በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ዕድሜ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ዕድሜ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ዕድሜ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?

የጥንት መጻሕፍት እንደ እሳት፣ እርጥበትና ሻጋታ የመሰሉ የተፈጥሮ ጠላቶች አጋጥመዋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን እነዚህ ጠላቶች አጋጥመውታል። ያሳለፈው ረዥም ዕድሜ ያስከተለበትን ፈተናዎች በሙሉ አሸንፎ በመላው ዓለም እንደ ልብ የሚገኝ መጽሐፍ ሊሆን የቻለበት ሁኔታ ከማንኛውም የጥንት ጽሑፍ የተለየ ግምት የሚያሰጠው ነው። ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጸው ታሪክ እንደ ዋዛ ታይቶ የሚታለፍ አይደለም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ጽሑፋቸውን ያሰፈሩት በድንጋይ ጽላቶች ላይ ወይም ለረዥም ዘመናት ሊኖሩ በሚችሉ የሸክላ ጽላቶች ላይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ጽሑፋቸውን ያሰፈሩት በቀላሉ አርጅተው ሊጠፉ በሚችሉ ነገሮች ማለትም በፓፒረስና (ፓፒረስ ተብሎ ከሚጠራ የግብፃውያን ተክል የሚሠራ) በብራናዎች (ከእንስሳት ቆዳ የሚሠሩ) ላይ ነበር።

የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች የት ደረሱ? ምናልባት በጥንትዋ የእስራኤል ምድር ተቀዳደው ጠፍተው ይሆናል። ኦስካር ፓሬት የተባሉት ምሁር እንዲህ ብለዋል:- “እነዚህ የጽሕፈት መሣሪያዎች [ፓፒረስም ሆነ ብራና] በእርጥበት፣ በሻጋታና በብል ሊጠቁ የሚችሉ ናቸው። ወረቀትና ቆዳ ለአየርና ለእርጥበት ሲጋለጥ በቀላሉ እንደሚበላሽ ከዕለታዊ ተሞክሮአችን እናውቃለን።”1

የመጀመሪያዎቹ በኩረ ጽሑፎች በጊዜያችን የማይገኙ ከሆኑ ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በጽሑፍ ላይ ያሰፈሯቸው ቃላት እስከ ዘመናችን ተጠብቀው ሊቆዩ የቻሉት እንዴት ነው?

በጣም ጠንቃቃ በሆኑ ጸሐፊዎች እየተገለበጠ ቆየ

የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ከተጻፉ በኋላ ወዲያው የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች መገልበጥ ጀመሩ። እንዲያውም በጥንቷ እስራኤል ቅዱሳን ጽሑፎችን መገልበጥ ራሱን የቻለ ሙያ ሆኖ ነበር። (ዕዝራ 7:​6፤ መዝሙር 45:​1) ሆኖም ቅጂዎቹ ይገለበጡ የነበሩት በቀላሉ ሊበላሹ በሚችሉ የጽሕፈት መሣሪያዎች ላይ ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች በሌሎች ቅጂዎች መተካት አስፈለጋቸው። በኩረ ጽሑፎቹ ቢጠፉም ከእነዚህ ግልባጮች በርካታ ሌሎች ቅጂዎች ተገልብጠዋል። ቅጂዎችን የመገልበጡ ሥራ ለበርካታ መቶ ዘመናት የቀጠለ ሂደት ነበር። በእነዚህ ሁሉ መቶ ዘመናት ቅጂዎቹን የገለበጡት ሰዎች የፈጸሟቸው ስህተቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት በከፍተኛ ደረጃ እንዲለወጥ አድርገዋልን? ማስረጃው እንደሚያሳየው መልሱ አላደረጉም የሚል ነው።

ባለሞያዎቹ ገልባጮች ራሳቸውን ለሞያቸው ያስገዙ ሰዎች ነበሩ። ለሚገለብጡአቸው ቃላት ከፍተኛ ከበሬታ ነበራቸው። በተጨማሪም በጣም ጠንቃቆች ነበሩ። በዕብራይስጥ “ገልባጭ” ማለት ሶፈር ሲሆን ቃልን እየቆጠሩ መመዝገብን ያመለክታል። ገልባጮቹ ምን ያህል ጠንቃቆች እንደነበሩ ለመገንዘብ ማሶሪቶች ያደርጉ የነበረውን እንመልከት። * ቶማስ ሃርትዌል ሆርን የተባሉት ምሁር ስለ ማሶሪቶች እንዲህ ብለዋል:- “የፔንታቱች [በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የሙሴ አምስት መጻሕፍት] መካከለኛ ፊደል የትኛው እንደሆነ፣ የእያንዳንዱ መጽሐፍ መካከለኛ ሐረግ የትኛው እንደሆነና እያንዳንዱ [የዕብራይስጥ] ሆሄ ስንት ጊዜ በመላው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደሚገኝ ይቆጥሩ ነበር።”3

ስለዚህ እነዚህ በሞያው የተካኑ ገልባጮች የሥራቸውን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡባቸው መሣሪያዎች ነበሯቸው ማለት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱሱ ግልባጭ ውስጥ አንድ ፊደል እንኳን አለመጉደሉን ለማረጋገጥ ሲሉ የገለበጧቸውን ቃላት ብቻ ሳይሆን ፊደሎቹን ጭምር ይቆጥሩ ነበር። ይህን ማድረግ ምን ያህል ድካም የሚጠይቅ ሥራ እንደሆነ ገምት። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 815,140 ፊደላትን ቆጥረው በትክክል መገልበጣቸውን ያረጋግጡ ነበር!4 ይህን የመሰለ ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ ይገለብጡ ስለነበረ ግልባጮቻቸው በጣም ከፍተኛ የሆነ የትክክለኛነት ደረጃ ሊኖራቸው ችሏል።

ቢሆንም ገልባጮቹ ፈጽሞ ሊሳሳቱ የማይችሉ ሰዎች አልነበሩም። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲገለበጥ የቆየ ቢሆንም በሚያስተማምን ደረጃ በትክክል ተገልብጦ እንደቆየልን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማግኘት ይቻላልን?

ለመተማመን የሚያስችል ጠንካራ ምክንያት

መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተማምን ሁኔታ በትክክል ተገልብጦ እንደቆየን ሊያሳምነን የሚችል ጥሩ ምክንያት አለ። በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሙሉ ወይም በከፊል የያዙ ወደ 6,000 ያህል የሚገመቱ የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎችና 5,000 የሚያክሉ የግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች ለዚህ ማስረጃ ይሆኑናል። ከነዚህ መካከል ቅዱሳን ጽሑፎች እንዴት ባለ ጥንቃቄ እንደተገለበጡ በማስረጃነት ሊጠቀስ የሚችለውና በ1947 የተገኘው አንድ በእጅ የተጻፈ የዕብራይስጥ ቅዱስ ጽሑፍ ቅጂ ይገኛል። ይህ ቅጂ “በዘመናችን ከተገኙት የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች በሙሉ የሚበልጥ ግኝት” የሚል ማዕረግ ተሰጥቶታል።5

በ1947 መጀመሪያ ላይ አንድ ወጣት ቤድዊን እረኛ መንጎቹን ሲያግድ በሙት ባሕር አጠገብ አንድ ዋሻ ያገኛል። በዚህ ዋሻ ውስጥ አብዛኞቹ ባዶ የሆኑ በርካታ የሸክላ ማሰሮዎች አገኘ። በደንብ ታስሮ በነበረ አንድ ማሰሮ ውስጥ ግን ከተልባ እግር በተሠራ ጨርቅ በጥሩ ሁኔታ የተጠቀለለ የቆዳ ጥቅልል አገኘ። ይህ ጥቅልል የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የኢሳይያስ ሙሉ መጽሐፍ የያዘ ነበር። ጥቅልሉ በጥሩ ሁኔታ የተጠበቀ ቢሆንም በአገልግሎት ብዛት የተጎሳቆለ ከመሆኑም በላይ የተጠገነ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉት። ወጣቱ እረኛ እጁ ውስጥ የገባው ይህ የጥንት ጥቅልል ከጊዜ በኋላ የመላው ዓለም ትኩረት የሚያርፍበት ጥቅልል ይሆናል ብሎ አላሰበም ነበር።

ይህን የእጅ ጽሑፍ ቅጂ ልዩ ያደረገው ነገር ምንድን ነው? በ1947 በእጅ ይገኝ የነበረው ጥንታዊ የሚባለው የተሟላ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂ በአሥረኛው መቶ ዘመን እዘአ የተጻፈ ነበር። ይህ የመጽሐፍ ጥቅልል ግን በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ * እንደተጻፈ ማለትም እስከዚያ ዘመን ከነበሩት ቅጂዎች በአንድ ሺህ ዓመት የሚበልጥ ዕድሜ እንዳለው ተገምቷል። * ምሁራን ይህ ጥቅልል ከብዙ ዘመናት በኋላ በእጅ ከተገለበጡ ቅጂዎች ጋር ሲመሳከር ምን እንደሚመስል ለማወቅ በጣም ጓጉተው ነበር።

በአንድ ጥናት ላይ ምሁራን የሙት ባሕርን የመጽሐፍ ጥቅልል 53ኛ የኢሳይያስ ምዕራፍ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ ከተጻፈ የማሶሪት ቅጂ ጋር አነጻጽረዋል። ኤ ጀነራል ኢንትሮዳክሽን ቱ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ የጥናቱን ውጤት እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “በኢሳይያስ 53 ውስጥ ከሚገኙት 166 ቃላት መካከል አጠያያቂ ሆነው የተገኙት አሥራ ሰባት ፊደሎች ብቻ ናቸው። ከእነዚህ መካከል አሥሩ በቃሉ ትርጉም ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ የማያመጡ የአጻጻፍ ልዩነቶች ናቸው። አራቱ ፊደላት በመስተጻምርነትና በመሳሰሉት ሁኔታዎች በገቡ ፊደላት ላይ የተደረጉ ልዩነቶች ናቸው። የቀሩት ሦስት ፊደላት በቁጥር 11 ላይ ለተጨመረው ‘ብርሃን’ የሚል ቃል የገቡ ፊደላት ሲሆኑ በምንባቡ ላይ ከቁም ነገር የሚገባ ለውጥ የሚያመጡ አይደሉም። . . . ስለዚህ 166 ቃላት ባሉት አንድ ምዕራፍ ውስጥ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ አጠያያቂ ሆኖ የተገኘው አንድ ቃል (ሦስት ፊደላት) ብቻ ነው፤ ይህም ቃል ቢሆን የምንባቡን ትርጉም እምብዛም አይለውጠውም።”7

በሙት ባሕር ጥቅልሎች ላይ የበርካታ ዓመታት ጥናት ያደረጉት ፕሮፌሰር ሚለር በሮዝ የጥቅልሎቹን ይዘት ከመረመሩ በኋላ ከዚህ ጋር ወደሚመሳሰል መደምደሚያ ደርሰዋል:- “በኢሳይያስ ጥቅልልና በማሶሪት ቅጂ . . . መካከል የሚገኙት ልዩነቶች በአብዛኛው የአገለባበጥ ስህተቶች ናቸው ሊባሉ የሚችሉ ናቸው። ከእነዚህ ውጭ ግን በመካከለኛው ዘመን ከተዘጋጁት ቅጂዎች ጋር በጣም አስደናቂ ስምምነት አለው። ረዥም ዕድሜ ካለው ቅጂ ጋር ይህን የመሰለ መመሳሰል መኖሩ በአሁኑ ጊዜ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው ቅጂ ትክክለኛ ለመሆኑ አስተማማኝ ምሥክር ነው።”8

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የተገለበጡበትን ሁኔታም በተመለከተ ‘አስተማማኝ ምሥክርነት’ መስጠት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል በ19ኛው መቶ ዘመን የተገኘውና ኮዴክስ ሲናይቲከስ የተባለው በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ የተጻፈ የብራና ጽሑፍ ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ የተገለበጡ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ትክክለኛ መሆናቸውን አረጋግጧል። በግብጽ አገር በፋዩም አውራጃ የተገኘው የዮሐንስ ወንጌል የፓፒረስ ቁራጭ በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የተጻፈ እንደሆነ ተገምቷል። የመጀመሪያው ጽሑፍ በተጻፈ 50 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተገለበጠ መሆኑ ነው። ለበርካታ መቶ ዘመናት በደረቁ አሸዋ ውስጥ ሳይበሰብስ ቆይቷል። ይህ ጽሑፍ ከብዙ ዘመናት በኋላ ከተጻፉት የእጅ ጽሑፍ ግልባጮች ጋር ልዩነት እንደሌለው ተረጋግጧል።9

ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች ጽሑፉን ልቅም አድርገው አንድ በአንድ በትክክል እንደገለበጡ ማስረጃው ያረጋግጣል። ቢሆንም አንዳንድ ስህተት መሥራታቸው አልቀረም። ምንም ዓይነት ስህተት የሌለው የእጅ ጽሑፍ ግልባጭ የለም። የሙት ባሕር የኢሳይያስ ጥቅልልም ቢሆን ከዚህ የጠራ አይደለም። ይሁን እንጂ ምሁራን እነዚህን የአገለባበጥ ስህተቶች ሊያውቁና ሊያስተካክሉ ችለዋል።

የገልባጮችን ስህተት ማረም

አንድ መቶ የሚያክሉ ሰዎች አንድን በጣም ረዥም ሰነድ በእጅ እንዲገለብጡ ተጠየቁ እንበል። ቢያንስ አንዳንዶቹ ገልባጮች መሳሳታቸው እንደማይቀር የታወቀ ነው። ቢሆንም ሁሉም አንድ ዓይነት ስህተት አይሠሩም። መቶዎቹንም ግልባጮች ወስደህ በጥንቃቄ ብታስተያይ የመጀመሪያውን ጽሑፍ ባታይ እንኳን ስህተቶቹ የትኞቹ እንደሆኑና ትክክለኛው አገለባበጥ የትኛው እንደሆነ ማወቅ አያቅትህም።

በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች በሙሉ አንድ ዓይነት ስህተት አልተሳሳቱም። በአሁኑ ጊዜ እርስ በርሳቸው ሊነጻጸሩና ሊተያዩ የሚችሉ በሺህ የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ግልባጮች ስላሉ ምሁራን ስህተቶቹን ለመለየት፣ በበኩረ ጽሑፉ ላይ ሠፍሮ የነበረውን ትክክለኛ ሐሳብ ለማወቅና አስፈላጊውን እርማት ለማድረግ ችለዋል። ምሁራኑ ባደረጉት ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው የመጀመሪያ ቋንቋዎች ለተከታይ ግልባጮች መሠረት የሚሆኑ ቅጂዎች ለማዘጋጀት ችለዋል። እነዚህ ታርመውና ተስተካክለው የተዘጋጁ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅጂዎች በበኩረ ጽሑፉ ላይ የነበሩ ናቸው ተብሎ በስፋት ተቀባይነት ያገኙትን ቃላት መርጠው የያዙ ሲሆን በአንዳንድ የእጅ ጽሑፍ ግልባጮች የሚገኙትን የተለዩ ቃላት በግርጌ ማስታወሻዎች ላይ በአማራጭነት አስፍረዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ዘመናዊ ቋንቋዎች በሚተረጉሙበት ጊዜ የተጠቀሙት እነዚህ ምሁራን ባዘጋጁአቸው የታረሙና የተስተካከሉ ቅጂዎች ነው።

ስለዚህ አንድን ዘመናዊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በምታነብበት ጊዜ ለትርጉሙ መነሻ የሆኑት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ያሰፈሯቸውን ቃላት በትክክል እንዳስቀመጡ እርግጠኛ የምትሆንባቸው በቂ ምክንያቶች አሉ። * በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ከአንዱ ቅጂ ወደ ሌላው በእጅ ጽሑፍ ሲገለበጥ ቆይቶ ሳይለወጥ መቆየቱ በጣም የሚያስደንቅ ነው። በዚህ ምክንያት ለረዥም ዘመናት የብሪታንያ ቤተ መዘክር ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን እንደሚከተለው ለማለት ችለዋል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ይዘት ፍጹም ትክክል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። . . . በመላው ዓለም ስለሚገኝ ማንኛውም የጥንት መጽሐፍ እንዲህ ለማለት አይቻልም።”10

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ማሶሪትስ የሚባሉት (“የባሕል ጌቶች” ማለት ነው) ከስድስተኛው እስከ አሥረኛው መቶ ዘመን እዘአ የኖሩ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ገልባጮች ነበሩ። እነርሱ የገለበጧቸው የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች የማሶሪት ጽሑፎች ተብለው ይጠራሉ።2

^ አን.14 ከዘአበ ማለት “ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት” ማለት ነው። እዘአ ማለት ደግሞ “እንደ ዘመናችን አቆጣጠር” ማለት ሲሆን በብዙዎች ዘንድ “ዓመተ ምህረት” ተብሎ የሚጠራውን ዘመን ያመለክታል።

^ አን.14 በኢማኑኤል ቶቭ የተጻፈው ቴክስቹዋል ክሪቲስዝም ኦቭ ዘ ሂብሩ ባይብል እንዲህ ብሏል:- “1QISaa [የሙት ባሕር የኢሳይያስ ጥቅልል] በካርቦን 14 ሲለካ ከ202 እስከ 107 ከዘአበ የተጻፈ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። (በፓሊዮግራፊ ሲለካ ጥቅልሉ የተጻፈው ከ125-100 ከዘአበ ባለው ጊዜ ነው።) . . . በቅርብ ዓመታት በጣም የተሻሻለውና የፊደላትን ቅርጽና አቀማመጥ ዕድሜያቸው በትክክል ከታወቁ በገንዘብና በድንጋይ ጽላቶች ላይ ከተቀረጹ ፊደላት ጋር በማስተያየት የሚደረገው የፓሊዮግራፊ የዘመናት አለካክ ዘዴ በአንጻራዊ ሁኔታ አስተማማኝ ሆኖ ተገኝቷል።”6

^ አን.22 እርግጥ የተለያዩ ተርጓሚዎች የዕብራይስጡን ወይም የግሪክኛውን በኩረ ጽሑፍ በሚተረጉሙበት ጊዜ ጠንቃቆች ወይም ግድየለሾች ሊሆኑ ይችላሉ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ችሎታ ባላቸው ገልባጮች ትክክለኛነቱ ተጠብቆ ሊኖር ችሏል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢሳይያስ የሙት ባሕር ጥቅልል (ቅጂው ከታች ይታያል) ከሺህ ዓመት በኋላ ከተገለበጠው የማሶሪት ግልባጭ ጋር ምንም ልዩነት የለውም ለማለት ይቻላል