በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከማንኛውም መጽሐፍ የበለጠ ስርጭት ያገኘ መጽሐፍ

ከማንኛውም መጽሐፍ የበለጠ ስርጭት ያገኘ መጽሐፍ

ከማንኛውም መጽሐፍ የበለጠ ስርጭት ያገኘ መጽሐፍ

“በታሪክ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙዎች ዘንድ የተነበበ መጽሐፍ የለም። . . . የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በሠፊው የተሠራጨ መጽሐፍ አይገኝም። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ብዙ ጊዜና በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ መጽሐፍ አይገኝም።”​—⁠“ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ”1

በአንዳንድ ሁኔታዎች ረገድ አብዛኞቹ መጽሐፎችና ሰዎች ይመሳሰላሉ። በጣት ከሚቆጠሩ ጊዜ የማይሽራቸው ጥቂት መጻሕፍት በስተቀር አብዛኞቹ በአንድ ወቅት ብቅ ብለው ከታዩና ከፍተኛ ዝና ካገኙ በኋላ ጊዜ ያለፈባቸው ይሆኑና ሞተው ይቀራሉ። ቁጥር ስፍር የሌላቸው መጻሕፍት የሚያነባቸው አጥተው በአብያተ መጻሕፍት ውስጥ ተቀብረው ቀርተዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን ጊዜ ከማይሽራቸው መጻሕፍትም እንኳን ፈጽሞ የተለየ ነው። መጻፍ የተጀመረው ከ3,500 ዓመታት በፊት ቢሆንም አሁንም ሕያው መጽሐፍ ነው። በስርጭት ረገድ አንድም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጽሐፍ ነው። * በየዓመቱ 60 ሚል​ዮን የሚያክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ወይም ከፊል ቅጂዎች በመላው ዓለም ይሰራጫሉ። ጀርመናዊው ዮሐንስ ጉተንበርግ በፈለሰፈው የማተሚያ መሣሪያ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ጽሑፍ፣ ተንቀሳቃሽ በሆነ የማተሚያ መሣሪያ የታተመው በ1455 ገደማ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አራት ቢልዮን የሚያክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ወይም ከፊል ቅጂዎች እንደታተሙ ይገመታል። ወደዚህ ቁጥር የሚጠጋ አንድም ሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ መጽሐፍ የለም።

በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዛት የተተረጎመ መጽ​ሐፍ የለም። በሙሉ ወይም በከፊል ከ2,100 በሚበልጡ ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ተተርጉሟል። * ከዓለም ሕዝቦች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቢያንስ የመጽሐፍ ቅዱስን የተወሰነ ክፍል በገዛ ቋንቋቸው ለማንበብ ይችላሉ።2 ስለዚህ ይህን መጽ​ሐፍ ሊገድብ የቻለ የብሔር ወይም የጎሣና የዘር ድንበር የለም።

አሓዛዊ መረጃዎች ብቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስን እንድትመረምር የሚያስገድዱ ምክንያቶች ላይሆኑ ይችላሉ። ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን የስርጭት መጠንና የተተረጎመባቸውን ቋንቋዎች ብዛት የሚጠቁሙት እነዚህ ቁጥሮች እጅግ የሚያስደንቁ ከመሆናቸውም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኘ መጽሐፍ ለመሆኑ በቂ ምሥክሮች ናቸው። በእርግጥም የሰው ልጅ ባሳለፋቸው የታሪክ ዘመናት ሁሉ በስርጭቱና በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎም ረገድ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘውን መጽሐፍ ልትመረምረው ይገባል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በስርጭቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ ሁለተኛ የሆነው ባለ ቀይ ሽፋኑ ኮቴሽንስ ፍሮም ዘ ወርክስ ኦቭ ማኦ ሴ ቱንግ የተባለው ቡክሌት ስርጭት ከ800 ሚልዮን አላለፈም።

^ አን.5 የቋንቋዎቹን ብዛት በተመለከተ የተገለጹት አሓዛዊ መረጃዎች የተገኙት ከተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ነው።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተንቀሳቃሽ የማተሚያ መሣሪያ የታተመው የመጀመሪያው መጽሐፍ በላቲን ቋንቋ የተዘጋጀው የጉተንበርግ መጽሐፍ ቅዱስ ነው