በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዲያብሎስ በእርግጥ አለ?

ዲያብሎስ በእርግጥ አለ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፣ ዲያብሎስ በእርግጥ አለ። እሱ “የዚህ ዓለም ገዥ” ነው፤ ይህ መንፈሳዊ ፍጡር ክፉ በመሆን በአምላክ ላይ ዓምጿል። (ዮሐንስ 14:30፤ ኤፌሶን 6:11, 12) መጽሐፍ ቅዱስ የዲያብሎስን ማንነት እንድናውቅ የሚረዱንን የሚከተሉትን መጠሪያዎችና አገላለጾች ይጠቀማል፦

የክፋት ሐሳብ ወይም የክፋት ባሕርይ አይደለም

 አንዳንዶች ሰይጣን ዲያብሎስ የሚባለው በውስጣችን ያለ የክፋት ሐሳብ ወይም የክፋት ባሕርይ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ከአምላክ ጋር እንደተነጋገረ ይገልጻል። አምላክ ፍጹም ስለሆነ በውስጡ ካለ የክፋት ባሕርይ ጋር ሊነጋገር አይችልም። (ዘዳግም 32:4፤ ኢዮብ 2:1-6) በተመሳሳይም ሰይጣን ምንም ኃጢአት የሌለበትን ኢየሱስን ፈትኖታል። (ማቴዎስ 4:8-10፤ 1 ዮሐንስ 3:5) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው፣ ሰይጣን በእውን ያለ አካል እንጂ በሰውኛ የተገለጸ የክፋት ባሕርይ እንዳልሆነ ነው።

 ብዙ ሰዎች ሰይጣን በእውን ያለ አካል መሆኑን አለማመናቸው ሊያስደንቀን ይገባል? በፍጹም፣ ምክንያቱም ሰይጣን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የማታለያ ዘዴዎችን እንደሚጠቀም መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ተሰሎንቄ 2:9, 10) ከሚጠቀምባቸው ውጤታማ ዘዴዎች መካከል አንዱ ደግሞ ሰዎች የእሱን መኖር እንዳያምኑ ማድረግ ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:4

ሌሎች የተሳሳቱ አመለካከቶች

የተሳሳተ አመለካከት፦ ሉሲፈር የዲያብሎስ ሌላኛው ስም ነው።

 እውነታ፦ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ሉሲፈር ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “አጥቢያ ኮከብ” የሚል ፍቺ አለው። (ኢሳይያስ 14:12) የጥቅሱ አውድ እንደሚያሳየው ይህ ቃል የሚያመለክተው የባቢሎንን ሥርወ መንግሥት ወይም ነገሥታት ነው፤ ይህ መንግሥት እብሪተኛ በመሆኑ አምላክ አዋርዶታል። (ኢሳይያስ 14:4, 13-20) የባቢሎናውያኑ ሥርወ መንግስት “አጥቢያ ኮከብ” እየተባለ በፌዝ የተጠራው ከተገለበጠ በኋላ ነው።

የተሳሳተ አመለካከት፦ አምላክ ሰዎችን ለመፈተን በሰይጣን ይጠቀማል።

 እውነታ፦ ዲያብሎስ የአምላክ ጠላት እንጂ የአምላክ አገልጋይ አይደለም። ሰይጣን ዲያብሎስ አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎችን የሚቃወም ከመሆኑም ሌላ በሐሰት ይከስሳቸዋል።​—1 ጴጥሮስ 5:8፤ ራእይ 12:10