በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በኑናቩት፣ ካናዳ በሚገኘው ባፊን ደሴት ኢካሉዊት ውስጥ የሚገኝ አፔክስ የተባለ መንደር

ሚያዝያ 17, 2020
ካናዳ

የ2020 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—በካናዳ

በምድር ሰሜናዊ ጫፍ የመታሰቢያውን በዓል ማክበር

የ2020 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—በካናዳ

ካናዳ ውስጥ በአርክቲክ ደሴቶች የሚገኘው የኢካሉዊት ጉባኤ 27 አስፋፊዎች የመታሰቢያውን በዓል በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት አክብረዋል። በጉባኤው ካሉ 55 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መካከል 12ቱ የመታሰቢያውን በዓል መከታተል ችለዋል፤ ለዚህም በጣም አመስጋኝ ናቸው።

ለአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመታሰቢያው በዓል ላይ በአካል መገኘት በጣም አስቸጋሪ፣ እንዲያውም የማይቻል ነው። እነዚህ ጥናቶች የሚኖሩት ርቆ በሚገኘው የጉባኤው ክልል ክፍል ነው፤ የጉባኤው ክልል ሁለት ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን በካናዳ ሰሜናዊ ጫፍ ከኪሚሩት እስከ ግሪስ ፊዮርድ ይደርሳል።

የኢካሉዊት ጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ወንድም አይዛክ ዴሚስቴር እንዲህ ብሏል፦ “ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን የመታሰቢያውን በዓል አብረውን አክብረዋል። በግሪስ ፊዮርድ የሚኖር አንድ ጥናት አራት ሰዎች በዓሉን አብረውት እንዲከታተሉ ጋብዞ ነበር፤ ስለዚህ በምድር ሰሜናዊ ጫፍ የሚኖሩ አምስት ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም ተከታትለዋል።”

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተፈጠረው ሁኔታ በኢካሉዊት ጉባኤ ያሉ ወንድሞችና እህቶች አዳዲስ ዘዴዎችን መሞከር ያለውን ጥቅም እንዲያስተውሉ ረድቷቸዋል።

እህት ካቲ ቡሬቻይሎ እንዲህ ብላለች፦ “በምሥራቃዊ አርክቲክ የሚኖሩ ሰዎችን በስልክ ለማነጋገር ሞክረናል። እጅግ ርቆ በሚገኘው የክልላችን ክፍል ካሉ ሰዎች ጋር አስደሳች ውይይት ማድረግ ችያለሁ። ሰዎች ቤታቸው ይገኛሉ፤ እንዲሁም ማጽናኛ ማግኘት ይፈልጋሉ።”

እህት ላውራ ማክግሬጎር ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በኢካሉዊት ያለነው ሰዎች የምንኖረው ርቀን ስለሆነ ይህ ወረርሽኝ ከፍተኛ ውጥረት አስከትሎብናል፤ ምክንያቱም የኢኮኖሚ ችግር ያጋጥመናል እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ስጋት ይሰማናል። የመታሰቢያውን በዓል ቂጣ ለቤተሰቤ ስጋግር ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው። አብረን ግሩም ጊዜ አሳልፈናል። በዓሉ ምን ያህል ቀለል ያለ እንደሆነ ይበልጥ ተገንዝበናል፤ እንዲህ ባለ ቀላል መንገድ በዓሉን ማክበር በመቻላችን በጣም አመስጋኞች ነን።”

ወንድም ዴሚስተር ሲደመድም እንዲህ ብሏል፦ “የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተለያዩ መንገዶች ቢያራርቀንም በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ጉባኤያችን ምን ያህል እንደተቀራረበ ማየታችን አስገርሞናል። የዘንድሮው የመታሰቢያ በዓል በሕይወታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል!”

የኢካሉዊት ጉባኤ በቅርቡ ሁኔታዎች ሲመቻቹ የስብሰባ አዳራሽ ለመገንባት ያስባል። እስከዚያው ግን ጉባኤው ምሥራቹን እስከ ምድር ዳር ይኸውም በካናዳ ሰሜናዊ ጫፍ ለማሰራጨት የሚያደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርከው እንተማመናለን!—የሐዋርያት ሥራ 1:8