በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በዎርዊክ ያሉትን የዱር እንስሳትና የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር ጠብቆ ማቆየት

በዎርዊክ ያሉትን የዱር እንስሳትና የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር ጠብቆ ማቆየት

የይሖዋ ምሥክሮች በኒው ዮርክ ስቴት ገጠራማ ክፍል ይኸውም ስተርሊንግ ፎረስት ሌክ (ብሉ ሌክ) በመባል በሚታወቀው ሐይቅ አቅራቢያ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት መገንባት ጀምረዋል። ታዲያ በዚያ አካባቢ ያሉትን የዱር እንስሳትና የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር ጠብቀው ለማቆየት ምን ጥረት እያደረጉ ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ቲምበር ራትልስኔክ በመባል የሚታወቀው የእባብ ዝርያም ሆነ ኢስተርን ቦክስ ተርትልና ዉድ ተርትል የሚባሉት የዔሊ ዝርያዎች ወደ ግንባታው አካባቢ ዘልቀው በመግባት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል የሕንፃው ግንባታ የሚካሄድበትን አካባቢ ለጊዜው አጥረውታል። እንስሳቱ ወደ ግንባታው ቦታ ሾልከው እንዳይገቡ ሲባል አጥሩ በየጊዜው ይፈተሻል። የግንባታው ሥራ ከተጠናቀቀና ጊዜያዊው አጥር ከፈረሰ በኋላ እባቦቹ ወደ ሕንፃው አቅራቢያ ከመጡ በሠለጠኑ ባለሙያዎች አማካኝነት ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ይደረጋል።

ኢስተርን ብሉበርድ

ዛፎቹ የሚቆረጡት ብሉበርድ በመባል የሚታወቁት የወፍ ዝርያዎች በአካባቢው በማይኖሩበት በክረምቱ ወራት ነው። የሕንፃው ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ ወፎቹ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ለማበረታታት ሲባል ለወፎቹ መኖሪያ የሚሆኑ አነስተኛ ሣጥኖች እንዲሰቀሉ ይደረጋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለመጥፋት የተቃረበው የሂሶጵ ተክል ዝርያ በደንብ እንዲባዛና እንዲሰራጭ ለማድረግ ሲባል ከጥቅምት እስከ መጋቢት ባሉት ወራት አንዳንድ ቦታዎችን የመመንጠርና የማረም ሥራ ይከናወናል። እነዚህ ተክሎች ከ2007 አንስቶ በአካባቢው ታይተው ባያውቁም ይህ ሥራ በወጣለት ፕሮግራም መሠረት እየተካሄደ ነው።

የግንባታ ቦታውን የሚያዋስነው ስተርሊንግ ፎረስት ሌክ የተባለው ሐይቅ የተለያዩ የውኃ ዳር አእዋፍና እንደ ትራውት፣ ባስ፣ ፒክረልና ፐርች ያሉ የዓሣ ዝርያዎች መኖሪያ ነው። ባለሙያዎች ሐይቁን ከጉዳት ለመጠበቅ የተለያዩ ዕቅዶችን ነድፈዋል። ከእነዚህም መካከል በሕንፃዎቹ አናት ላይ ዕፀዋት መትከል ይገኝበታል፤ ይህም በዝናብ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ በካይ ንጥረ ነገሮች ለማጣራትና ጎርፍ ለመቀነስ ይረዳል። በተጨማሪም በሐይቁ ዙሪያ ያሉት ዕፀዋት ጥበቃና እንክብካቤ ይደረግላቸዋል።

በፕሮጀክቱ ላይ ከሚሳተፉት የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ አካባቢውን ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ማድረግ ተጨማሪ ዕቅድ መንደፍና ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም የዎርዊክ ሥነ ምሕዳር ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል።”