በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአንተ የሚሆን መጽሐፍ ነው?

ለአንተ የሚሆን መጽሐፍ ነው?

ለአንተ የሚሆን መጽሐፍ ነው?

ሰሎሞን ከ3,000 ዓመታት በፊት “ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም” ብሎ ነበር። (መክብብ 12:​12) ይህ አባባል ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ እውነተኛ ሆኗል። ከታወቁት የጥንት ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በተጨማሪ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ መጻሕፍት ይታተማሉ። እነዚህ ሁሉ መጻሕፍት እያሉ መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብበት ምን ምክንያት አለ?

ብዙ ሰዎች ለመዝናናት አለበለዚያም እውቀት ለማግኘት ሲሉ ወይም ለሁለቱም ምክንያቶች መጻሕፍትን ያነባሉ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስም ተመሳሳይ ነገር ለመናገር ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አእምሮ ሊገነባም ሆነ ሊያዝናና ይችላል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ይህ ብቻ አይደለም። በዓይነቱ ልዩ የሆነ የእውቀት ምንጭ ነው።​—⁠መክብብ 12:​9, 10

መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ሰዎች ስለ ቀድሞው፣ ስለ አሁኑና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለሚጠይቋቸው አሳሳቢ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። የሰው ልጅ የመጣው ከየት ነው? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? በሕይወታችን ደስታ ለማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ሕይወት ምንጊዜም በምድር ላይ ይኖራልን? የወደፊቱ ጊዜ ምን ነገር ይዞልናል? የሚሉት ጥያቄዎች የሚያሳስቧቸው ሰዎች በጣም በርካታ ናቸው።

በዚህ ጽሑፍ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛና እውነተኛ እንደሆነ በግልጽ ያረጋግጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸው ተግባራዊ ምክሮች ትርጉም ያለውና ደስተኛ ሕይወት እንድንኖር እንዴት ሊረዱን እንደሚችሉ ተመልክተናል። ስለ ጊዜያችን የሚሰጠው መልስ የሚያረካ ከሆነ ስላለፈው ጊዜም ሆነ ስለወደፊቱ የሚናገራቸው ነገሮች በትኩረት ሊመረመሩ የሚገባቸው ናቸው።

የተሟላ ጥቅም ለማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ይጀምሩና መረዳት በሚከብዷቸው ቦታዎች ላይ ሲደርሱ ያቆማሉ። አንተም እንደነዚህ ካሉት ሰዎች አንዱ ከሆንክ ሊረዱህ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች አሉ።

እንደ አዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የመሰለ በዘመናዊ ቋንቋ የተዘጋጀ አስተማማኝ ትርጉም ምረጥ። * አንዳንድ ሰዎች ስለ ሰው ባሕርይና ኑሯችንን እንዴት ልናሻሽል እንደምንችል የሚገልጹት እንደ ተራራው ስብከት የመሰሉ ጥልቅ የሆኑ ትምህርቶች የሚገኙበትንና ስለ ኢየሱስ ሕይወት የሚተርኩትን ወንጌሎች በማንበብ ይጀምራሉ።​— ማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7​ን ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ከማንበብ በተጨማሪ በርዕስ፣ በርዕስ ከፋፍሎ ማጥናትም ከፍተኛ እውቀት ሊያስገኝ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል መመርመር ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ነፍስ፣ ሰማይ፣ ምድር፣ ሕይወትና ሞት ስላሉት ርዕሰ ጉዳዮች እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥት ምንነትና የአምላክ መንግሥት ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ስታውቅ በጣም ልትደነቅ ትችላለህ። * የይሖዋ ምሥክሮች አለ ምንም ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስን በአርዕስት ከፋፍለው የሚያስጠኑበት ፕሮግራም አላቸው። ስለዚህ ፕሮግራም በገጽ 2 በሚገኘው አድራሻ ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጆች በመጻፍ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትችላለህ።

ብዙ ሰዎች ማስረጃዎቹን ከመረመሩ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅዱሳን ጽሑፎች “ይሖዋ” ብለው ከሚጠሩት አምላክ የመጣ መሆን አለበት ወደሚለው መደምደሚያ ደርሰዋል። (መዝሙር 83:​18 NW) አንተ በግልህ መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ምንጭ አለው ብለህ አታምን ይሆናል። ግን ለምን አንተ ራስህ አትመረምረውም? ካጠናህ፣ ካሰላሰልክና ምናልባትም መጽሐፉ የሚሰጠው ጊዜ የማይሽረው ጥበብ ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዳለው በራስህ ተሞክሮ ካረጋገጥህ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ለሁሉም ሰው ብቻ ሳይሆን ለአንተም ለግልህ የሚሆን መጽሐፍ እንደሆነ እንደምታምን እርግጠኞች ነን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀ።

^ አን.9 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመው መጽሐፍ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ርዕስ በርዕስ እንዲያጠኑ ረድቷል።