በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም አርሲን አቫንዬሶቭ፣ ወንድም ቪልዬን አቫንዬሶቭ እና ወንድም አሌክሳንደር ፓርኮቭ

ግንቦት 12, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ | ሦስት ወንድሞች ማረፊያ ቤት ለረጅም ጊዜ ቢቆዩም ጸንተዋል

ወቅታዊ መረጃ | ሦስት ወንድሞች ማረፊያ ቤት ለረጅም ጊዜ ቢቆዩም ጸንተዋል

ሰኔ 23, 2022 አራተኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወንድም ቪልዬን አቫንዬሶቭ እና ወንድም አሌክሳንደር ፓርኮቭ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል። አቃቤ ሕጉ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ፍርድ ቤቱ የወንድም አርሲን አቫንዬሶቭን ጉዳይ ወደ መጀመሪያው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት መልሶታል። በመሆኑም ወንድም አርሲን ይበልጥ ከበድ ያለ ቅጣት ሊበየንበት ይችላል። ሦስቱም ወንድሞች እስር ቤት ይቆያሉ።

ታኅሣሥ 6, 2021 የሮስቶቭ አውራጃ ፍርድ ቤት አርሲን፣ ቪልዬን እና አሌክሳንደር ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። ሦስቱም ወንድሞች እስር ቤት ይቆያሉ።

ሐምሌ 29, 2021 በሮስቶቭ-ኦን-ዶን ከተማ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም አርሲን እና ወንድም አሌክሳንደር በስድስት ዓመት ተኩል ወንድም ቪልዬን ደግሞ በስድስት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ወሰነ። ሦስቱም ወንድሞች እስካሁን ከሁለት ዓመት በላይ ማረፊያ ቤት ያሳለፉ ሲሆን አሁንም እስር ቤት ይቆያሉ።

አጭር መግለጫ

አርሲን አቫንዬሶቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1983 (ባኩ፣ አዘርባጃን)

  • ግለ ታሪክ፦ ምሕንድስና አጥንቷል፤ በግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ነበር። ልጅ እያለ ራግቢ መጫወት ይወድ ነበር። እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ተምሯል

    ወላጆቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲወድ ረድተውታል። በ2005 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

ቪልዬን አቫንዬሶቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1952 (ባኩ፣ አዘርባጃን)

  • ግለ ታሪክ፦ የኤሌክትሪክ እና የግንባታ ባለሙያ ሆኖ ይሠራ ነበር። ምግብ ማብሰል፣ ዳቦ መጋገር እና ማንበብ ይወዳል። ወጣት እያለ በጣም ከሚወዳቸው መጻሕፍት አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር

    በ1980 ከስቴላ ጋር ትዳር መሠረተ። ወንድ ልጃቸው አርሲን ይባላል፤ ሴት ልጃቸው ደግሞ ኤሊና ትባላለች። ቤተሰቡ በ1988 በስደት ወደ አርሜንያ ሄዶ ነበር። በዚያው ዓመት በየርመን፣ አርሜንያ የተከሰተው የምድር ነውጥ እና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መሄዱ መኖሪያቸውን እንደገና እንዲቀይሩ አስገደዳቸው። በመሆኑም ወደ ሮስቶቭ-ኦን-ዶን፣ ሩሲያ ተዛወሩ። ቪልዬን በ2006 ተጠመቀ

አሌክሳንደር ፓርኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1967 (ስፓስክ፣ ኬሜሮቮ ግዛት)

  • ግለ ታሪክ፦ ከልጅነቱ ጀምሮ በእርሻ እና በከብት አርቢነት ሥራ ላይ ተሰማርቶ ስለነበር ታታሪ ሠራተኛ ነው። የትራክተር ሹፌር እንዲሁም የመዳብ ቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ሆኖ ይሠራ ነበር

    በ1990 ከገሊና ጋር ትዳር መሠረተ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመሩት አብረው ነው። አሌክሳንደር በ1992 ተጠመቀ። ሦስት ሴቶች ልጆችና ሁለት የልጅ ልጆች አሏቸው

የክሱ ሂደት

ግንቦት 22, 2019 ባለሥልጣናቱ በሮስቶቭ-ኦን-ዶን የሚኖሩ በርከት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ። ወንድም ቪልዬን አቫንዬሶቭ እና ልጁ አርሲን እንዲሁም ወንድም አሌክሳንደር ፓርኮቭ ተይዘው ማረፊያ ቤት እንዲገቡ ተደረጉ፤ ይህ ከሆነ ሁለት ዓመት ገደማ ሆኗል። መጋቢት 2021 ሦስቱም ወንድሞች ወደ ሌላ ማረፊያ ቤት ተዛወሩ

የቪልዬን ባለቤት ስቴላ ባሏንና ልጇን ማግኘት የሚፈቀድላት በገደብ ነው። ከዚህም ሌላ የገቢ ምንጯን አጥታለች። የአሌክሳንደር ባለቤት ገሊናም በእምነቷ ምክንያት ስደት እየደረሰባት ነው። ጥፋተኛ እንደሆነች የተፈረደባት ሲሆን ፍርድ ቤቱ በሁለት ዓመት ከሦስት ወር የገደብ እስራት እንድትቀጣ ወስኗል።

በዓለም ዙሪያ ያለው የወንድማማች ማኅበር በወንድሞቻችን ላይ በደረሰው እንዲህ ያለ የፍትሕ መጓደል በእጅጉ አዝኗል። ‘በእስር ላይ ያሉትን ከእነሱ ጋር ታስረን እንዳለን አድርገን በማሰብ ሁልጊዜ እናስታውሳቸዋለን።’—ዕብራውያን 13:3