም ከእሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ ዘላቂ ዝምድና መመሥረት ታላቅ ክብር ነው። የእሱ እንግዶች ሆነን መቀጠል ከፈለግን ምን ዓይነት ምግባር ሊኖረን ይገባል? አንድ ሰው ወደ ቤቱ ከጋበዘህ ከአንተ ምን እንደሚጠብቅ ማወቅ እንደምትፈልግ ጥያቄ የለውም። ለምሳሌ ወደ ውስጥ ከመግባትህ በፊት ጫማህን እንድታወልቅ ሊጠብቅብህ ይችላል፤ አንተም እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆንህ አይቀርም። በተመሳሳይም ይሖዋ በድንኳኑ ውስጥ በእንግድነት መቀጠል ከሚፈልጉ ሰዎች ምን እንደሚጠብቅባቸው ማወቅ እንፈልጋለን። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ‘እሱን ሙሉ በሙሉ ለማስደሰት’ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ቆላ. 1:10) ከዚህም ሌላ ይሖዋን እንደ ወዳጃችን አድርገን የምንመለከተው ቢሆንም እንኳ አምላካችንና አባታችን እንደሆነም እንገነዘባለን፤ በመሆኑም አክብሮት ይገባዋል። (መዝ. 25:14) ከዚህ አንጻር፣ ይሖዋ ያለውን ሥልጣን በመገንዘብ ምንጊዜም ለእሱ ጥልቅ አክብሮት ሊኖረን ይገባል። እንዲህ ያለው አክብሮት እሱን የሚያሳዝን ምግባር እንዳይኖረን ይረዳናል። ‘ልካችንን አውቀን ከአምላካችን ጋር መሄድ’ እንፈልጋለን።—ሚክ. 6:8

ይሖዋ እስራኤላውያንን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ ይዟቸዋል

10-11. ይሖዋ በሲና ምድረ በዳ የነበሩትን እስራኤላውያን የያዘበት መንገድ የማያዳላ አምላክ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

10 ይሖዋ እንግዶቹን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ ይይዛቸዋል። (ሮም 2:11) እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ እነሱን የያዘበት መንገድ የማያዳላ አምላክ መሆኑን ያሳያል።

11 ይሖዋ ሕዝቡን ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣቸው በኋላ በማደሪያው ድንኳን የሚያገለግሉ ካህናትን ሾመ። ሌዋውያን ደግሞ ከቅዱሱ ድንኳን ጋር በተያያዘ ሌሎች ኃላፊነቶች ነበሯቸው። ይሖዋ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ለሚያገለግሉ ወይም በአቅራቢያው ለሰፈሩ እስራኤላውያን የተለየ እንክብካቤ ያደርግላቸው ነበር? በፍጹም! ይሖዋ አያዳላም።

12. ይሖዋ አዲስ ከተመሠረተው ብሔር ጋር በተያያዘ የማያዳላ ጋባዥ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው? (ዘፀአት 40:38) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 ሁሉም እስራኤላውያን የይሖዋ ወዳጆች የመሆን እኩል አጋጣሚ ነበራቸው። ይህ የተመካው አንድ እስራኤላዊ ባለው ልዩ የአገልግሎት መብት ወይም በማደሪያ ድንኳኑ አቅራቢያ በመስፈሩ ወይም ባለመስፈሩ ላይ አይደለም። ለምሳሌ ይሖዋ በማደሪያ ድንኳኑ ላይ ያለውን ተአምራዊ የደመና ዓምድና የእሳት ዓምድ መላው ብሔር ማየት እንዲችል አድርጎ ነበር። (ዘፀአት 40:38ን አንብብ።) ደመናው መንቀሳቀስ ሲጀምር ከማደሪያ ድንኳኑ በጣም ርቀው የሰፈሩ እስራኤላውያን እንኳ ማየት ይችሉ ነበር፤ እነሱም ዕቃቸውን ሰብስበው፣ ድንኳናቸውን አፍርሰው ከቀረው ብሔር ጋር መጓዝ ይችላሉ። (ዘኁ. 9:15-23) በተጨማሪም ሕዝቡ ተነስቶ መጓዝ እንዲጀምር ምልክት የሚሰጡ ሁለት የብር መለከቶች ይነፉ ነበር፤ ሁሉም እስራኤላውያን ይህን ኃይለኛ ድምፅ መስማት ይችላሉ። (ዘኁ. 10:2) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ አንድ ሰው በማደሪያ ድንኳኑ አቅራቢያ መኖሩ ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዳለው የሚያሳይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ አዲስ በመሠረተው ብሔር ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው የእሱ እንግዳ መሆን እንዲሁም አመራሩንና ጥበቃውን ማግኘት ይችላል። ዛሬም በተመሳሳይ የምንኖረው የትም ይሁን የት የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤና ጥበቃ ማግኘት እንችላለን።

አምላክ ከማደሪያ ድንኳኑ ጋር በተያያዘ ያደረገው ዝግጅት የማያዳላ አምላክ እንደሆነ ያሳያል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)


ይሖዋ እንደማያዳላ የሚያሳዩ ዘመናዊ ምሳሌዎች

13. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እንደማያዳላ የሚያሳይበት አንዱ መንገድ የትኛው ነው?

13 በዛሬው ጊዜ አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦች የሚኖሩት በዋናው መሥሪያ ቤት ወይም በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች አቅራቢያ ነው። አንዳንዶች ደግሞ በእነዚህ ቦታዎች ውስጥ ያገለግላሉ። በዚህም የተነሳ በእነዚህ ቦታዎች በሚካሄዱት በአብዛኞቹ እንቅስቃሴዎች መካፈል እንዲሁም አመራር ከሚሰጡ ወንድሞች ጋር በግል መቀራረብ ይችላሉ። በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ወይም በሌሎች የልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች የሚካፈሉም አሉ። አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ግን እንዲህ ያሉ መብቶች የሏቸውም። አንተም ከእነሱ አንዱ ከሆንክ፣ ጋባዣችን ይሖዋ ሁሉንም እንግዶቹን እንደሚወዳቸው እርግጠኛ ሁን። ሁሉንም በግለሰብ ደረጃ ይንከባከባቸዋል። (1 ጴጥ. 5:7) ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ፣ መመሪያና ጥበቃ ያገኛሉ።

14. ይሖዋ የማያዳላ ጋባዣችን እንደሆነ የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ጥቀስ።

14 ይሖዋ የማያዳላ ጋባዣችን እንደሆነ የሚያሳየው ሌላው ምሳሌ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት እንዲችሉ ማድረጉ ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት በመጀመሪያ የተጻፉት በሦስት ቋንቋዎች ማለትም በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክኛ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸውን ቋንቋዎች ማንበብ የሚችሉ ሰዎች ቋንቋዎቹን ከማይችሉ ሰዎች ይበልጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ ይችላሉ? አይችሉም።—ማቴ. 11:25

15. ይሖዋ እንደማያዳላ የሚያሳይ ማስረጃ ጥቀስ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር በትምህርት ደረጃችን ወይም በቋንቋ ችሎታችን ላይ የተመሠረተ አይደለም። ይሖዋ ጥበቡን፣ የተማሩ ሰዎች ብቻ እንዲያገኙት ከማድረግ ይልቅ የተማሩም ይሁኑ ያልተማሩ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች እንዲያገኙት አድርጓል። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ በሺዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በመሆኑም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም እንዲሁም የይሖዋ ወዳጆች መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር ይችላሉ።—2 ጢሞ. 3:16, 17

መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ በስፋት መገኘቱ አምላክ እንደማያዳላ የሚያረጋግጠው እንዴት ነው? (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)


በይሖዋ ዘንድ ያላችሁን “ተቀባይነት” እንዳታጡ ተጠንቀቁ

16. በሐዋርያት ሥራ 10:34, 35 መሠረት በይሖዋ ዘንድ ያለንን ተቀባይነት እንዳናጣ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

16 በይሖዋ ምሳሌያዊ ድንኳን ውስጥ እንግዳ ሆኖ መስተናገድ ትልቅ መብት ነው። ይሖዋ ከየትኛውም ጋባዥ ይበልጥ ደግ፣ አፍቃሪና እንግዳ ተቀባይ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ አያዳላም። የምንኖርበት ቦታ፣ አስተዳደጋችን፣ የትምህርት ደረጃችን፣ ዘራችን፣ ጎሳችን፣ ዕድሜያችን ወይም ፆታችን ምንም ይሁን ምን ሁላችንንም እንግዶቹ አድርጎ ተቀብሎናል። ያም ቢሆን የይሖዋ እንግዶች የሚሆኑት መሥፈርቶቹን የሚያሟሉ ሰዎች ብቻ ናቸው።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35ን አንብብ።

17. በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንግዳ ከመሆን ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

17 በመዝሙር 15:1 ላይ ዳዊት እንዲህ ሲል ጠይቋል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በድንኳንህ ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ማን ነው? በተቀደሰ ተራራህ የሚኖር ማን ነው?” መዝሙራዊው በመንፈስ መሪነት የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ተናግሯል። ቀጣዩ ርዕስ በይሖዋ ዘንድ ያለንን ተቀባይነት ሳናጣ ለመኖር ልናሟላቸው የሚገቡ አንዳንድ ብቃቶችን ይዘረዝራል።

መዝሙር 32 ከይሖዋ ጎን ቁም!