በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች የክረምት ኦሎምፒክ በተካሄደበት አንድ ስታዲየም አቅራቢያ እህቶች በጽሑፍ ጋሪ አጠገብ ቆመው

የካቲት 29, 2024
ደቡብ ኮሪያ

የይሖዋ ምሥክሮች በ2024ቱ የደቡብ ኮሪያ የወጣቶች የክረምት ኦሎምፒክ ላይ በብዙ ቋንቋዎች ምሥክርነት ሰጡ

የይሖዋ ምሥክሮች በ2024ቱ የደቡብ ኮሪያ የወጣቶች የክረምት ኦሎምፒክ ላይ በብዙ ቋንቋዎች ምሥክርነት ሰጡ

የ2024 የወጣቶች የክረምት ኦሎምፒክ ከጥር 19 እስከ የካቲት 1, 2024 በአራት የደቡብ ኮሪያ ከተሞች ተካሂዷል። ከ70 በላይ አገራት የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች፣ ጋዜጠኞችና ታዳሚዎች የተገኙበት ውድድር ነው። ይህን ውድድር ምክንያት በማድረግ ከ2,600 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች በልዩ የስብከት ዘመቻ ተካፍለዋል። የጽሑፍ ጋሪዎች በ34 የተለያዩ ቦታዎች የቆሙ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ በአራት ቋንቋዎች ለእይታ ቀርቧል።

በደቡብ ኮሪያዋ የጋንግንንግ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ከቆሙት ጋሪዎች መካከል ሁለቱ

የማንዳሪን ተናጋሪ የሆነ አንድ ወጣት፣ የጽሑፍ ጋሪዎቻችንን በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች እንደተመለከተ ለሁለት ወንድሞች ነገራቸው። ስለ ደስተኛ ቤተሰብ የሚገልጽ ፖስተር የተለጠፈበት ጋሪ ሲያይ ግን ቆም ብሎ መረጃ ለመጠየቅ ወሰነ። ወንድሞች ከ​jw.org ላይ ደስተኛ ቤተሰብ ሊኖርህ ይችላል! የተሰኘውን ብሮሹር በማንዳሪን ቋንቋ እንዴት ማውረድ እንደሚችል አሳዩት። ወጣቱ ወዲያውኑ ስልኩ ላይ ድረ ገጻችንን ከፍቶ የተመለከተ ሲሆን ወንድሞችን ላደረጉለት ትብብር አመሰገናቸው።

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት ከዩክሬን ከመጣ አንድ ሰው ጋር መጨዋወት ጀመሩ። የእሱን ቋንቋ መናገር ስለማይችሉ ግን ግለሰቡን ያወያዩት ስልካቸው ላይ ባለ አንድ አፕሊኬሽን በመጠቀም ነው። በውይይታቸው መሃል ሰውየው፣ የሚሳይል ጥቃት በትውልድ ከተማው ላይ ያደረሰውን ውድመት የሚያሳይ አንድ ፎቶግራፍ አሳያቸው። ባልና ሚስቱ የተሰማቸውን ሐዘን ከገለጹለት በኋላ ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚወገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አነበቡለት። ሰውየው በራሱ ቋንቋ ይህን ጥቅስ ሲያነብ ልቡ ተነካ። ባልና ሚስቱ ውይይቱን ለመቀጠል ከሰውየው ጋር ቀጠሮ ይዘዋል።

ጋንግንንግ ኦሎምፒክ ፓርክ ውስጥ አንዲት እህት ከአንድ ባልና ሚስት ጋር ስትጨዋወት

ኢን ሱክ የተባለች እህታችን ከአውሮፓ ከመጡ አንዲት ወጣት ስፖርተኛና እናቷ ጋር በእንግሊዝኛ ውይይት ጀመረች። በውይይታቸው ላይ፣ እህታችን ድረ ገጻችን ላይ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆችን ማሳደግ” በሚለው ክፍል ሥር የሚገኙ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን አነሳችላቸው። እናትየው ባገኘችው መረጃ የተደሰተች ሲሆን ድረ ገጹን ደግማ የመመልከት ሐሳብ እንዳላት ገልጻለች።

የደቡብ ኮሪያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዚህ ዓለም አቀፍ ዝግጅት ላይ እንዲህ ያለ ሰፊ ምሥክርነት መስጠትና ‘የይሖዋን ስም ማወደስ’ በመቻላቸው ተደስተናል።​—መዝሙር 148:13