በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 29, 2019
አዘርባጃን

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በአዘርባጃን ለሚገኙ አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በአዘርባጃን ለሚገኙ አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

ጥቅምት 17, 2019 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት (ECHR) በአዘርባጃን የሚገኙ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ወንድሞቻችን እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ሊከሰሱ እንደማይገባ ፈረደ። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት የማይሰጡ ሰዎችን መቅጣት የግለሰቦችን የሕሊና፣ የሐሳብ እና የሃይማኖት ነፃነት መጣስ እንደሆነ አረጋግጧል። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ በአዘርባጃን ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሲፈርድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከ2008 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ ለቀረቡ አራት የተለያዩ አቤቱታዎች ምላሽ ሰጥቷል። አቤቱታዎቹ የቀረቡት ከአምስት ወንድሞች የፍርድ ሂደት ጋር በተያያዘ ሲሆን እነሱም ሙሽፊግ ማማዶቭ፣ ሳሚር ሁሴይኖቭ፣ ፋሪድ ማማዶቭ፣ ፋክራዲን ሚርዛዬቭ እና ካምራን ሚርዛዬቭ ናቸው። አምስቱም ወንድሞች ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አዘርባጃን ውስጥ ታስረዋል። ወንድሞቻችን ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑት “በሃይማኖታዊ እምነታቸው” ምክንያት ስለሆነ የአዘርባጃን መንግሥት በወንድሞቻችን ላይ የወሰደው እርምጃ ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ጋር እንደሚጋጭ ፍርድ ቤቱ ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ አማራጭ አገልግሎት የመስጠት መብት ሊኖራቸው የሚገባው ቀሳውስትና ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚከታተሉ ተማሪዎች ብቻ እንዳልሆኑ ገልጿል። የአዘርባጃን መንግሥት ለታሰሩት ወንድሞች ካሳ እንዲከፍልም ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ፍርድ ቤቱ አዘርባጃን በ2001 የአውሮፓ ምክር ቤት አካል በሆነችበት ወቅት ዜጎች በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ አማራጭ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ሕግ ለማውጣት ተስማምታ እንደነበር ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ የአዘርባጃን ሕገ መንግሥት በእምነታቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት የማይሰጡ ሰዎች አማራጭ አገልግሎት የመስጠት መብት እንዳላቸው ይናገራል። ያም ሆኖ ባለሥልጣናቱ ይህን ሕግ ተግባራዊ አላደረጉም፤ በመሆኑም አሁንም ድረስ ወንድሞቻችን ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት እየተከሰሱ ነው።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የአዘርባጃን መንግሥት በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ አማራጭ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ዝግጅት እንዲያደርግ እንደሚያነሳሳው ተስፋ እናደርጋለን። እስከዚያው ግን በአዘርባጃን የሚገኙ ወንድሞቻችን ይሖዋን በድፍረት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ እንጸልያለን።—መዝሙር 27:14