በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስከረም 2, 2019
ሩዋንዳ

የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በሩዋንዳ የምልክት ቋንቋ የክልል ስብሰባ አካሄዱ

የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በሩዋንዳ የምልክት ቋንቋ የክልል ስብሰባ አካሄዱ

ከነሐሴ 16 እስከ 18, 2019 ወንድሞቻችን በኪጋሊ፣ ሩዋንዳ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩዋንዳ የምልክት ቋንቋ የክልል ስብሰባ አካሄዱ። ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 620 የነበረ ሲሆን መስማት የተሳናቸው 8 ሰዎች በስብሰባው ላይ ተጠምቀዋል።

ተሰብሳቢዎቹ በምልክት ቋንቋ መዝሙር ሲዘምሩ

በእሁዱ ስብሰባ ላይ ሁለት ባለሥልጣናት ተገኝተው ነበር፤ እነሱም የሩዋንዳ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ብሔራዊ ኅብረት የዳይሬክተሮች ቦርድ ኃላፊ የሆኑት ሚስተር ዣን ዳማሴርን ቢዚማና እና የብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሚስተር ኢማንዌል ንዳዪሳባ ናቸው። ከዚህም ሌላ የኡክዌዚ ጋዜጣ ዘጋቢዎች የእሁዱን ስብሰባ በተመለከተ ኢንተርኔት ላይ አዎንታዊ ዘገባ አውጥተዋል።

ሚስተር ቢዚማና እንዲህ ብለዋል፦ “ስብሰባው በጣም ግሩም ነበር! ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ማየት በጣም ያስደስታል። የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት በጣም እናመሰግናቸዋለን። የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲህ ያለውን አንድነት የሰፈነበት ስብሰባ ማየትና መኮረጅ አለባቸው።”

አንዲት እህት ማየትና መስማት ለተሳናት ሴት ታክታይል የምልክት ቋንቋ በመጠቀም ስብሰባውን ስታስተረጉም

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሩዋንዳ የምልክት ቋንቋ መስክ ሌሎች ሁለት ታሪካዊ ክንውኖች ነበሩ። መስከረም 2017 የሩዋንዳ ቅርንጫፍ ቢሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩዋንዳ የምልክት ቋንቋ የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት አካሂዶ ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም መስከረም 2018 ደግሞ ቅርንጫፍ ቢሮው ጽሑፎቻችንን ወደ ሩዋንዳ የምልክት ቋንቋ መተርጎም ጀመረ።

በክልል ስብሰባው ላይ የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ ሆኖ የሄደው ወንድም ዣን ዳሙር ሃቢያሬምንዬ እንዲህ ብሏል፦ “በሩዋንዳ የምልክት ቋንቋ መስክ የሚታየውን እድገት በማየታችን በጣም ተደስተናል፤ ይህ የክልል ስብሰባም ይህን እድገት የሚያሳይ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች ፍቅር በማሳየት ‘ፍቅር ለዘላለም ይኖራል!’ የሚለውን የስብሰባውን ጭብጥ በተግባር ያሳያሉ።”

በሩዋንዳ የምልክት ቋንቋ መስክ ያለው እድገት የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት በግልጽ ያሳያል!—መዝሙር 67:1