በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

“ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ”! የተባለው የ2020 የክልል ስብሰባ ትርጉም

“ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ”! የተባለው የ2020 የክልል ስብሰባ ትርጉም

ሐምሌ 10, 2020

 በሐምሌ እና በነሐሴ 2020 ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ዓይነት የክልል ስብሰባ በተመሳሳይ ወቅት እያደረገ ነው። ይህ ፕሮግራም እንዲሳካ ለማድረግ በቪዲዮ የተዘጋጀው ስብሰባ ከ500 ወደሚበልጡ ቋንቋዎች መተርጎም ነበረበት። እንዲህ ያለውን ፕሮጀክት ለማቀድና ለማጠናቀቅ በአብዛኛው አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ይፈጃል። ሆኖም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፈጠረው አስቸጋሪ ሁኔታ የተነሳ “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ”! የተባለውን የ2020 የክልል ስብሰባ የተረጎሙት ተርጓሚዎች ከአራት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሥራውን ማጠናቀቅ ነበረባቸው።

 በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኙት የትርጉም አገልግሎት ክፍልና ዓለም አቀፉ የዕቃ ግዢ ክፍል ለዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት መሳካት ትልቅ እገዛ አበርክተዋል። የትርጉም አገልግሎት ክፍል በርካታ የትርጉም ቡድኖች ሥራቸውን ለማከናወን ተጨማሪ መሣሪያዎች በተለይም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ማይክሮፎኖች እንደሚያስፈልጓቸው አስተዋለ። ዓለም አቀፉ የዕቃ ግዢ ክፍል ደግሞ 1,000 ማይክሮፎኖችን ለመግዛትና 200 ገደማ ወደሚሆኑ አካባቢዎች ለመላክ ዝግጅት አደረገ።

 ገንዘብ ለመቆጠብ ሲባል ማይክሮፎኖቹ በጅምላ ተገዝተው ወደ አንድ ቦታ እንዲላኩ ተደረገ፤ ከዚያም ማይክሮፎኖቹ በዓለም ዙሪያ ወደሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ተሰራጩ። የእያንዳንዱ ማይክሮፎን ዋጋ የመላኪያ ወጪውን ጨምሮ በአማካይ 170 የአሜሪካ ዶላር ነበር፤ በመሆኑም እያንዳንዱ ማይክሮፎን በችርቻሮ ቢገዛ ኖሮ ከሚያወጣው ዋጋ የ20 በመቶ ቅናሽ ማግኘት ተችሏል።

 ዓለም አቀፉ የዕቃ ግዢ ክፍል እነዚህን መሣሪያዎች መግዛትና መላክ የነበረበት በሚያዝያና በግንቦት ወራት ነው፤ በዚህ ወቅት ደግሞ አብዛኞቹ የንግድ ድርጅቶች በወረርሽኙ ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ነበር። ያም ቢሆን አብዛኞቹ የርቀት የትርጉም ቢሮዎች፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎችና በሌሎች ቦታዎች ያሉ ተርጓሚዎች የሚያስፈልጋቸውን መሣሪያ እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ ማግኘት ችለዋል።

 የዓለም አቀፉ የዕቃ ግዢ ክፍል የበላይ ተመልካች የሆነው ጄይ ስዊኒ እንዲህ ብሏል፦ “ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ በቤቴል ዲፓርትመንቶችና በዕቃ አቅራቢ ድርጅቶች መካከል ጥሩ የትብብር መንፈስ ነበር። የይሖዋ መንፈስ እርዳታ ባይኖረን ኖሮ ይህን ቲኦክራሲያዊ ሥራ እንደዚህ በፍጥነትና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ማከናወን አንችልም ነበር።”

 በትርጉም አገልግሎት ክፍል ውስጥ የሚሠራው ኒኮላስ አላዲስ እንዲህ ብሏል፦ “ብቻቸውን ተገልለው ያሉት ተርጓሚዎች መሣሪያዎቹን በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። ምክንያቱም ከሌሎቹ ተርጓሚዎች ጋር በአካል መገናኘት ባይችሉም እንኳ በቡድን መሥራት እንዲሁም ንግግሮቹን፣ ድራማዎቹንና መዝሙሮቹን ከ500 በሚበልጡ ቋንቋዎች መተርጎምና መቅዳት ችለዋል።”

 ይህ ፕሮጀክት ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ”! የተባለውን የ2020 የክልል ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ እንዲችል አስተዋጽኦ ካበረከቱት በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው። በ​donate.pr418.com አማካኝነት ወይም በሌሎች መንገዶች ተጠቅማችሁ በልግስና ያደረጋችሁት መዋጮ እነዚህን አስፈላጊ ቁሳቁሶች ለመግዛት አስችሏል።