ታላቂቱ ባቢሎን ማን ናት?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በራእይ መጽሐፍ ላይ “ታላቂቱ አመንዝራ” ተብላ የተገለጸች “አንዲት ሴት” አለች፤ “ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል “ሚስጥራዊ ስም” እንዳላትም ተገልጿል። (ራእይ 17:1, 3, 5) ይህች ሴት “የአምላክን እውነት በሐሰት [የለወጡትን]” የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች በቡድን ደረጃ ታመለክታለች። a (ሮም 1:25) እነዚህ የሃይማኖት ድርጅቶች በተወሰነ ደረጃ በመካከላቸው ልዩነት ቢኖርም ሁሉም፣ ሰዎች ከእውነተኛው አምላክ ከይሖዋ እንዲርቁ አድርገዋል።—ዘዳግም 4:35
የታላቂቱ ባቢሎንን ማንነት ለማወቅ የሚያስችሉ ቁልፎች
ታላቂቱ ባቢሎን ምሳሌያዊ ናት። የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው “በምልክቶች” እንደ መሆኑ መጠን ታላቂቱ ባቢሎን የሚለው ስያሜም ቃል በቃል አንዲትን ሴት ሊያመለክት እንደማይችል ግልጽ ነው። (ራእይ 1:1) በተጨማሪም ‘በብዙ ውኃዎች ላይ እንደተቀመጠች’ እና እነዚህ ውኃዎች ደግሞ “ወገኖችን፣ ብዙ ሕዝብን፣ ብሔራትንና ቋንቋዎችን” እንደሚያመለክቱ ተገልጿል። (ራእይ 17:1, 15) መቼም አንዲት ሴት እንዲህ ልታደርግ እንደማትችል የታወቀ ነው።
ታላቂቱ ባቢሎን ዓለም አቀፍ ድርጅትን የምትወክል ናት። ‘በምድር ነገሥታት ላይ መንግሥት ያላት ታላቂቱ ከተማ’ ተብላ ተጠርታለች። (ራእይ 17:18) ይህ አገላለጽ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳላትና በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ እንደምታሳድር የሚያሳይ ነው።
ታላቂቱ ባቢሎን የሃይማኖት ድርጅት እንጂ የፖለቲካ ወይም የንግድ ድርጅት አይደለችም። የጥንቷ ባቢሎን ሃይማኖት የገነነባት ከተማ ነበረች፤ እንዲሁም በውስጧ በሚፈጸመው ‘ድግምትና ጥንቆላ’ ትታወቅ ነበር። (ኢሳይያስ 47:1, 12, 13፤ ኤርምያስ 50:1, 2, 38) እንዲያውም የዚህች ከተማ ነዋሪዎች የሚከተሉት ሃይማኖት እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን በቀጥታ የሚቃወም ነበር። (ዘፍጥረት 10:8, 9፤ 11:2-4, 8) የባቢሎን ነገሥታት ራሳቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ ለይሖዋም ሆነ ለእሱ አምልኮ ንቀት እንዳላቸው አሳይተዋል። (ኢሳይያስ 14:4, 13, 14፤ ዳንኤል 5:2-4, 23) በተመሳሳይም ታላቂቱ ባቢሎን ‘በመናፍስታዊ ድርጊቶቿ’ ትታወቃለች። ይህም ሃይማኖታዊ ድርጅት መሆኗን ያሳያል።—ራእይ 18:23
ታላቂቱ ባቢሎን የፖለቲካ ድርጅት ልትሆን አትችልም፤ ምክንያቱም እሷ ስትጠፋ ‘የምድር ነገሥታት’ እንዳለቀሱ ተገልጿል። (ራእይ 17:1, 2፤ 18:9) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የምድር ነጋዴዎችን’ ከእሷ ለይቶ ስለሚጠቅስ የንግድ ድርጅት ልትሆን አትችልም።—ራእይ 18:11, 15
ታላቂቱ ባቢሎን ለሐሰት ሃይማኖቶች ተስማሚ ተምሳሌት ናት። የሐሰት ሃይማኖት፣ ሰዎች ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚችሉበትን መንገድ ከማስተማር ይልቅ ሌሎች አማልክትን እንዲያመልኩ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ድርጊት “መንፈሳዊ ምንዝር” በማለት ይጠራዋል። (ዘሌዋውያን 20:6፤ ዘፀአት 34:15, 16) ብዙ የሐሰት ሃይማኖቶች ከጥንቷ ባቢሎን የመነጩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ዛሬም እያስተማሩ ነው፤ ከእነዚህም መካከል አምላክ ሥላሴ ነው እና ነፍስ አትሞትም የሚሉት ትምህርቶች እንዲሁም ምስሎችን ለአምልኮ እንደመጠቀም ያሉ ልማዶች ይገኙበታል። በተጨማሪም እነዚህ ሃይማኖቶች አምልኳቸውንና ለዓለም ያላቸውን ፍቅር ጎን ለጎን ለማስኬድ ይሞክራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው የክህደት ድርጊት መንፈሳዊ ምንዝር እንደሆነ ይናገራል።—ያዕቆብ 4:4
መጽሐፍ ቅዱስ ታላቂቱ ባቢሎን “ሐምራዊና ደማቅ ቀይ ልብስ” እንደለበሰች እንዲሁም “በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁዎች” እዳጌጠች ይናገራል፤ ይህም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ያላቸውን ሀብትና ይህ ሀብታቸው እንዲታይላቸው የሚያደርጉትን ጥረት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። (ራእይ 17:4) ታላቂቱ ባቢሎን “የምድር አስጸያፊ ነገሮች” ማለትም አምላክን የማያስከብሩ ትምህርቶችና ድርጊቶች ምንጭ ናት። (ራእይ 17:5) የሐሰት ሃይማኖት አባላት በሙሉ ታላቂቱ ባቢሎንን የሚደግፉ ‘ወገኖች፣ ብዙ ሕዝብ፣ ብሔራትና ቋንቋዎች’ ናቸው።—ራእይ 17:15
ታላቂቱ ባቢሎን ‘በምድር ላይ ለታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም’ ተጠያቂ ናት። (ራእይ 18:24) የሐሰት ሃይማኖቶች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ጦርነትን ሲቆሰቁሱና ሽብርተኝነትን ሲያባብሱ ኖረዋል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የፍቅር አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋም እውነቱን ለሰዎች አላስተማሩም። (1 ዮሐንስ 4:8) ይህም በዓለም ላይ ለተከሰተው ለአብዛኛው ደም መፋሰስ አስተዋጽኦ አድርጓል።
አምላክ ስለ ታላቂቱ ባቢሎን ምን ይሰማዋል?
በአምላክ ዓይን የታላቂቱ ባቢሎን “[ኃጢአት] እስከ ሰማይ ድረስ ተቆልሏል።” (ራእይ 18:4, 5)) የሐሰት ሃይማኖቶች ስለ ማንነቱ ውሸት ማስተማራቸው እና ተከታዮቻቸውን በአግባቡ አለመያዛቸው አምላክን ያስቆጣዋል።
ታላቂቱ ባቢሎን የሚጠብቃት ነገር ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አምላክ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ “ፈርዶባታል።” (ራእይ 18:20) መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በሐሰት ሃይማኖቶች ሁሉ ላይ የሚያመጣውን ጥፋት ምሳሌያዊ በሆነ አነጋገር ይገልጸዋል። (ራእይ 18:8) አምላክ ደማቅ ቀይ ቀለም ባለው አውሬ የተመሰለ አንድ ትልቅ የፖለቲካ ተቋም በሐሰት ሃይማኖቶች ላይ እንዲነሳና ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፋቸው ያደርጋል። (ራእይ 17:16, 17) “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ በፍጥነት ቁልቁል ትወረወራለች፤ ዳግመኛም አትገኝም።” (ራእይ 18:21) በዚህም ምክንያት አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ ‘ከመካከላቸው መውጣት’ ይኸውም ራሳቸውን ከሐሰት ሃይማኖቶች መለየት ይኖርባቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 6:14-17
a “እውነተኛውን ሃይማኖት ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።