በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ፖርኖግራፊ መመልከት የሌለብህ ለምንድን ነው?

ፖርኖግራፊ መመልከት የሌለብህ ለምንድን ነው?

 በቆራጥነት እምቢ ማለት ትችላለህ?

 ኢንተርኔት የምትጠቀም ከሆነ አንድ ዓይነት ፖርኖግራፊ ሊያጋጥምህ እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብሃል። የ17 ዓመቷ ሄይሊ ፖርኖግራፊን በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “አሁን አሁን እናንተ ራሳችሁ ገብታችሁ መፈለግ አይጠበቅባችሁም። እሱ ራሱ ፈልጓችሁ ይመጣል።”

 ፖርኖግራፊ መመልከት የማይፈልጉ ሰዎች እንኳ ለመመልከት ሊፈተኑ ይችላሉ። ግሬግ የተባለ የ18 ዓመት ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ራሴን መቆጣጠር እንደምችል ይሰማኝ ነበር፤ ግን ለፈተናው መሸነፌ አልቀረም። በእኔ ላይ ሊደርስ አይችልም ልትሉት የምትችሉት ነገር አይደለም።”

 ፖርኖግራፊ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ እንደ ልብ ይገኛል። ሴክስቲንግ በጣም እየተለመደ መምጣቱ ደግሞ ብዙ ወጣቶች የራሳቸውን ፖርኖግራፊ እንዲያዘጋጁና እንዲያሰራጩ አጋጣሚ እየከፈተ ነው።

 ዋናው ነጥብ፦ አንተ ያለህበት ሁኔታ ወላጆችህ ወይም አያቶችህ በአንተ ዕድሜ ከነበሩበት ጊዜ ይበልጥ ፈታኝ ነው። ታዲያ ፖርኖግራፊ እንድትመለከት የሚፈትን ሁኔታ ሲያጋጥምህ በቆራጥነት እምቢ ማለት ትችላለህ?—መዝሙር 97:10

 አዎን፣ ከፈለግክ ትችላለህ። በመጀመሪያ ግን ፖርኖግራፊ መጥፎ የሆነበትን ምክንያት በሚገባ ማወቅ አለብህ። እስቲ ሰዎች ስለ ፖርኖግራፊ ያላቸውን አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶችና እውነታውን እንመልከት።

 እውነታው ምን እንደሆነ ማወቅ

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ፖርኖግራፊ መመልከቴ አይጎዳኝም።

 እውነታው፦ ማጨስ ሳንባዎችህን እንደሚጎዳቸው ሁሉ ፖርኖግራፊም አእምሮህ ላይ ጉዳት ያስከትላል። ንጹሕ እንዳትሆን ያደርግሃል። ፖርኖግራፊ፣ አምላክ በሁለት ሰዎች መካከል የጠበቀና ዘላቂ የሆነ ጥምረት እንዲፈጠር አስቦ ያዘጋጀውን ነገር የሚያዋርድ ነው። (ዘፍጥረት 2:24) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ትክክል እና ስህተት ስለሆኑት ነገሮች ያለህ ስሜት እንኳ እንዲደነዝዝ ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ አዘውትረው ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ወንዶች በሴቶች ላይ ስለሚፈጸም ጥቃት ያላቸው ስሜት እየደነዘዘ ሊሄድ እንደሚችል አንዳንድ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ “የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘ” አንዳንድ ሰዎች ይናገራል። (ኤፌሶን 4:19) የእነዚህ ሰዎች ሕሊና ከመደንዘዙ የተነሳ መጥፎ ነገር ሲፈጽሙ ሕሊናቸው ምንም አይወቅሳቸውም።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ ፖርኖግራፊ ስለ ፆታ ግንኙነት ትምህርት ይሰጣል።

 እውነታው፦ ፖርኖግራፊ የሚያስተምረው ነገር ቢኖር ራስ ወዳድ መሆንን ነው። ሰዎች የተፈጠሩት የፆታ ስሜትን ለማርካት ብቻ እንደሆነ እንድታስብ በማድረግ ለእነሱ ያለህ ክብር እንዲቀንስ ያደርጋል። ከዚህ አንጻር አንድ ጥናት የደረሰበት መደምደሚያ ምንም አያስገርምም፤ በዚህ ጥናት መሠረት አዘውትረው ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በትዳራቸው ውስጥ ከፆታ ግንኙነት የሚያገኙት እርካታ አነስተኛ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች ‘ከዝሙት፣ ከርኩሰት፣ ከፆታ ምኞት፣ ከመጥፎ ፍላጎትና ከመጎምጀት’ እንዲርቁ ይናገራል፤ ፖርኖግራፊ ደግሞ እነዚህ ነገሮች ትክክል እንደሆኑ አድርጎ ያቀርባል።—ቆላስይስ 3:5

 የተሳሳተ አመለካከት፦ አንዳንድ ሰዎች ፖርኖግራፊ የማይመለከቱት የፆታ ግንኙነት ስለሚያስፈራቸው ነው።

 እውነታው፦ ፖርኖግራፊ ለመመልከት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የፆታ ግንኙነትን አቅልለው አይመለከቱትም። የፆታ ግንኙነት የአምላክ ስጦታ እንደሆነና አምላክ የጋብቻ ቃል ኪዳን የፈጸሙ አንድ ወንድና ሴት ዝምድናቸውን እንዲያጠናክሩ በማሰብ የፈጠረው ነገር እንደሆነ ያምናሉ። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች በፆታ ግንኙነት ረገድ በትዳራቸው የበለጠ እርካታ ያገኛሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ለባሎች እንዲህ የሚል ምክር ይሰጣል፦ “በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ። . . . ፍቅሯም ሁልጊዜ ይማርክህ።”—ምሳሌ 5:18, 19

 ፖርኖግራፊ ለመመልከት እንዳትፈተን ምን ማድረግ ትችላለህ?

 ፖርኖግራፊ ለመመልከት ስትፈተን ራስህን መቆጣጠር በጣም ከባድ ይሆንብሃል? “ፖርኖግራፊ ለመመልከት እንዳትፈተን ምን ማድረግ ትችላለህ?” የሚለው የመልመጃ ሣጥን ሊረዳህ ይችላል።

 ፖርኖግራፊ ለመመልከት እንድትፈተን የሚያደርግ ሁኔታ ሲያጋጥምህ በቆራጥነት እምቢ ማለት እንደምትችል እወቅ። ፖርኖግራፊ ማየት ጀምረህ ከሆነም እንዲህ ማድረግህን ማቆም ትችላለህ። ይህን ማድረግ ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል።

 የካልቪንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ካልቪን ፖርኖግራፊ መመልከት የጀመረው በ13 ዓመቱ ነበር። ካልቪን እንዲህ ብሏል፦ “ስህተት እንደሆነ አውቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ ራሴን ተቆጣጥሬ ፈተናውን መቋቋም አልቻልኩም። ሁልጊዜ ፖርኖግራፊ ከተመለከትኩ በኋላ መጥፎ ስሜት ይሰማኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ አባቴ የማደርገውን ነገር አወቀ፤ እውነቱን ለመናገር፣ ይህ ትልቅ እፎይታ አስገኝቶልኛል! በመጨረሻም የሚያስፈልገኝን እርዳታ ማግኘት ቻልኩ።”

 ካልቪን ፖርኖግራፊ የመመልከት ልማዱን ማቆም ቻለ። እንዲህ ብሏል፦ “ከዚህ በፊት ፖርኖግራፊ መመልከቴ በጣም ትልቅ ስህተት ነበር፤ ምክንያቱም በዚያ ወቅት ያየኋቸው ምስሎች ወደ አእምሮዬ ስለሚመጡ ያኔ የሠራሁት ስህተት ዋጋ እያስከፈለኝ ነው። አሁንም እንኳ ማየት የሌለብኝን ነገር ለመመልከት የምፈተንበት ጊዜ አለ። በዚህ ጊዜ ግን ይሖዋ የሚፈልገውን ነገር ሳደርግ ምን ያህል ደስተኛና ንፁሕ እንደምሆን እንዲሁም ወደፊት የማገኘውን ብሩህ ተስፋ አስባለሁ።”