በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ጳውሎስ እያሱ፣ ይስሃቅ ሞገስ እና ነገደ ተኽለማርያም ከመስከረም 17, 1994 ጀምሮ ኤርትራ ውስጥ በእስር ቆይተዋል

መስከረም 17, 2019
ኤርትራ

ኤርትራ ያሉ ወንድሞቻችን ከታሰሩ ሩብ ምዕተ ዓመት ሞላቸው

ኤርትራ ያሉ ወንድሞቻችን ከታሰሩ ሩብ ምዕተ ዓመት ሞላቸው

በዘመናችን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከባድ ስደት እያደረሱ ካሉ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ኤርትራ ነች። መስከረም 17, 2019፣ በኤርትራ የታሰሩ ሦስት ወንድሞቻችን ማለትም ጳውሎስ እያሱ፣ ይስሃቅ ሞገስ እና ነገደ ተኽለማርያም ከታሰሩ 25 ዓመት ሞላቸው። ሌሎች 39 ወንድሞችና 10 እህቶችም እስር ቤት ይገኛሉ።

በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሙሉ ክስ ተመሥርቶባቸው፣ ፍርድ ቤት ቀርበውም ሆነ ፍርድ ተበይኖባቸው አያውቅም። ከእስር የሚፈቱት መቼ እንደሆነም አያውቁም። አራት ወንድሞቻችን እስር ቤት እያሉ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ሦስት ወንድሞች ደግሞ እስር ቤት ሳሉ በደረሰባቸው አስከፊ ሥቃይ የተነሳ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ሞተዋል።

በኤርትራ ያለው ስደት እየተባባሰ የመጣው ከጥቅምት 25, 1994 በኋላ፣ ማለትም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ራስ ገዝ አገር ከሆነች ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ ነው። የኤርትራው ፕሬዝዳንት የኤርትራ ተወላጅ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አገሪቱ ዜጋ እንደማይቆጠሩ ተናግረው ነበር፤ ይህ የደረሰባቸው በዋነኝነት ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን በመጠበቃቸው ምክንያት ነው። ፕሬዝዳንቱ፣ ወንድሞቻችን ሊያገኟቸው የሚገቡ መሠረታዊ የሆኑ መብቶችንም ነፍገዋቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ማድረግ ከማይችሏቸው ነገሮች መካከል የቀለም ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ፣ የግል ሥራ መሥራት እንዲሁም ከአገር መውጣት ይገኙበታል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ታዋቂ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እየደረሰ ያለውን ስደት ጨምሮ ኤርትራ በምትፈጽማቸው ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ የሚጻረሩ ድርጊቶች ላይ የሚያቀርቡት ተቃውሞ እየጨመረ መጥቷል። ኤርትራ ከእነዚህ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የተሰጣትን ማሳሰቢያ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነችም።

ልዩ ዘገባ፦ በኤርትራ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ እየደረሰ ያለው ስደት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ለመንግሥት ባለሥልጣናት እና ኃላፊነት ላላቸው አካላት በኤርትራ እየተከናወነ ስላለው ሁኔታ ማሳወቃችንን እንቀጥላለን። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጭካኔ የተሞላበት ስደት እየደረሰባቸውም ጠንካራ እምነትና ድፍረት ማሳየታቸውን ቀጥለዋል፤ እኛም ይሖዋ እንደሚረዳቸውና ‘መጠጊያ ዓለት’ እንደሚሆንላቸው ሙሉ እምነት አለን።—መዝሙር 94:22