በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ትምህርት ቢያስጠላኝስ?

ትምህርት ቢያስጠላኝስ?

 የማያፈናፍኑ አስተማሪዎች። የእኩያ ተጽዕኖ። ከባድ ፈተናዎችና የቤት ሥራ ናዳ። አዎ፣ ትምህርት ቢያስጠላህ የሚያስገርም አይደለም። a ሬቸል b የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦

 “ትምህርት ቤት ሂጂ ከምባል ሌላ የትም ቦታ ሂጂ ብባል ይቀለኛል። ባሕር ዳርቻ ብሄድ ወይም ከጓደኞቼ ጋር ብዝናና እመርጣለሁ፤ ሌላው ቢቀር ምግብ በማብሰል ወይም ቤት በማጽዳት ወላጆቼን ባግዝ ይሻለኛል!”

 አንተም እንደ ሬቸል የሚሰማህ ከሆነ የትምህርት ቤት ሕይወትህ እስር ቤት ሊሆንብህና የምትፈታው ስትመረቅ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ይሁንና በትምህርት ቤት የምታሳልፈውን ጊዜ ከዚህ በተሻለ መንገድ ልትመለከተው ትችል ይሆን?

 ይህን ታውቅ ነበር? ለትምህርት ያለህን አመለካከት ካስተካከልክ ትምህርት ቤት እስር ቤት አይሆንብህም። ከዚህ ይልቅ አዋቂ ስትሆን የሚያስፈልጉህን ክህሎቶች የምታዳብርበት ቦታ ይሆንልሃል።

 ለትምህርት ያለህን አመለካከት ለማስተካከል በሚከተሉት ነገሮች ላይ ለማተኮር ሞክር፦

 በምታገኘው ትምህርት ላይ አተኩር። ጎበዝ ተማሪ ከሆንክ ወደፊት በሥራ ቦታህም ሆነ በሌሎች የሕይወትህ ዘርፎች ችግሮች ሲያጋጥሙህ ሁልጊዜ የሌሎችን እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ በተሳካ ሁኔታ ልትወጣቸው ትችላለህ። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ትምህርት እንዲያስጠላኝ የሚያደርጉ ነገሮች ቢኖሩም ከትምህርቴ ምን ጥቅም እያገኘሁ ነው?’

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን ጠብቅ።”​—ምሳሌ 3:21

 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “የትምህርት ውጤቴ ዝቅተኛ ከሆነ ምን ላድርግ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

 በልማዶችህ ላይ አተኩር። ከትምህርት ቤት ሕይወትህ ጊዜህን በአግባቡ መጠቀምን፣ በፕሮግራም መመራትን እንዲሁም ጥሩ የሥራ ልማድ ማዳበርን ልትማር ትችላለህ፤ እነዚህ ክህሎቶች አዋቂ ስትሆንም ይጠቅሙሃል። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘የትምህርት ቤት ሕይወቴ በፕሮግራም እንድመራና ታታሪ ሠራተኛ እንድሆን የሚረዳኝ በየትኞቹ መንገዶች ነው? በዚህ ረገድ ምን ማሻሻያዎችን ላደርግ እችላለሁ?’

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል።”​—ምሳሌ 14:23

 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀም የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

 ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት ላይ አተኩር፦ አብረውህ ከሚማሩ ልጆች ጋር ያለህ ግንኙነት የሌሎችን ስሜት ለመረዳትና ሌሎችን ለማክበር ሊረዳህ ይችላል። ጆሹዋ የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ከሌሎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን መማር ታሪክና ሳይንስ የመማርን ያህል አስፈላጊ ነው። ይህ ክህሎት በመላው ሕይወትህ ይጠቅምሃል።” ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በትምህርት ቤት ሕይወቴ ከእኔ የተለየ አስተዳደግና እምነት ያላቸውን ጨምሮ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረኝ የሚረዳ ምን ትምህርት አግኝቻለሁ?’

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ።”​—ዕብራውያን 12:14

 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ከሰዎች ጋር የመጨዋወት ችሎታዬን ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

 በወደፊት ሕይወትህ ላይ አተኩር። ትምህርት ያለህን ችሎታ እንድታውቅና በዚያ ላይ ተመሥርተህ ግብ እንድታወጣ ይረዳሃል። ብሩክ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እንደ እኔ አንድ ሙያ ከተማርክ ስትመረቅ ሥራ ማግኘት ትችላለህ።” ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ከተመረቅኩ በኋላ ራሴን ማስተዳደር የምችለው እንዴት ነው? ያንን ክህሎት ከወዲሁ መማር የምችለውስ እንዴት ነው?’

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለምታደርገው ነገር ሁሉ ዕቅድ ይኑርህ።”​—ምሳሌ 4:26 የ1980 ትርጉም

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አብዛኞቹ ሐሳቦች ከቤት ሆነው ለሚማሩ ወጣቶችም ይጠቅማሉ።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።