በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰኔ 6, 2019
ቬኔዙዌላ

ቬኔዙዌላ—ወቅታዊ መረጃ፦ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ጨምሯል

ቬኔዙዌላ—ወቅታዊ መረጃ፦ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ጨምሯል

በቬኔዙዌላ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። የምግብ፣ የውኃ፣ የነዳጅና የመድኃኒት አቅርቦት በእጅጉ የተመናመነ ሲሆን ዋጋውም የማይቀመስ ነው። በተደጋጋሚ በሚቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት ምግቦችን ማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ አለመቻሉ የምግብ እጥረቱ እንዲባባስ አድርጓል። የወንጀል መበራከትም በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል።

እነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም በቬኔዙዌላ ያሉት ከ136,500 የሚበልጡ አስፋፊዎች ምሥራቹን በቅንዓት ማወጃቸውን ቀጥለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በጥር 2019 የተመዘገበው የአስፋፊዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ7,000 የሚያንስ ቢሆንም አስፋፊዎቹ በስብከቱ ሥራ ያሳለፉት ሰዓት በ90,000 ይበልጣል። በሚያዝያ 2019 ከ195,600 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል። የዘወትር አቅኚዎች ቁጥር አድጎ ከ30,000 በላይ ሆኗል። ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ ከተደረገው ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ ጋር በተያያዘ የረዳት አቅኚዎች ቁጥር 20,400 ደርሷል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ያደረጉት ጥረት በመታሰቢያው በዓል ላይ 471,000 የሚያህሉ ማለትም ከአስፋፊዎቹ ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንዲገኙ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም በርካታ ሰዎች በስብሰባዎች ላይ እየተገኙ ነው። ለዚህ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ነገሮች መካከል አንዱ ወንድሞቻችን ለችግሮቻቸው አስተማማኝ መፍትሔ እየፈለጉ ላሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እየሰበኩ መሆናቸው ነው።

የቬኔዙዌላ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ወንድሞቻችን መሠረታዊ የምግብ አቅርቦት እንዲያገኙ የሚደረገውን ጥረት ማስተባበሩን ቀጥሏል። ቅርንጫፍ ቢሮው በአጎራባች አገሮች ያሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ድጋፍና ወንድሞች ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚያደርጉትን መዋጮ በመጠቀም በ1,595 ጉባኤዎች ለሚገኙ 75,000 አስፋፊዎች በመቶዎች ቶን የሚቆጠር ምግብ በየወሩ ያከፋፍላል።

በቬኔዙዌላ የሚገኙ ወንድሞቻችን በርካታ ችግሮች ቢደራረቡባቸውም አሁንም ‘በይሖዋ ሐሴት እያደረጉና አዳኛቸው በሆነው አምላክ እየተደሰቱ’ መሆኑን ማወቃችን ሁላችንንም ያበረታታናል።—ዕንባቆም 3:17, 18