በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለይሖዋ ምሥክሮች የተበረከተው የግንባታ ጥራት ሽልማት ለራማፖ ግንባታ በተዘጋጀው ሞዴል ላይ ተቀምጦ

መጋቢት 28, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የዋናው መሥሪያ ቤት ፕሮጀክት በራማፖ

የኒው ዮርክ ግዛት ለራማፖ ፕሮጀክት የወጣውን ንድፍ አስመልክቶ ለይሖዋ ምሥክሮች ሽልማት አበረከተ

የኒው ዮርክ ግዛት ለራማፖ ፕሮጀክት የወጣውን ንድፍ አስመልክቶ ለይሖዋ ምሥክሮች ሽልማት አበረከተ

የኒው ዮርክ ግዛት የኃይል ምርምርና ልማት ባለሥልጣን (NYSERDA) የግንባታ ጥራትን መሠረት አድርጎ ባካሄደው ውድድር ለይሖዋ ምሥክሮች አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሽልማት አበረከተ። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሽልማት ያገኙት የራማፖ ፕሮጀክት መኖሪያ ቤቶች ንድፍ ለሥነ ምህዳር ተስማሚ በሆነ መልኩ በመዘጋጀቱ ነው። a በራማፖም ሆነ በሮክላንድ ካውንቲ ለግንባታ ፕሮጀክት ሽልማት ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው ነው።

በግንባታ ፕሮጀክት ኮሚቴው ውስጥ የሚሠራው ኪት ካዲ እንዲህ ብሏል፦ “የራማፖን የግንባታ ንድፍ ስናወጣ ዓላማችን አካባቢን የማይበክሉና ኃይል የሚቆጥቡ አማራጮችን መጠቀም ነበር። የኒው ዮርክ ግዛት ገና ግንባታውን ሳንጀምር ይህን ሽልማት በመስጠት፣ ላደረግነው ጥረት እውቅና የሰጠን መሆኑ በጣም አስደስቶናል። ይህን የገንዘብ ሽልማት ጨምሮ የይሖዋ ምሥክሮች በፈቃደኝነት የሚያደርጉት መዋጮ በሙሉ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል።”

ይህ የግንባታ ጥራት ውድድር በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ውድድር ነው። ውድድሩ የጀመረው መጋቢት 2019 ሲሆን እስካሁን ድረስ 63 ለሚያክሉ ፕሮጀክቶች ሽልማት ተሰጥቷል። የኒው ዮርክ ግዛት የኃይል ምርምርና ልማት ባለሥልጣን በዋና ድረ ገጹ ላይ እንዳወጣው ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ሽልማት መሰጠቱ “ሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶችም የእነሱን ምሳሌ በመከተል ለወደፊቱ በተቻለ መጠን የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ እንዲነሳሱ ያደርጋል።”

ባለሥልጣናቱ እንዲህ ያለ እውቅና ስለሰጡን በጣም አመስጋኞች ነን፤ ይህ ደግሞ ለይሖዋ ስም ክብር ያመጣል።—ማቴዎስ 5:16

a የተወዳደርነው “የስተርሊንግተን መኖሪያ ሕንፃዎች” በሚል ስም ነው።