በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወት በሚገኙ ቋንቋዎች “የሚናገር” መጽሐፍ

በሕይወት በሚገኙ ቋንቋዎች “የሚናገር” መጽሐፍ

በሕይወት በሚገኙ ቋንቋዎች “የሚናገር” መጽሐፍ

አንድ መጽሐፍ የተጻፈበት ቋንቋ ከሞተ መጽሐፉም መሞቱ የማይቀር ነገር ነው። በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን የጥንት ቋንቋዎች ሊያነቡ የሚችሉ ሰዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ቢሆንም መጽሐፉ ገና ሕያው ነው። በሕይወት ሊኖር የቻለው በሕይወት ያሉትን የሰው ልጆች ቋንቋዎች ለመማር በመቻሉ ነው። ሌሎች ቋንቋዎችን ለመጽሐፍ ቅዱስ “ያስተማሩት” ተርጓሚዎች መወጣት የማይቻሉ የሚመስሉ ችግሮችን ለመጋፈጥ የተገደዱባቸው ጊዜያት ነበሩ።

ከ1,100 የሚበልጡ ምዕራፎችና ከ31,000 በላይ ቁጥሮች ያሉትን መጽሐፍ ቅዱስ መተርጎም ቀላል ሥራ አይደለም። ቢሆንም ባለፉት መቶ ዘመናት ለዚህ ሥራ ከፍተኛ ፍቅር ያደረባቸው ተርጓሚዎች ፈተናውን ለመጋፈጥ ፈቃደኞች ሆነዋል። ብዙዎቹ ይህን ሥራ ለማከናወን ሲሉ መከራንና አልፎ ተርፎም ሞትን ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቋንቋዎች ስለተተረጎመበት ሁኔታ የሚገልጸው ታሪክ ትልቅ ችሎታና ቆራጥነት የተንጸባረቀበት ታሪክ ነው። ከዚህ አስደናቂ የሆነ ታሪክ ጥቂቱን ክፍል ብቻ ተመልከት።

ተርጓሚዎች ያጋጠሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች

አንድን መጽሐፍ በጽሑፍ የሰፈረ ፊደል ወደሌለው ቋንቋ ልትተረጉም የምትችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም የተገደዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ለምሳሌ ያህል በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረው ኡልፊላስ መጽሐፍ ቅዱስን በጊዜው ዘመናዊ ወደነበረውና ፊደል ወዳልነበረው የጎቲክ ቋንቋ ለመተርጎም ተነሳ። ኡልፊላስ 27 ሆሄያት ያሉት በአብዛኛው በግሪክኛና በላቲን ፊደላት ላይ የተመሠረተውን የጎቲክ ፊደል በመፈልሰፍ ይህን ችግር ሊወጣ ችሏል። መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ሊያካትት ምንም ያልቀረው የኡልፊላስ ትርጉም ከ381 እዘአ በፊት ተጠናቅቆ አልቆ ነበር።

በዘጠነኛው መቶ ዘመን ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ሲሪል (ቀድሞ ኮንስታንቲን ተብሎ ይጠራ የነበረ) እና መቶድየስ የተባሉ ሁለት ወንድማማቾች መጽሐፍ ቅዱስን ለስላቭ ቋንቋ ተናጋሪዎች ለመተርጎም ፈለጉ። እነዚህ ወንድማማቾች የቋንቋ ሊቃውንት ከመሆናቸውም በላይ እውቅ ምሁራን ነበሩ። ይሁን እንጂ የዘመናችን ስላቭ ቋንቋዎች አባት የሆነው ስላቮኒክ በጽሑፍ የሰፈረ ፊደል አልነበረውም። ስለዚህ እነዚህ ሁለት ወንድማማቾች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለማዘጋጀት ሲሉ ራሱን የቻለ ፊደል ፈለሰፉ። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ በስላቫዊው የዓለም ክፍል ለሚኖሩ በርካታ ሰዎች “መናገር” ችሏል።

በ16ኛው መቶ ዘመን ዊልያም ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ከበኩረ ልሳናቱ ወደ እንግሊዝኛ ለመተርጎም ተነሳና ከቤተ ክህነትና ከመንግሥት የከረረ ተቃውሞ አጋጠመው። ትምህርቱን በኦክስፎርድ ተከታትሎ ያጠናቀቀው ቲንደል “እርፍ ጨብጦ የሚያርሰው ተራ ገበሬ” ሳይቀር ሊረዳ የሚችለው ትርጉም ለማዘጋጀት ፈልጎ ነበር።1 ይህን ለማድረግ ግን ወደ ጀርመን አገር ለመሰደድ ተገዷል። በዚያም በ1526 የእንግሊዝኛውን “አዲስ ኪዳን” አሳተመ። የዚህ ትርጉም ቅጂዎች ወደ እንግሊዝ አገር በስውር በገቡ ጊዜ ባለሥልጣኖች እጅግ ተቆጥተው ቅጂዎቹን በአደባባይ ማቃጠል ጀመሩ። በኋላም ቲንደል ለባለሥልጣኖቹ አልፎ እንዲሰጥ ተደረገ። ተሰቅሎ ከመገደሉና አስከሬኑ ከመቃጠሉ በፊት ጮክ ብሎ “አቤቱ ጌታ ሆይ፣ የእንግሊዝን ንጉሥ ዓይን ግለጥ!” ብሏል።2

መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎሙ ሥራ ቀጠለ። ተርጓሚዎቹ ከትርጉም ሥራቸው እንዲታቀቡ ማድረግ አልተቻለም። በ1800 እጅግ ቢያንስ የመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ክፍሎች 68 ቋንቋዎችን “ተምረው” ነበር። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት በመመስረታቸው፣ በተለይም የብሪታንያና የባሕር ማዶ አገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በ1804 በመቋቋሙ መጽሐፍ ቅዱስ በከፍተኛ ፍጥነት አዳዲስ ቋንቋዎችን “ተማረ።” በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣት ወንዶች በባዕድ አገሮች ሚስዮናዊ ሆነው ለማገልገል በፈቃደኝነት ተሰለፉ። የብዙዎቹ ተቀዳሚ ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አገሬው ቋንቋ መተርጎም ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ የአፍሪካውያንን ቋንቋዎች እንዲማር ማድረግ

በ1800 በአፍሪካ ፊደል የነበራቸው ቋንቋዎች ከአንድ ደርዘን አያልፉም ነበር። ሌሎቹ በመቶ የሚቆጠሩ የንግግር ቋንቋዎች በጽሑፍ ለማስፈር የሚያስችል ዘዴ እስኪፈለሰፍላቸው ድረስ መቆየት ነበረባቸው። ሚስዮናውያን መጡና አላንዳች የመዝገበ ቃላትም ሆነ የማስተማሪያ መጻሕፍት እገዛ ቋንቋዎቹን ተማሩ። ከዚያም በብዙ ድካም ቋንቋዎቹን በጽሑፍ ማስፈር የሚቻልበት ዘዴ ከፈጠሩ በኋላ የአገሩን ሰዎች ጽሑፉን እንዴት እንደሚያነቡ ማስተማር ተያያዙ። ይህን ሁሉ ያደረጉት አንድ ቀን ሕዝቦቹ መጽሐፍ ቅዱስን በገዛ ራሳቸው ቋንቋ ማንበብ እንዲችሉ ለማድረግ በማሰብ ነበር።3

እንዲህ ካደረጉት ሚስዮናውያን አንዱ ሮበርት ሞፋት የተባለ የስኮትላንድ ተወላጅ ነበር። ሞፋት በ25 ዓመት ዕድሜው በ1821 በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ የጽዋና ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል የሚስዮን ጣቢያ አቋቋመ። ይህን ፊደል ያልነበረውን ቋንቋ ለመማር ሲል ወደ ሕዝቡ ዘልቆ በመግባት የሕዝቡን ኑሮ መኖር ጀመረ። በኋለኞቹ ጊዜያት እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ሰዎቹ በጣም ደጎች ነበሩ። ቋንቋውን ስናገር የማደርገው ስህተት በእጅጉ ያስቃቸው ነበር። የእኔን አነጋገር ኮርጆ ሌሎቹን ከልብ ከማሳቁ በፊት ያረመኝ አንድም ሰው ኖሮ አያውቅም።”4 ሞፋት በዚህ ተስፋ ቆርጦ ጥረቱን አላቋረጠም፤ በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ቋንቋውን ጠንቅቆ ማወቅ በመቻሉ ለቋንቋው ፊደል ፈለሰፈ።

ሞፋት ከጽዋና ሕዝቦች ጋር ለስምንት ዓመታት ያህል ከኖረ በኋላ በ1829 የሉቃስን ወንጌል ተርጉሞ ጨረሰ። ይህን ትርጉሙን ለማሳተም 900 ኪሎ ሜትር ያህል በበሬ በሚጎተት ጋሪ ተጉዞ ወደ ባሕር ጠረፍ ከደረሰ በኋላ በመርከብ ተሳፍሮ ወደ ኬፕታውን መጣ። እዚያም እንደደረሰ የአገሩ ገዥ በመንግሥቱ የማተሚያ መሣሪያ እንዲጠቀም ፈቀደለት። ይሁን እንጂ ሞፋት ራሱ ፊደሎቹን ማዘጋጀትና ማተም ነበረበት። ከዚህ ሁሉ ድካም በኋላ በ1830 የሉቃስን ወንጌል አትሞ አወጣ። የጽዋና ተናጋሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን አንድ ክፍል በገዛ ቋንቋቸው ማንበብ ቻሉ። በ1857 ሞፋት መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በጽዋና ቋንቋ ተርጉሞ ጨረሰ።

ሞፋት የጽዋና ተናጋሪዎች የሉቃስን ወንጌል በገዛ ራሳቸው ቋንቋ ሲያገኙ ምን እንደተሰማቸው ገልጿል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የቅዱስ ሉቃስን ወንጌል ቅጂ ለማግኘት በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዘው የመጡ ሰዎች አውቃለሁ። . . . ‘ተዉ መጽሐፋችሁን በእንባችሁ አርሳችሁ ታበላሻላችሁ’ ብዬ እስክከለክላቸው ድረስ የደስታና የአመስጋኝነት ሲቃ እየተናነቃቸው መጽሐፋቸውን አቅፈው ያለቀሱ ብዙ ሰዎች አይቻለሁ።”5

እንደ ሞፋት ያሉ ለተሰማሩበት ዓላማ ራሳቸውን መሥዋዕት ያደረጉ ብዙ ተርጓሚዎች ከዚያ በፊት በአብዛኛው የጽሕፈትንና የፊደልን ጥቅም እንኳን ለማያውቁ በርካታ አፍሪካውያን በጽሑፍ የመግባባትን አጋጣሚ ከፍተዋል። ተርጓሚዎቹ ለአፍሪካ ሕዝቦች ከዚህ እጅግ የሚልቅ ዋጋ ያለው ስጦታ፣ ማለትም በቋንቋቸው የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳበረከቱ እምነት ነበራቸው። ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከ600 በሚበልጡ የአፍሪካ ቋንቋዎች “መናገር” ችሏል።

የእስያን ቋንቋዎች እንዲማር ማድረግ

በአፍሪካ የሚኖሩ ተርጓሚዎች ሥነ ጽሑፍ የሌላቸውን ቋንቋዎች በጽሑፍ ለማስፈር በሚጣጣሩበት ጊዜ በሌላው የዓለም ክፍል የተሰማሩ ተርጓሚዎች ደግሞ ከዚህ የተለየ ከባድ ችግር ገጥሟቸው ነበር። በዚህ የዓለም ክፍል የነበረው ችግር ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በጣም ውስብስብ የሆኑ ሆሄያት ወደነበሯቸው ቋንቋዎች የመተርጎም ሥራ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ወደ እስያውያን ቋንቋዎች የተረጎሙ ተርጓሚዎች የተደቀነባቸው ከባድ ችግር ይህን የመሰለ ነበር።

በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ዊልያም ካሪ እና ጃሹዋ ማርሽማን ወደ ሕንድ አገር ሄዱና በርካታ ቋንቋዎችን ከነአጻጻፋቸው ተማሩ። ዊልያም ዋርድ በተባለ የኀትመት ሠራተኛ እርዳታ የመጽሐፍ ቅዱስን አንዳንድ ክፍሎች 40 በሚያክሉ ቋንቋዎች አዘጋጅተው አወጡ።6 ጄ ኸርበርት ኬን የተባለው ደራሲ ስለ ዊልያም ካሪ እንዲህ በማለት ገልጿል:- “ለመጻፍ አመቺና ቀላል የሆነ ማራኪ የአጻጻፍ ስልት ፈልስፎ የጥንቱን የቤንጋል ቋንቋ አጻጻፍ በመተካቱ ቋንቋው ዘመናዊ አንባብያንን የሚስብና በቀላሉ የሚገባ ሊሆን ችሏል።”7

አዶኒራም ጀድሰን የተባለ ውልደቱና እድገቱ በዩ​ናይትድ ስቴትስ የነበረ ሰው ወደ በርማ ሄዶ በ1817 መጽሐፍ ቅዱስን በበርማ ቋንቋ መተርጎም ጀመረ። የሩቅ ምሥራቅ አገሮችን ቋንቋዎች መማርና መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም በሚያስችል መጠን ቋንቋውን መቻል ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:- ‘ከእኛ ፈጽሞ የተለየ የአስተሳሰብ መስመር፣ ለእኛ ፍጹም ባዕድ የሆነ የሐሳብ አገላለጽ ሥርዓት፣ ከዚህ በፊት አጋጥሞን ከሚያውቅ ከማንኛውም ቋንቋ ጋር ምንም ዓይነት ተመሳሳይነት የሌላቸው ፊደላትና ቃላት ያሉትን ቋንቋ አላንዳች መዝገበ ቃላት ወይም አስተርጓሚ እርዳታ፣ ስለ ቋንቋው በቀሰምናት ጥቂት እውቀት ብቻ በአገሬው አስተማሪነት ለመማር ስንነሳ ምን ያህል ከባድ ሥራ መጀመራችን እንደነበረ ግልጽ ነው!”8

ጀድሰን ይህን አድካሚ ሥራ ለማከናወን 18 ዓመት ፈጅቶበታል። የበርማ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ክፍል በ1835 ታተመ። ይሁን እንጂ የበርማ ቆይታው ብዙ መከራ አስከትሎበታል። የትርጉም ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ በሰላይነት ተከሶ ለሁለት ዓመታት የትንኞች መጨፈሪያ በሆነ ወህኒ ቤት ውስጥ ቆይቷል። ከእስር ቤት ተፈትቶ ብዙም ሳይቆይ ሚስቱና ወጣት ሴት ልጁ በትኩሳት ሕመም ሞቱበት።

በ25 ዓመት ዕድሜ ላይ ይገኝ የነበረው ሮበርት ሞሪሰን በ1807 ወደ ቻይና ሄደና እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ቻይና ቋንቋ የመተርጎም ሥራ ጀመረ። የቻይና ቋንቋ እጅግ ውስብስብና አስቸጋሪ ከሆኑት የሥነ ጽሑፍ ቋንቋዎች አንዱ ነው። የቻይናን ቋንቋ ማጥናት የጀመረው ወደ ቻይና ከመጓዙ ከሁለት ዓመት በፊት ስለነበር ስለ ቋንቋው የነበረው እውቀት አነስተኛ ነበር። በተጨማሪም ቻይና ከዓለም ተገልላ እንድትኖር ለማድረግ የወጣው የአገሪቱ ሕግ ለሞሪሰን ከባድ እንቅፋት ሆኖበት ነበር። ቻይናውያን ቋንቋቸውን ለባዕዳን ቢያስተምሩ በሞት ይቀጡ ነበር። አንድ የውጭ አገር ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በቻይና ቋንቋ ቢተረጉም በሞት ያስቀጣው ነበር።

ሞሪሰን በእነዚህ ሁሉ እንቅፋቶች ተስፋ ሳይቆርጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ ቋንቋውን በመማር ፈጣን እድገት አደረገ። በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢስት ኢንድያ ተብሎ በሚጠራ ኩባንያ በተርጓሚነት ተቀጠረ። ቀን ቀን ለኩባንያው ሲሠራ ከዋለ በኋላ ማታ ማታ በምሥጢር መጽሐፍ ቅዱስ የመተርጎም ሥራውን ያከናውን ነበር። ይህን የትርጉም ሥራ ሲያከናውን ቢያዝ ከፍተኛ ቅጣት ሊደርስበት ይችል ነበር። ቻይና ከገባ ከሰባት ዓመታት በኋላ በ1814 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ተርጉሞ ለኅትመት አዘጋጀ።9 ከአምስት ዓመታት በኋላ በዊልያም ሚልን እርዳታ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ተርጉሞ አጠናቀቀ።

እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የሥራ ውጤት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ ከሚገኙ ቋንቋዎች በሙሉ እጅግ ብዙ ተጠቃሚዎች ባሉት ቋንቋ “መናገር” ቻለ። ከፍተኛ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ተርጓሚዎች ምስጋና ይግባቸውና በሌሎች የእስያ ቋንቋዎችም የሚደረገው የትርጉም ሥራ ቀጠለ። በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከ500 በሚበልጡ የእስያውያን ቋንቋዎች ተተርጉመው ይገኛሉ።

እንደ ቲንደል፣ ሞፋት፣ ጀድሰንና ሞሪሰን የመሳሰሉት ሰዎች ሕይወታቸውን ሳይቀር ለአደጋ አጋልጠው ለማያውቋቸው ሕዝቦች፣ አልፎ ተርፎም በጽሑፍ የሠፈረ ቋንቋ ለሌላቸው ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ይህን ያህል የደከሙት ለምንድን ነው? ክብር ወይም ሀብት ለማግኘት እንዳልነበረ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነና ለሁሉም ሕዝቦች በገዛ ቋንቋቸው “መናገር” እንደሚገባው ስላመኑ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የምታምን ሰው ሆንክም አልሆንክ፣ እነዚህ ራሳቸውን ለዚህ ሥራ መሥዋዕት ያደረጉ ተርጓሚዎች በዛሬው ዓለም በጣም ብርቅ የሆነው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንደነበራቸው ማመንህ አይቀርም። ታዲያ ሰዎች እንዲህ ያለ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንዲያድርባቸው ያደረገውን መጽሐፍ መመርመር ተገቢ አይሆንምን?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ከ1800 ወዲህ መጽሐፍ ቅዱስ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ የታተመባቸው ቋንቋዎች ብዛት

68 107 171 269 367 522 729 971 1,199 1,762 2,123

1800 1900 1995

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጉም

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮበርት ሞፋት

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዶኒራም ጀድሰን

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮበርት ሞሪሰን