በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 24

መዝሙር 24 ኑ! ወደ ይሖዋ ተራራ

ለዘላለም የይሖዋ እንግዶች ሆናችሁ ኑሩ!

ለዘላለም የይሖዋ እንግዶች ሆናችሁ ኑሩ!

“ይሖዋ ሆይ፣ በድንኳንህ ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ማን ነው?”መዝ. 15:1

ዓላማ

የይሖዋ ወዳጆች ሆነን ለመቀጠል ምን እንደሚጠበቅብንና ወዳጆቹን እንዴት መያዝ እንዳለብን እንመረምራለን።

1. መዝሙር 15:1-5⁠ን መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

 ባለፈው ርዕስ ላይ፣ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች ከእሱ ጋር የቀረበና የግል ዝምድና በመመሥረት በምሳሌያዊ ድንኳኑ ውስጥ እንግዶች መሆን እንደሚችሉ ተመልክተን ነበር። ታዲያ እንዲህ ለመሰለው ወዳጅነት ብቁ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህ ጋር በተያያዘ ከመዝሙር 15 ብዙ ትምህርት እናገኛለን። (መዝሙር 15:1-5ን አንብብ።) ይህ መዝሙር ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚረዱ ተግባራዊ ትምህርቶችን ይዟል።

2. ዳዊት ስለ ይሖዋ ድንኳን የተናገረው ምን ነገር በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል?

2 መዝሙር 15 የሚጀምረው “ይሖዋ ሆይ፣ በድንኳንህ ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ማን ነው? በተቀደሰ ተራራህ የሚኖር ማን ነው?” በማለት ነው። (መዝ. 15:1) መዝሙራዊው ዳዊት፣ ስለ ይሖዋ “ድንኳን” የተናገረው ለተወሰነ ጊዜ በገባኦን የነበረውን የማደሪያ ድንኳን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። ዳዊት የአምላክን ‘የተቀደሰ ተራራም’ ጠቅሷል፤ ይህን ሲል በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የጽዮን ተራራ ማመልከቱ ሊሆን ይችላል። ዳዊት ለቃል ኪዳኑ ታቦት ቋሚ ማረፊያ እስኪገነባ ድረስ ከገባኦን በስተ ደቡብ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኘው በዚህ አካባቢ ለቃል ኪዳኑ ታቦት ድንኳን ተክሏል።—2 ሳሙ. 6:17

3. መዝሙር 15 ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

3 እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ እስራኤላውያን የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደሚገኝበት ድንኳን ውስጥ መግባት ይቅርና በማደሪያ ድንኳኑ ማገልገል እንኳ አይፈቀድላቸውም ነበር። ነገር ግን ሁሉም የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የይሖዋ ወዳጆች በመሆንና ወዳጅነታቸውን ይዘው በመቀጠል በምሳሌያዊ ድንኳኑ ውስጥ መስተናገድ ይችሉ ነበር። ሁላችንም ብንሆን የምንፈልገው ይህንኑ ነው። መዝሙር 15 ላይ የይሖዋ ወዳጆች ሆነን ለመቀጠል ልናዳብራቸውና ልናንጸባርቃቸው የሚገቡ አንዳንድ ባሕርያት ተጠቅሰዋል።

በዳዊት ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንግዳ ሆኖ መስተናገድ የሚለውን ሐሳብ በምናባቸው መሣል አይከብዳቸውም (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት)


ያለነቀፋ ተመላለሱ፤ ትክክል የሆነውን አድርጉ

4. ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው እንድንጠመቅ ብቻ እንዳልሆነ በምን እናውቃለን? (ኢሳይያስ 48:1)

4 መዝሙር 15:2 የአምላክ ወዳጅ የሚሆነው “ያለነቀፋ የሚመላለስ” እና “ትክክል የሆነውን የሚያደርግ” ሰው እንደሆነ ይናገራል። “የሚመላለስ” እና “የሚያደርግ” የሚሉት ቃላት ማዘውተርንና ቀጣይነትን የሚጠቁሙ ናቸው። ይሁንና በእርግጥ ‘ያለነቀፋ መመላለስ’ እንችላለን? አዎ። ፍጹም የሆነ ሰው ባይኖርም ይሖዋን ለመታዘዝ የምንችለውን ያህል ጥረት የምናደርግ ከሆነ ‘ያለነቀፋ እንደምንመላለስ’ አድርጎ ይመለከተናል። ራሳችንን ስንወስንና ስንጠመቅ ከአምላክ ጋር የምናደርገውን ጉዞ ገና መጀመራችን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ሰው የእስራኤል ብሔር አባል መሆኑ ብቻውን የይሖዋ እንግዳ ለመሆን ብቁ እንደማያደርገው ልናስታውስ ይገባል። አንዳንዶች አምላክን የሚጠሩ ቢሆንም የሚጠሩት “በእውነትና በጽድቅ” አልነበረም። (ኢሳይያስ 48:1ን አንብብ።) የይሖዋ እንግዶች የመሆን ልባዊ ፍላጎት ያላቸው እስራኤላውያን የይሖዋን መሥፈርቶች መማርና ተግባራዊ ማድረግ ነበረባቸው። ዛሬም በተመሳሳይ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መጠመቃችንና ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር መሰብሰባችን ብቻ በቂ አይደለም። ‘ትክክል የሆነውን ማድረጋችንን’ መቀጠል ይኖርብናል። ይህ ምንን ይጨምራል?

5. በሁሉም ነገሮች ይሖዋን መታዘዝ ምንን ያካትታል?

5 በይሖዋ አመለካከት ‘ያለነቀፋ መመላለስና ትክክል የሆነውን ማድረግ’ በአምልኮ ቦታችን በሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች አዘውትሮ መካፈል ማለት ብቻ አይደለም። (1 ሳሙ. 15:22) ብቻችንን የምንሆንበትን ጊዜ ጨምሮ በማንኛውም የሕይወታችን ክፍል አምላክን ለመታዘዝ ጥረት ልናደርግ ይገባል። (ምሳሌ 3:6፤ መክ. 12:13, 14) በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቃቅን በሚመስሉ ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር ይሖዋን ለመታዘዝ ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋችን እሱን ከልባችን እንደምንወደው ያሳያል፤ ይህ ደግሞ በእሱ ዘንድ ተወዳጅ ያደርገናል።—ዮሐ. 14:23፤ 1 ዮሐ. 5:3

6. በዕብራውያን 6:10-12 መሠረት ከዚህ ቀደም ካደረግናቸው የታማኝነት ድርጊቶች የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ምንድን ነው?

6 ይሖዋ ከዚህ በፊት እሱን ለማስደሰት ላደረግናቸው ነገሮች ከፍተኛ አድናቆት አለው። ነገር ግን በይሖዋ ድንኳን ውስጥ እንግዶች ሆነን ለመቀጠል ከአሁን በፊት ያከናወንናቸው የታማኝነት ድርጊቶች ብቻቸውን በቂ አይደሉም። ዕብራውያን 6:10-12 ይህን ግልጽ ያደርግልናል። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሖዋ ከዚህ ቀደም ያደረግናቸውን መልካም ነገሮች አይረሳም። ሆኖም “እስከ መጨረሻው” በሙሉ ነፍስ አምልኮ ማቅረባችንን እንድንቀጥል ይፈልጋል። “ካልታከትን” ለዘላለም ወዳጆቹ ሆነን የመኖር መብት በመስጠት ይባርከናል።—ገላ. 6:9

በልባችሁ እውነትን ተናገሩ

7. በልባችን እውነትን መናገር ሲባል ምን ማለት ነው?

7 አንድ ሰው ይሖዋ በድንኳኑ ውስጥ በእንግድነት እንዲቀበለው የሚፈልግ ከሆነ ‘በልቡ እውነትን የሚናገር’ መሆን አለበት። (መዝ. 15:2) ይህ ሲባል አለመዋሸት ማለት ብቻ አይደለም። ይሖዋ በሁሉም ነገር ሐቀኞች እንድንሆን ይፈልጋል። (ዕብ. 13:18) ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም “ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋል . . . ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው።”—ምሳሌ 3:32

8. ከምን ዓይነት ምግባር መራቅ አለብን?

8 ‘በልባቸው እውነትን የሚናገሩ’ ሰዎች በድብቅ የአምላክን ሕግጋት እየጣሱ በሰዎች ፊት ታዛዥ ለመምሰል አይሞክሩም። (ኢሳ. 29:13) ከማታለል ይቆጠባሉ። አታላይ ሰው አንዳንድ የይሖዋ መመሪያዎች ጥበብ ያዘሉ መሆናቸውን መጠራጠር ሊጀምር ይችላል። (ያዕ. 1:5-8) ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆኑ በሚሰሙት ጉዳዮች ይሖዋን ላይታዘዝ ይችላል። አለመታዘዙ ምንም መዘዝ እንዳላስከተለበት ከተሰማው ደግሞ የይሖዋን ሕግጋት የባሰ ለመጣስ ሊደፋፈር ይችላል፤ አምልኮቱም የግብዝነት ይሆንበታል። (መክ. 8:11) እኛ ግን በሁሉም ነገር ሐቀኞች መሆን እንፈልጋለን።

9. ኢየሱስ ናትናኤልን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያገኘው ከተናገረው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 ኢየሱስ ናትናኤልን ሲያገኘው ከተከሰተው ሁኔታ ሐቀኛ ልብ የመያዝን አስፈላጊነት እንመለከታለን። ፊልጶስ ጓደኛውን ናትናኤልን ወደ ኢየሱስ ባመጣው ጊዜ ትኩረት የሚስብ ነገር ተከስቷል። ኢየሱስ ከዚያ በፊት ናትናኤልን አግኝቶት ባያውቅም “ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይኸውላችሁ!” አለ። (ዮሐ. 1:47) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ሌሎች ደቀ መዛሙርቱም ሐቀኞች እንደሆኑ ያውቃል፤ ነገር ግን በናትናኤል ልብ ውስጥ አስደናቂ የሆነ ሐቀኝነት ተመልክቷል። ናትናኤል ልክ እንደ እኛ ፍጽምና የጎደለው ሰው ነው። ሆኖም ምንም ዓይነት ግብዝነት አልነበረበትም። ኢየሱስ ናትናኤልን ለሐቀኝነቱ አድንቆታል እንዲሁም አመስግኖታል። ኢየሱስ ስለ እኛም ተመሳሳይ ነገር ቢናገር ምንኛ ደስ ይለናል!

ፊልጶስ ምንም ተንኮል የሌለበትን ጓደኛውን ናትናኤልን ወደ ኢየሱስ አቀረበው። ስለ እኛስ ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል? (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)


10. አንደበታችንን ያለአግባብ ከመጠቀም መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው? (ያዕቆብ 1:26)

10 በመዝሙር 15 ላይ ከተዘረዘሩት መሥፈርቶች መካከል አብዛኞቹ ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ላይ ያተኮሩ ናቸው። መዝሙር 15:3 እንደሚናገረው በይሖዋ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት የተጋበዘ ሰው “በአንደበቱ ስም አያጠፋም፤ በባልንጀራው ላይ መጥፎ ነገር አይሠራም፤ የወዳጆቹንም ስም አያጎድፍም።” አንደበታችንን እንደዚህ በመሰሉ መንገዶች ያለአግባብ መጠቀማችን በሌሎች ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስና ይሖዋ በድንኳኑ ውስጥ በእንግድነት እንዳይቀበለን ሊያደርግ ይችላል።—ያዕቆብ 1:26ን አንብብ።

11. ስም ማጥፋት ምንድን ነው? ንስሐ በማይገቡ ስም አጥፊዎች ላይስ ምን እርምጃ ይወሰዳል?

11 መዝሙራዊው ስም ማጥፋትን ለይቶ ጠቅሷል። ስም ማጥፋት ምንድን ነው? አንድ ሰው በሌሎች ዘንድ ያተረፈውን መልካም ስም ለማጠልሸት ተብሎ የሚነገር የሐሰት ወሬ ነው። ንስሐ የማይገቡ ስም አጥፊዎች ከክርስቲያን ጉባኤ ይወገዳሉ።—ኤር. 17:10

12-13. ሳይታወቀን የወዳጆቻችንን ስም ልናጎድፍ የምንችለው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 መዝሙር 15:3 በይሖዋ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገዱ ሰዎች በባልንጀሮቻቸው ላይ መጥፎ ነገር እንደማይሠሩና የወዳጆቻቸውን ስም እንደማያጎድፉም ይናገራል። ይህ ምንን ያካትታል?

13 ስለ አንድ ሰው አሉታዊ መረጃ በማስተላለፍ ሳይታወቀን ስሙን ልናጎድፍ እንችላለን። አንዳንድ ሁኔታዎችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፦ (1) አንዲት እህት የሙሉ ጊዜ አገልግሎቷን አቆመች፤ (2) አንድ ባልና ሚስት በቤቴል ማገልገላቸውን አቆሙ፤ (3) አንድ ወንድም የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ማገልገሉን አቆመ። ለእነዚህ ለውጦች ምክንያት የሆነውን ነገር መገመትና ግምታችንን ለሌሎች መናገር ተገቢ ይሆናል? ለእነዚህ ለውጦች ምክንያት የሚሆኑ እኛ የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በይሖዋ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ሰው “በባልንጀራው ላይ መጥፎ ነገር አይሠራም፤ የወዳጆቹንም ስም አያጎድፍም።”

ስለ ሌሎች አሉታዊ መረጃ ማሰራጨት ቀላል ነው፤ ይህም ስም ወደማጥፋት ሊያመራ ይችላል (አንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት)


ይሖዋን የሚፈሩትን አክብሩ

14. የይሖዋ እንግዶች ‘ነውረኛ የሆነን ሰው የሚንቁት’ እንዴት እንደሆነ አብራራ።

14 መዝሙር 15:4 የይሖዋ ወዳጅ ስለሆነ ሰው ሲናገር “ነውረኛ የሆነን ሰው ሁሉ ይንቃል” ይላል። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ፍጽምና የሚጎድለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን አንድ ሰው ነውረኛ መሆን አለመሆኑን ለመወሰን ብቃቱ የለንም። ለምን? የአንዳንድ ሰዎች ባሕርይ ደስ ሊለን፣ የሌሎች ሰዎች ባሕርይ ደግሞ ሊያበሳጨን ይችላል። ሆኖም ልንንቅ የሚገባን በይሖዋ ዓይን “ነውረኛ” የሆኑ ሰዎችን ብቻ ነው። (1 ቆሮ. 5:11) ከእነዚህ ሰዎች መካከል መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙና ንስሐ የማይገቡ፣ እምነታችንን የሚያቃልሉ ወይም መንፈሳዊነታችንን ለማዳከም የሚሞክሩ ሰዎች ይገኙበታል።—ምሳሌ 13:20

15. ‘ይሖዋን የሚፈሩትን ማክበር’ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

15 በሌላ በኩል ግን መዝሙር 15:4 ‘ይሖዋን የሚፈሩትን እንድናከብር’ ያሳስበናል። ስለዚህም ለይሖዋ ወዳጆች ደግነትና አክብሮት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች እንፈልጋለን። (ሮም 12:10) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? መዝሙር 15:4 አንዱን መንገድ ሲጠቅስ በይሖዋ ድንኳን ውስጥ ያለ ሰው ‘ጉዳት ላይ ሊጥለው ቢችልም እንኳ ቃሉን እንደማያጥፍ’ ይናገራል። ቃላችንን ማጠፋችን ሌሎችን ሊጎዳ እንደሚችል ግልጽ ነው። (ማቴ. 5:37) ለምሳሌ ይሖዋ እንግዶቹ የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸዋል። ወላጆች ለልጆቻቸው የገቡትን ቃል ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ሲመለከትም ይደሰታል። ለአምላክና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር ቃላችንን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል።

16. የይሖዋን ወዳጆች የምናከብርበት ሌላኛው መንገድ ምንድን ነው?

16 የአምላክን ወዳጆች ማክበር የምንችልበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ ለጋሶችና እንግዳ ተቀባዮች በመሆን ነው። (ሮም 12:13) ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በመዝናናት የምናሳልፈው ጊዜ ከእነሱም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማጠናከር ይረዳናል። ከዚህም ሌላ እንግዳ ተቀባይ ስንሆን ይሖዋን እንመስለዋለን።

ከገንዘብ ፍቅር ራቁ

17. በመዝሙር 15 ላይ የገንዘብ ጉዳይ የተነሳው ለምንድን ነው?

17 መዝሙር 15 እንደሚናገረው በይሖዋ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ሰው “ገንዘቡን በወለድ አያበድርም፤ ንጹሕ የሆነውን ሰው ለመወንጀልም ጉቦ አይቀበልም።” (መዝ. 15:5) በዚህ አጭር መዝሙር ውስጥ የገንዘብ ጉዳይ የተጠቀሰው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለገንዘብ ሚዛናዊ ያልሆነ አመለካከት ካለን ሌሎችን ልንጎዳና ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ልናበላሽ እንችላለን። (1 ጢሞ. 6:10) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንዳንዶች ለድሃ ወንድሞቻቸው ገንዘብ በወለድ በማበደር መጠቀሚያ ያደርጓቸው ነበር። በተጨማሪም አንዳንድ ዳኞች ጉቦ በመቀበል ምንም ባላጠፉ ሰዎች ላይ ኢፍትሐዊ ፍርድ ያስተላልፉ ነበር። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን ይጸየፋል።—ሕዝ. 22:12

18. ለገንዘብ ያለንን አመለካከት ለመመርመር የሚረዱን የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው? (ዕብራውያን 13:5)

18 እያንዳንዳችን ለገንዘብ ያለንን አመለካከት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ራሳችንን እንዲህ እያልን ልንጠይቅ ይገባል፦ ‘ስለ ገንዘብና ስለምገዛቸው ነገሮች ብዙ ጊዜ አስባለሁ? ገንዘብ ከተበደርኩ በኋላ አበዳሪዬ ገንዘቡ አያስፈልገውም በማለት ለመክፈል እዘገያለሁ? ገንዘብ ስላለኝ አስፈላጊ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል? ለጋስ ለመሆንስ ይከብደኛል? ወንድሞቼና እህቶቼ ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ፍቅረ ነዋይ እንደተጠናወታቸው ይሰማኛል? ከሀብታሞች ጋር ለመወዳጀት እየሞከርኩ ድሆችን ችላ እላለሁ?’ በይሖዋ ድንኳን የመስተናገድ ታላቅ መብት አግኝተናል። አኗኗራችን ከገንዘብ ፍቅር ነፃ እንዲሆን በማድረግ ይህን ልዩ መብታችንን ጠብቀን ማቆየት እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ፈጽሞ አይተወንም።—ዕብራውያን 13:5ን አንብብ።

ይሖዋ ወዳጆቹን ይወዳቸዋል

19. ይሖዋ አምላክ መሥፈርቶቹን ያወጣበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

19 መዝሙር 15 የሚደመደመው “እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ ፈጽሞ አይናወጥም” የሚል ዋስትና በመስጠት ነው። (መዝ. 15:5) እዚህ ላይ መዝሙራዊው፣ ይሖዋ አምላክ መሥፈርቶቹን ያወጣበትን ዋነኛ ምክንያት ግልጽ አድርጎልናል። ይሖዋ ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። ስለዚህም የእሱን በረከትና ጥበቃ የሚያስገኙልንን መመሪያዎች ይሰጠናል።—ኢሳ. 48:17

20. በይሖዋ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገዱ ሰዎች ምን ተስፋ ይጠብቃቸዋል?

20 ይሖዋ በእንግድነት የሚቀበላቸው ሰዎች ብሩህ የወደፊት ተስፋ አላቸው። ኢየሱስ ታማኝ ለሆኑት ቅቡዓን “ብዙ መኖሪያ ቦታ” አዘጋጅቶላቸዋል። (ዮሐ. 14:2) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ደግሞ በራእይ 21:3 ላይ የተጠቀሰው ተስፋ ሲፈጸም ለማየት ይጓጓሉ። አዎ፣ ይሖዋ ወዳጆቹ እንድንሆን ማለትም በድንኳኑ ውስጥ ለዘላለም እንድንስተናገድ ግብዣ ስላቀረበልን ታላቅ ክብር ይሰማናል!

መዝሙር 39 በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ማትረፍ